የዲፕሎማሲው ጥረት ፍሬ ያፈራበት የመተማመኛ ምዕራፍ

  ዘአማን በላይ
የኢፌዴሪ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሰሞኑን ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የታላቁ ህዳሴ ግድብ አማካሪዎች የሆኑት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች እንዲያጠኑ የሚያስችለውን ውል ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ለመፈራረም መቃረባቸውን ገልፀዋል። በዚህም በሚቀሩ ጥቂት ጉዳዩች ዙሪያ ሶስቱም ሀገራት ውሉን እያጠኑትና እየተነጋገሩበት መሆኑንም ዘገባዎች አስረድተዋል። 
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከወደ ግብፅ የሚወጡ ዘገባዎችም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ “በቴክኒክ ጥናቶቹ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር ለሁሉም ሀገሮች መተማመን የሚፈጥር ነው” ማለታቸውም ተሰምቷል። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም በበኩሉ፤ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ ጥቅሞች ላይ ወደ ተመሰረተ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውቋል። በእኔ እምነት ግብፆች አሁን ለደረሱበት አቋም ሀገራችን ያካሄደችው በድል የታጀበ የዲፕሎማሲ ጥረት ነው። ምንም እንኳን ይህ የስምምነት ምዕራፍ በመካሄድ ላይ ባለው የግድቡ ግንባታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም፤ ምዕራፉ ግን የዚሁ የዲፕሎማሲ ድል ውጤት ይመስለኛል። 
እርግጥ ሀገራችን ከህዳሴው ግድብ አኳያ እያከናወነችው ያለችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ዛሬ ላይ የታችኛዎቹን የተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብፅንና ሱዳንን በጊዜ ሂደት አሁን ለያዙት አቋም አብቅቷቸዋል። በእኔ እምነት ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት የትናንት ገፅታችንን ከመቀየር ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ምክንያቱም ባለፉት ስርዓቶች ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነትና እነዚያ መንግስታት የነበራቸው የአስተሳሰብ ውስንነት ዛሬ ላይ በመሰበሩ ነው።
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 25 ዓመታት ተጉዟል። በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል። በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጨጠጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።
እርግጥም ኢትዮጵያ ላለፉት 13 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት የአቋም ለውጥ መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 
ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ እርግጥ ሀገራችን የኢንቴቤውን ስምምነት ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው። 
በዚህ የግንዛቤ መነሻዋም የተፋሰሱ ሀገራት የኢንቴቤውን ስምምነት እንዲፈርሙ ለዓመታት ያላሰለሰ ጥረቶችን አድርጋለች። ይህ ጥረቷም ቀደም ሲል ስምምነቱን ላለመቀበል ስታንገራግር የነበረችውን ግብፅን ጭምር በቅርቡ ‘ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት ልመለስ’ የሚል ጥያቄ እንድታነሳ ጭምር አድርጓታል። ይህም ሀገራችን በግድቡ ዙሪያ በፊትም ይሁን አሁን የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው። 
በታላቁ መሪያችን በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መሰረቱ የተጣለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል። 
አዎ! ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የ“ይቻላል” መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “ኑ አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን። 
ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች። ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች።
እናም የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ በመቀጠሉ ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ መምጣት የቻሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል— የሱዳንና የግብፅ መንግስት አሁን የያዙትን አቋም መፍጠር መፍጠር የተቻለው። ይህ በጎ መንገድ እንዲበረታታም የግብፅን መንግስት ኦፊሴላዊ መግለጫን ከዚያች ሀገር ሚዲያዎች ለይቶ መመልከት ተገቢ ነው። እግር በእግሩም እስካሁን እየተደረገ እንዳለውና ፍሬ እያፈራ እንደሚገኘው ዓይነት የዲፕሎማሲ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው። 
ለዚህም በአንድ በኩል፣ የሀገራችንን መቼም የማይቀየር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ዕውን የሚያደርግና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ በዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ማሳየት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከህዳሴው ግድብ አኳያ ሶስቱም ሀገራት የሄዱበት በሰከነ መንገድ የመደማመጥ መንፈስ እንዲጠናከር ተገቢውን ጥረት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። 
በአንፃሩም በሀገራቱ የተመረጡት ሁለቱ የፈረንሳይ አጥኚ ኩባንያዎች የቀረበው ውልም በሀገራቱ መካከል መተማመንን ለመፍጠር የሚያስችል እንጂ ሌላ ምንም ዓይነት ግብ የሌለው መሆኑን በዝርዝር ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተጀመረውንና ፍሬ እያፈራ የሚገኘውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያጎለብታል። 
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ስለ አማካሪ አጥኚ የፈረንሳይ ኩባንያዎቹ የውል ስምምነትን አስመልክቶ ሀገራቱ ለመፈራረም ተቃርበዋል ማለታቸው፤ ውሉ በሀገራቱ መካከል የመተማመን መንፈስን ለመፍጠር ብቻ ያለመ እንዲሁም ሀገራችን ያካሄደችው የዲፕሎማሲ ጥረተ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል።