የዜሮ ድምር ፖለቲካ ዳግም በመሬት ሸሚያና በሊዝ አዋጅ ሽፋን

ሙሉጌታ ከጋምቤላ

ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆኑኝ መሬት አንድና ሁለት፣ ልማትና ጥፋት በሚሉ ርዕሶች የተፃፉትና በፍትህ ጋዜጣ ለንባብ የበቁት የፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም አንድ እግራቸውን ጋምቤላ ላይ አንዱን ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ያለአንዳች ምሰሶ የተከሉት መጣጥፎች የመጀመሪያዎቹ ናቸው፡፡ ሁለተኛው መነሻዬ ደግሞ የባዮሎጂው ምሁርና “ፖለቲከኛው” ፕሮፌሰር በየነ የተቅማጥ መድኃኒት ግኝት ነው፡፡ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሣለኝ ‹‹ወድቆ በተነሣው ባንዲራ›› የጀባቦነው የሊዝ አዋጅና ማቆሚያ የሌለው ዘለፋ፤ የሂውማን ራይትስ ዎች ዳግም ቅጥፈትና የበሬ ወለደ ሪፖርት ሦስተኛውና አራተኛው የጽሁፌ መነሻዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መጣጥፎች የዓይጥ ምስክሯ ድንቢጥ የመሆኗን ብሂል በዞረ ድምር ፖለቲካ ወጥ ተውኔት ደራሲውንና ተዋናዩን፣ ፕሮዲዩሰሩንና፣ ሎጅስቲክሱን፣ ካሜራ ማኑንና፣ ስፖንሰሩን ለመረዳት ያስቻሉኝ በመሆናቸው ጽሁፌ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከተውኔቱና ተዋናዩ እንዲሁም ከስፖንሰሩ አንፃር በመቃኘት ብስሉን ከጥሬው ለመለየት ይሞክራል፡፡

የጽሁፌ አወራረድ የእነ ፕሮፌሰርን እና የሂውማን ራይትስ ዎችን እንዲሁም የእነ ተመስገን ደሣለኝንና የቢጤዎቻቸውን አስተያየት ለማሳያ በሚሆን መልክ መጀመሪያ ያነሳና በመቀጠል የሊዝ አዋጁን መሠረታዊ ነጥቦች በመዳሰስ በዛሬይቱ ጋምቤላ ያለውን የኢንቨስትመንትና የመንደር ማሰባሰብ ተጨባጭ ሁኔታ በማስቃኘት የሚደመደም ነው፡፡ ‹‹መሬት ሁለት›› በፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም ተጽፎ በፍትህ ጋዜጣ ለንባብ ከበቃው መጣጥፍ ልነሳ፡፡                     

‹‹መሬት ማለት ብዙ ነገር ነው፡፡›› በማለት የሚጀምረው የፕሮፌሰሩ ጽሁፍ ለገበሬው፣ ለከብት አርቢው፣ ለመሐንዲሱና ለመሳሰሉት የመሬት ትርጓሜ ልማት እንደሆነ በማውሳት፤ ለደለላውና ለኪራይ ሰብሳቢው መሬት ሸቀጥ እንደሆነ ያትታል፡፡
ጽሁፉ በመግቢያው አካባቢ ሰፋፊ የሆኑ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት ሥራዎችን ኪራይ ሰብሳቢነትና ኢትዮጵያን መግደል እንደሆነ በሚመስል አንደምታ የተፃፈ ነው፡፡ በነፍስ ወከፍ ዜጐች ሊደርሳቸው ይችል የነበረውን መሬት በሂሳብ ስሌት ጭምር አስፍሯል፡፡ ቀጥሎም የሊዝ አዋጁን የተመለከተ ስለመሆኑ በግልጽ ባልተቀመጠ ቋንቋ የመቃብር ቦታን ጭምር አዋጁ እንደሚያሳጣ በመጠቆም የሊዝ አዋጅን የሚኮንነው የፕሮፌሰሩ ጽሁፍ መልሶ የአስከሬን መቃጠልን አስፈላጊነት በማስመር ምክር ይለግሳል፡፡ በመጨረሻም ደርግ ሃብታሙን በነጠቀ ጊዜ  በሃብታሙ መደህየት ደሃው የሚያተርፍ መስሎት እንደተደሰተ በዛሬውም አዋጅ ቤት የሌላቸው ግለሰቦች አዋጁን ሊቃወሙ አይገባም በማለት አንዱ ጮሌ ሹም በቲቪ ሲናገር ሰማሁት በማለት የሊዝ አዋጁን ከደርግ የከተማ ትርፍ ቤቶች ውርስ ጋር ለማመሳሰል በመሞከር ይደመድማል፡፡ 

በሣምንቱ ‹‹ልማትና ጥፋት›› በሚል ርዕስ የቀጠለው የፕሮፌሰሩ ጽሁፍ ለኢትዮጵያውያን መሬት የኑሮአቸው መሠረት ስለሆነ የመሬት ባለቤትነት ከሀገር ባለቤትነት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ በመግለጽ ስለልማት ስንነጋገር የጋራ ሃብታችን መሬት መሆኑን እያሰብን ነው ይልና የጋራ ዓላማችንን በጋራ ህግና ሥርዓት ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ይዘረዝራል፡፡ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ ዜጐችን የሚያደኸይ ስለመሆኑ ደግሞ የሸራተን ሆቴል የቦታ አያያዝን በማሣያነት አቅርቧል፡፡  

ተመስገን ደሣለኝና ቢጤዎቹም የሊዝ አዋጁን የመሬት ቀማኛነትና የድህነት መንገድ መሆኑን በማተት ኢህአዴግን ህዝቡን በተለያየ መንገድ ለመደቆስ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አዋጁ እንደ አንዱ የሚቆጠር መሆኑን በዜናና በሃተታ ገጾቻቸው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ርዕሰ አንቀጻቸውና በነፃ አስተያየት አምዶቻቸው ደግሞ በተለይም የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት መሠረት በማድረግ በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለውን የመንደር ማሰባሰብ ሥራና ኢንቨስትመንት እንደተለመደው ተችተዋል፡፡

የባዮሎጂው ምሁርና ‹‹ፖለቲከኛው›› ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሰፋፊ የእርሻ ልማት ሥራዎች ላይ እየተመረተ የሚገኘውን የሩዝ ምርት ጥቅም የለሽ ሲሉ በማጣጣል የሩዝን ጠቀሜታ የተቅማጥ መድኃኒት ከመሆን የማይዘል እንደሆነ በአንደበታቸው ሲናገሩ ከሰሞኑ በቀረበው የኢቲቪ ዶክሜንታሪ ሰምተናል፤ አይተናል፡፡

ወደ ሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርትና ሪፖርቱን ተከትሎ ወደነበሩ ዓለም አቀፋና ሀገር አቀፍ ዘገባዎች እንመለስ “Waiting here for death… ” ይላል የሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን የተመለከተው ሪፖርት፡፡ ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ የውጭ ሀገራት ሚዲያዎች እንደዘገቡት መንግሥት በጋምሌላ ክልል እያካሄደ ያለው የሰፋፊ እርሻዎች ልማት በምዕራብ የክልሉ ክፍል የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በኃይል ‹‹በማፈናቀል›› እንደተካሄደና ነዋሪዎቹን በሰፈራ ፕሮግራሙ ‹‹የማፈናቀሉ›› ሂደት እየተከናወነ ያለው ብዙም ምክክር ሳይደረግበትና ‹‹ለተፈናቃዮች›› አነስተኛ ካሣ በተሰጠበት ሁኔታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሰፈራው በዛቻ፣ በኃይል፣ ጥቃትና እሥራት እየተከናወነ ከመሆኑ በላይ በሰፈራው አካባቢ በቂ ያልሆነ የምግብ አቅርቦት፣ የጤና እንክብካቤና ለትምህርት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች የለም ሲሉም በዘገባዎቻቸው አስደምጠውናል፡፡

በተለይ The … የተባለው ድረ ገጽ ሪፖርቱን ተንተርሶ ኢትዮጵያ ለም መሬታቸውን ለውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች በገፍ መሸጡን የሙጥኝ ካሉ የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሶ ከ2ዐ ሺህ በላይ ቤተሰቦች ለብዙ ዘመናት ከኖሩበት ቦታ በሰፈራ ፕሮግራም ምክንያት ‹‹እየተፈናቀሉ›› ቢሆንም ብሪታንያን ጨምሮ ሌሎች ለጋሽ ሀገራት እያዩ እንዳላዩ በመሆን ፈንድ ማቅረባቸው ከአጥኚ ቡድኖች ትችትን አስከትሏል ሲል የዘገበው ከሰሞኑ ነው፡፡ Global pest የተባለው ድረ ገጽ ደግሞ በጋምቤላ እየተካሄደ ያለውን በመንደር የማሰባሰብ ሥ››ራ በደርግ ዘመን በቁጥጥር ከተደረገው የሰፈራ ሂደት ጋር በማነፃፀር ዘግቧል፡፡

በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ፕሬሶችም ሆኑ የውጭ ሚዲያዎች ሂውማን ራይትስ ዎችና ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ምንጮቻችን ናቸው ሲሉ በመንደር የማሰባሰቡን ሥራና ሰፋፊ የሆኑት የእርሻ ልማት ሥራዎችን በመኮነን በየአምዶቻቸው አስነብበውናል፡፡

‹‹እናስ?›› ነው ቁም ነገሩ፡፡ ስለሆነም እነዚህን ዘገባዎች መሠረት በማድረግ የሊዝ አዋጁን መሠረታዊ ጭብጦችና የጋምቤላን ክልል የመንደር ማሰባሰብ ሂደትና የኢንቨስትመንት አጠቃላይ እውነታዎች በማመላከት የዘገባዎቹን፣  የሀተታ ፀሐፊዎቹን እና ጽሁፎቻቸውን ከዚያም የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት የዜሮ ድምር ፖለቲካ የተለመደ ሂደትና ቁማር እናያለን፡፡

በህገ መንግሥታችን በግልጽ እንደተመለከተው መጀመሪያ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ሀብት መሆኑ በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም የሊዝ አዋጁ መሬትን የሕዝቦች እኩል የመጠቀም መብት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ እድሉን አግኝቶ መሬቱን የመጠቀም መብት ያገኘው አካል ከሚከፍለው የሊዝ ክፍያ ለሌላው ደሀ ሕዝብ መሠረተ ልማት በመገንባት ኑሮው እንዲሻሻል የሚያደርጉ ሥራዎችን በማከናወን ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

የሊዝ አዋጁ የመኖሪያ ቤትን በተመለከተ ለሕዝቡ የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጧል፡፡  በራስ አገዝ የመኖሪያ ቤት ለሚሰሩ በምደባ ቦታ እንዲያገኙና ይህም በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሆን ደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ለኮንዶሚኒየም ግንባታ የሚሆኑ ቦታዎችን በማዘጋጀት መንግሥት ገንብቶ እንዲያስተላልፍ በማድረግና በመሳሰሉት ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀም እድል የሚሰጥ መሆኑም ሌላውና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ነው።

ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ለማምረቻና መሸጫ ቦታዎች በማዘጋጀት ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል መስራትና ሀብት ማፍራት እንዲችል የሚያደርግ የሊዝ አዋጅ መሆኑም ሊሸሸግ አይገባም።

መሬት የሕዝብና የመንግሥት በመሆኑና በዚህም አዋጅ በግልጽ በተቀመጠው መሠረት መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ወጣት ማዕከል፣ የውኃ ፕሮጀክት እና የመሳሰሉት እንዲገነቡና ሕዝቡ እንዲጠቀም አዋጁ እድል የሚሰጥ መሆኑ በህገ መንግሥታችን የተቀመጠውን መሬት የሕዝብና የመንግሥት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሀቅ ነው።

ትክክለኛ አልሚዎች ለሥራ የሚሆን መሬት በተረጋጋ የሊዝ ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው በመሆኑና በስፋት ወደ ልማት እንዲገቡ ስለሚያደርጋቸው የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሆነ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሕዝቡ ተጠቃሚ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ እውነታ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ቤት መገንባት የሚያስችል አቅም እንደሌለው የታወቀ ጉዳይ ነው። ባዶ መሬት ቢኖረውም እንኳን መብቱን ለሌላው ያስተላልፋል እንጂ መገንባት አይችልም። ይህ ደግሞ በተጨባጭ የታየ ጉዳይ ነው።  በመሆኑም መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ የኮንዶሚኒየም ቤት ገንብቶ በረዥም ዓመታት ክፍያ ለሕዝቡ ማስተላለፍ እንዳለበት ተረድቶ ሥራውን መጀመሩ የልማታዊ መንግሥት መገለጫ ቢሆን እንጂ ነጣቂ ሊያሰኘው አይገባም። በረዥም ዓመታት ክፍያ ለሕዝቡ የሚያስተላልፈውን ቤት ኅብረተሰቡ መክፈል እንዲቻለው በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን በመፍጠርና የቁጠባ ባህልን በማበረታታት ሕዝቡን ከዕዳ ነፃ የማድረግ እቅድንም ያካተተ አዋጅ ነው¬፡፡ ¬¬አዲሱ የሊዝ አዋጅ፡፡ በ40% እና 60% ፖሊሲው ዜጎች የተወሰነ ገንዘብ ቆጥበው ቀሪውን መንግሥት በረዥም ጊዜ ክፍያ አበድሯቸውና የመሥሪያ ቦታ በምደባ አዘጋጅቶላቸው ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ቤት እንዲገነቡ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱም መዘለል የሌለበት እውነት ነው።

በህገ መንግሥታችን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ፣ በእውቀቱ እና በገንዘቡ ተጠቅሞ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት ተሰጥቶቷል። ይህ መብት ደግሞ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ ሀብት የማፍራት የመሬት ተጠቃሚነቱን ማዘዋወር የመሳሰሉትን የሚያካትት ነው። በሊዝ አዋጁም እንደተደነገገው በመጀመሪያ በመሬቱ እጠቀማለሁ እስካለ ድረስ ይጠቀምበታል፣ ሊያወርሰውም ይችላል። በመሬቱ ላይ ደግሞ ግንባታ አሳርፎ አዲስ ሀብት ሊጨምር ይችላል። ይህንን ሀብቱንና በመሬት የመጠቀም መብቱን ደግሞ በፈለገው ጊዜ ይሸጣል ያስተላልፋል። አዲስ በፈጠረው ሀብት ላይ ገበያው የፈቀደውን ዋጋ የማግኘትና ትርፍ የማግኘት መብቱም የተጠበቀ ነው። በመሆኑም መጠቀም እስከፈለገ ጊዜ ድረስ መጠቀም፣ ተጨማሪ ሀብት ማፍራት ሆነ ሀብቱን መሸጥ፣ የመጠቀም መብቱን ማስተላለፍ እንደሚችል ሁሉ በአዋጁ በግልጽ መቀመጡ መዘንጋት የለበትም።

ሌላው በመግቢያዬ የጠቀስኳቸውን የዜሮ ድምር ፖለቲካ አስተሳሰብ ሰለባ የሆኑ መጣጥፎች ምንጭ ለማሳየት ከሊዝ አዋጁ ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ነጥብ ኢንቨስትመንትንና ነባር ይዞታን የተመለከተው የአዋጁ ፍሬ ነገር ነው።

አዋጁ በመሬት ግብይትና አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ያለውን ኪራይ ሰብሳቢነት በማስወገድ የመሬት እና የንብረት ግብይት ዋጋን የሚያረጋጋ መሆኑ በግልጽ ተመልክቷል። ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የመሬት አቅርቦት በሥፋትና በቀጣይነት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ኢንቨስተሩ ወይንም ትክክለኛው አልሚ ሊሰራበት የሚፈልገውን መሬት ግልጽ በሆነ አሰራር ያለብዙ ውጣ ውረድ እንደሚያገኝና በዚህም ልማትና የሥራ እድል በስፋት መፍጠር እንደሚችል ተጠቁሟል።

በመሬቱ ላይ ንብረት ያረፈበትና ሀብት የፈራበት አድርጎ መሸጥ አሰራሩ የሚፈቅድና የገበያውን ዋጋ ተከትሎ የሚሄድ ብሎም የቤቶች ዝውውር ፍላጎትና አቅርቦትን በተከተለ የገበያ መርህ የሚከናወን መሆኑም በግልጽ የተመለከተ ጉዳይ ነው።

