የአሸባሪዎች ትራጀዲ ተውኔት ሲጋለጥ

ቃልቤሳ ኦላና

በዳውሮ ተርጫ ከተማ አንድ ትራጀዲ ድራማ ለመጀመር ሴራ የማዋቀሩ ስራ ብዙ ጊዜ ተወስዶ በሚገባ ተጠንቷል። የትራጀዲው ድራማ መድረክ አቀናባሪዎች ሥራቸውን አቀላጥፈው ጨርሰዋል፡፡ የትራጂዲው አስተባባሪ የትራጀዲው ዋነኛ ተዋናይ ተፈልጐ በሚገባ ተጠንቶ እንዲዘጋጅ አድርገዋል።ለትራጀዲው ትወና የተመረጠ ዋና ተዋናይ የጤንነቱ ሁኔታ ለትራጀዲው ተውኔት ተስማሚ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡  በመስከረም ወርም ካለበት ቦታ ወደ  ዳውሮ ዞን ከተማ ተርጫ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ የትራጀዲውን ተውኔት የሚያቀላጥፋ የመድረክ አድማቂዎችና ተዋናዮች ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ አስተባባሪው በአሜሪካ፣ በስዊድንና በተርጫ ተዋናዮቹን እንዲሁም ትራጀዲውን የሚቀርፅና የሚያሰራጭ፣ የሚቀበልና ሚዲያ ላይ የሚያውል መሳሪያ አሰናድተዋል።  ስዊድን ያለው “የትራጀዲው ተውኔት አድማቂና አስተዋዋቂ” ፍሰሃ ተሰማ የተውኔቱን መጀመር እንደ “ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋው ቴሌቪዠን(ኢሣት)” ሁሉ በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነው፡፡ በተለይ “እሣት” ከተርጫ ከተማ የሚላክለትን የተቀረፀ ትራጀዲያዊ ተውኔት በአየር ላይ ለማዋልና ጠቅላላ የሴራውን መረብ ለማንቅሳቀስ በተረከዙ ላይ ቁጭ ብሏል፡፡ የፍሰሃ ተሰማን ማድመቂያ ቃለ-መጠይቅ አሰናድቶ ጨርሷል፡፡ ትራጀዲ ተውኔቱን የመድረስ ቅፅበት ብቻ ነው የሚጠብቀው፡፡

