የሠብአዊ መብት ዋጋው ስንት ነው?

ሄኖክ ሳሙኤል

ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ ሰብአዊ መብትን በማስጠበቅ ላይ ተሰማርተናል የሚሉ ድርጅቶች እንደምንጠብቃቸው በጭቆና ስር ላሉና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትህ እንዲያገኙ የሚሰሩ አሊያም መፍትሄ የሚያፈላልጉ አይደሉምይልቁንም የተዘፈቁበትን የገንዘብና የሃብት ማካበት ተግባር በማጠናከር ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የገንዘብ ለጋሾቻቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም ሌት ተቀን በትጋት የሚሰሩ እንጂ ሲል ይገልፃቸዋል ታዋቂው እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ Jonathan Cook

Jonathan Cook ለረዥም ጊዜ በሚታወቅበት የጋዜጠኝነት ሙያው ለህዝብ ጥቅም መዋል ሲገባቸው በሚስጥር በመንግስታት የተደበቁና የተያዙ መረጃዎችን የትኛውንም ሃይል  ሳይፈሩና ለውለታና ለጥቅማጥቅም ሳይንበረከኩ እውነተኛውን መረጃ ለህዝብ ይፋ ካደረጉ ጋዜጠኞች አንዱ በመሆን The Martha Gellhorn Special Prize for journalism በሚል እኤአ በሰኔ ወር 2011 በለንደን የተዘጋጀው ሽልማት አሸናፊ ለመሆን የበቃ ታዋቂ ጋዜጠኛ ነው

founder of Wikileaks በሚል ሚታወቀው julian assange ጋር የዚህ አዋርድ  አሸናፊ የሆነው Jonathan Cook እኤአ ከ1988 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባሉት የሀያ አራት አመታት ጊዜ ብጥብጥ ተለይቶት በማያውቀው መካከለኛው ምስራቅ ላይ የጋዜጠኝነት ሙያውን በብቃት እየተወጣ ያለ ጋዜጠኛ መሆኑን በርካታ የሽልማቱን ዜና ይፋ ያደረጉ ሚዲያዎች ሁሉ የገለፁት እውነታ ነው

ጆናታን ኩክ ከጋዜጠኝነት የሙያ ባህሪው ጋር በተያያዘ አዲስ ባወቃቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶም በርካታ መፅሃፍትን ለማሳተም የበቃ እውቅ ጋዜጠኛ መሆኑም በሽልማት ስነስርአቱ ወቅት ተወስቶለታል። ባሳተማቸው በርከት ባሉ መፅሃፍቱም ላይ ጋዜጠኛው ያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች በምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) ላይ የደረሰባቸው እውነታዎችና ሃቆች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን በርካቶቹ ይስማሙበታል

ይህ እውቅ ጋዜጠኛ ሰብአዊ መብትን እናስጠብቃለን የሚሉ ሂዩማን ራይትስን የመሰሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን አላማ ማስፈፀም ላይ ሳይሆን የሃብት ማካበቻ ምንጫቸውን አላማ ማስጠበቅ ላይ አተኩረው መንቀሳቀሳቸው የተቋማቱን የዴሞክራሲያዊ እሴት ውድቀትን የሚያመላክት በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማል በፅሁፉ

በሂዩማን ራይትስ ዎችና መሰል ድርጅቶች ላይ ጥናት ያደረጉ ሌሎች ምሁራንና ተመራማሪዎችም በጥናታቸው እነዚህ ድርጅቶች ሰብአዊ መብት የሚለው ሽፋን የለጋሾቻቸውን የፖለቲካል አይዲዎሎጂ ለማስፈፀም እንደ ንግድ ፈቃድ የሚያገለግላቸው መሳሪያ መሆኑን ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝም የሰሞኑን የሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ላይ አተኩሮ ያወጣው መግለጫ በመሆኑ ስለ ድርጅቱ ይህን ያህል ካልኩ መግለጫውንና ይዘቱንና የመግለጫውን አላማ አስመልክቶ አንዳንድ ነገሮችን ለማለት እሞክራለሁ ።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ድርጅት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ የሚካሄዱ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በማጣጣልና በማንቋሸሽ በአመት ውስጥ አነሰ ቢባል ሶስት አራት ጊዜ መግለጫ ሲያወጣ መሆኑን ማንም ሊክደው የማይችል ፀሃይ የሞቀው እውነታ ነው።

ድርጅቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንኳን ያወጣቸውን መግለጫዎችን ስጠቅስ በ2001 ዓ.ም በኦጋዴን ጉዳይ በ2002 በፀረ ሽብር ህጉና በአገር አቀፉ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት በ2003 በድርቅ ጉዳይ ዘንድሮ ደግሞ በጋምቤላ እየተካሄደ ባለው ህዝብን የማስፈር ጉዳይ ላይ እንደተለመደው ከእውነት የራቀ ተጨባጭነት የጎደለውና መሰረተ ቢስ ሪፖርት አውጥቷል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ያወጣው ባለ 125 ገፅ በላይ ሪፖርት “የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ለውጭ ባለሃብቶች ኔዘርላንድን የሚያክል የቆዳ ስፋት ያለው መሬት ሰጥቷል” “ይህ አልበቃ ብሎትም በቅርቡም በጋምቤላ የሚገኙ ዜጎችን

ከመሬታቸውና ነባር ይዞታቸው አንስቶ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወዳልተዘረጉበት አካባቢ በማፈናቀል ተጨማሪ መሬት ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ቀጥሎበታል” የሚሉና በተጨባጭ በክልሉ ካለው ሃቅ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝና ፍፁም የተቃረነ ውንጀላዎችን አጭቆበታል።የተለያዩ የውጭ አገራት ሚዲያዎችም ይህንን ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ግን ለድርጅቱ ውንጀላዎች በሰጠው ምላሽ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በታዳጊ ክልሎች ማለትም በጋምቤላ በሶማሌና በቤንሻንጉል ያሉ ዜጎችን ወደ ተሻለ አካባቢ በማስፈር ከቀድሞው ወደ ተሻለ አመራረትና አኗኗር ለማሸጋገር እያደረገ ባለው ጥረት እስካሁን 125 ሺህ ዜጎችን ማስፈር መቻሉን ገልፆ ከእነዚህ መካከልም 20 ሺህው በጋምቤላ እንደሚገኙ አመልክቷል።

ሆኖም ይህ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በተሳሳተ መልኩ እንደገለፀው ሳይሆን በጋምቤላ ክልል በ43 መንደሮች እየተካሄደ ባለው የሰፈራ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ 22 የጤና ኬላዎችን 19 ትምህርት ቤቶችን 72 የመስኖ ጠለፋ 407 የውሃ ፓምፖችን 18 የእንስሳት ክሊኒኮችን እንዲሁም 30 የእህል ወፍጮዎችን መገንባቱንና 128 ኪሎሜትር መንገዶች መስራቱንም ነበር የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የገለፀው።

እነዚህ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመሰረተ ልማት አውታሮች ከተዘረጉበት ሁኔታ በተጨማሪም የሰፈራ ፕሮግራሙ ከሰፋሪዎች ጋር በተካሄደ ምክክር በሙሉ ፈቃደኝነት የተከናወነ  እንደነበርም ገልፆ ሆኖም የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት አውጭዎች ግን ይህንን እውነታ ለማካተት ምንም አይነት ፈቃደኝነተቱ እንዳልነበራቸውም አካቷል።

የተቋሙ መግለጫ የኢፌዴሪ መንግስት በመላ አገሪቱ እየተመዘገበ ባለው ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለዘመናት በተፈፀመባቸው አድሏዊነትና የእኩል እድገት የተጠቃሚነት እድል ተነፍገው የኖሩ የታዳጊ ብሄረሰቦች ህዝቦች በልዩ ትኩረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ አመታትን ማስቆጠሩን ያመለክታል።