ነባር ይዞታን በተመለከተም ህጋዊ ነባር ይዞታ ያለው ሰው ራሱ ሊጠቀምበት እስከፈለገ ጊዜ ድረስ በሊዝ አሰራር ውስጥ ሳይገባ በነባር ይዞታነት ይዞ ሊቆይ እንደሚችል፤ ነባር ይዞታን የያዘ አካል ወይም ግለሰብ የይዞታ ባህሪውን ሳይቀይር በውርስ ሊያስተላልፈው እንደሚችልና ወራሾቹ ከአንድ በላይ ቢሆኑም እንኳ ሲከፋፈሉ ተለያይተው መሬቱን ቢካፈሉ የሚካፈሉት የመሬት ድርሻ የሚፀናላቸው በነባር ይዞታነት እንደሆነ እንዲሁም በህጋዊ ነባር ይዞታ ይጠቀም የነበረ ነዋሪ በመልሶ ማልማት ምክንያት የሚነሳ ቢሆን በምትክ የሚሰጠው ቦታ በነባር ይዞታነት መሆኑም በአዋጁ ላይ በግልጽ የተቀመጠ እውነታ ነው።

ይሁንና ነባር ይዞታ በሽያጭ ወደሌላ አካል የሚተላለፍ ከሆነ ሻጭ በገበያ ዋጋ ቤቱን ይሸጣል፣ በመሬቱ የመጠቀም መብቱን ያስተላልፋል በመሆኑም ባለንብረቱ በዚህ የሊዝ አዋጅ ምክንያት የሚያጣው ጥቅም አይኖርም።

ገዥም በገበያው ዋጋ ንብረቱን ይገዛል፣ በመሬቱ የመጠቀም የሻጭ መብትም ይተላለፍለታል። መሬቱ በሊዝ ሥርዓት ውስጥ የሚገባ ቢሆንም የሚፈፀመው ክፍያ ለመኖሪያ ከሆነ የሊዝ መነሻ ዋጋ ሲባዛ የቦታው ስፋት ሲካፈል ለ99 ዓመት በመሆኑ ገዥ በየዓመቱ የሚከፍለው ገንዘብ በመቶዎቹ ከሚቆጠር ብር የሚዘል ባለመሆኑ ገዥ የሚጎዳበት ምክንያት አይኖርም።

ታዲያ እነዚህ መሠረታዊና ተጨባጭ የሆኑ እውነታዎቸ በሊዝ አዋጁ ላይ ተመልክተው ሳለ እነ ፕሮፌሰርና የመጣጥፋቸው ደንበኛ የሆኑት እነ ተመስገን በምን ሂሳብ ይሆን አዋጁን ከደርግ የከተማ ትርፍ ቤቶች ውርስ አዋጅ ጋር የሚያያይዙት? የሸራተን ሆቴል በተገነባበት ቦታ ላይ ሲኖሩ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ የት እንዳሉና በመልሶ ማልማት ግንባታ የሚነሱት ሁሉ በምን ዓይነት መንገድ የቤት ባለቤት እየሆኑ ስለመሆናቸው እነ ፕሮፌሰር መረጃ አይኖራቸው ይሆን? ተነሺውን ተፈናቃይና መድረሻ ያጣ ዜጋ አድርገው የመቁጠራቸው ሚስጥር ታዲያ ምንድን ነው? ስለልማት ስንነጋገር የጋራ ሀብታችን መሬት መሆኑን እያሰብን ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ይህንኑ የጋራ ዓላማ በጋራ ህግና ሥርዓት ማስተናገድ አንደሚያስፈልግ በጽሁፋቸው ላይ አብራርተው ነበር፡፡ ዳሩ ዓላማቸው ሌላ ስለሆነ የጋራ የሆነውን መሬት … በጋራ ህግና በጋራ ሥርዓት ለማስተዳደር የሚያስችለውን የሊዝ አዋጅ መልሰው ይኮንኑታል፡፡ በመኮነን ብቻም አያበቁም፡፡ መሬት የጥቂቶች ብቻ ሆኖ መቆየት እንዳለበት በሚያመላክት ውስጠ ወይራ ዓይነት መንገድ በጽሁፋቸው ያረጋግጣሉ፡፡ መሬት ለገበሬው፣ ለመሐንዲሱ ለሌላውም ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጹት ፕሮፌሰር በፍፁም ለኪራይ ሰብሳቢው መዋል የለበትም ብለው ካስረገጡ በኋላ የኪራይ ሰብሳቢውን መንገድ ለመናድ የሚያስችለውን አዋጅ የአፈናና የጭቆና ያደርጉታል፡፡ እነ ተመስገንም እሳቸውንና መሰሎቻቸውን ተቀብለው የማስተጋባቱን ሚና ይተውኑታል፡፡ ደግሞ መሬት ሁለት ብለው ቀጥለዋል፣ ልማትና ጥፋት ብለውም ሰልሰዋል፤ አራተኛውንም እጠብቃለሁ፡፡ ግን መደጋገም ካልሆነ በስተቀር የሚሉትን ብለው ስለጨረሱ የሚቀጥሉበት አይመስለኝም፡፡ አራተኛውን እጠብቃለሁ ያልኩት አንድ፣ ሁለት እያሉ በመጀመራቸው ብዙ ሀሳብ ይኖራቸዋል ብዬ ከመገመት ነው፡፡

