ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ከትምክህተኞችና ከጠባብ ብሄረተኞች መጓተት እንጠብቅ!

 

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የተለያያ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አገር ነች። እነዚህብሄሮች፤ ብሄረሰቦችናሕዝቦች አንዱን  ከሌላው የሚለያቸው ቋንቋ፤ ባህልና ወግ፤ ታሪክ… ባለቤቶች ናቸው።የዚያኑ ያህል፤ በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ በአንድ አሃዳዊ ሥርዓት ስር በተዳዳሩባቸው ዓመታት በክፉም ይሁን በደግ ያፈሯቸው የጋራ እሴቶች አሏቸው። ለምሳሌ፤-በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ አባላት ቢያንስ ለመግባቢያ ያህል አማርኛ ቋንቋ ያውቃሉ። በሌላ በኩል፤የኢትየጵያ የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነት ግን በጥናታዊ ፅሁፎች፤ በመጻህፍት ላይ ከመጠቀስ ያለፈ ሕጋዊ እውቅና ተነፍጎት ነበር የቆየው፤ ከተጠቀሰውጊዜ በኋላ አሁን ያለው የአገሪቱ ወሰን በዘውዳዊ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረ በኋላ ባለው አንድ ክፍለ ዘመን ያህልእድሜ፤

የሕግ እውቅና ተነፍጓቸው ነበር ማለት በቋንቋቸው ፍትህን ጨምሮ የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት መብት፤ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት የመጠቀም  መብት አልነበራቸውም ማለት ነው። ይህም ብቻ አይደለም፤ ታሪካቸው ሥርዓቱ የወሰን አንድነቱን ለማጽናት ባነጸው መሰረት ነበር ሲነገር የነበረው፤ እውነተኛ ታሪካቸው ተሸሽጎ ነበር። ባህላቸው አልፎ አልፎ ለይስሙላ ያህል ወይም ጭፈራ ለማድመቅ ያህል ጣል ጣል ከሚደረጉ ዘፈኖችና ጭፈራዎች የዘለለ ብዙም ዋጋ አልተሰጠውም ነበር። በአጠቃላይ የባህል ትንሽ ያለው ይመስል ዝቅ ተደርጎ ነበር የሚታየው፤

ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አባላት በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ፣ ማንነታቸውን እንዲደብቁ ያደረገ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል። ማንነታቸውን የሚገልጸውን ስማቸውን ይቀይሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ዘውዳዊውሥርዓት ይህን ሲያደርግ የነበረው በአጋጣሚ ወይም በየዋህነት ስህተት አልነበረም። ሆን ተብሎ ብዘሃነትን በማቅለጥ ሥርዓቱ የአገዛዙን ቅቡልነት ለማረጋጋጥ የእኔ ነው ብሎ በያዘው አንድ ብሄራዊ ማንነት፤ ቋንቋ፣ ባህል . . . ቀጥቅጦ ለመቅረፅ ታስቦና ስትራቴጂ ተነድፎለት የተካሄደ ነበር።

ዘውዳዊው ሥርዓት አቅልጦ፤ በአንድ ብሄራዊ ማንነትቀጥቅጦ ለመቅረፅ የሞከረው የብሄር ብዝሃነትን ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፤ የሃይማኖትንና የአመለካከትን ብዝሃነት ጭምር እንጂ፤ ዘውዳዊው ሥርዓትመንግሥታዊ ሃይማኖት ነበረው። በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ሃይማኖቶች ሕጋዊ እውቅና አልነበራቸውም። ለምሳሌ፤- ሙስሊሞች እንደ ኢትዮጵያዊ አይቆጠሩም ነበር። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ነበር የሚባሉት፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አይባሉም። የአመለካከት ብዝሃነትም ክልክል ነበር። ማንኛውም ዜጋ የዘውዳዊውን ሥርዓት ምሉዕ በኩለሄነት የሚክድ ወይም የሚጻረር አቋምየመያዝ፤የማራመድ፤የመግለጽ፤ በዚህ አመለካከት የመደራጀት መብት አልነበረውም።