የትራጀዲው ተውኔት ዋና ሴራ አዋቃሪው ግንቦት ሰባት የትራጀዲው ድራማ አላባዊያንን፣ተዋንያንና አድማቂዎቹን በየቦታቸው አዘጋጅቶ ጥቅምት 3ዐ ጉዳዩን በማስመልከት በginbot7.org ድረ-ገፁ አማካይነት መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫውም “ትኩረት በሣይበር ለሚደረገው ትግል” የሚል ነው፡፡ ይህ መግለጫ ጥቅምት 3ዐ ሲሰጥ ህዳር 1 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ለሚደረገው እና በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ፣አሜሪካንና ስዊድን አስተሳስሮ የተቀናበረው ትራጀዲያዊ ድራማ ተዋናዮቹ የድርጊታቸው አፈፃፀም መርሀ-ግብር ተቀምሮ ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ ጉዳዩን  ለመቀባበልና ለማሰራጨት ጥሪ መድረጉ ነበር፡፡ የተርጫ ከተማ የትራጀዲው አቀናባሪ አካላት ህዳር 1 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም  ከቀኑ 9 ሰአት የትራጀዲው ዋና ተዋናይ እንዲሆን የተመረጠው “ምስኪኑ የኔሰው ገብሬ” በቤንዚን ራሱን እንዲያቃጥልና ወደ ስብሰባ ቦታ እንዲገባ አድርገው የቀረፃ ሥራውን እያቀላጠፉ ነበር፡፡ ያቀላጠፉትንም የትራጀዲ ድራማ የመድረክ ትውና ወደ ኢሣት በቅፅበት ያስተላልፋሉ። የየኔሰው ገብሬ ፎቶዎችም ቀድመው ተሰብስበው የተበተኑ ይመስላሉ።የመረጃ አቀባይና ተቀባይ የግንኙነት ሰንሰለት ብዙ ጊዜ የታሰበበት መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ በአጭር ደቂቃዎች ከተርጫ ከተማ ተነስቶ አሜሪካ ደርሶ በኢሣት ይሰራጫል፡፡ ስርጭቱን ተከትሎ የትራጀዲው ደራሲና አቀናባሪና በሀገር ክህደትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በመሞከር የሞት ፍድር የተወሰነበት የግንቦት 7  መሪ በሆነው ብርሃኑ ነጋ የተዘጋጀውና ስዊድን ያለው ፍሰሃ ተሰማ የትራጀዲውን ማጉያና ማጀቢያ ቃለ-ምልልስ ለኢሣት ለመስጠት ጥድፊያ ላይ ነው፡፡ አሸባሪዎቹ አሜሪካ፣ አውሮፓ ስዊድንና ከዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ በአውቶማቲክ የጥፋት መረብ ተሣስረው ደባ እያቀላጠፉ ነው፡፡ ያውም አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ምስኪን አቃጥሎ በመግደል “በፍትህ መዛባትና በመልካም አስተዳደር እጦት ራሱን አቃጠለ” በማለት መሴሪ ሴራ ፈጥረው በምድረ-ኢትዮጵያ ህዝባዊ ነውጥ በመፍጠር ሥልጣን ያስይዘናል ያሉትን ትስስር በሚገባ ተዘርግተዋል ፤ሁሉም አስፈላጊ ስልቶች፣ አጀንዳዎችና ፈፃሚዎች በብርሃኑ ነጋ ሪሞት ኮንትሮል ይንቀሣቀሣሉ፡፡ ይህ አይደል- ሁሉን አቀፍ የአሸባሪው የግንቦት 7 ትግል ስልት፣ የቀለም አብዮቶኞች፣ የአመፅ ናፋቂ የሀገር ውስጥ የጥፋት ሃይሎችና ልሳኖቻቸው  ሥራስ?  ይህ ትራጄዲ በዚህ መልክ ተቀምሮ በየኔሰው ገብሬ ላይ ለተፈፀመው ሰይጣናዊ ስራ ሌላ ትርጉም ለመስጠት የተሰናዳው አጀንዳና ስልት እንዲሁም የአሰላለፍ ቅንብር በሀገራችን የተተበተበውን የአሸባሪዎች መረብ ከማጋለጥ ውጭ ምንም የሚያመጣው ለውጥ አልነበረውም፣አኖረውምም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ቀንና ሌሊት በመረባረብ  ሀገራቸውን እየገነቡ ነውና። እነዚህ ክቡር የሰው ልጅን አቃጥለው፣ ያውም በአእምሮው ችግር ያለበት ህመምተኛ በአሜሪካ በኢሣትና ግንቦት 7፣ በአውሮፓ ስዊድን ባለው ፍሰሃ ተሰማና በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ የተዘረጋው የጥፋት ድርጊት ለማቀላጠፊያና ድርጊቱን ለእኩይ ተግባር ለመጠቀም የተዘረጋው መረብ የመጨረሻ ይሆን እንደሆነ እንጂ የመጀመሪያ ግን አይደለም፡፡ ስለ የኔሰው ገብሬ የአዕምህሮ ህመምተኝነት ጉዳይ የጥፋት ሃይሎቹ ራሳቸው የትራጀዲው ትወና ከመጀመሩ በፊት ለጥፋት ባሰናዱት በፌስ ቡካቸውና ድረ-ገፃቸው ላይ  የለጠፉት  ፎቶ ራሱ የሚመሰክርባቸው ነው፤ ህመምተኛ መሆኑን ያሳብቅባቸዋል። እህቱና ዘመዶቹ ህመምተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፤ወደ ተርጫም መስከረም ውስጥ መምጣቱን አስረግጠዋል።

