አንዱ አኩሪ ባህላችን- መቻቻል

ዮናስ

በህገ መንግስታችን ከአንቀጽ 29-44 ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን እውቅና አግኝተዋል፡፡ ከነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፤ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች የጽሁፌ ማጠንጠኛና ማጠናከሪያዎች ናቸው፡፡

አክራሪነት በሃይማኖት አስተምህሮ ሽፋን የተለያዩና የተቆነጣጠሩ ሃሳቦችን በመውሰድ እና ተከታዮችን በማሳሳት የሌላውን ሃይማኖት እና እምነት በማውገዝና አመፅ በመቀስቀስ ህገመንግስታዊ ግዴታዎችን ባለማክበር የሚገለጽ ትምህርትና ድርጊት ነው፡፡

በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካን ማራመድ፣ በሃይማኖት እና እምነት ተቋማት ውስጥ በአመራሩና በተከታዮቻቸው ሰርጎ በመግባት የፓርቲ አጀንዳ ማራመድ በዚህም ህዝብን ለአመጽ በመቀስቀስና ከዚሁ በሚገኘው ትርፍ የመንግስት ተአማኒነትን በማሳጣት የግል ወይም የቡድን የፖለቲካ ፍላጎትንና እምነትን ወይም አመለካከትን በሌሎች ላይ ዴሞክራሲያዊነትን ባልተከተለ መንገድ በኃይል ለመጫንና ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ አንዱ ተግባር ነው፤ አክራሪነት፡፡

ከሃገሪቱ ታሪክ ጋር የራሳቸውን ሁነኛ ስፍራ በመያዝ ምንጊዜም የሚወሱት  ሃይማኖቶች በሃገራችን ለዘመናት ያሳለፉት የመቻቻል ታሪካቸውም ቀዳሚ ሆኖ ይገኛል። ዛሬ ግን ሃይማኖቶቹ ምንም እንኳን የተጋነነ ባይሆንም ከላይ እስከነትርጉሙ የገለጽኩት የአክራሪነት ሰለባ የመሆን ምልክት እየታየባቸው ነው፡፡ ለምን? የሚለው ጥያቄ ባግባቡ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን ለመመለስ ደግሞ ቢያንስ ያለፉትን ሁለት ሥርዓቶችና አሁን ያለንበትን ሥርዓት ሃይማኖታዊ እይታ መቃኘት ተገቢ ይሆናል፡፡

ከአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ስንነሳ በኢትዮጵያ በመንግስትና በዜጎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ የ1923ቱን ህገ መንግስት እናስታውሳለን፡፡ ይህ ህገ መንግስት ሁሉንም ነገር /ህዝቡንም መሬቱንም/ ጠቅልሎ የንጉሠ ነገስቱ “ንብረት” እንደሆኑ የሚያስብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚሁ ሥርዓት በ1948ቱ አዋጅ የተሻሻለውን ህገመንግስት ስንመለከት ደግሞ ለርዕሠ ጉዳያችን ጥሩ ማሳያና የሥርዓቱንና የሃይማኖቱን ግንኙነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በተለይ አንቀጽ 21፡፡

“ከቅዱሳን ነገስታት ከአብርሃ ወአጽብሃ ጀምሮ በኢትዮጵያ ጸንቶ የኖረውን ከእስክንድሪያ ከቅዱስ ማርቆስ መንበር የተመሠረተውን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አጽንተን ጠብቀን እንኖራለን” ይላል አንቀጽ 21 “የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችንን ሃይማኖት አጽንቼ እኖራለው፡፡” የሚለው ድንጋጌ ደግሞ በዚሁ አንቀጽ ላይ የሰፈረ የአልጋ ወራሹ ቃለመሃላ ነው፡፡

ይህ የሚያመለክተው የመንግስት ሃይማኖት በወቅቱ ስለመኖሩና ይኸውም የኦርቶዶክስ እምነት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታዲያ በሃገሪቱ ታሪክ የየራሳቸው ድርሻ ያላቸው ሃይማኖቶችና ተከታዮቻቸው በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ተቻችለው ኖሩ? የሚለው ጥያቄ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በንጉሠ ነገስቱ ዘመነ መንግስት በነበረው ህገመንግስት ስለሃይማኖት ነፃነት የተገለጸው አንድ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለሃይማኖቶቹ ተቻችሎ መኖር በቂ ዋስትና ነው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ስለሚሆን፣

አንቀጽ 40 “የህዝብን መልካም ፀባይ ወይም ፀጥታን በፖለቲካ ረገድ የሚያውክ ካልሆነ በቀር በንጉሠ ነገስቱ ግዛት የሚኖሩ ሰዎች የሃይማኖታቸውን ሥርዓት አክብረው በነፃ ከመፈጸም አይከለከሉም፡፡”
ይላል፡፡  ይህ ታዲያ ለብቻው ለመቻቻል ዋስትና ሆኖ ይሆን? ምላሹን ለታሪክ ተማራማሪዎች ልተወው፡፡ በኔ በኩል የየትኛውም እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያዳበሩት መልካም ሥነ ምግባር የመቻቻላችን ሚስጥር ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤቶች ነን ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡

ወደ ደርግ ሥርዓት ስንመጣም በዋናነት የምናገኘው የ1980ውን ህገመንግስት ነው፡፡ ከዚህ ህገ መንግስት ከአጀንዳችን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ደግሞ አንቀጽ 46 ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት የተረጋገጠ መሆኑን የሚገልጸው ይህ አንቀጽ የሃይማኖት ነጻነት አጠቃቀምን በተመለከተ የአገርንና የአብዮትን ደህንነት እንደዚሁም የህዝብን መልካም ሥነ ምግባርና የሌላውን ዜጋ ነፃነት የሚነካ መሆን እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡ ዳሩ ግን ሃይማኖት የአድሃሪዎች መሳሪያ ጎታችና የፀረ አብዮት መሳሪያ ነው ብሎ ለሚያምነው ደርግ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት አልተዋጠለትም፡፡ ከዚሁ እምነቱ የተነሳም ብዙ የሃይማኖትና የእምነት ተቋማትን የዘጋበትን ተከታዮቻቸውን ለእንግልትና ለስደት የዳረገበትን ሁኔታ እናስታውሳለን፡፡

በአጠቃላይ እስከ ደርግ ውድቀት የነበረውን ሆኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል መንግስታት ከሃይማኖት ገለልተኛ ያልነበሩበት አልያም ጸረ  ሃይማኖት የነበሩባቸው መሆኑን መገንዘብ ያስችለናል፡፡

በዚህ ረገድ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት መነሻችንን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ ህዳር 1987 የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አምነውና ፈቅደው መቀበላቸውንና ማጽደቃቸውን እንዲሁም ህገ መንግስቱ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ስለመሆኑ በመግቢያው ላይ ሰፍሯል፡፡  ህገ መንግስቱ  የሃይማኖት ነፃነትን በተመለከተ በአንቀጽ 11 ላይ  የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን አስፍሯል፡፡

ይህ አንቀጽ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን መንግስታዊ ሃይማኖት እንደሌለ፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባና ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ የሚገልጽ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የሃይማኖት ነጻነትን በተመለከተ መነሻና መሰረታዊ መርሆዎች ናቸው፡፡

በሌላም በኩል በአንቀጽ 27 የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነትን የተመለከተውን ድንጋጌ እናገኛለን፡፡ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊና እና የሃይማኖት ነፃነት ያለው እንደሆነ ይህ መብት ደግሞ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክና የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን እንደሚያካትት የሚያመላክት ነው፡፡

ሌላውና ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በተያየዘ በዚህ አንቀጽ የተገለጸው ነጥብ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸውን የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉ የተገለጸውና ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በሃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከላከል እንደማይቻል የሚደነግገው ነጥብ ነው፡፡

ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖሊቲካ አመለካከቶች እና ከባህላዊ ተጽእኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ እንዳለበት ወይም በዚሁ ህገ መንግስት የማህበራዊ ነክ ዓላማዎች በተዘረዘሩበት አንቀጽ 90 ተገልጿል፡፡ ባጠቃላይ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ዜጎች ማንኛውንም እምነት የመከተል መብታቸውን፣ ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

ይህ መልካም ሁኔታና መብት በተረጋገጠበት ሁኔታ ታዲያ በምን ምክንያት ነው የአክራሪነት ዝንባሌ እያቆጠቆጠ የሚገኘው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡

በአገራችን የሃይማኖት እኩልነት መከበር መርሆና የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት መርሆዎች ቀደም ብለን ባየናቸው ሁለት ሥርዓቶች ይጣሱ ነበር፡፡ በታሪካችን አንዱ ሃይማኖት የቤተ መንግስት ሃይማኖት እየሆነ የተወሰደበት ሁኔታም እንደነበር በመጀመሪያ ካየነው የአፄው ሥርዓትና ህገመንግስት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ
በዘመናዊውም ይሁን ባህላዊ እምነቶችና የአካባቢው ፖለቲካዊ አስተዳደር አንድ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደነበርም አይተናል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ሰዎች የሚያነሱት ነጥብ አለ፡፡ ይኸውም ቀደም ባለው ታሪካችን በተወሰኑ የሃገሪቱ ክፍሎች የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት፣በሙስሊም ሱልጣኔቶች ደግሞ የእስልምና እምነት እንደ መንግስት ሃይማኖት ተደርጎ የሚወሰድበት አመለካከት በአንዳንዶች ዘንድ ሰርጾ ስለነበረ አስተሳሰቡ አሁንም ድረስ በአንዳንዶች ዘንድ መኖሩ  ነው የሚል ነው፡፡

