ከወደሙት ሀገራት እንማር !!

     ይነበብ ይግለጡ

ሶሪያንና ሊቢያን እንደ አገር በማፈራረሱ በኩል በውጭ ኃይሎች ገንዘብ የተገዙት የራሷ ልጆች እንደገናም የተለያየ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው የምዕራቡ ዓለም አገራት ይህ ቀረሽ የማይባል ሚና ተጫውተዋል፡፡ ህዝቡ እንዲጫረስ በሚሊዮኖች ከሚፈሰውና ከሚላከው ዶላር ውጭም እጅግ የዘመኑ የጦር መሣሪያዎች ተቃዋሚዎች እንዲታጠቁ በማድረግ የእርስ በርሱ ጦርነት አገሪቷን በከፋና ደም መፈሰስ ውስጥ በመክተት ዳግም ለማንሰራራት ረዥም ዘመን በሚወስድ መልኩ ጭርሱንም እንዳትነሳ አድርገው አጥፍተዋታል፡፡ ቀብረዋታል፡፡

እነሱ ምን ያድርጉ፤ ዋናው የአገሪቷ ልጆች የራሳቸውን ቤት በቁሙ እሣት ሲለቁበት እንዳልነበረ አድርገው ሲያፈራርሱት አገሬና ወገኔ ብሎ ያልተቆረቀረ መንጋ ድፍን አገርን ሲያወድሙ ለምን አገር ይጠፋል ብሎ የተቆረቀረ እምብዛም አልነበረም፡፡ የሊቢያውም የየመኑም ይኸው  ነው፡፡

ሊቢያ ዛሬ ሠላምና መረጋጋት ብሎ ነገር የላትም፡፡ ሁለት ጎራ ሁለት ቦታ ተከፍላ አንዴም ወደ አንድ መንግሥት እንምጣ አሊያም እንከፈል ሲሉ ያቺ ለብዙዎች ተርፋ የነበረች አገር እንዳልነበር እንዳልነበር ሆና ጠፋች፤ ወደመች፡፡ አውሬዎቹ እንዲህ ህዝቡን አባልተውና ከፋፍለው ሲያበቁ ዛሬም ዓለም አቀፎቹ ኩባንያዎች ነዳጁን የተፈጥሮ ጋዙን ንጹህ ወርቁን ያለገደብ ያለከልካይ እየጫኑ ያግዙታል፡፡ የተፈለገውም ይህ ነበር፡፡ ማድረግ የፈለጉትንም አደረጉ፡፡ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡

ቀድሞም ባለቤትና ተቆርቋሪ ተከራካሪ ለምን የሚል ሞጋች የሌላት አገር ሆና እንደልብ ለመዝረፍና ሀብቷን ለማጋዝ ነበር ያ ሁሉ አመጽ እንዲነሳ ሁከትና ትርምስ በአገሪቷ እንዲነግስ አቅደው የሰሩት፡፡ ተሳክቶላቸዋል፡፡

ሞኞቹ ሊቢያውያን ዛሬ ደም እንባ ቢያለቅሱ አገራቸውን ቀድሞ በነበረችበት ሊያገኟት አልቻሉም፡፡ አይታሰብም፡፡ አምባገነን በሚባለው ጋዳፊ የመንግሥትነት ዘመን እያንዳንዱ ሊቢያዊ ለቤት ኪራይ፣ ለመብራት፣ ለውኃ፣ ለትምህርትና ለህክምና አይከፍልም፤ ሲያገባ ግማሽ ወጪው የሚሸፈነው በመንግሥት ነበር፡፡

እርሻ ልጀምር ካለ ግማሽ ወጪው ተሸፍኖ የእርሻ መሣሪያ ተገዝቶ የሚሰጠው በመንግሥት ወጪ ሲሆን አገር ውስጥ አልማርም ውጭ ሄጄ እማራለሁ ካለ ወይንም ውጪ ሄጄ እታከማለሁ ካለ ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው እንደገናም ለኪስ ገንዘብ ተብሎ 1200 ዶላር በየወሩ የሚላክለት በጋዳፊ መንግሥት ነበር፡፡

ሌላው ይቅር አፍሪካ ለአውሮፓ ቴሌኮም በየዓመቱ የምትከፍለውን የሣተላይት አገልግሎት ክፍያ ሙሉ በሙሉ ዕዳውን ከፍሎ አፍሪካ ራሷን እንድትችል አድርጎ ነጻ ያወጣት ዛሬ የምንጠቀምበትን ሞባይል ከውጭ ክፍያ ነጻ አድርጎ ገቢው ለየአገራቱ እንዲሆን ያደረገው መሐመድ ጋዳፊ ነበር፡፡

ከምዕራባውያኑ ጋር ትልቁ ቅራኔና አለመግባባት የተፈጠረው አፍሪኮም የተባለ አፍሪካን በባህር ኃይል ጥምጥም ዙሪያዋን እንደመቀነት ቀንፎ የሚይዝ የአሜሪካ ሠራዊት ወታደራዊ ቤዙን አፍሪካ መሬት ላይ ማድረግ አለበት ብለው ሲነሱ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ሀሳቡን በስብሰባ እንዲያፀድቁት መደለያ ጉቦ ተሰጣቸው፡፡ ጋዳፊ በተራው ብር እየሰጠ ሀሳቡን ውድቅ አደረገባቸው፡፡ በአፍሪካ መሬት የአውሮፓ ሠራዊት መግባት የለበትም በሚል፤ ተሳካለትም፡፡

የኋላ ኋላ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለያጠፉት ተነሱ፤ ዘመቱበት፡፡ ጋዳፊ አምባገነን በመሆኑ የሚጠይቀው የሊቢያ ህዝብ እንጂ የአውሮፓ መንግሥታት አልነበሩም፡፡ አያገባቸውምም፡፡ ተቃዋሚዎቹን በሥልጠናና በመሣሪያ እያደራጁ ዘመቱበት፡፡ በጦር አውሮፕላን ጭምር ደበደቡት፡፡ አገሪቷንም አፈራረሷት፡፡ እሱም በአሰቃቂ ሁኔታ አለፈ፡፡

ይህ ሁሉ ጦርነት የሊቢያን የተፈጥሮ ሀብት ነዳጅና ወርቅ ለመዝረፍ ሲባል ጋዳፊን ማስወገድ ወሣኝ መሆኑን አምነው ያቀናበሩት ዘመቻ ነበር፡፡ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሞኞቹ ሊቢያውያንና ቅጥረኞቹም ጭምር ተረባርበው ያቺን ሀብታም አገር እስከወዲያኛው በሚባል መልኩ አፈራረሷት፡፡

ሊቢያውያን የቱንም ያህል አምባገነን የነበረ ቢሆንም ያንን ሰው የሚተካ ለአገሩም ለአፍሪካም ፍቅርና ክብር የነበረውን መሐመድ ጋዳፊን ከሞት ባይመልሱትም አምሣያውን እንኳን ለማግኘት አይታሰብም፡፡ እናም የሊቢያና የሊቢያውያን ዕጣ ፈንታ ምድራዊ  የሰቆቃ ህይወት ሆነ፡፡ አገራቸውም ፈራረሰች፡፡ ተመልሰው እንደነበር ሊያደርጓት አልቻሉም፡፡

ሊቢያን ዛሬ ላለችበት ቀውስና ትርምስ ያበቋት በተቃዋሚነት ስም በዴሞክራሲ ስም ወዘተ… በለውጥ ስም አመጽ ሲቀሰቅሱ የአደባባይ ሰልፍ ሲያዘጋጁ የነበሩ ምንም ሳያውቁ በየዋህነት ተታለው በቅጥረኞች ገንዘብ ተደልለው የተሰለፉ ሊቢያውያንና እያወቁ የራሳቸውን አገር አፈራርሰው ህግና ሥርዓት ጠፍቶ ለባዕዳን አሳልፈው የሰጧት ሊቢያውያን ናቸው፡፡