ወደ ጋምቤላው የመንደር ማሰባሰብ ሥራና ኢንቨስትመንት ስናመራ ምላሹን በከፊል እያገኘን እንሄዳለን፡፡ በጋምቤላና ሌሎችም መሰል ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ በሆኑ ክልሎች ላይ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ደራሲያኑና ተዋናዩ በዋናነት የሚያነሷቸውና ኢንቨስትመንቱን ከመሬት ሽሚያ ጋር የሚያስተሳስሩት ከክልሎቹ ነዋሪዎች የምግብ ዋስትና ጋር በዋናነት በማያያዝና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይን በተለይም የደን ምንጣሮንና መሰል ጉዳዮችን እንደ ምክንያት በማንሳት ነው፡፡

የሂውማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት ተከትሎ ትኩረቱን በጋምቤላ ክልል የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ባደረገው የኢቲቪው ዶክመንታሪ ላይ ሲናገሩ ያዳመጥናቸው የባዮሎጂው ተመራማሪም ሆኑ የፍትህ ቋሚ አምደኛ ወደመሆን በመጠጋጋት ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ለኢንቨስትመንቱ የተለየ ትርጉም ቢሰጡትም አጠቃላዩን የጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስትመንት በተመለከተ መንግሥት የሰጣቸው ማብራሪያዎችና ምላሾች እንደተጠበቁ ሆነው የዜሮ ድምር ደራሲያኑና ተዋናዮች ከተነሱበት የክልሉ ሕዝብ የምግብ ዋስትናና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች አንፃር በቂ ምላሽ ሊሆን ይችላል ስል የመረጥኩት የክልሉን የግብርና ቢሮ የበጀት ዓመቱ የአምስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ነው፡፡

ሰነዱ እንደሚያመለክተው በዘንድሮው በጀት ዓመት በግብርና ቢሮው የተሰሩ አራት መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ የክልሉ አርሶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር በምግብ ሰብል ራሱን እንዲችል ስፔሻላይዜሽንን መሠረት ባደረገ የዳይቨርስፊኬሽን አመራረት ስልት ታጠቃሚ ማድረግና ይህንኑም በማስፋፋት የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘርጋት የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ የግብርና ምርምር ሥራዎች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የኅብረተሰቡን ችግር ማዕከል በማድረግ የተጀመረውን የአርሶ አደር ጥምረት የግብርና ምርምር አኤክስቴንሽን አጠናክሮ ማስቀጠል ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡

በሪፖርቱ ላይ የተመለከተው ሦስተኛው የትኩረት አቅጣጫና እኛ እያወራን ካለው ቁም ነገር ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ በጥናት ላይ የተመረኮዘና ውኃን መሠረት ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ማካሄድ የሚለው ነው፡፡

ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር በክልሉ እንዲኖር በማድረግ የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥና ለግብርና ኢንቨስትመንት ሊውል የሚችለውን መሬት ለይቶ አገልግሎት መስጠት የሰፈረው ደግሞ በአራተኛነት የተቀመጠው ሌላው ቁልፍ ተግባርና የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡

እነዚህ አራት መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች በዋናነት የተመረጡበት ምክንያት በዘርፉ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮችን ማስወገድና የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንዲቻል መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች ናቸው ከተባሉት ስትራቴጂክ ጉዳዮች መካከል የሕዝቡ አሰፋፈር ወንዝን የተከተለና የተበታተነ መሆኑ፣ አብዛኛው አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ከድህነት ጋር ተስማምቶ የመኖር ወይም በድህነት ላይ የመረረ ጥላቻ ያለማሳየት እና ከድህነት ለመውጣት የሚጠበቀውን ያህል ጥረት አለማድረግ የሚሉት ጉዳዮች ናቸው፡፡

ታዲያ ይህ ከሆነ በኢንቨስትመንቱ ሰበብ የክልሉ ነዋሪ የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ነው በተባለበት ጋምቤላ ሌላውን ትተን ባሳለፍናቸው አምስት ወራት ብቻ ምን ተሰራ? የሚለውን ጥያቄ እዚህ ጋር መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከትኩረት አቅጣጫው በመነሳት ሥራዎቹን በሁለት ከፍሎ መፈተሹ ደግሞ የበለጠ ጉዳዩን ግልጽ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ውጤት እንዲሚያመጣ እምነት የተያዘበትን የግብርና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር ከማደራጀትና ከማስፋፋት አንፃር ምን ተፈፀመ የሚለውን በአንድ በኩል በማየት በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች የተከናወኑ ተግባራትን ደግሞ በሌላ በኩል እንመልከት፡፡

