ሕዝብ ጥቅሙን እንዲቃወም የተካሄደ ዘመቻ

አዲስ ቶልቻ

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለማይዝ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀደቆ ሕዳር 18/2004 ዓ/ም በነጋሪት ጋዜጣ የወጣው አዋጅ የሠሞኑ የመወያያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡ የዚህን አዋጅ መሰረታዊ ይዘት ለመረዳት ከአዋጁ ከመነሣት ይልቅ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ላይ ስለመሬት ይዞታና አጠቃቀም የተደነገገውን መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀፅ 4ዐ ንዑስ አንቀፅ 3 “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ይላል፡፡ ባለሃብቶች በዚህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት በሆነ መሬት የሚጠቀሙበትም ሁኔታ በዚሁ አንቅፅ ንኡስ አንቀጽ 6 ላይ “መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሠናል” በሚል ሰፍሯል፡፡

“የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ” በሚል በቅርቡ የወጣው አዋጅ፣ በዋነኛነት ከላይ በተጠቀሱት የሕጎች ሁሉ  ምንጭ የሆነው ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአዋጁ ላይ አስተያየት የሰጡ አንዳንድ ግለሰቦችና የፖሎቲካ ፓርቲዎች፣ የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጅ ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች፣ ከዚህ ቀደም የማይታወቅና አዲስ አድርገው ያቀረቡበትን ሁኔታ አስተውለናል፡፡ በተለይ አነጋጋሪ የሆነው የአዋጁ ክፍል ነባር ይዞታን የሚመለከተው ነበር፡፡ አዋጁ “ነባር ይዞታዎችን ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየርበት ሁኔታ” በሚለው ርዕስ ንዑስ (አንቀፅ 6) ስር ይህን ጉዳይ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን በግልፅ አስፈሯል፡፡ በዚሁ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 3 በነባር ይዞታ ላይ የሠፈረ ንብረት ባለቤትነት ከውርስ በስተቀር በማንኛውም መንገድ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ፣ ንብረቱ የተላለፈለት ሰው የቦታው ባለይዞታ ሊሆን የሚችለው በሊዝ ሥሪት መሠረት ይሆናል” ይላል፡፡ ከዚህ ባለፈ፣  የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ከዚህ፣ “ነባር ይዞታዎች በቀጥታ ወደሊዝ ይተላለፋሉ” የሚል ድንጋጌ የለውም፡፡ ነባር ይዞታ ወደሊዝ ሥርዓት የሚገባው፣ ባለይዞታው በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት በቃኝ ብሎ መሬቱን ከውርስ ውጭ ወደሌላ ወገን ሲያስተላልፍ ብቻ ነው፡፡ በውርስ ሲዘዋወር  ነባር ባለይዞታነቱ እንደነበረ ይቀጥላል፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሕዝቡ ዘንድ የተነሳና ጎልቶ የወጣ አንድ ጥያቄ ተስተውሏል፡፡ይህም አዋጁ ነባር ባለይዞታዎች “የእኔ ነው” ብለው ይዘውት የቆዩትን መሬት በሽያጭ ወደ ሌላ ሰው አዘዋውረው የመጠቀም መብታቸውን ያሳጣል  የሚለው ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ እይታ ይኖረን ዘንድ ቀደም ሲል ከጠቀስነው  የሕገመንግስቱ አንቀፅ 40 ንኡስ አንቀጽ 3 አኳያ ማየት ይኖርብናል፡፡ በዚሁ የሕገመንግስቱ  አንቀፅ መሠረት መሬት የግለሰቦች የግል ሃብት አይደለም፣ የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሐብት እንጂ፡፡ በመሆኑም በቅርቡ ከወጣው የሊዝ አዋጅ  ቀደም ሲል  መሬት የያዙ ግለሰቦችም በመሬቱ ላይ ያላቸው መብት የመጠቀም መብት ብቻ ነበር፡፡ መሬቱን የያዙት ከመንግስት ጋር በገቡት የኪራይ ውል በመሆኑ  የኪራይ ይዞታ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ባለይዞታዎች የቦታ ግብር በሚል መሬቱ እንደሚገኝበት ከተማ በካሬ ሜትር የተወሰነ የኪራይ ክፍያ በየአመቱ ሲከፍሉ መቆየታቸውም ይታወቃል፡፡ ለማለት የተፈለገው ይህ አሁን የወጣው የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጅ የነባር ባለይዞታዎችን የኪራይ ባለይዞታነት መብት አልነካም፡፡ ይሁን እንጂ ነባር ባለይዞታው በኪራይ የያዘው መሬት ላይ ያለውን የመጠቀም መብት “በቃኝ” ብሎ ከውርስ  ውጭ ወደ ሌላ ሦስተኛ ወገን ሲያዘዋውር፣ አዲሱ ባለይዞታ መሬቱን የሚይዘው ከመንግስት ጋር በሚገባው የሊዝ ስምምነት ይሆናል፡፡   የከተማን መሬት አጠቃቀምና ባለይዞታነት የሚወስን አዋጅ ወጥቶ በስራ ላይ በመዋሉ አዲሱ ባለይዞታ በዚህ አዋጅ መሠረት ከመንግስት ጋር የሊዝ ውል ተስማምቶ መሬቱን እንዲይዝ  ይደረጋል ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ በብዙዎች ዘንድ መደናገርን የፈጠረው፣ “ነባሩ ባለይዞታ በመሬቱ ላይ የነበረውን  የመጠቀም መብቱን ለሦስተኛ ወገን አሣልፎ ሲሰጥ የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው?” የሚለው ነው፡፡ ይህ መደናገር የተፈጠረው መሬትን ሕገመንግስቱ ላይ ከሰፈረው ድንጋጌ ውጭ እንደሚሸጥና እንደሚለውጥ የግል ንብረት በመመልከት ነው፡፡ ይህም “ባለይዞታው መሬቱን የመሸጥ መብት ነበረው፣ አዋጁ ይሕን መብቱን ነጠቀው” የሚል የተሳሳተ መነሻ አለው፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቦች ወትሮም የባለቤትነት መብት ያላቸው በመሬቱ ላይ ሳይሆን፣ በመሬቱ ላይ ባፈሩት ንብረት ላይ ብቻ ነው ፡፡ ይህም ሆኖ፣ ማለትም ነባር ባለይዞታዎች የባለቤትነት መብቱ የሕዝብና የመንግስት በሆነው መሬት የመጠቀም መብት ስላላቸው፣ ይህን የመጠቀም መብታቸውን አሳልፈው መስጠት ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ  መጪው የመሬቱ ባለይዞታ መሬቱን የሚይዘው ከመንግስት ጋር በበሚገባው የሊዝ ስምምነት መሰረት ነው ካልን፣ ይህ መሬቱን የመጠቀም መብቱን አሳልፎ የሚሰጠው ነባሩ ባለይዞታ ወደሚያገኝው ጥቅም እንመለስ፡፡

