ኀዳር 29 የዕኩልነትና የኀብረት ቀን


ከንጋቱ ደስታ

የአገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አስከፊ ጭቆና የተላቀቁበትና የእኩልነትና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ያረጋገጡበት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ህዳር 29 “የኢትየጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንበሀገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ከጀመሩ እነሆ 6 ዓመታት ሞላቸው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ 80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ቅርሶች፣ ወጐችና እምነቶች ባለቤቶች በመሆናቸው የቋንቋና የብሔረሰቦች ተመራማሪዎች አገራችንን የብሔረሰቦች ሙዚየም የሚል ስያሜ አሰጥተዋታል፡፡ ዛሬ በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ በጋራ የሚኖሩት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሁን በሚገኙበት የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የልማት ዘመን ከመድረሳቸው በፊት እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፉ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችውን ቅርፅና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ይዛ የተፈጠረችው በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ በፊት የአገራችን ሕዝቦች በተለያዩ ራሳቸውን በቻሉ የተለያዩ ነፃና ከፊል ነፃ መንግሥታት ይተዳደሩ ነበር፡፡ በአገሪቱ ሰሜናዊና ማዕከላዊ ክፍል ከሰፈሩት የትግራይ፣ የአማራና የአገው ሕዝቦች ባሻገር የኦሮሞ፣ የሱማሌ፣ የአፋር፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የከፋ፣ የጉራጌ፣ የሃድያ፣ የከንባታ፣ የሃረሪወዘተ ሕዝቦች የራሳቸው እጅግ ጠንካራ አስተዳደሮች እንደነበራቸው ታሪክ ያስረዳል፡፡

የአፄ ምኒሊክ ጦር በሕዝቦች ላይ ያካሂደው የነበረው በኃይል የማስገበር እንቅስቃሴ ተቃውሞ የገጠመው በተናጠል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የምኒሊክ ወረራ ያሰጋቸው የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የሐረሪና የሶማሌ ሕዝቦች ክንዳቸውን በማስተባበር በጦር መሣሪያም ሆነ በአደረጃጀት ከነርሱ በተሻለ ደረጃ ይገኝ የነበረውን የምኒሊክ ጦር ተፋልመዋል፡፡

ከምኒሊክ በኋላ ሥልጣኑን የጨበጡት አፄ ኃይለሥላሴም በምኒልክ የተፈጠረውን የተማከለ አገዛዝ አጠናክረው ቀጠሉበት፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓትም በገጠር የመሬት ከበርቴዎች የሚደገፍና እጅግ የተማከለ አገዛዝ በመመሥረት በአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ላይ እጅግ ከባድ የብሔሮች ጭቆናና የብዝበዛ ቀንበር የጫነ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ግፍና ጭቆና ሕዝቡ አሜን ብሎ የተቀበለበት ወቅት አልነበረም፡፡ ለዚህም የትግራይ፣ የባሌ፣ የሲዳማ፣ የሶማሌና ሌሎች ሕዝቦች ፀረኃይለሥላሴ የአመጽ እንቅስቃሴ በምሣሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ 1960ዎቹ መጀመሪያ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ በመሠረቱ ያነገባቸው መፈክሮች መላ ያገራችን ሕዝቦች ለዘመናት ሲታገሉላቸው የነበሩ መፈክሮች ናቸው፡፡ መሬት ላራሹ፣ ህዝባዊ መንግሥት ይመስረት፣ የብሔርና የሃይማኖት ጭቆና ይወገድ የሚሉት ጥያቄዎች በወቅቱ ይነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት ነው በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በተማረው የኀብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተነስቶ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው፡፡

በገጠርና በከተማው የተቀጣጠለው የህዝብ አመፅ የኃይለሥላሴን ሥርዓት ሲያንኮታኩተው በወቅቱ የተደራጀ ፖለቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ የመንግሥት ሥልጣን በወታደራዊ መኰንኖች እጅ ወደቀ፡፡ ሥልጣኑን በእጁ ያስገባው ወታደራዊ ደርግ የሕዝቡን ጥያቄዎች የተቀበለ መስሎ የተነሳውን አመጽ ለማብረድ አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድም የቀድሞው ሥርዓት ይከተለው የነበረውን የተማከለ ሥርዓት አስተዳደር ነበር የቀጠለው፡፡ የብሔር፣ ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በደርግም ሊከበር አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎም ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችን ገንጣዮች፣ አስገንጣዮች በሚል ቅፅል በመለጠፍ በኃይል ለማፈን ተንቀሳቀሰ፡፡

የብሔር ጥያቄ የአገራችን ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጥያቄዎች ሁሉ ማጠንጠኛ በመሆኑ በአብዛኛው የአገራችን ሕዝቦችም በዚህ ጥያቄ ሥር ተሰልፈው ደርግን ታግለው ሊጥሉ ችለዋል፡፡ በዚህም የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነ በአገራችን አንድ የጋራ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኀበረሰብን መገንባት ዓላማ ያደረገ ሕገ መንግስት ሊፀድቅ ችሏል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ቀደም ሲል የነበሩት አሃዳዊ መንግሥታት የህዝቦችን ልዩነቶች በኃይል ለማጥፋትና ካለፍላጐታቸው ለማዋሃድ ያደረጉት ሙከራ እንዲከስም ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህሎቻቸውን፣ ወጐቻቸውንና ታሪካቸውን በእኩልነት እንዲያዩ፣ እንዲንከባከቡና እንዲያዳብሩ የሚያበረታታ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህም ልዩነትን በመቀበልና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲፈጠርና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ፣ የማኀበራዊና የኤኮኖሚያዊ መግባባቶች እንዲዳብሩ አስችሏል፡፡

ኀዳር 29 ቀን የሚከበረው ይህ በዓል በአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የመቻቻልና የኀብረት መንፈስ እንዲጠናከር የጋራ ሃብታቸውን በጋራ እየተቋደሱ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል፡፡በየዓመቱ ይህንን የነፃነታቸውንና የእኩልነታቸውን ቀን በጋራ በማክበር እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትን፣ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚመክሩበትን፣በቀድሞ ገዥዎች ምክንያት በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና መፈራራት /ቅራኔ/ እያስወገዱ አንድነታቸውን የሚያጐለብቱበትን፣ ልዩነታቸው ውበታቸው፣ ያንድነታቸውና የጥንካሬያቸው መገለጫ መሠረት መሆኑን የሚያረጋግጡበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

መላ የአገራችን ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን የዘንድሮውን ኀዳር 29 ቀን ሲያከብሩ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትግል አገራችን እያስመዘገበች ያለውን ልማት ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ ቃል የሚገቡበትና ለቀጣይ ልማታቸው ኀብረታቸውንና አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆን አለበት፡፡