የዘውዳዊው ሥርዓት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፊውዳሊዝም ነበር። የፊውዳሊዝም ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው መሬት በመሳፍንቱ፤ በመኳንነቱና በሌሎች ሥርዓቱ በተለያያ ደረጃ በሚሾማቸው ቢሮክራቶችና ዳኞች ይዞታ ስር ገሚሱ በርስትነት፤ የተቀረው በጉልትነት ነበር። በተለይ የሥርዓቱ ቢሮክራቶችና ዳኞች ጉልተኞች ነበሩ። ሥርዓቱ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ለቢሮክራቶችደመወዝ የሚከፍለው በገንዘብ ሳይሆን በጉልት ነበር። የሥርዓቱ መሳፍንት፤መኳንንት፤ ቢሮክራቶችና ሌሎች በርስትነትና በጉልት የያዙት መሬት የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አቅንተው ይኖሩበት የነበረውን ነው።በተለይ ዘውዳዊው ሥርዓት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ወሰኑን በማስፋት ያካተታቸው የመካከለኛው፤የደቡብ፤ የምስራቅና ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለአገሩ መሬቱን ተነጥቆ በገዛ መሬቱ ላይ በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ መሬት በርስትነትና ጉልት ለተሰጣቸው መሳፍንት፤መኳንንትና ቢሮክራቶች ገባር ጭሰኛነት ተዳርገዋል። ምርታቸውንና ጉልበታቸውን ለባለርስቶችና ለባለጉልቶች የሚገብሩ ምንም የሌላቸው ያጡ የነጡ ደሀ ገባር ጢሰኛ አርሶ አደሮች ሆነው ነበር።

ይህ የአገሪቱን የብሄር፤የሀይማኖት፤ የአመለካከት ብዝሃነት እውቅና የነፈገና ብዝሃነትን አቅልጦ በአንድ ማንነትና አመለካከት የመቅረጽ ስትራቴጂ የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት ስትራቴጂውን አሳክቶ አንድ የተለየ ማንነት ያላቸው ዜጎች መፍጠር አልቻለም። ከዘውዳዊው ሥርዓትመንግሥታዊ ሃይማኖት ውጭ የሆኑ ሃይማኖቶች ምንምያህል ቢገፉ የተወሰኑ ወደሥርዓቱ መጠጋት የፈለጉ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ከማድረግ ያለፈ ሃይማኖቶቹን ግን ማደብዘዝ አልቻለም። ሰዎች የማሰብ ችሎታቸው እስካለ ደረስ ነባራዊውንዓለም ከሚረዱበትና ከሚተነተኑበት የገሃዱ ዓለም አተያይ ወይም ርዕዮተ ዓለም አልቦ ሆነው መኖር ስለማይችሉ የአመለካከት ብዝሃነትን ከማዳፈን ያለፈ ማጥፋት አልቻለም።

የተለያያ ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይህንንበማንነታቸው ላይ የተጫነቀንበር በጸጋ ተቀብለው አያውቁም። በመጀመሪያ ለዚህ የዳረጋቸውን ነባራዊ ሁኔታ በመርህ ተንትኖ በሥርዓት ደረጃ (system) መረዳት የሚያስችል ግንዛቤ ስላልነበራቸው ተቃውሟቸው በሥርዓቱ ላይሳይሆን፤ይልቁንም በተበታታነ ሁኔታ አጠገባቸው በነበረ አስገባሪ ወይም ቢሮክራት ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ የተቃውሞና የትግል አካሄድ አርሶ አደሮቹን ለሞት፤ለእስር፤ ለአደባባይ ግርፋትና ለውርደት ከመዳረግ ያለፈ ጭቆናቸውን ግንከላያቸው ላይ ሊያወርድላቸው አልቻለም። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደው የነበሩ “የገበሬ አመፅ” የሚባሉ የአርሶ አደር ንቅናቄዎችን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