በቅረቡ የወጣው የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጅ የነባር ይዞታን የመጠቀም መብትን የማስተላለፍ ጥያቄን በተመለከተ ግልፅ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የአዋጁ አንቀፅ 6 ንኡስ አንቀፅ 7 “ወደ ሊዝ ሥሪት የሚገቡ ይዞታዎችን በተመለከተ ተፈፃሚ የሚሆነው የሊዝ ክፍያ መጠን በአካባቢው የሊዝ መነሻ ዋጋ መሠረት ይሆናል” ይላል፡፡ እዚህ ላይ በሊዝ መነሻ ዋጋና በጨረታ የሊዝ ዋጋ መሃከል ሠፊ ልዩነት ያለ መሆኑ ሊታወስ ይገባል፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ ላይ እስካሁን የሚሰራበት የሊዝ የመነሻ ዋጋ በካሬ ሜትር 200 ብር ነው፡፡ ይሁን እንጂ መሬቱ እንደሚገኝበት ሁኔታ በካሬ ሜትር ከ 20 ሺህ ብር በላይ የሊዝ ጨረታ ዋጋ የተሸጠበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ በሊዝ የመነሻና የጨረታ ዋጋ መሃከል ያለው ልዩነት ይህን ይመስላል፡፡

እንግዲህ አንድ ነባር ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት ለሌላ ግለሰብ /ድርጅት/ አሣልፎ ሲሰጥ፣ መንግስት ከአዲሱ ባለይዞታ ጋር የሊዝ ሥምምነት የሚገባው በጨረታ ሣይሆን በሊዝ መነሻ ዋጋ ነው ማለት ነው፡፡ ነባር ባለይዞታውና አዲሱ ባለይዞታ በመነሻና በጨረታ ዋጋ መሃከል ባለው ልዩነት ላይ ይደራደራሉ፡፡ በሁለቱ ስምምነት መሰረት ከሊዝ መነሻ ዋጋ በላይ ያለውን ክፍያ የሚያገኘው ነባር ባለይዞታው ይሆናል፡፡ እርግጥ በሊዝ መነሻና በጨረታ ዋጋ መሃከል ነባር ባለይዞታውን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ጉልህ ልዩነት እንዲኖር መሬቱ በአግባቡ የለማ ሊሆን ይገባል፡፡ መሬቱ በሚገኝበት አካባቢ የመሰረተ ልማትና  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም በዋጋው ልዩነት ላይ ተፅእኖ አለው፡፡ የመሬት አቅርቦትና ፍላጎት ሚዛንም እንዲሁ ትፅእኖ  ይኖረዋል፡፡ መንግስት ለሊዝ የሚያቀርበው መሬት፣ ማለትም የመሬት አቅርቦት መጠን ከፍላጎት ጋር ያለው ንፅፅር በጨረታ መድረሻ ዋጋ ላይ እንዲሁ ተፅእኖ ይኖረዋል ማለት ነው ፡፡

እዚህ ላይ ዋናው ትኩረት ሊሠጠው የተፈለገው ነባር ባለይዞታው የመጠቀም መብቱን ለሦስተኛ ወገን ሲያሣልፍ ከጨረታ መነሻ በላይ ባለ ዋጋ ላይ የመደራደር መብት ያለው መሆኑና፣  የሚያገኘው ጥቅምም ከሊዝ መነሻ ዋጋ ባላይ ያለው በመሬት የመጠቀም መብቱን ተደራድሮ ያስተላለፈበት ዋጋ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንግስት ከአዲሱ ባለይዞታ ጋር የሊዝ ውል ከሚገባበት መነሻ ዋጋ በላይ ያለው የመሬት ዋጋ ለነባር ባለይዞታው የሚከፈል ነው፡፡

ነባር ይዞታን ከማዘዋወር ጋር በተያያዘ አዋጁ የሚለው ከላይ የተጠቀሱት ቢሆንም፣ አዋጁ የመጣባቸውና ድንጋጤ ላይ የወደቁ ወገኖች እንዳሉ ግን ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች መሬት ከያዙ በኋላ፣ ካፒታላቸውን ኢንቨስት አድርገው ከማልማት ይልቅ አጥረው በማቆየት  በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያጋብሱ የቆዩ ናቸው፡፡ የዚህ አይነት ግለሰቦች በከተማዎች አካባቢ ካፒታላቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ኢንቨስት አድርገው ትርፍ የሚያስገኝ አንድም የልማት ሥራ ሣይሠሩ ንብረትነቱ የሕዝብና የመንግስት የሆነን መሬት በማቀባበል ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ “ከሠማይ ወረደላቸው እንዴ!” እስከሚያስብል ድረስ ሚሊየነር ለመሆን በቅተዋል፡፡ አሁን የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ይህን ሕገወጥና ተገቢ ያለሆነ ከፍተኛ ጥቅም ያስቀራል፡፡ በአዋጁ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያቀረቡትም እነዚህ ሕገወጥ ጥቅም የቀረባቸው ጥቂት ግለሰቦች  ናቸው፡፡ እነዚህ አዋጁ የመጣባቸው ግለሰቦች አደናግረው  ከጎናቸው የሚሰለፉ ዜጐችን ለማፍራት ካነሱዋቸው ማደናገሪያዎች መሃከል፣ “አዋጁ ዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል መሬት የሚያገኝበትን ዕድል ይዘጋል፡፡ የሚጠቅመው ገንዘብ ላላቸው ባሐብቶች ብቻ ነው” የሚለው  ይገኝበታል፡፡ እነዚሁ ግለሰቦች  እንደግለሰብም እንደዜጋም ከአዋጁ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጐችን አደናግረው ለተቃውሞ አብረዋቸው እንዲሠለፉ ለማድረግም ጥረዋል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ለተፈጠረው መደናገር ዕውነታውን አዛብተው ያቀረቡ የተወሰኑ የመገናኛ ብዙሃን አስተዋፅኦም አለበት፡፡