የውስጥ ችግራቸውን አገር ሳይፈርስ ተመካክረው በሠላም መፍታት ይችሉ ነበር፡፡ እብደት፣ ጀብደኝነት፣ ስሜታዊነት፣ ግትርነት፣ ሲጮሁ ውሎ ማደር አስተዋይነት ማጣት ለውጭ ኃይሎች በመሣሪያነት መገዛት ትርፉ በማነህ ማነህ የገዛ አገራቸውን በገዛ አገራቸው አፈራርሰዋት አውድመዋት ቁጭ አሉ፡፡ ጠላቶቻቸውም ፈነጠዙ፡፡ እውነተኛ ዜጎችም አንገታቸውን ደፉ፡፡ የተሰደደው ተሰደደ፡፡ ያለቀውም አለቀ፡፡

ዛሬ ሊቢያ የዓለም አቀፉ አይሲስ ዋና መናኸሪያ የነአልቃይዳ መፈንጪያ ሆነች፡፡ ምዕራባውኑ ሊቢያን በጦር ጄት በሚደበድቡበት ወቅት የጋዳፊ ሠራዊት ያለበት ቦታ ላይ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ዋና ትኩረታቸው የሊቢያን መሠረታዊ  ልማት ማፈራረስ ነበር፡፡ ድልድይ ግድቦች የኤሌክትሪክ መስመር ተቋማት ትምህርት ቤቶች ፋብሪካዎች ወዘተ…እነዚህ የአገርም የህዝብም መገልገያ ሀብቶች መሆናቸውን ያውቃሉ፡፡ ምህረት ግን አልነበራቸውም፡፡

አንድን በጦርነት የወደመች አገር መልሶ ለመገንባት ጊዜና በጀት ይጠይቃል፡፡ ይገንባ ቢባልም ተመልሰው እነሱ ተከፍሏቸው እንደሚመጡ ያውቃሉ፡፡ ይህን ዓይነት ወንጀል ነበር የተሰራው፡፡

አገር ማፍረስ የመጨረሻው ቀላል ሥራ ነው፡፡ ወደ ፍርስራሽነትና አቧራነት መለወጥ፡፡ ታሪክን የአገር ቅርስና ኢኮኖሚን ልማትን የህዝብን ቤትና ንብረት መጠጊያና መጠለያ አንድ ሀገር ስንት ለፍታና ደክማ በየትውልዱ ፈረቃ የገነባችውን መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ ማውደምና ባዶ አውድማ እንዲሆኑ ሰውም እንስሳትም የማይኖሩበት አድርገው ነው ሶሪያንም ሊቢያንም ያወደሟቸው፡፡ የመንን ደግሞ ይዘዋታል፡፡

ከሞኝ ደጃፍ ማረሻ ድግር ይቆረጣል ይሏል ይኼ ነው፡፡ በገዛ እጃቸው የራሳቸውን አገር  ተው የሚል አይሆንም አያዋጣንም አገር ይጠፋል ይወድማል አገር እናጣለን የሚል ጠፍቶ የራስን አገር አፈራርሶ ሠላም ጠፍቶ የጦር አውድማ እንድትሆን አድርጎ በሰው አገር ስደት መሄድ፡፡ የግትርና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የለውጥና የዴሞክራሲ ጩኸትና ትግል በሥርዓቱ እስካልተሄደ ድረስ የመጨረሻው ግብ ይኸው ነው፡፡ የአገር መፍረስና ውድመት፡፡