እየከረመ፤ ዘመናዊ ትምህርት ወደሕዝቡ እየዘለቀ፤ የተለያዩ ብሄሮች፤ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አባላት የሆኑ ልሂቃን አየተፈጠሩ ሲመጡ፤ ፊውዳላዊውን ዘወዳዊ ሥርዓትምንነት በመተንተን የጭቆናውን ምንጭ መለየት ተቻለ። ይህን ተከትሎ በሥርዓቱ ላይ ያተኮረ ተቃውሞ መቀሰቀስ ጀመረ። የአገሪቱን አርሶ አደር ከገባር ጭሰኝነት ለማላቀቅ የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ሲቀርብ፤ ከዚሁ ጋር የብሄርና የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ ጎልቶ መውጣት ጀመረ። ይሄኔ ነበር ተቃውሞው በሥርዓቱ ላይ ያተኮረው።

ይሁን እንጂ ይህ ትግል የልሂቃን ማፍሪያ በሆኑ የ2ኛ ደረጃና ጥቂት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተገደበ ነበር። ትግሉም የተደራጀና መደረሻውን የሚያውቅ አልነበረም። በመጨረሻ ይህ የተማሪዎችና የልሂቃን ተቃውሞ ስርአቱን መነቅነቅ ቢችልም የተነቃነቀውን ስርአት አስወግዶ በህዝባዊ መንግስት መተካት ግን አልቻለም። ይህ የሆነው ትግሉ የተደራጀና መድረሻውን አንጥሮ የሚያውቅ ሰላልነበረ ነው። አናም በወቅቱ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለመድፈን የሚያስችል አደረጃጃትና አቅም የነበረው ያንኑ ዘውዳዊ ስርአት ሲያገለግል የነበረው መለዮ ለባሹ ነበር።

መለዮ ለባሹ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደስልጣን ሲመጣ፤ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት ዓላማ አልነበረውም። በጥገናዊ ለውጥ ሥርዓቱን ማስቀጠል ነበር ዓላማው፤ ይሁን እንጂ፤በወቅቱ ጎልቶ የወጣውን 90 በመቶ ገደማ የአገሪቱን ሕዝብ በሚወከለው አርሶ አደር ላይ የተጫነውን የገባርነት ጭቆና በጥገና ማለፍ የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። በመሆኑም ታሽቶ ታሸቶ ወደስልጣን በመጣ በስድስተኛው ወር የመሬትለአራሹን አዋጅ አወጣ። በዚህ አዋጅ የኢትዮጵያ አርሶ አደር በባለርስትና በባለጉልትተጭኖበት የነበረው የገባርነት ጭቆና ተነሳለት። የራሱ መሬትምኖረው፤

ወታደራዊው ቡድን አስከፊነቱ ጎልቶ ወጥቶ ለነበረው ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ምላሸ ቢሰጥም የኢትዮጵያን የብሄር፤ የአመለካከትና የሃይማኖት ብዝሃነት ማክበር ግን አልፈቀደም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እውቅና መነፈጋቸው ቀጠለ። በቋንቋቸው የመንግሥት አገልግሎት አያገኙም። ልጆቻቻውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር አይችሉም። ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደግና ማስተዋዋቅ፤ ትክክለኛ ታሪካቸውን ማውጣትና መንከባከብ፤በሚኖሩበት ወሰን ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት መነፈጋቸው ቀጠለ።

ጭቆናው ሲቀጥል ትግሉም ቀጠለ። በወቅቱ ሃያ ገደማ የሚሆኑ በብሄራዊ ማንነት ተደራጅተው ወታደራዊውን ሥርዓት ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ የብሄራዊ ነፃነት ድርጅቶችን የፈጠረው ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው። በአመለካካት ተደራጀተው ሥርዓቱን ለማስወገድ የሞከሩና በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶችም ነበሩ። ወታደራዊውን አገዛዝ ለመጣል በተካሄደው ትግልውስጥ የነበራቸው ድርሻ የአንዳቸው ከሌላው የተለያየ መሆኑ ባይካድም፤ ወታደራዊው ደርግ ለውድቀት የበቃው በዚህ የነፃነት ትግል ነው።