መንግስት ያወጣው የሊዝ አዋጅ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ባለመኖሪያ ቤት ለማድረግ የተያዘውን ፖሊሲ አይፃረርም፡፡ የጋራ የተፈጥሮ ሃብት ከሆነው መሬት ላይ መንግስት የሚያገኘውን ገቢ በማሳደግ መሰረተ ልማት በተሟላባቸው አካባቢዎች የኮነዶሚኒየም ቤቶችን የማስገንባት አቅሙን ያሳድጋል፡፡  በተጨማሪም ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጐች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ ላይ ላተኮረው ለሪል ስቴት ግንባታ  መሰረተ ልማት  የተሟላለት  የመሬት አቅርቦት ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡

በግል የመኖሪያ ቤት ለመገንባት ለሚፈልጉ ዜጐችም መሬት በጨረታ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጐች ይጎዳል የሚባለው ለሊዝ የሚከፍሉትን ዋጋን በማሰብ ከሆነ፣ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰበ ክፍል ላይ ያተኮረው የኮንዶሚኒየም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እነደተጠበቀ ሆኖ፣ መኖሪያ ቤት ለመገንባት በሊዝ መሬት የሚወስዱት ሰዎች የሊዝ ክፍያውን የሚፈፅሙት በአንድ ጊዜ ሣይሆን በ5ዐ ዓመት በመሆኑ ክፍያው ከአቅም በላይ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ አሁን የከተማ መሬት ግብር እየተባለ ነባር ባለይዞታዎች  ከሚከፍሉት ኪራይ የበለጠ አለመሆኑም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከምንም በላይ መታወቅ ያለበት ግን መሬት የሕዝብ የጋራ ሐብት የሆነና ዋጋ ያለው የምርት ግብአት በመሆኑ፣ መንግስት ከመሬት የሚያገኘውን ገቢ በማሳደግ በአጠቃላይ ለዜጐች ሊያስገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ነው፡፡

አዋጁ መሬትን እንደ ግብአት በመጠቀም ሐብት ማፍራት ለሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መሬት ለማግኘት በሚከፍሉት የሊዝ ክፍያ የሚገኘው ገቢ የከተማን መሠረተ ልማት ለማስፋፋትና ለመገንባት ይውላል፡፡ ዜጐች የተሟላ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል … አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስቻል የመንግስትን አቅም ያጐለብታል፡፡ በዚህ አኳኋን ባለሐብቶችም ይሁኑ አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጐች አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በሕገመንግስቱ መሰረት የሕዝብ የጋራ ሃብት ከሆነው መሬት፣ ሕዝብ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ማለት ነው፡፡

አዋጁ  ከባለሐብቶች፣ አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጐችና በአጠቃላይ ከሕዝብ ጋር በተያያዘ በተገናኘ የሚኖረውን ፋይዳ በዝርዝር ማቅረብ ሌሎች አዋጆችን ደንቦችንና ፖሊሲዎችን መጥቀስ ስለሚፈልግ ለመጠነኛ ዕይታ ይህን ያህል ካልኩ ይብቃኝ፡፡ አሁን በአዋጁ ላይ የተወሰኑ ፖለቲከኞች ወደያዙት አቋም ልመለስ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አዋጁን በተመለከተ በቅርቡ  መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ መድረክ በአዋጁ ላይ ባወጣው መግለጫ “የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጁ የከተማ ነዋሪዎችን ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የማስተላለፍ መብት የሚሸረሽር ነው፤ አዋጁ በተዘዋዋሪ የዜጐች ሃብት ነጠቃ ነው፤ የከተማ ነዋሪ ዜጐችን ሕገመንግሥትዊ መብት ገፎም የመንግስት ጪሰኛ ያደርጋል፤ ሕገመንግሥቱ ለሕዝቡ ያረጋገጠውን የንብረት ባለቤትነት መብት /ቤትና ከቤት ጋር የተያያዘ መሬትን ጨምሮ/ ያይፃረራል” ይላል፡፡ ይሄው የመድረክ መግለጫ በማጠቃለያው “በገጠር ነዋሪው አርሶ አደር የይዞታው ባለቤት መሆን እንዳለበት ሁሉ የከተማ ነዋሪውም የመኖሪያ ቤት የሠራበት መሬት ባለቤትነት እንዲረጋገጥ ትግሉን እቀጥላለሁ” ይልና ፣ በመጨረሻም ለዚህ ትግሉ ሕዝቡ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡ እስቲ እነዚህን የመድረክ አቋሞች አንድ በአንድ እንመልከት፡፡

