ከልዩነት አንድነት ይቅደም

 

ኢብሳ ነመራ

በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ወደኢትዮጵያ ተመልሷል። የአትሌቲክስ ቡድኑ በተለይ ባለፉት ስድስት የኦሎምፒክ ውድድሮች እንደነበረው ባይቀናውም አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብርና አምስት የነሃስ ሜዳልያዎችን በማግኘት በሜዳልያ ብዛት ከአፍሪካ የ3ኛነት ደረጃን አግኘቷል። ይህ ላለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ባልተለመደ ሁኔታ አንድ የወርቅ ሜዳልያ ብቻ የመገኘቱ ነገር ህዝቡን ትንሽ ቅር ቢያሰኘውም፣ ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ኬንያ፣ እንግሊዝ ወዘተ አጋጥሟቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በመሰራታቸው ማሻሻል የቻሉት በመሆኑ የኢትዮጵያም ሊስተካከል የሚችል መሆኑ ሁላችንንም ያስማማናል። በዘነድሮው የሪዮ ኦሎምፒክ ህዝቡን የበለጠ ቅር ያሰኘው ሃገሩን ወክሎ በወንዶች ማራቶን ተሰልፎ የብር ሜዳልያ ያገኘው ፈይሳ ሌሊሳ አሸንፎ ከገባ በኋላ የሃገሩን ሰንደቃላማ ለማውለብለበ መጠየፉ ነው።

ፈይሳ ሌሊሳ እጁን ሽቅብ በመስቀልና በማጣመር (X ምልክት በመስራት) በወቅቱ ኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ላለው ተቃውሞ ያለውን ድጋፍ መግለጹ ምንም አዲስ ነገር አይደለም። በሃገር ውስጥ ያሉ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች በይፋ የሚገልጹትና በየጋዜጣው ላይ ተፅፎ የምናነበው ጉዳይ ነው። የፖለቲካ አቋምን ከፖለቲካ ልዩነት ውጭ ሃገራት ስፖርታዊ  ውድድር በሚያደርጉበት ኦሎምፒክ ላይ ማንፀባረቁ ከኦሎምፒክ መንፈስ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ተገቢ ባይሆንም፣ አትሌት ፈይሳ የተቃውሞ አቋም መያዙ በራሱ እንደነውር የሚወሰድ አይደለም፤ ይህን ሃገር ቤት በሰላማዊ መንገድ ሊያደረገው ይችል ነበርና። የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆን ጭምር በሰላማዊ መንገድ በይፋ ሊያራመደው ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ አመለካከትን በግልም ሆነ ከሌሎች ጋር በመደራጀት የማራመድ፣ በአመለካካት ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር መብት በህገመንግስት ተረጋግጧል፤ በተግባርም እየታየ ያለው ይሄው ነው።

ከፖለቲካ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተከለከለው፣ አቋምና አመለካከትን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ማለትም የሌሎችን መብትና ነፃነት በሚጋፋ የሃይል መንገድ ማካሄድ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ሳይሆን የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ባላቸው ሃገራትም የተከለከለ ነው። ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸውን ሃገር አቋራጭ አውራ ጎዳናዎች በመዝጋት፣ በድንገት ተነስቶ እውቅና የሌለው የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማት፣ . . . ላይ ድንጋይ እየወረወሩ በማፈራራስ፣ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የተሰማሩ የፖሊስ ሰራዊት አባላትን በድንጋይና በዱላ በመደብደብ፣ በጥይትና በቦምብ በመግደል፣ መሳሪያ ለመንጠቅ ግብግብ በመግጠም ወዘተ ተቃውሞን መገለፅ የተከለከለ ነው፤ ይህን ማድረግም ወንጀል ነው። አሜሪካና አወሮፓ ሰዎች ውስጥ ለውስጥ ተጠራርተው እውቅና የሌለው ሰላማዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ከላይ በተገለጸው ሰላማዊ ያልሆነ መንገድ ተቃወሞ ቢያነሱ ፖሊሰ ጭጭ ብሎ እንደማይመለከታቸው የታወቀ ነው። በኢትዮጵያም የዚህ አይነት ተቃውሞ ብቻ ነው የተከለከለው። ኦሮሚያ ውስጥ በዚህ አኳኋን ለሃይል ተቃውሞ የወጡና ሰላም ለማስከበር ስራ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት ህይወት መጥፋቱ ይታወቃል። ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳዘነና መሆን ያልነበረበት ነው።

እናም አትሌት ፈይሳ ተቃውሞውን በኦሎምፒክ አደባባይ ላይ መግለጽ ሳያስፈልገው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ በሃገሩ ላይ መገለጽ ይችል ነበር። አትሌት ፈይሳ አሁንም ወደሃገሩ ተመልሶ ጀግናው አትሌት እየተባለ መኖር ይችላል፤ ይህን መንግስትም አረጋግጦለታል። ይህ መብቱ አሁን ስልጣን ላይ ባለው መንግስት ወይም በአንድ ባለስልጣን የተቸረው ሳይሆን ቀድሞውኑም በህገመንግስት የተረጋገጠለት ግለሰባዊ መብትና ነፃነቱ ነው።

ያም ሆነ ይህ ፈይሳ ሌሊሳ ተሳስቶም ይሁን የሚሰራውን በወጉ ተረድቶ የሚፈልገውን አድርጓል። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ድርጊቱን ከደንብ ውጭ ነው በሚል፣ ኢትዮጵያ በፈይሳ በኩል ያገኘችውን የብር ሜዳልያ እንዳይነጥቅ እንጂ ድርጊቱ በሃገርና በህዝብ ላይ – በህገመንግስታዊ ስረአቱ ላይ የሚያመጣው የተለየ ትፅአኖ ይኖራል የሚል ግምት የለኝም። ባይሆንና ባያደርገው ግን ጥሩ ነበር።

ፈይሳ ተቃውሞውን በምልክት አሳይቶ ውድድሩን በሁለተኝነት እንዳሳረገ ጋዜጠኞች አነጋግረውት ነበር። በዚህ ቃለመጠይቅ ከተቃውሞው ጋር በተገናኘ ከቤተሰቦቹ አንድም የታሰረ ወይም ሌላ ጉዳት የደረሰበት ሰው አለመኖሩን፣ ሚስትና ልጆቹም ሃገር ቤት መሆናቸውን አረጋግጧል። ይሁን እንጂ ፈይሳ ወደሃገሬ ከተመለስኩ ይገድሉኛል፣ ባይገሉኝ እንኳን ይከሱኛል፣ ባይከሱኝ እንኳን ከሃገር መውጣት ይከለክሉኛል ብሏል።

ፈይሳ በስፖርት ሞያው ተጠምዶ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ አላስተዋለው እንደሆነ እንጂ ሰዎች ስርአቱን፣ ወይም አንድን ድርጊት ወይም ህግ ስለተቃወሙ ብቻ የሚገደሉበት ሁኔታ የለም፤ ይተደርጎም አያውቅም። ሰዎች በአመለካከተቻው፣ በተቃውሞ አቋማቸው ወዘተ ይገደሉ የነበረበት ስርአት ፈይሳ ሳይወለድ ከወታደራዊው ደርግ ስርአት ጋር ጠፍቷል። እናም ፈይሳ ስለተቃወምኩ ብቻ ይገድሉኛል ብሎ ማሰቡ ስህተት ነው። እርግጥ ነው ሰዎች በህግ የተደነገገነ ወንጀል ፈፅመው ሲገኙ በይፋ ፍርድ ቤት ክስ ይመሰረትባቸዋል። ፈይሳ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደውን ተቃውሞ መደገፉን በምልክት መግለጹ ብቻ እንደማያስከስሰው ግን ግልፅ ነው፤ እሱም አሳምሮ ያውቀዋል።

እንግዲህ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት የኢትዮጵያ ህዝብ ፈይሳ ተቃውሞውን መግለጹ ሳይሆን የኢፌዴሪ ሰንደቅ አላማን አለማንሳቱ ቅር አሰኝቶታል። የሻአቢያ ኢትዮጵያን የማጠፋት ዓላማ የሚደግፉ ካልሆኑ በሰተቀር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዚህ ቅር ተሰኝቷል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ፈይሳ እነደአበዛኞቹ በትምክህተኝነት የኢፌዴሪን ሰንደቃላማ የሚቃወሙ ሰዎች አይደለም። ፌደራላዊ ስርአቱን ይደግፋል። ፈይሳ ከአዲስ አበባ ወደሪዮ ለመብረር ሲነሳ ኤር ፖርት ላይ ቃለመጠይቅ በሰጠበት ግዜ ይህን አረጋግጧል። ለቃለመጠይቁ በኦሮሚኛ ምላሽ በሰጠበት ወቅት አንገቱ ላይ ጥቁር፣ ነጭና ቀይ  ቀለማት ያለው የኦሮሚያን ሰንደቃላማ የሚወክል የአንገት ልብስ ማድረጉ ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል። የመዳሊያ ሽልማቱን ሲቀበል ለተቃውሞ ያጣመረው አጁ ላይም ይህንኑ የኦሮሚያ ሰንደቃላማን የሚወክል ጨርቅ አስሯል።

ይህ የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ ማሰተዳደር መቻሉን የሚያመለክት የክልላዊ መንግስቱ ሰንደቅዓላማ በኢፌዴሪ ህገመንግስት የተረጋገጠ ነው። ባለሰማያዊው  አርማ የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ደግሞ ራስን በራስ በማስተዳደር የተገለፀውን የብሄሮች እኩልነት የሚያንፀባርቅ ነው። እናም አትሌት ፈይሳ እንደትምክህተኞች ከፌደራላዊ ስርአቱ ጋር ፀብ የለውም። ከኢፌደሪ ሰንደቃላማ ጋርም እንዲሁ ፀብ ሊኖረው አይችልም። አሁን የፈይሳን ጉዳይ ለትርምስ ፖለቲካ ፍጆታነት ለመጠቀም የሚቅበዘበዙ ቡደኖች ፈይሳ እንደማንነቱ መገለጫ የሚወደውን የኦሮሚያን ሰንደቃላማ ይፀየፉታል። ለፈይሳም አክብሮት እንደሌላቸው ግልፅ ነው። ፈይሳ ሰንደቃላማውን አለማንሳቱ በዙዎችን ቅር ያሰኘው በዚህ ምክንያት ነው። ሰንደቃላማውን የሸሸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት በፈለጉ ሰዎች ተመክሮ ሊሆን እንደሚችል  ግን እንገተምታለን፣ ምልክቶችም አሉ።

በአጠቃላይ ፈይሳ በኢፌዴሪ ስርአት ላይ ጥላቻ ያለው ሰው መሆኑን የሚያመለክት አንዳችም ነገር የለም። አፍ በፈታበት ኦሮሚኛ ቋንቋ እየተማረ ነው ያደገው። በኦሮሚኛ ቋንቋ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት በሚችልበት ስርአት ውስጥ ነው ያደገው። እኔ ባደኩበት ዘመን እንደነበረው ኦሮሞነት በማያሸማቅቅበት፣ የብሄሮች እኩልነት በተረጋገጠበት ስርአት ውስጥ ነው ያደገው። እነዚህ የኢፌዴሪ መንግስት ትሩፋቶች ናቸው። በኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የኢፌዴሪ ስርአትን የመቃወም ሳይሆን፣ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የልማት ጥያቄ የቀሰቀሰው ነው። ይህን የክልሉ መንግስትም ያምናል። በመሆኑም ትምክህተኞች ግዚያዊ ውዥንብር ከመፍጠር ያለፈ ከፈይሳ አቋም የሚያገኙት ትርፍ የለም።

ፈይሳ በኦሮሞ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና አጠቃላይ የሃገሪቱን ሁኔታ በተውገረገረ መንገድ ተረድቶ ወይም በክፉዎች ምክር ተታሎ የወሰደው ከሃገሩ የመኮብለል እርምጃም ብዙዎችን አሳዝኗል። በዚህ እርምጃ ግን ከማንም በላይ ራሱን ነው የሚጎዳው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሃገራቸው ያላቸውን ክብር ቢያስታውስ መልካም ነው። እርግጥ መቼም ቢመለሰ ሃገሩ የእርሱ ነች። ከነሙሉ የአትሌትነት ክብሩ ትቀበለዋለች።

ፈይሳ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰንደቃላማ ያለውን ክብር ገልፆ ለዚህ ሰንደቃላማ መኖር ምክንያት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ዋጋ አለመስጠቱ ብዙዎች ዘንድ አንድ ጥያቄ ጭሯል። ይህም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በኖሩባቸው ያለፉ ሃያ አምስት ዓመታት ከጋራ አሴቶቻችን ይልቅ በልዩነታችን ላይ አተኩረናል ከሚል ስጋት የመነጨ ነው። ኦሮሞዎች፣ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች፣ አፋሮች፣ ሃራሪዎች . . . እርስ በርስ የሚያስተሳስር የጋራ እሴቶች ያላቸው የአንዲት ኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው። እናም በዜግነት ያለን የጋራ አሴት  የሁሉም ብሄሮች አባላት በሆኑ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ቦታ ሊኖረው የገባል።  በልዩነት ውስጥ ያለ ጠንካራ አንድነት የሚኖረን ይህ ሲሆን ነው። ለጋራ አሴቶቻችን ዋጋ ካልሰጠን፣ የሚያሰተሳስሩንን የጋራ አሴቶች ካልፈጠርንና ካላጎለበትን የላላ አንደነት ነው የሚኖረን። በእስካሁኑ የፌደራል ስርአት ሂደታችን ለክልላዊ ማንነታችን እንጂ ለብሄራዊ ማንነታችን/ለዜግነታችን ብዙም ዋጋ አልሰጠንም፤ በፈይሳ ላይ የተንፀባረቀውም ይሄው ነው። ይህም በበኩሉ፣ በቀጣይነት የጋራ እሴቶቻችን ላይ በበቂ ሁኔታ መስራት ያለብን መሆኑን በግልፅ ያመለከታል፤ ከማስጠንቀቂያ ጭምር።

በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት ይጠንክር!!!