የእብደት ተቃውሞና ጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ ተደምሮበት ያልተጠበቀ መዓትን ያወርዳል፡፡ የመጨረሻው መጨረሻ ቀደምት ታላቅ የነበረችውን አገራቸውን አፈራርሰው የዓለም መሳቂያ ሆኑ፡፡ ዛሬ ህዝቡ ቢፀፀት ቢያዝን ደም እንባ ቢያለቅስ በአበዱና ማስተዋል በተሳናቸው ኃይማኖታዊ ፖለቲከኞች የተነሳ በባዶ ተስፋ እየነዱ የማይወጣበት መቀመቅ ውስጥ ይዘውት መውረዳቸውን ሲያስበው አገሩንና ሠላሙን ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ በጭራሽ ሊመልሰው አልቻለም፡፡

በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል ሆኖ ወርቃቸውን በገዛ እጃቸው አጡት፡፡ አገር ጠፋች፡፡ ታሪካዊ ቅርስ ወደመ፡፡ ህዝብም አለቀ፡፡ አገርም አጡ፡፡ የአበዱና በጥላቻ የተክለፈለፉ ፖለቲከኞች ለህዝባቸው ያስገኙት የመጨረሻው መጨረሻ ትሩፋት ይኸው ነው፡፡

የዓረቡ ዓለም አብዮት የተጠበቀውን ሠላም ዴሞክራሲ ፍትህ መልካም አስተዳደር ለህዝቡ አላስገኘም፡፡ አገርና ህዝብ ገድሎ ሞተ፡፡ ለአክራሪና አሸባሪዎች የተመቸ ገነት ፈጠረ፡፡

የእኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የዓረቡ አለም አብዮት በኢትዮጵያ ይደገማል ብለው ነበር፡፡ ሥርዓት አልበኝነት የአገር ኢኮኖሚ ውድቀት ትርምስ ቀውስ የከፋ ብሔራዊ አደጋ መበታተን የእርስ በርስ ጦርነትን የሚመኝ የሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ አገራችን አማን ውላ አማን ትደር፡፡ ችግሮችን ህዝቡ በሠላም ተነጋግሮ ይፈታል እንጂ እንደ አበዱት ዐረቦች አገሩን አያጠፋም፡፡ ስደት የህጻናት የአረጋውያን የእናቶች የወጣቶች ሞትንና እንደ ቅጠል መርገፍን ማየትም መስማትም አይፈቅድም፡፡

የዐረቡ አለም አብዮት በአክራሪዎችና በአሸባሪዎች የተመራ እስላማዊ ንቅናቄ ነበር፡፡ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የሆነ ቀውስና ውድመት አስከትሎ አለፈ፡፡ ዛሬም ድረስ ሕዝቡ በተረጋጋና ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ኑሮውን መምራት አልቻለም፡፡

አብዛኛዎቹ የመንግሥትና የግል ኢኮኖሚ ተቋማት ተሸመድምደዋል፡፡ ወድመዋል፡፡ እንደገና መልሶ ለመሥራት በቢሊዮኖች የገንዘብ አቅምን ይጠይቃል፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ የየአገራቱ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኛ የሆነው የቱሪዝም ገቢያቸውም ወድቋል፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮች አገራቱ በነበራቸው ሠላምና መረጋጋት የተነሳ ለኢንቨስትመንት ያዋሉትን ሀብት ወደ ሌላ አገር አሻግረውታል፡፡ አዲስ ኢንቨስትመንት ለማዋል አይታሰብም፡፡ መረጋጋት በሌለበት አገር ሀብቱን የሚያፈስ ባለሀብት የለም፡፡

የሊቢያውም የሶሪያውም የየመኑም የግብጹም ህዝብ በዐረቡ አብዮት የጠበቁት እንዳልጠበቁት ሆኖ ሠላም ጠፍቶ ህዝብ አልቆ ኢኮኖሚያቸው ወድሞ አሸባሪነትና አክራሪነት ነግሶ ያለቀው አልቆ የተሰደደው ተሰዶ ቤታቸው ሀብታቸው ወድሞ ልጆቻቸውን አጥተው ግማሹም አካለ ጎዶሎ ሆኖ ቀሪ እድሜያቸውን በሰቆቃ እያነቡ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

አደጋውን መከላከልና አገራቸውን መጠበቅ ሲገባቸው አብረው ከአጥፊዎች ጋር እያጫፈሩ አገራቸውን አወደሟት፡፡ የሕዝብ ማዕበል ቀንና ሌሊት ያናወጣቸው የዐረቡ አለም አገራት እንደተጠበቁት ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አላገኙም፡፡ ያመጡት አዲስ ነገር ነፍሰ በላውን አይሲስና ሌቫንትን ያጎለበቱት አልቃይዳን ነው – የወደድሽው ቂጣ ሰተት ብሎ ወጣ እንዲሉ፡፡

ዛሬ ማጣፊያው ቢያጥር ቢያነቡ የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም ሆነና መፍትሄ የለም፡፡ አገራቱ ወዳልተጠበቀ የጥፋት ጎዳና አምርተዋል፡፡ ካሉበትም የባሰ ሊፈጠር ሊመጣም ይችላል፡፡

አንድ ሕዝብ አምባገነንነትን፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን መድሏዊና ኢፍትሃዊ አሠራርን ቀይሮ የተሻለ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለመብቱ መቆሙ መታገሉ ተገቢ ነው፡፡ የነበረው ሁሉ ጠፍቶ ሠላሙንም አጥቶ አገሩም ወድማ ማየት ባይፈልግም ለማየት ግን በግድ ተገደደ፡፡

ከስሜታዊነትና ከጥላቻ ያልወጣ ስክነትና ማስተዋል የጎደለው በጭፍን ድንብሩ በፖለቲካ እብደትና ቅዠታዊ ጡዘት የተሞላ ለምን እንደተነሳና ወደየትስ መሄድ እንዳለበት መመልከት የተሳነው የጎዳና አብዮት ሁከት ግርግርና ጩኸት ትርምስ ትርፉ የአገር ጥፋትና ውድመት የዜጎች እልቂትና ቀውስ ብቻ ሆኖ ተቋጨ፡፡

መንግሥት ወርዶ በምትኩ ሌላ መንግሥት በሰለጠነ ዴሞክራሲዊ የህዝብ ምርጫና ድምጽ በሠላማዊ መተካካትና ቅብብል የሚከወንበት ሕጋዊ ሥርዓት በአግባቡ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚነሱና በአብዮት ስም የሚካሄዱ የጎዳና ነውጦችና ግርግሮች ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚና ሠላማዊ ለውጥን አያመጡም፡፡ እልቂት፣ ውድመትና የአገርን መፍረስና መበታተን ብቻ ነው የሚወልዱት፡፡

ዛሬም ግብጽ፣ የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ አልተረጋጉም፡፡ በቀውስ እየተናጡ እየራዱ ይገኛሉ፡፡ አብዮት ማለት የከፋ ውድቀት የአገር ውድመት ከሆነ ምነው ባልጀመርነው ኖሮ የሚሉ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገራት ዐረቦች አሉ፡፡ ሁሉም ነገር ቀደም ቀረ እንደሚባለው ሆነ፡፡ አገር ከወደመና ከጠፋ ህዝብም በሞትና በስደት ካለቀ በኋላ መፀፀቱ ለውጥ አያመጣም፡፡ በግርግር፣ በነውጥ፣ በሁከትና በትርምስ መነሻነት ከፈረሱ አገራት ዓለም ብዙ ተምሯል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰቅጣጭ ድርጊት በሌላ አገር እንዲደገም እንዲታይ በእኛም እንዲከሰት ማንም ዜጋ አይፈቅድም፡፡ በሠላም ሥር ሁሉንም ችግር መፍታት አገርንም ከጥፋትና ውድመት ማትረፍ ይቻላል፡፡