የአሁኑ ትራጀዲያዊ ድራማ በጥፋቱ መረብ የተሣሰሩት ሃይሎች ምን ያህል       ኢ-ሰብአዊ አቋምና እምነት እንዳላቸው በይፋ አረጋግጧል፡፡ ይህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ምን ያህል ታስቦበት እንደተካሄደና የድርጊት መርሀግብር፣ የአፈፃፀም ስልቶች፣ አጃቢ ሚዲያዎችና ፈፃሚ አካላት ከሦስት አህጉር መተሣሰራቸውን ከማረጋገጡም ሌላ ጥፋት ለመፈፀም የማይተኙ መሆናቸውን አሣይቷል፡፡ ይህ የአሸባሪዎች ድርጊት የመጨረሻ ይሆን እንደሆነ እንጂ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በ1997 በአዲስ አበባ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ነውጠኛው ቅንጅት ሞክሮታል፡፡ ግንቦት ሰባትም ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን ለማውደምና የመንግስት ባለስልጣናት ለመግደል፤ ህዝብን አፋጅቶ ስልጣን ለመያዝ ተፍጨርጭሮ ነበር፡፡ ህገ- መንግስታዊ ሥርዓቱን በአመፅና በሽብር ለመናድ አሸባሪዎቹ ተራውጠዋል፡፡ በዚህ ወቅት አሁን መረጃ ተገኝቶ በሽብርተኝነት የሚፈለገው አብይ ተክለ ማሪያም “የመፈንቅለ መንግስቱ ድራማ ጥቁሯን ድመት ጨለማ ውስጥ መፈለግ ሆነብኝ” በማለት የጉዳዩ አካል ሆና ሲያበቃ መሳለቁ ይታወሳል። የእነዚህ የጥፋት አካላት ድርጊት አሸባሪነት መሆኑ በመረጋገጡ ለህግ ውሳኔ ተፈፃሚነት የሚፈለጉ ናቸው፡፡

በመሆኑም እነዚህ ተስፋ የቆረጡ አሸባሪዎች እንደዚህ ያሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን መፈፀማቸውም አይገርምም፡፡ የሚገርመው የዚህ ድርጊት አቀናባሪ የሆነው አሸባሪው ግንቦት 7 ከነውጠኛው ቅንጅት የወጣ መሆኑ ትዝ ብሎት ወይም ደግሞ “የቅንጅት ወራሽ እኔ ነኝ” የሚለው አቋሙ የሚያስረግጥ በሚመስል መልኩ አንድነት ይህንን ትራጀዲያዊ ትይንት ወይም ድራማ ከላይ በመረጃ ላይ ተመስርቶ  የተቀነባበረውን እኩይ ድርጊት የመንግስት ሃጥያት አድርጎ አዲስ አበባ ለሚገኙት ኤምባሲዎች፣ ለአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን  ማሰራጨቱ ነው፡፡ ይህ የአንድነት ድርጊት ከዚህ በፊት አንዳንድ አመራሮችን ብቻ ይመለከት የነበረው የአሸባሪነት ጉዳይ አሁን ድርጅቱ የት እንደቆመ እያመላከተ ነው፡፡ አሁን የተደበቀው የአሸባሪዎች የጥፋት መዋቅር ለመጨረሻ ዘመቻው የተጋለጠ ይመስላል፡፡ “የድል ቀን”፣ “በቃ” ፣ “የወያኔ ባርነት ይብቃኝ!እርሶስ?”፣ “የለውጥ ዋዜማ”፣ “የወጣቶች ንቅናቄ”   በሚሉት የአሸባሪዎቹና ተባባሪዎቻቸው በፌስ ቡኮችና መሰል መረቦች ከዓመት በፊት የተጀመሩት የጥፋት ዘመቻዎች ፈፅመው አልተሳኩም።ወደፊትም አይሳኩም። የአሸባሪ መረቦች ህዝብን ለማጫረስ ሲቅምጡ ህዝቡ በትግሉ እያመከናቸው ነውና።

አሁን አሁን የኢትዮጵያ ህዝቦች የአሸባሪዎቹ ድብቅ የጥፋት መዋቅር የትየት እንደተሣሰረና ህዝቡን ለማጫረስ አመቺ ሁኔታ ሲያገኝ እንደሚጋለጥ በግልፅ ተገንዝበዋል። በዚህ ትራጀዲ  ደግሞ ይበልጥ በይፋ የሚገነዘቡበት ትክክለኛ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ህዝቡም ከሀገር ውጭ ያሉት በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኛ አሸባሪዎች ምን እየሰሩ እንዳሉና ከሀገር ውስጥም ከማን ጋር እንደተሳሰሩ  አሁን ብዙ አስረጂ አላስፈለገውም፡፡ የአደባባይ ሚስጥር እየሆነ ነው።