ወታደራዊው ደርግ ተወግዶ ግዙፉ ሰራዊቱ ሲበተን አገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ የነፃነት ትግል ሲያካሂዱ በነበሩ ኃይሎች ተቦጫጭቃ ለመበታተንበሚያበቃ ሁኔታ ለአደጋ ተጋልጣ ነበር።ይሁን እንጂ፤ ሁሉም በብሄር ላይ ተመስርተው የተደራጁና በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት ሌሎችም ኃይሎች በየአቅጣጫው አገሪቱን ከመቀራመትይልቅ፤ ተጭኖባቸው የነበረውን ጭቆና አስወግደው አብረው መኖር ይችሉ እንደሆነ በአንድ አዳራሽ ታድመው መከሩ። እናም አሃዳዊውንየመንግሥትሥርዓት ሸረው ብዝሃነትን የተቀበለ፤ሕዝቦች በፈቃዳቸው የሚሳተፉበትናበእኩልነት አብረው የሚኖሩበት መንግሥት ለመመስረት ተስማሙ። ወደዚህየሚያደርሳቸውን የሽግግር መንግሥትም አቋቋሙ። 

የሽግግር መንግስቱ ዋና ተግባር የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ፤በእኩልነት፤በመከባባርና በመቻቻልየሚኖሩበት፤ የወሰን ሳይሆን የሕዝቦች አንድነት ያላት አገር መመሰረት የሚያስችል ሕገመንግሥት በሕዝብ ተሳትፎና ውሳኔ እንዲዘጋጅ ማድረግ ነበር። የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት የተዘጋጀውና የጸደቀው፤ የኢፌዴሪ መንግሥትም የተመሰረተው በአጭሩ ይህን ሂደት ተከትሎ ነበር። ይህን የኢፌዴሪ መንግሥት ምስረታ ሂደት ጠቅለል አድርጌ ያቀረበኩት የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አካል በመሆኑ ሁሉም ለአካለ መጠን የደረሱ ኢትዮጵያውያን ያውቁታል በሚል እምነት ነው።

እንግዲህ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ባለቤቶች ማንነታቸውን እንደጠበቁ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በፈቃዳቸው ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዜጎች ሆነው በእኩልነት ለመኖር የተስማሙብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው። ይህን እውን ማድረግየሚያስችለውየመንግሥትአወቃቀርደግሞ ፌዴራላዊ አወቃቀር ነው። በዚህ መሰረትበሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 1 “የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ” በሚል ርዕስ ስር፤ ይህ ሕገመንግሥት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀርን ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ በሚል ስም ይጠራል።የሚል ድንጋጌ ሰፍሮ እናገኛለን።

ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የአገሪቱ ህልውና መቀጠል ወይም ያለመቀጠል ጥያቄ ነው። አገሪቱ የብሄርና የአመለካከት ብዝሃነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከተፈለገ ምትክ የሌለው አማራጭ ነው።

እንግዲህ፤ ፌዴራሊዝም የየራሳቸው የስልጣን ወሰን ያላቸውን የሁለት መንግሥታት ሥርዓት አጣምሮ የያዘ ነው። ማለትም ማዕከላዊውን ወይም የፌዴራል መንግሥቱንና እንደየአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ የተዋቀሩ የግዛትወይምየክልልመንግሥታትን የያዘ ነው። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራሉ አካል የሆኑት ክልላዊ መንግሥታት የተዋቀሩት በአመዛኙ በብሄር አሰፋፈር ላይ በመመሰረት ነው። የክልልንአወቃቀርበተመለከተ ሕገመንግሥቱ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብአሰፋፋር፤ ቋንቋ፤ ማንነትና ፈቃድ ላይ ነው”ሲል ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የፌደራል መንግሥቱ አካላት የሆኑ ዘጠኝ ክልሎች ተወቅረዋል።የፌዴራል መንግሥቱ ማለትም፤የኢፌዴሪ መንግሥትበእነዚህክልሎች የተዋቀረ ብቻ ሳይሆንስልጣኑም የመነጨው ከእነዚህ ክልሎች ነው።የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎቹ የተነጠለ የራሱ ህልውና የለውም።