በዚህ ሂደትም በመላ አገሪቱ ጥቅም ላይ ሳይውል የኖረውና ህዝብ ከሰፈረበት አካባቢ ውጭ የሚገኘውን ለግብርና የተመቸ መሬትም ለአገር ውስጥና ለውጭ አልሚዎች በመስጠት እንዲለማ እያደረገ ነው።ከዚህ በተጨማሪም በተበታተነ አሰፋፈር በከፊል አርብቶ አደርነትና በቁፋሮ አስተራረስ ዘይቤ ዝቅተኛ ምርት እያመረቱ የሚኖሩትን የታዳጊ ብሄረሰብ አባላትን በማስፈር የአመራረት ዘይቤያቸውን ለመቀየር እየሰራ እንደሚገኝም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ተመልክቷል።

ታድያ ይህ በህዝቦች ሙሉ ፈቃደኝነት ለጋምቤላ ህዝብ ኑሮ መለወጥና መሻሻል እየተከናወነ ያለው የሰፈራ ተግባርና እንዲሁም ለዘመናት ጥቅም ላይ ሳይውል የኖረውና ህዝብ ከሰፈረበት አካባቢ ውጭ የሚገኘውን ለግብርና የተመቸ መሬት ለአገር ውስጥና ለውጭ አልሚዎች በመስጠት እንዲለማ መደረጉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ለምን ይዘምትበታል? አገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠል ወሳኝ የሆነው ይህ አበረታች ተግባርስ ለምን የድርጅቱ አሉታዊ መግለጫና ሪፖርት ሰለባ ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ የሚገኘው መልስ እጅግ አስገራሚ ይሆናል።

ጆናታን ኩክ ቀደም ሲል እንደገለፀው የተቋቋመለትን ሰብአዊ መብት የማስጠበቅ ተግባር ሳይሆን የሃብት ምንጮችን ፍላጎት በማስጠበቅ ላይ የተጠመደው ይህ ድርጅት ቀዳሚ አላማውም ሆነ ተግባሩ የኮርፖሬት መብት ማስጠበቅ እንጅ የሰብአዊ መብት ማስጠበቅ አይደለም።ሰብአዊ መብት የሚለው አጀንዳ  ሂዩማን ራይትስ ዎች እንደ ተኩላ ከላይ የደረበው የበግ ለምድ መሆኑ ፀሃይ ከሞቀው ውሎ አድሯል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች ድርጅት ጆርጅ ሶሮስን ከመሰለ የገበያ አክራሪነት የተጠናወተውና ይህንኑ አላማውን አገራትን በማጠባጥ ጭምር ለማስፈፀም ድርጅት መስርቶ ከሚንቀሳቀሰው ቢሊየነር እስካሁን ካገኘው እጅግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በተጨማሪ በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ብቻም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያሳፍሰው ቃል እንደተገባለት የአደባባይ ሚስጥር ነው። በመሆኑም ይህ ድርጅት በሰብአዊ መብት ስም የለጋሹን የጆሮጅ ሶሮሰ ርእዮተ አለማዊና ፖለቲካዊ አላማ ለማስፈፀም ላይ ታች ቢታትር ምን ያስገርማል?