አሁንም አንባቢዎቼን ደግሜ ለማስታወስ የምሻው ወይም የተመስገን ደሣለኝን ቃል ልዋስና ደግሜ የምጮኸው በዜሮ ድምር ፖለቲካው መድረክ የቀረበው ተውኔት የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅነቱ እንዲመዘን ጠቅላላውን እንኳን ትተን የአምስት ወራቱን የጋምቤላ ክልል አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ተጨባጭ ሁኔታ እያነሳን መሆኑን ነው፡፡ የእናንተ መደምደሚያ ከመስፈሪያው በመነሳት በእናንተው የሚቀር ወይም ቀጣይ አስተያየት የምትሰጡበት ሆኖ እኔ ደግሞ ከቀረበው የአምስት ወራት አፈጻጸም በመነሳት በስተመጨረሻ ተውኔቱ ላይ ሂሴን እሰነዝራለሁ፡፡ ሂሤን ከድርሰቱ ይዘት በመነሳት ወጪውን፣ የገጸ ባህሪያቱን አሳሳል፣ መቼት አመራረጥና ስፖንሰሩን እንዲሁም ተውኔቱ ያገኘውን የሚዲያ ሽፋን የሚያካትት ነው፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን ተግባር በአግባቡ ሊፈፀም የሚችለው በሥልጠና መታገዝ ሲችልና ጥሩ ተሞክሮዎችን በማስፋፋት እንደሆነ በርካታ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ መሠረት በበጀት ዓመቱ መግቢያ ላይ ይፋ በሆነው የጋምቤላ ክልል ግብርና ቢሮ ዓመታዊ  እቅድ ላይ እንደተመለከተው 344 የቀበሌና 115 የቀጠና ኤክስቴንሽን ዩኒት ለማቋቋምና ለማጠናከር፣ 1265 የልማት ቡድኖችን ለማደራጀትና ለማጠናከር፣ ለ53,3ዐዐ አርሶ አደሮችና ለ332 የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት የተጠናከረ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ለመዘርጋትና አርሶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን የዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ እንደተጣለ ያሳያል፡፡ በዚሁ መሠረት 612 የቀበሌና 166 የቀጠና ኤክስቴንሽን ዩኒት የማቋቋምና የማጠናከር ሥራ፣ ለ26,885 አርሶ አደሮች እና ለ4ዐዐ አዳዲስ የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች ባሳለፍናቸው አምስት ወራት ብቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የተሰጠ ስለመሆኑና በየደረጃው የሚገኘው ፈጻሚና አርሶ አደር እንዲሁም የክልሉ አመራር ማረጋገጣቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በምግብና ቋሚ ሰብሎች የመኸር እርሻ 52,85ዐ አርሶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደሮችን በተለያዩ ፓኬጅ በማሳተፍ 58,37ዐ.3ዐ ሄክታር መሬት ለምቶ 1,125,219 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ በተጣለው ግብ መሠረት 49,923.ዐ7 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 571,874.25 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመስኖ ሥራን ለማስፋፋት ለ14ዐ አርሶ አደሮች በክልልና በወረዳ ደረጃ ስለመስኖ ልማትና የመሬት ክፍፍል ለሦስት ቀናት ሥልጠና በሌላ ዙር ለ15ዐ አርሶ አደሮች፣ ለ15 ባለሙያዎችና ለሰባት የልማት ጣቢያ ሠራተኞች መሰጠቱ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያመላክት ነው፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎችን በጥራት ለመተግበር የባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ማሳደግ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በተሳትፏዊ የደን አስተዳደር አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ለ23 ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የተቀናጀ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት ዕቅድ ዙሪያ ለ23 የክልል፣ የዞንና የወረዳ ባለሙያዎች ለ1ዐ ቀናት ሥልጠና የተሰጠው በዚሁ በያዝነው በጀት ዓመት አምስት ወራት ውስጥ ነው፡፡

በእነዚህ ወራት ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በተመለከተ ሌላው የተሰራው 29 የደን ጥበቃ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ 13.5 ኪ.ሜ የእሣት መከላከያ … ተሰርቷል፤ 45ዐ የተለያዩ የደን ዘር ለሦስት ወረዳዎች ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም 1,ዐ41,ዐዐዐ የተለየዩ የዛፍና የፍራፍሬ ችግኞች በማፍላት በ418.4 ሄክታር በመንግሥትና በግል ይዞታ ላይ ተተክሎ በተደረገው ክትትል መሠረት 85 በመቶ የሚሆነው ችግኝ መፅደቁም ተረጋግጧል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት በ39 የመንደር ማሰባሰቢያ ማዕከላት 15,ዐዐዐ አባወራ/ እማወራ በመንደር ለማሰበሰብ ታቅዷል፡፡ በአምስት ወራት ውስጥም 14,367 አባወራዎች በፈቃደኝነት ተመዝግበዋል፡፡ በ21 ነባርና 39 አዳስ በሚመሰረቱ መንደሮች ላይ የተጠናከረ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ የትምህርት፣ የጤና ተቋማትና መሰል ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ለአዳዲሶቹ መንደሮች የእርሻ መሣሪያ ግዥ እየተፈፀመ ነው፡፡ የወፍጮ ተከላም በመከናወን ላይ ይገኻል፡፡ ከሞላ ጎደል ጋምቤላ ያለችው በዚህ ሁኔታ ላይ ነው። ታዲያ የእነ ፕሮፌሰር ድርሰት የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው ወይስ አኒሜሽን?