በክልሎች የተዋቀረው ፌዴራላዊ መንግሥት ብሄሮች፤ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውንበራሳቸውየማስተዳደር መብት አስገኝቶላቸዋል። በሚኖሩበት ክልል፤ዞንወይም ወረዳ በመረጧቸውወኪሎቻቸው አማካኝነት ይተዳደራሉ። በቋንቋቸው የመንግሥት አገልገሎት ያገኛሉ።ልጆቻቻውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውያስተምራሉ።ታሪካቸውንይንከባከባሉ። ባህላቸውን ያሳድጋሉ። በወሰናቸው ውስጥ ያለውንእምቅየኢኮኖሚ  አቅምለሕዝባቸው የተሻለ ህይወት ጥቅም ላይ ያውላሉ። ወዘተ. ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩና ፌዴራል መንግሥቱን የመሰረቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል በሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝባቸው ቁጥር ልክ ስልጣን ይጋራሉ።ሕገመንግሥታቸውንየመተርጎምስልጣን ባለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥም ውክልና አላቸው። አበስፈጻሚው አካል ውስጥም በተመሳሳይ የብሄር ተዋጽኦንና ብቃትን ታሳቢ ባደረገ አኳኋንይሳተፋሉ።

በኢፌዴሪ የመንግሥት ሥርዓትውስጥአንድብሄር የበላይ ሆኖ ሌሎችን ከፈቃዳቸው ውጭ መግዛት፤ወይም በክልላዊ ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚያስችል እድል የለም። ኦሮሚያን የሚያስተዳድሩት ኦሮሞዎቸ ናቸው። አማራን፤ትግራይን፤የኢትዮጵያ ሶማሌን፤አፋርን፤ ወዘተ.የሚያስተዳድሩትክልሎቹን የመሰረቱትብሄሮችናብሄረሰቦች ናቸው። አማራ ወይም ትግራይ የኢትዮጵያ ሶማሌን ወይም ኦሮሚያን ወይም አፋርንበበላይነት ማስተዳደር የሚያስችላቸው አንድም መንገድ የለም። ይህ አሁንበአገሪቱ በተጨባጭ እየታየ ያለ ዕውነታ ነው። እናም በአገሪቱ የአንድ ብሄር ወይም አንድን ብሄር የሚወክል ፓርቲ የበላይነት አለብለው በግድ እመኑ የማለትያህል የሚጨቃጨቁ፤በተለይ አሃዳዊ ሥርዓት የመመሰረት ህልም ያላቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ያሳያል።

ያም ሆነ ይህ፤ ኢትዮጵያ በአገሪቱ የነበረውን መሰረታዊ ቅራኔ፤ ማለትም የብሄርን ቅራኔና ብዝሃነትን ታሳቢ በማድረግ የአገሪቱ አንድነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ያለአማራጭ ተመራጭ ሆኖ የተዋቀረውፌዴራላዊ ሥርዓት ግን ሥራ ላይ በቆየባቸው ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቃውሞዎችገጥመውታል። ቀዳሚዎቹ የፌደራላዊ ሥርዓቱ ተቃዋሚዎች የአገሪቱንብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አቅልጠው ማንነታቸውን አጥፍተው በአንድ መለያ ማንነት የመግዛት ህልም ያላቸው የአሃዳዊ ሥርዓት አራማጆች ናቸው። እነዚህቡድኖች ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገሪቱ ተከፋፈለች፤ተበጣጣሰች፤ አንድነቷ ጠፋወዘተ. እያሉ ውዥንብር ሲነዙ፤ለዚህም ተጠያቂ ያሉትንወገንበጠላትነትፈርጀው ሲያወግዙና ሕዝብ እንዲነሳበት ሲቆሰቁሱቆይተዋል። እነዚህቡድኖችአገሪቱ በብሄር ላይ ወደተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት የመጣቸው የአገሪቱ ህልውና ዘላቂ እንዲሆን ብቸኛው አማራጭ ስለሆነ መሆኑን አያውቁም ወይም ማወቅ አይፈልጉም። አገሪቱን ወደአሃዳዊ ሥርዓት መመለስምመድረሻው መበታተን ብቻ መሆኑን ማሰብ አይፈልጉም። በእርግጥ  ከቅርብ ግዜ ወዲህ እኛ የምንመኘው አሃዳዊ ሥርዓት መምጣት ወይም መመለስ ካልቻለ አገሪቱ ትጥፋ የሚል አቋም የያዙ ይመስላሉ። ኢትዮጵያን እርስ በርስ በማተራመስ ለመበታተን ስትራቴጂ ነድፎ በሚሰራው የኤርትራ መንግሥት ስር በትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚነት የተሰለፉ የአሃዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች ለዚህ በአስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ የአሃዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች በጥቅሉ ትምክህተኛ ብሄረተኞች ናቸው። ብዝሃነትን ጨፍልቀው አንድ ማንነት የበላይ መሆን አለበት የሚል እምነት ያላቸው ትምክህተኞች፤