የግንቦት 7 የጥቅምት 3ዐ ትራጀዲው ቅንብሩን ለመቀባበል ለጥፋት መረቡ ያስተላለፈው ተዘጋጁ መግለጫ ፤የምስኪኑ የኔሰው ገብሬን አቃጥሎ የመግደል ትራጀዲ ድራማ በተርጫ ከተማ ማቀነባበርና ማሠራጨትን ተከትሎ ፍሰሃ ተሰማ ከስዊድን ለኢሣት ቃለ ምልልስ መስጠት እንዲሁም የአንድነት ፓርቲንና የኢራፓ ጉዳይን ለማቀጣጠል በይፋ ተገልጠው በአስቸኳይ ማሠራጨት የጥፋት ቅመራና ቅንብር የአሸባሪዎቹ የጣረሞት ርብርብ ኢትዮጵያ የጀመረችው የፀረ-ሽብር ትግል ስኬታማ ለመሆኑ አንዱ ማሣያ ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ ህዳሴ የፀረ-ኢትዮጵያና የፀረ-ህዝብ ሃይሎች የመጨረሻው ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ከንቱ ዘመቻ አካል መሆኑን አረጋግጧል፤ለሰፊው ህዝብም አጋልጧቸዋል። በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት ፈፅሞ አይሣካም፡፡ ይህ የማይሣካው አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሥርዓት ህዝባዊ መሠረቱ 85 በመቶ በላይ የገጠሩ አርሶ አደርና አርብቶ አደር እንዲሁም በከተማ አብዛኛው የሚኖረው ሰርቶ አደር ስለሆነ ነው፡፡ በጥቂት “የጥፋት የምፅአት ቀን” ናፋቂዎች ከንቱ መፍጨርጨር የሚወለድ አብዮት ሆነ ጥፋት አይኖርም።

ኢትዮጵያ አሁን የታላላቅ ኢንቨስተሮች መዳረሻ ነች። ሀገሪቷን በመሠረቱ የሚለውጡ ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሚካሄዱባት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች ነገ ታላላቅ ኩባንያዎችንና ኢንዱስትሪዎች መሠረት በሚሆኑት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተሰማርተው ሀገራቸውን የሚገነቡበት ሀገር ናት፡፡ በ31 ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩትን ጨምሮ ከ2ዐ ሚሊዮን የሚሆኑ ዘጎች አሁን ለኢትዮጵያ ህዳሴና የህዝቦችን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትምህርት ላይ ናቸው፡፡ የአብዛኛዎቹን የአለም ሀገራት ህዝብ ብዛት የሚበልጥ ዜጋ በኢትዮጵያ በትምህርት ላይ ነው፡፡ መንግስትም ሀገሪቷ መሠረታዊ ለውጥ አምጥታ ወደ ኢንዱስትሪ እንድትሸጋገር  የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አውጥቶ በመተግበር ላይ ነው፡፤ ለገቢራዊነቱም ህዝቡ ከዳር ዳር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስቷ ዜጎች ሥራ ፈላጊ ብቻ ሣይሆኑ ሥራ ፈጣሪ ሆነው ሁሉም በሥራው ልክ የሚጠቀምባት ሀገር መሆኗ ተረጋግጧል።፡ ኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ሆና በዜጎቿና በውጭ ሀገራት ጭምር ከፍተኛ ተስፋ ያላት ሀገር ሆናለች፤አሁን በኢህአዴግ አመራር፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ በማይናወጥ ዘላቂ ሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ እየታነፀ ያለች በመሆኗ ሁሉም ዜጋ ሰላሙና ልማቱ እንዳይደናቀፍ በንቃት ይጠብቃል፡፡ በወጣቶች እጅ እሣት በመያዝና በንፁሃን ደም ስልጣን የሚያዝበት ኋላቀር አስተሳሰብና ተግባር አሁን ቦታ የለውም፡፡ የጥፋት ሃይሎች የጥፋት ቅንብር በመፍጠር ህዝብ ከህዝብ በማጋጨትና በንፁሃን ወጣቶች ደም ስልጣን ለመያዝ የሚያደርጉት ቀበፀ-ተስፋ መፍጨርጨር ፈፅሞ አይሣካም፡፡

“ቀበሮ የበሬ ምንትስ ይወድቅልኛል ብላ ስትባክን ዋለች” እንደሚባለው እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ከንቱ ልፋት የራሳቸው ጉዳይ ቢሆንም ክቡር የሰው ልጅን አቃጥሎ በመግደል ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉትን ሰይጣናዊ ድርጊት ግን ለሰብአዊ ክብር የቆመና ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ሊታገለው ይገባል።