መድረክ “አዋጁ  የከተማ ነዋሪዎችን ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የማስተላለፍ መብትን ይነጥቃል፡፡ ይህም የዜጐችን ሕገመንግሥታዊ መብት ይሸረሽራል” ብሏል፡፡ ይህን የመድረክ አቋም ለመረዳት በቅድሚያ የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ላይ ስለንብረት ባለቤትነት የተደነገገውን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ ሕገመንግስቱ በአንቀፅ 4ዐ ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል/ይከበርላታል፡፡ ይህ መብት የሕዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጐች መብቶች እስካልታቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንግድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል” ይላል፡፡

በዚሁ አንቀፅ በንዑስ አንቀጽ 2 ስለግል ንብረት ምንነት ሲገልጽም፣ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት በሕግ የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ማህበራት ወይም አግባብ በአላቸው ሁኔታዎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንደሆኑ የተፈቀደላቸው ማህበረሰቦች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው፣ ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ጠባይ ሣይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው” ይላል፡፡ ሕገመንግስቱ ከላይ ከተጠቀሰውና ለንብረት ምንነት ከሰጠው ትርጉም አኳያ በቅርቡ የወጣው የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጅ፣ በሕገመንግስቱ የተደነገገውን ንብረት የማፍራት መብት አይፃረርም፡፡

መሬት የተፈጥሮ ሃብት ሲሆን ጉልበትን፣ የፈጠራ ችሎታን ወይም ካፒታልን በመጠቀም ሀብት ማፍራት የሚያስችል መሰረታዊ ግብዐት ነው፡፡ መሬት በራሡ እንደግል ንብረት  የሚቆጠር  ሀብት ሣይሆን፣ ሀብት መፍጠር የሚያስችል ግብአት ነው፡፡ በመሆኑም እንደግል ንብረት ሊታይ የሚችልበት የመርህ አግባብ የለም፡፡ ሰዎች በመሬቱ ላይ ያፈሩት ሐብት ግን እንደ ግል ንብረታቸው ይቆጠራል፡፡ የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ሁሉም ዜጐች በተፈጠሩበትና የዜግነት መብት ባላቸው አገራቸው ላይ በጋራ የመሬት ባለቤትነት መብት አላቸው ሲል የደነገገውም፣ መሬትን ማንም ጠፍጥፎ ያልሰራው በመሆኑና ሰዎች ምድር ላይ በመፈጠራቸው ማንም ሊከለክላቸው የማይችለው የመጠቀም መብት ያላቸው የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን መነሻ በማድረግ  ነው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው መሬት ንብረት ለማፍራት አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ግብአት በመሆኑ በአንቀጽ 4ዐ ንኡስ አንቀጽ 6 ላይ “መንግስት ለግል ባለሐብትና በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል” ይላል፡፡ አፈፃፀሙ በሕግ እንደሚወሰንም ይገልፃል፡፡ (በቅርቡ የፀደቀው የከተማ ቦታ ሊዝ አዋጅ አፈፃፀሙን ለመወሰን የወጣ ህግ ነው፡፡) እንግዲህ አዋጁ በሕገመንግስቱ ላይ የሰፈረውን የዜጎችን ሀብት የማፍራት ሕገመንግሥታዊ መብት የሚፃረረው በምን አኳኋን ይሆን? ይህን ጥያቄ ለመድረኮች መተው ይቀላል፡፡