ሌላው ፌዴራላዊ ሥርዓቱን በመቃወም የተሰለፈው ወገን በብሄር ላይ የተደራጀ ጎራ ነው። በዚህ ጎራ ያሉ ቡድኖች እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄር በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከተረጋጋጠውየሕዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መንገድ ውጭ አንድን ብሄር ገንጥለው የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ቡድኖች መገንጠልን መድረሻ ያደረጉም ናቸው። በመሰረቱ መገንጠል መብትና ነፃነት ወደተረጋገጠበት ሥርዓትመሸጋገርን የሚያረጋግጥ አካሄድ አይደለም። ኤርትራን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። የኤርትራ መገንጠል የኤርትራውያንን መብትና ነፃነት ማስከበር አልቻለም። መገንጠል ብቸኛ አማራጭ የሚሆነው በተለይ አሃዳዊ ሥርዓትየሚኖሩብሄሮች መብትና ነፃነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችልምንም አማራጭ ሲጠፋ ብቻ ነው። ያኔ መገንጠል የመጨረሻ አማራጭ ነው። ከእነዚሀ ሁኔታዎች ውጭ የአንድን ብሄር መገንጠልየሚፈልጉ ቡድኖች በአብዛኛው ጠባብ ብሄረተኞች ናቸው። ይህን ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄር ገንጥለው ለመግዛት የሚፈልጉ ቡድኖችም እንደአሃዳዊውሥርዓትተስፈኞች ሁሉ በኤርትራ መንግሥት ስር ኢትዮጵያን የማፈራረስ ስትራቴጂውንለማስፈፀም ተሰልፈው እናገኛቸዋለን።

ከሁሉም የሚያስገርመው እነዚህ ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ፤ ምንም የጋራ ነገር የሌላቸውና ሊኖራቸውምየማይችል ትምክህተኛ ብሄረተኞችና ጠባብ ብሄረተኞች በኤርትራ መንግሥት ትእዛዝ ግንባር ፈጥረው በየፊናቸው አገሪቱን እየጎተቱ የአገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ የሚችለውን ብቸኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማፈራረስ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ሰሞኑን በተወሰኑ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በማህበራዊ ሚዲያ በሚነዛ ውዥንብር የተቀሰቀሱት ሁከቶችና ሊቀሰቀሱ የታቀዱ ብጥብጦች አገሪቱን ከሁለት ከማይታረቁ ፅንፎች እየጎተቱበእርስ በእርስ ብጥብጥ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የማፈራረስ ፍላጎትና ሙከራ ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት መርህ ላይ በመመስረት በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ያጸናውን ፌደራላዊ ሥርዓት ማፍረስ ማለትአገሪቱን ማፍረስመሆኑን ተገንዝቦ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ከትምክህተኛናከ ጠባብ ብሄረተኞች መጓተት መጠበቅ አለበት።