ፕሮፌሰር መሥፍን ‹‹መሬት አንድ››፣ ‹‹መሬት ሁለት›› ብለው እስከ ምናምን ሊሄዱ ነው ብዬ ሳስብ መውጫቸውን መሬትና ልማት ብለው ባሰለሱት ጽሁፍ ቋጭተዋል፡፡ ዓላማቸው ቀድሞም ቢሆን የታወቀ በመሆኑ በሣምንቱ ከጋምቤላ ለቀው የአፍሪካ ህብረት ላይ ዘመቱበት። የአፍሪካ ህብረት የመላው አፍሪካውያን እንጂ የአቶ መለስ ዜናዊ ወይም የኢህአዴግ እንዳልሆነ እያወቁት ከዚህም በመለስ አፄ ኃይለ ሥላሴ ስለአፍሪካ አንድነት እንጂ ስለአፍሪካ ህብረት /pan Africanism/  የነበራቸውን ሚና ጠንቅቀው እያወቁ የህብረቱ አቀንቃኝ ለነበረው ክዋሜ ንኩሩማህ ለምን ሃውልት ተቀረፀ ብለው ደግሞ ለማጯጯህ ሞከሩ። ዳሩ መድረኩ የዜሮ ድምር ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ ገና መቀጠላቸውም አይቀርም፡፡ ነገር ግን የሚጽፉት ሁሉ ቆርጦ ቀጥል እንደሆነ በተጨባጭ እየታየ ስለሆነ የወደፊቱ መውጫቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ደግሞ መጠበቅ ነው።
ወደ ሌላው ተዋናይ ስንመለስ የምሁር ገፀ ባህርይ የተላበሱትን ፕሮፌሰር እናገኛለን። ፕሮፌሰሩ ባደረጉት ምርምር ይሁን ተብሎ የተላበሱት ገፀ ባህሪ ሩዝ የተቅማጥ መድኃኒት መሆኑን እንዲሰብኩ ሆነው ነው። ኧረ እንደው ለመሆኑ የዓለምን ሲሶ ሕዝብ የያዙት ህንዳውያንና ቻይናውያኑ ሁሉ በሆድ ቁርጠት ተይዘው ይሆን ሩዝ ተመጋቢ የሆኑት? ምላሹን ለባዮሎጂው ተመራማሪ እተዋለሁ። ለመቃወምና ለማሳጣት ሲባል ብቻ ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ አስተሳሰብ አንዴ ወዲህ አንዴ ወዲያ እያላጋ ሙያቸውን ጭምር አስረስቶ በመንፈስም እያናገራቸው በመሆኑ አልፈርድባቸውም፡፡ ነገር ግን የሚሊኒየሙ ተመራጭ ምግብ ሩዝ እንደሆነ ጥናቶችን ሁሉ እንዲመለከቱ በዚህ አጋጣሚ ልነግራቸው ፈልጋለሁ።

እጮሃለሁ የሚለው ተመስገን ደሣለኝ ደግሞ  ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ምናልባት ግራ በገባቸው ምሁራን ግራ እየተጋባና የአስተሳሰቡ ሰለባ በመሆን (የግሉ አቋም እንደሆነ እጠረጥራለሁ) በርዕሰ አንቀጹና በሀተታ ጽሁፎቹ ብስል ከቀሊሉን ሳይለይ እያነኮረው ነው። የሊዝ አዋጁን አንዴ በመኮነን አንዴ በመደገፍ መለስ ብሎ ደግሞ ቀደም ብሎ ሕዝቡ ሊወያይበት በተገባ ነበር በሚል ለመከራከር ይሞክራል። መንግሥት እንደ መንግሥት ሕዝቡን ቀደም ብሎ ማወያየት ተገቢ እንደነበር ቢናገርም በእኔ በኩል በዚህም አልስማማም። በሚወጡ አዋጆች ላይ ሁሉ እንዲመክር የመረጥነውና ውክልና የሰጠነው አካል በፓርላማ ሳለ ሕዝቡን በውኃ ቀጠነ እየሰበሰቡ ማወያየት የሞራልም የህግም ድጋፍ አለው ብዬ አላስብም። ስለሆነም ለሕዝብ የሚጠቅሙ አዋጆችን በማውጣት በሥራ ላይ ማዋል የፓርላማውና የአስፈፃሚው ሥራ እንጂ የሕዝቡ መሆን የለበትም፣ አይገባምም። በእርግጥ ኮሽ ባለበት ሁሉ የማስጮህና የማተራመስ ዓላማ ያላቸው እነተመስገን ብዙ ብለው አልሆን ሲላቸው በጩኸት የፈረሰች ከተማ ብትኖር ኢያሪኮ ብቻ አይደለችም፤ ኢያሪኮ አንደኛ ነች ሁለተኛ ደግሞ አለ ብሎ በአግቦ ጽፎልናል። ዳሩ የማፍረስና የመናድ ፍላጎት ያለው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰለባና የፈረንጅ ባለሟል ይህን ቢል አይገርምም፡፡ ይልቅ የሚገርመው ተመስገን የኢያሪኮን ዘመንና ባህሪ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማነፃፀር አለመሞከሩ ነው። የኢያሪኮ ጩኸትና መፍረስ መነሻና መድረሻው ከሥነ መለኮታዊ ጉዳይ ጋር የተያያዘ እንጂ ለእኛዎቹና መሰል ምድራውያን በምሣሌነት የሚቀርብ አልነበረም።
ወደ ሂውማን ራይትስ ዎች ስመለስ የጋምቤላን ክልል በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት የተለመደና ፍሬ አልባ ከመሆን የዘለለ ሆኖ አላገኘሁትም። ድርጅቱ መረጃ ሰብስቤያለሁ የሚልባቸው መንገዶችና የመረጃ ምንጮች የሚላቸው በፍፁም ከመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት ያፈነገጡና ሊታመኑ የማይችሉ ናቸው። ሂውማን ራይትስ ዎችንና ሌሎች የቀለም አብዮት አራማጅ የሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በተመለከተ ራሱን የቻለ አጀንዳ ዘርግቼ በሌላ ጽሁፌ የምመለስበት ሆኖ ሳለ ጥቂት ነገሮችን ስለሂውማን ራይት ዎች ለመናገር ያህል፡- ድርጅቱ በሥራ ላይ በቆየባቸው 34 ዓመታት ከገነባው ዓለም ዓቀፋዊ ስምና አቅም በላይ በሚገራርሙና ግራ በሚያጋቡ ወቀሳዎች የተከበበ ነው። ሲብስም የተቋሙን ዓለም ዓቀፋዊ አቅም የተገነዘቡ በርካቶች “የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ልዕለ ኃያል” ሲሉት ይደመጣል። የሚሰነዘሩበት ወቀሳዎች ይዘትና ዓይነት ግን ከዚህ አቅሙ ጋር የማይመጣጠኑ የመሆናቸው እውነት አያሌ ጥያቄዎች በተቋሙ ዙሪያ እንዲነሱ አድርጓል፡፡ እያደረገ ነው፡፡ ወደፊትም እንደሚቀጥል እርግጥ ይመስላል።