የከተማ ቦታን በሊዝ የመያዝ አዋጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዜጐች ሀብት ነጠቃ መሆኑንም መድረክ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ዙሪያ ሕገመንግስቱ የሚለውን ከመጥቀሳችን በፊት፣ ከሀብት/ንብረት ጋር በተያያዘ የሊዝ አዋጁ ላይ የሰፈረውን ለግንዛቤ ይሆነን ዘንድ እንመልከት፡፡  ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግንኙነት ያለው ሆኖ ያገኘሁት የአዋጁን ክፍል 4 “የከተማን ቦታ ስለማስለቀቅ” የሚለው ድንጋጌ ነው፡፡ በዚህ የአዋጅ ክፍል (አንቀፅ 25 ንኡስ አንቀጽ 1) ስር፣ “ቦታ በሊዝ ወስዶ በሕጉ መሠረት ጥቅም ላይ ያልዋለ፣ ቦታው ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለሌላ አገልግሎት ሲወሰን ወይም የሊዝ ይዞታ ዘመኑ ሲያበቃ፣ ከቦታው ላይ ለሚነሳው ንብረት/ሃብት በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሣ ይከፈላል፣ ምትክ ቦታም ይሰጠዋል፡፡” ይላል፡፡

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው መሬት ለሕዝብ ፋይዳ ያለውን ልማት ለማከናወን የሚያስችል መሰረታዊ ግብአት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ መሬት በሊዝ ሲይዝ ዋና አላማው በመሬቱ መጠቀም ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ መሬት ጌጥ አየደለም፡፡ እናም ግለሰቡ መሬቱን ካላለማው፣ ከመሬቱ ሊገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም በማስቀረቱ መሬቱ ተነጥቆ ለሌላ ማልማት ለሚችል ሰው መሰጠት አለበት፡፡ እንግዲህ ይህ የሊዝ አሰራር ሰዎች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው፣ በካፒታላቸው ያፈሩትን ሀብት ወይም ንብረት መወረስ የሚሆነው በምን አኳኋን ነው?

“አዋጁ የከተማ ነዋሪውን ሕገመንግስታዊ መብት ገፍፎ የመንግስት ጢሰኛ ያደርጋል” ብሏል፣ መድረክ በመግለጫው፡፡ ይህን የመድረክ የተቃውሞ  ሃሳብ ለመረዳት በቅድሚያ የጢሰኛን ምንነት እንመልከት፡፡ ጢሰኛ ማለት በግለሰብ ርስትነት የተያዘ መሬት ላይ የግለሰቡን መሬት እያለማ ምርቱን ለባለሬቱ እየገበረ መሬቱ ላይ የሚኖርበት ጥግ ብቻ ስለተሰጠው ጉልበቱንም ጭምር እየገበረ የሚኖር ሰው ነው፡፡ ጢሰኛ መሬቱን በርስትነት ለዘለአለም የመያዝ፣ የመሸጥና የመለወጥ መብት የሌለው ማለት ሣይሆን፣ በመሬቱ ላይ  በጉልበቱና በዕውቀቱ የሚያመርተው ምርት ላይ  የባለቤትነት መብት የሌለው፣ የራሱም ጉልበት ላይ ሙሉ በሙሉ የማዘዝ መብት የተነፈገውና የገዛ ምርቱን ባለቤትነት ያጣ አርሶ አደር ማለት ነው፡፡  እናም መሬትን በሊዝ በመያዝ ሀብት/ንብርት የማፍራት መብትን የሚፈቅደው አዋጅ በምን አኳኋን ነው ባለሊዙን ጢሰኛ የሚያደርገው?  መድረኮችም ሆኑ ሌሎች ይህን ቢያስቡበት መልካም ይመስለኛል።

በአጠቃላይ፣ በቅርብ የወጣው የከተማ ቦታ የሊዝ አዋጅ ላይ የቀረበው ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ የሕዝብ ሃብት ከሆነው መሬት ሲያጋብሱ የቆዩትን ሕግ ወጥ ጥቅም ያስቀረባቸው ደላሎች ናቸው፡፡ ከየትም የመነጨ ተቃውሞን ከህዝቡ ጥቅምና ፍላጎት፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለመመርመር ፋታ ሳይወስዱ ለተቃውሞ ፖሎቲካ ፍጆታነት በማዋል አመላቸው የሚታወቁ የተወሰኑ ፖለቲከኞችም ሕገወጥ የመሬት ደላሎችን ወሬ በማራገብ ተባባሪነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁለቱም ሕዝብ ተደናግሮ የራሱን ጥቅም እንዲቃወም ለማነሳሳት መሞከራቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