የኢፌዴሪን ህገ መንግስት በተመለከተ የቀረቡ የተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶች እንዲሚያመለክቱት አንዳንድ ሰዎች የሃይማኖት እኩልነት መረጋገጡ የአንድን እምነት ክብርና ታሪካዊ ድርሻ ዝቅ ማድረግ ሆኖ እንደሚታያቸውና የሁሉንም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የእኩልነት መብት ማክበር የአንድን ብሄርና ብሄረሰብ ክብርና ድርሻ ዝቅ የማድረግ፣ የሴቶችን እኩልነት ማክበር የወንዶችን ክብርና ድርሻ ዝቅ ማድረግ መስሎ እንደሚታያቸው ይጠቁማሉ፡፡

እኩልነትን ማረጋገጥ የአንዱን ክብርና ድርሻ ዝቅ የሌላውን ደግሞ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን የሁሉንም ክብርና ድርሻ በእኩልነት ለማስቀመጥ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ሃይማኖት መሠረታቸውን ህገ መንግስት እስካደረጉ ድረስ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩትን ያህል ቀደም ብለን የጠቀስናቸው አመላካከቶች ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታ እንቅፋት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

አክራሪነት የሌላውን ነፃነት በመድፈቅና በማፈን የራስን እምነት  በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን የሚደረግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ይህ የአክራሪነት አመለካከት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የእምነት ተከታዮች ዘንድ የታየና አልፎ አልፎም ግጭት ያስከተለ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ምሳሌ ማነሳት ቢያስፈልግ አንዳንድ ሙስሊሞች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሙስሊሞች እንኳ ሳይቀር ሃቀኛ ሙስሊሞች አይደሉም ብለው በመፈረጅ የእምነት ተቋሞቻቸውን ለማፍረስ የከጀሉበትን ሁኔታ ታዝበናል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ  ከዚህ ሁኔታ መገንዘብ የቻለው አገልግሎትን ወይም ሸቀጥን ለገበያ አቅርቦ ከመጠቀም ይልቅ ሃይማኖታዊ እምነትን ለገበያ አቅርቦ መጠቀምን የመረጡ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን ነው፡፡

የሃይማኖት አክራሪነትን የሃይማኖት መሪዎች የቅዱሳን መጻህፍትን መሠረታዊ መርሆዎች የሚፃረር እንደሆነ በማስረዳት ያወግዙታል፡፡ ወደ መንግስት ስንመጣም የራሱን ፍላጎት በሌላው ላይ ለመጫን የሚሞክረው ፀረ ህገ መንግስት ሃይል እንደሚያወራው ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ወይም አንድን ወይም ሌላውን ሃይማኖት ለመደገፍና ለማራመድም ሳይሆን ሁሉንም ዜጎች በልማትና በዴሞክራሲ ዙሪያ ለማንቀሳቀስ የተደራጀ መንግስት በመሆኑ አክራሪነትን የሚተረጉመው በልማትና ዴሞክራሲ አጀንዳ ላይ ካለው ተጽእኖ በመነሳት ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የአክራሪነት ዘመቻም በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ከታሪክ ናሙናነት አልፈው ሰፋ ያለ ተቀባይነትን ሊያገኙ የሚችሉት እነዚህን የሚሸከምና የሚያራግብ ፖለቲካዊ ሁኔታና ይህንን ሊቀበል የሚችል ነባራዊ ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ ለዚህም ነው በአገራችን የአክራሪነት አደጋ ቀላል ተደርጎ የማይወሰድበት ደረጃ ላይ የደረሰው፡፡

አንዳንድ  በተቃውሞ  ጎራ ለተሰለፉ ሃይሎች የተጀመረውና በማበብ ላይ የሚገኘው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ ጥገኛ ጥቅማቸውን ስለሚነካባቸው ሃይማቶታዊ ጉዳዮችን በማራገብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይም  ሁሉን ታገኛለህ ወይ ሁሉን ታጣለህ የ /zero sum game politics/ አጃቢ የሆኑት አንዳንድ ፕሬሶችም ጥማቸውን ማርካት የሚችሉት ይህንኑ የተቃውሞውን ጎራ አጀንዳ በማራገብ በመሆኑ ይህንኑ እያደረጉት ነው፡፡

ለማጠቃለል መንግስት ህገ መንግስቱ የሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሰረት በማድረግና ሃይማኖታዊ መርሆዎችን አክብሮ ይህን ለሰላማችንና እድገታችን ፀር የሆነ አስተሳሰብ ከሥሩ መመንጠር እንዳለበት ሁሉ እኛም እንደዜጋ የዚህኛው ወይም የዛኛው ሃይማኖት ተከታይ ስለሆንን ሳይሆን፣ የዚህኛው ወይም የዛኛው ፓርቲ ደጋፊ ወይም አባል ስለሆንን
ሳይሆን ሃይማኖትን በሽፋንነት የሚጠቀሙ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ለይተን በመታገል ማስወገድ ካልቻልን በውጤቱ የማልማት መብታችንንና ከልማቱ የመጠቀም እድላችንን ክፉኛ የሚጎዳው በመሆኑ አክራሪነትን አምርረን ልንቃወምና ልንታገለው ይገባል፡፡