የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት እየጨመረ ሲሄድ የሲሚንቶ ፍላጎትም በተመሳሳይ መንገድ እያደገ እንደሚሄድ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያም እየተካሄደ ባለው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴና የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገት የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።
በተለይም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ ላይ የሲሚንቶ ፍላጎቱ ወደ 27 ሚሊዮን ቶን ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ጠቋሚ የሆኑ ማሳያዎች እንዳሉ ይታመናል።
በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተቀመጠው የሲሚንቶ ፍላጎት ትንበያ እንደሚያሳየው በ2002 ዓ.ም አጠቃላይ አመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት 8 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን የነበረ ሲሆን፣ በ2003 ደግሞ ወደ 11 ሚሊዮን ቶን ደርሶ ነበር። በዘንድሮው የበጀት ዓመትም 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን የሲሚንቶ ፍላጎት እንደሚኖር ነው ትንበያው የሚጠቁመው።
እንዲሁም በሚቀጥለው የበጀት ዓመት መጨረሻ 17 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን ይደርሳል፣ በ2006 ዓመተ ምህረት 21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ሊደርስ የሚችል ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ማለትም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ ላይ የሀገሪቱ አጠቃላይ የሲሚንቶ ፍላጎት 27 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
መንግስትም በ2007 ዓ.ም መጨረሻ 27 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ገበያ ውስጥ በማቅረብ አሁን ያለውን 35 ኪሎ ግራም የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍላጎት ወደ 300 ከፍ ለማድረግ አቅዷል።
በሀገር ውስጥ ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገርም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠር የሚል ዓላማን በመያዝ የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎችን ከወሰደ አመታት ተቆጥረዋል።
ከወሰዳቸው የአጭር ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሲሚንቶ ምርትን ከውጭ ማስገባት ነው። በዚህም በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን የሲሚንቶ እጥረት በተወሰነ ደረጃ መፍታት ተችሏል።
በሌላ በኩልም ዕድገቱ የፈጠረውን ወቅታዊ የሲሚንቶ እጥረት ለዘለቄታው ከመፍታት አኳያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመዘርጋት ልማታዊ ባለሀብቶች በስፋት በሲሚንቶው ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩና እንዲሳቡ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረጉ 37 አዳዲስና ነባሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 54 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ካፒታል የግንባታና የማስፋፊያ ስራዎችን ለማካሄድ ፈቃድ ወስደው ወደ ልማት ከገቡ ውለው አድረዋል።
ፍቃድ ወስደው ወደ ልማቱ ከገቡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከልም ነባሮቹን የሙገር፣ የመሰቦና የናሽናል የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ 7 የሚሆኑ ማምረት ጀምረዋል።
ፋብሪካዎቹ ማምረት በመጀመራቸውም በአሁኑ ወቅት 7 ሚሊዮን 836 ሺ ቶን ሲሚንቶ ለገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይም 12 ነጥብ 61 ሚሊዮን ቶን ለገበያ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የሲሚንቶ ፍላጎት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን 215 ሺ 941 ቶን ጨምሮ 8 ሚሊዮን ቶን ደርሷል።
ይህንኑ ፍላጎት ለማሟላትም በዘንድሮው አመት ሰባት የሚሆኑ ፋብሪካዎች ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከሰባቱ ሁለቱ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ናቸው።
በሚቀጥለው የበጀት ዓመትም አንድ ፋብሪካ የማስፋፊያ ስራውን በማጠናቀቅ ወደ ማምረት ይሸጋገራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በ2006 ዓመተ ምህረት ደግሞ ሁለት አዳዲስና አንድ የማስፋፊያ ፋብሪካ ወደ ማምረት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2007 የበጀት ዓመት ደግሞ አንድ ፋብሪካ ወደምርት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ ፋብሪካዎች ባስቀመጡት የስራ እቅዳቸው መሰረት መሄድ ከቻሉ ከመሰረታዊ የኮንስትራክሽን ግብአቶች መካከል ዋነኛውና ለአንድ አገር የመሰረተ ልማት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለውን ሲሚንቶ በማምረት በሀገሪቱ የተጀመረውን ፈጣን ልማት ያስቀጥላሉ። ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬትም ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።