በገበያ አክራሪነት የተጠመቀው የእነ ጆርጅ ሶሮስ ድርጅት በአለም ላይ ያሉ አገራት ሁሉ በሊበራል ኢኮኖሚ ብቸኛ መንገድ እንዲጓዙ እንደ መድሃኒት የሚያዙ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ መንግስት የራሳቸውን የልማት መንገድ ቀይሰው የሚጓዙ መንግስታት ደግሞ በእነርሱ የታዘዘላቸውን መድሃኒት ለመዋጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብቻ የተከታታይ ሃሰተኛና ጥላሸት የሚቀቡ መግለጫዎች ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ራልፍ ማጌ የተሰኘ ምሁር እኤአ በ1999 ይፋ ባደረገው ፅሁፍ ሂዩማን ራይትስ ዎች  የቻይና መንግስት ራሱ በነደፈው የልማትና የኢኮኖሚ እድገት በመጓዙና የኒዎሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ባለመከተሉ ሳቢያ በአሜሪካው ሲአይኤ እየታገዘ ተመሳሳይ ዘመቻ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ስም ሲያደርግበት እንደነበር በአፅንኦት አስምሮበታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ድርጅት “የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ለውጭ ባለሃብቶች ኔዘርላንድን የሚያክል የቆዳ ስፋት ያለው መሬት ሰጥቷል” “ይህ አልበቃ ብሎትም በቅርቡም በጋምቤላ የሚገኙ ዜጎችን ከመሬታቸውና ነባር ይዞታቸው አንስቶ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወዳልተዘረጉበት አካባቢ በማፈናቀል ተጨማሪ መሬት ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ቀጥሎበታል በሚል የሚያሰማውን ሃሰተኛ ክስ አስመልክቶም እውነታው ምን እንደሚመስል እንመልከት።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ መጠነ ሰፊ የተባለ የአምስት አመት የእድገትና የትራስንፎርሜሽን እቅድ ነድፎ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በዚህ ሂደትም በጋምቤላ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በሶማሌ ክልል እስካሁን ያለማ ሆኖም ቢለማ ግን ለአገራዊ እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ የሚውል 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚገኝ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።ሆኖም ከዚህ መካከል እስካሁን አልሚዎች የወሰዱት 42 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ሲሆን ይህም ሊለማ ከሚገባው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መልማቱን ነው መረጃው የሚጠቁመው።

ሂዩማን ራይትስ ዎች እውነተኛ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም አሳቢና የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት ቢሆን ኑሮ ግን የኢትዮጵያ መንግስት አገሪቱ ያላትን መሬትን የመሰለ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ከመጠቀም ቸልተኝነትን ቢያሳይ ነበር ይህን መሰል ሪፖርትና መግለጫ ማውጣት የሚገባው ።

ሆኖም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና ድርጅቱ በኢትዮጵያ በተከታታይና ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተመዘገበ የሚገኘውንና ከዚህም በተለያየ ደረጃ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠል የተነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በተከታታይ እንቅልፍ አጥቶ ሲቃወምና በመግለጫና በሪፖርት ጋጋታ የአገሪቱን የልማት ጉዞ በተቻለው አቅም ለማደናቀፍ በየጊዜው የተቻለውን ሁሉ ሲጥር መታየቱ በተለይም የኢትዮጵያ  ህዝብ የድርጅቱን ማንነት ይበልጥ እንዲያውቀው አድርጎታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ድርጅት ከትናንቱ ትምህርት ለመውሰድ የታደለ አይደለም እንጅ አገር አቀፉ የ2002 ምርጫ ውጤት ሲገለፅ የኢትዮጵያ ህዝብን ድምፀ ውሳኔ ባለማክበር አላማዬን ያሳኩልኛል ያላቸው ሃይሎች ለምን የስልጣን ኮረቻ አልተፈናጠጡም በሚል የሞኝ ዘፈን የተለመደውን መግለጫ ሲያወጣ በአራቱም ማእዘን የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ነቅሎ አደባባይ በመውጣት “ሂዩማን ራይትስ ዎች እጅህን ከአገራችን አንሳ ድምፃችንም ይከበር” በሚል ዳር እስከ ዳር መራር የተቃውሞ ድምፅ ማስተጋባቱ ድርጅቱን ጨምሮ በሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚዘነጋ አይደለም።

ሆኖም ለለጋሾቹ ፍላጎትና እነርሱ ለሚጥሉለት ፍርፋሪ እንጂ የህዝቦችን ድምፅ የመስማትና የማክበር ታሪክም ሆነ ጊዜ የሌለው ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬም ይህን ድምፅ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከ2002 ምርጫ ወዲህ እንኳን ሊያነግሳቸው በኢትዮጵያ ከጅሎ ያልተሳካላትን መድረክን ከመሰሉ ተቃዋሚ ሃይላት ጋር ተቀናጅቶ ድርቅንና የመሳሰሉትን የቅብብሎሽ ዜማዎች የተለያየ ስልተ ምቶችን በመጠቀም ሊያቀነቅን ቢሞክርም እየው እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን ህዝብ ጆሮ ሊያገኝ አልቻለም።

ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር የማይሞክረው ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ባይሰማውም መሰል ዜናዎችን ማነፍነፍ የሚቀናው የኒዮ ሊበራሉ ሚዲያ አፍሪካ ላይ የሚያዥጎደጎደውና የሚያሟርተው ሰቅጣጭ ዜና ባጣ ሰሞን እየደረሰ የወሬ ጥም ሱሱን ይቆርጥለታል።

መድረክን የመሳሰሉ ጭፍንና ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችም የተቃውሞና የጩሀት አጀንዳ አጥተው አገሩ ጭር ሲልና እነርሱም የአጀንዳ ያለህ  እያሉ ሲጉላሉ ሲመቸው  “በአገሪቱ ለጋሾች ለድርቅ የለገሱት እርዳታ ለፖለቲካ አላማ ይውላል———  ይሀኛው ሲሰለች ደግሞ ዜማውን ቀይሮ የፕሬስ ነፃነት ታፍኗል ይሀኛው ብዙ አላራምድ ሲለው ደግሞ ——– የመሬት ሽሚያ——–የግዳጅ  ሰፈራና ሌሎችንም እያነሳና እንዲህ እንዲህ እያለም አንድም ድርጅቱ የድርሰትና የደራሲ ችግር የሌለበት መሆኑን ሲያስመሰክር በሁለተኛ ደረጃ የሚያቀነቅነው የተቃውሞ አጀንዳ ድርቀት ብዙ ጊዜ ለሚያጋጥመው የፅንፈኛ ተቃዋሚ ጎራ እንዲህ እንደ ሰሞኑ ብቅ እያለ አጀንዳ ጣል ያደርግለታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ድርጅት ሁሌም ቢሆን የሚያወጣቸውን ተከታታይ ሪፖርቶችና መግለጫዎችን በመጨረሻ የሚቋጫቸው ለጋሾች ለኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ እንዳይሰጡ በሚማፀኑ የመደምደሚያ አረፍተ ነገሮች በማጀብ ነው።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ብድርና እርዳታን ተማምነውና ይህንኑ እየጠበቁ እጃቸውን አጣጥፈው ያልተቀመጡ መሆናቸውን ከማንም ይልቅ ሂዩማን ራይትስ ዎች ተብዬውን ድርጅት ለሚያስተዳድሩት ከፍተኛ ሃላፊዎች ግልፅና ያልተሰወረ ሆኖ ሳለ ይህን ጥሪ በመደጋገም ማላዘኑ ለሰሚውና አንባቢው ግራ የሚያጋባ ሆኗል። ከዚህ ባለፈ ግን በአገሪቱ የሚካሄዱ ልማቶችን እንቅልፍ አጥቶ የሚቃወምና እርዳታም አትስጡ የሚል ሂዩማን ራይትስን የመሰለ ድርጅት በምን ሂሳብና ስሌትና እንዲሁም በምን አይነት አንጀቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰብአዊ መብት እንደሚቆረቆር ፍርዱን ለአንባቢ የምተወው ይሆናል።

ትናትና ቅኝ ገዥዎችን አሳፍሮ ሲመልስ የኖረው ኩሩውና ጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ትናንት ሰብአዊ መብቱንና ክብሩን ደፍረው አንገቱን ሊያስደፉት የሞከሩትን በማንበረከክ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቹ ኩራት እንደሆናቸው ሁሉ  ዛሬም በሰብአዊ መብት ካባ እየተጀቦኑ ከሶስት ወር አንድ ጊዜ በውንጀላና በጥላሸት የተቀባ ሪፖርት ይዘው ከች የሚሉትን እነሂዩማን ራይትስ ዎችን እንዳልተፈጠሩ ከመቁጠር አልፎም የፃፉት ሪፖርት ከተፃፈበት ቀለምና ወረቀት በላይ ዋጋ እንደሌለው በተግባር እያሳያቸው ይገኛል።