በሰብዓዊ መብቶች ጥላ ስር ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ማራመድ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ኢ ሥነ ምግባራዊ ጥናቶችን በማሰራጨት፣ ሉዓላዊነትን የሚጥሱ፣ በወገንተኝነት የሚመሩ ጣልቃ ገብነቶች በማድረግ፣ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎችን በማገዝና በማስተባበር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጋኖና አዛብቶ በማቅረብ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በሚል ሽፋን የመንግሥታትን ሥልጣን በመሻማትና ሀገራዊ ሠላምን በማደፍረስ፣ ግለሰባዊ የፖለቲካ አቋሞችን በማራመድ ሀገራትን በአድልኦ በመመልከት፣ ምንጫቸው ያልተጣሩ የገንዘብ ምንጮችን በመጠቀም ወዘተ…ወንጀሎች በየአደባባዩ የሚከሰሰው ሂውማን ራይትስ ዎች በየጊዜው በየሚዲያው ከሚያወጣቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ተዛማጅ ጉዳዮች ሪፖርቶቹ እኩል እጅግ ብዙ ሀገራት ከቀላል እስከተደራጀ መልስ ይሰጡታል።

በርካታ የተቋሙን ኢፍትሃዊነት የሚያሳዩ ጥናቶች በየሀገራቱ ተሰርተዋል። ጥናቶቹን ወደፊት በስፋት እናያለን፤ ግን ይህ ድርጅት ነው በጋምቤላ ክልል በሰፋፊ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት ሰበብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽማል ሲል የሚከራከረው፡፡ የመረጃ ምንጮች ሲል ያቀረባቸውም የሚገርሙና ድርጅቱ ያለበትን የወረደ ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው። ከሁለት ያልበለጡ ግለሰቦችን በማናገርና አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ የተቃዋሚዎችን የቁራ ጩኸት መሠረት በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል ሪፖርት ታዲያ ድርሰት ወይም ተረት ከመሆን ሌላ ምን ሊሆን ይችላል።
የዜሮ ድምር ፖለቲካ ይሏል ጫወታ እንዲህ ነው፡፡ ዐይጥ ከምስክሯ ድንቢጥ ጋር ተገማምዳ ከዴሞክራሲያው ኃይል ጋር የምትፋለምበት መድረክ ነው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጨዋታ። የዓይጧን ምስክሮች ይዘን ወደምርጫ 2002 በመመለስ ወጋችንን እንቋጭ።

በ2002ቱ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ሰሞን አቶ ዳንኤል ብርሃኔ (Daniel Berhane’s Blog |10 የሂውማን ራይትስ ዎች አሳፋሪ፣ ዝርክርክ፣ በንቀት የተሞሉ ስህተቶች´ን (HRw’s 10 flagrant Blunders አስነብቦናል፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች ‹‹ሕዝቡ ለምርጫ እንዲመዘገብና እንዲመርጥ´ ይደረግበት የነበረውን ግፊት በሪፖርቱ ሲገልጽ እንዲህ በሚል መንገድ ነበር፡፡ ‹‹ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አልመርጥም የሚል ሕዝብ እንዳይበዛ በመስጋቱ በሚያዝያ እና በግንቦት ወር ውስጥ ባለሥልጣናትና ሚሊሺያዎችን (በአማርኛ ታጣቂ የሚባሉትን) ቤት ለቤት በማሰማራት ሕዝቡ እንዲመዘገብና ገዥውን ፓርቲ እንዲመርጥ ሲያደርግ ነበር።››

አቶ ዳንኤል በዚህ መልኩ  የድርጅቱን ሪፖርት በአጭሩ ከገለጹ በኋላ ሦስት ጥያቄዎችን ያነሳሉ። በሚያዝያና ግንቦት የመራጮች ምዝገባ ነበርን? በአዲስ አበባ ኧረ እንዲያውም በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችስ ሚሊሺያ የሚባል ነገር አለን? ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ፖሊሲን በስህተት እንኳን ታጣቂ ወይም ሚሊሺያ ሲል የሚጠራ አንድ ሰው ይገኝ ይሆን?

ሂውማን ራይትስ ዎች |ትዝብቴ´  |በምርምር ያረጋገጥኳቸው´ |በጥልቅ ጥናቴ ያገኘኋቸው´ እያለ በዓለማችን ግዙፍ በሆኑ ሚዲያዎች ላይ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች እንዲህ የምርምር ብቃታቸው የወረደ፣ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው። ሂውማን ራይትስ ዎች ጋምቤላን የመዘነበት ልክ እንደምርጫ 2002 ሁሉ በዘፈቀደ መሆኑን ልብ ይሏል። የዜሮ ድምር ፖለቲካ ቁማርና ቆማሪዎች እንግዲህ እነዚህ ፍሬ አልባ ገለባዎች መሆናቸውንም ልብ ይበሉ፡፡