አገርህን ጠብቅ!!

 ይነበብ ይግለጡ

በዓለም ታሪክ ውስጥ የገዛ አገራቸውን በገዛ እጃቸው ያፈረሱ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም – ሶሪያ ሊቢያና የመን፡፡ ስክነትና ማስተዋል ጠፍቶ እልህ ንዴት ስሜታዊነት ጥላቻ በአደባባይ ነግሶ ተው የሚል መካሪና አስተዋይ በሌለበት ከኋላቸውም ባለው የውጭ ኃይሎች ግፊት እየተነዱ አገራቸውንና ህዝባቸውን ታላቅ አደጋ ውሰጥ ከተቱ፡፡ አገራቸውን መጠበቅ ከጥፋትም ማዳን አልቻሉም፡፡

የተቃውሞ ሰልፉን ነጋ ጠባ ከማቀጣጠልና ቁጣቸውን ከመግለጽ ውጪ ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ በአገራቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሳያገናዝቡ በአደባባይ እየጮሁ፣ እየጨፈሩ፣ እያቃጠሉ፣ እያነደዱ፣ እያወደሙ በዓይናቸው በብረቱ እያዩ የገዛ አገራቸውን ወደመቃብር አወረዱ፡፡ አገራቸውን መጠበቅ ሲገባቸው አፈራረሷት፡፡

በእነዚህ አገራት ውስጥ የህዝብ ብሶት ችግር በደል በመንግሥት መመረርና መከፋት የዴሞክራሲ እጦት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወዘተ…ሞልተው የተረፉ ነበሩ፡፡ ተቃዋሚዎች ይህን ለመፍታት የሄዱበት የተሳሳተ መንገድ ታላቅ አገራዊና ትውልዳዊ ዋጋ አስከፈላቸው፡፡ አገራቸውንም ሠላማቸውንም አጡ፡፡

አገርን ሠላምና ደህንነቷን መጠበቅ ከቅርብና ሩቅ ጠላቶቿ መከላከል የዜጎች ሁሉ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ መተኪያ የሌላትን አገርህን ጠብቅ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የራሷ ዜጎች ልጆቿ ሊጠብቋት ሲገባ በእልህ በጥላቻ ተናንቀው አፈረሷት፡፡ የአገር ሠላም ማጣትና መፍረስ አደጋ ያስከተለባቸውን መጠነ ሰፊ ችግር እነሱም ዓለምም አዩት፡፡ ዛሬ ለሶሪያውያን፣ ለሊቢያውያን፣ ለየመኖች ስደት ሞት መከራ ችግር ዕጣ ፈንታቸው ሆነ፡፡

ቀድሞ ነበር ተቃዋሚውም ህዝቡም ከስሜትና ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቀው የጋራ ስለሆነችው አገራቸው በስክነት ማሰብና መጨነቅ የነበረባቸው፡፡ ተው አይሆንም በእርጋታ እናስብ አደጋው ሰፊ ነው ማለት ይገባቸው ነበር፡፡ ዛሬ ቢያነቡ ቢፀፀቱ የነበረውን መመለስ ከቶውንም አልተቻላቸውም፡፡ በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ምጣድ ጥዶ ማልቀስ እንዳለው የአገሬ ሰው፡፡

በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በየመን ወዘተ…ጭፍንና ግትር ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በዋና አጋፋሪነት ተሰይመው ህዝቡን ዴሞክራሲና ለውጥ እናመጣለን በሚል ቀስቅሰው አደባባይ አክርመው  የመሩበት የተሳሳተ አቅጣጫ ለአገራቱ ውድቀት መፍረስ መበታተን ዋና ምክንያት ሆነ፡፡ ዘግናኝ ሰቆቃ የህዝብ እልቂት የአገር ሀብትና ኢኮኖሚ የመሠረተ ልማት የታሪካዊ ቅርስ ውድመት ነግሶ ታየበት፡፡ ዓለምም ብዙ ተማረች፡፡

ይህ ዓይነቱ አገር አፍራሽ ድርጊት ከጀርባው ተልዕኮ ባላቸው የውጭ ኃይሎች አደራጅነትና አቀናባሪነት የሚመራ ፖለቲካ እንደ መልካም ተሞክሮ ተወስዶ በኢትዮጵያ እንዲደገም የሚሹ ካሉ እንደማይሆን መቼም እንደማይሳካ ደግመው ደጋግመው እንዲያውቁት ማድረግ የሁሉም አገሬን እወዳለሁ ወገኔን አፈቅራለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ ግዴታ መሆን አለበት፤ ነውም፡፡

ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በጠላት የተከበበች አገር ነች፡፡ ውድቀቷን መጥፋቷን የሚመኙት ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ድሮም፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የነበሩትን የሚሉትን ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በደርግም ዛሬም የሚረዱት የሚያደራጁት ወታደራዊ ሥልጠና የሚሰጡት የሚያስታጥቁት ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚከፍቱት የኢትዮጵያን ሠላምና መረጋጋት ልማትንና ዕድገትቷን ማየት የማይፈልጉት እንደ አገርም መኖሯን ሳይሆን መፍረሷን አጥብቀው የሚመኙት ታሪካዊ ጠላቶቿ ናቸው፡፡

ተቃዋሚ ለሚሏቸው የተለያዩ ኃይሎች በተለያየ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በቀጥታ ሥርጭት ወይንም በራድዮ የአየር ሞገድ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ሥራ በመሥራትና በማሰራጨት በህዝቡ ውስጥ የሥነ ልቦና ጫና ውዥንብርና የሀሳብ መከፋፈል እንዲፈጠር ሲሰሩ የኖሩትና ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ የህዝብ አመጽ እንዲቀሰቀስ ያለማቋረጥ የሚሰሩት ግብጽና አንዳንድ የዐረብ አገራት ናቸው፡፡

የግብጽ ጉዳይ ከአባይ ውኃና ግድብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ብዙ ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ የአባይን ወንዝ ውኃ ከምንጩ ለመቆጣጠር አስባ ወታደራዊ አማራጭ ተጠቅማ ሠራዊት ወደኢትዮጵያ አዝምታ በጀግኖቹ አባቶቻችን ታላቅ ተጋድሎ ተሸንፋ በውርደት ተመልሳለች፡፡ ዛሬም ከዲፕሎማሲው ጨዋታ ጀርባ በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ተግታ እየሰራች ትገኛለች፡፡

ሣዑዲ ዐረቢያ፣ ኩዌትና ኳታር ደግሞ የዘመኑን አክራሪ እስላማዊ እምነት ዋኸቢዝምን በሰፊው ወደ ኢትዮጵያ ለማስረጽና ለማስገባት በስፋት ለበርካታ ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ፡፡ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል ሰፊ መሠረት ለመጣላቸውም ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ፡፡

ዊኪሊክስ የአሜሪካን ኤምባሲ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን በኬብል ያስተላለፈውን ሪፖርት አግኝቶ እንዳጋለጠው ኢትዮጵያን የዋኸቢ አክራሪ እስላማዊ አደጋ እንደሚያሰጋት ከዓመታት በፊት በመረጃ አስደግፎ ገልጾታል፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው አደጋ አይሲስ ዓለም አቀፉ አሸባሪ ኃይል አዲስ ባወጣው የይዞታ ካርታ ውስጥ ሱዳንን፣ የመንን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በነዚህ አገራት በሸሪአ የሚመራ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት የያዘው ዕቅድና ይፋ ያደረገው ካርታ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሆናል አይሆንም ክፍተት ያገኛሉ አያገኙም ሁኔታውን የሚወስነው የኢትዮጵያ አገራዊ አቅምና ጥንካሬ መጎልበት ብቻ ነው፡፡ ደካማ በብጥብጥ ትርምስና ሁከት የምትናጥ፣ ሠላምና መረጋጋት የሌላት አገር ከሆነች ህዝቡ መከፋፈል ውስጥ ከገባ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ለነአይሲስም ሆነ ለነአልቃይዳ ትልቅ ፌሽታና ፈንጠዝያ ነው የሚሆነው፡፡

ይህን ክፍተትና ዕድል ካገኙ በቀላሉ በአገር ውስጥ መሠረታቸውን በማስፋፋት በጦር መሣሪያ የታገዘ ጦርነትና እልቂት ሊከፍቱ ይችላሉ፡፡ አስጊም ይሆናል፡፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ይህ እንዳይፈጠር ሥጋት አለው፡፡ እስካሁን አደጋውን በርቀት መመከትና መቆጣጠር የተቻለው ኢትዮጵያ የተረጋጋችና ሠላም ያላት አገር ስለሆነች ነው፡፡

የአገራችን ሠላምና መረጋጋት ዙሪያ ገባዋን ከከበባትና አመቺ ጊዜ ብቻ ከሚጠብቀው የጠላት ኃይል አንጻር ሲታይ በህዝቡ ውስጥ ያሉትን ሥር የሰደዱ የመንግሥታዊ አስተዳደርና አመራር ችግሮች ፈጥኖ በመፍታት ለውጭ ኃይሎች ቀዳዳ እንዳይኖር አድርጎ በመድፈን በብዙ አሳማኝ ተጨባጭ ምክንያቶች ሠላምና መረጋጋቷ ፀንቶና  ጎልብቶ መቀጠል አለበት፡፡

በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የኢትዮጵያን መዳከምና መውደቅ መፈረካከስ የሚመኙ አክራሪና ጽንፈኛ እስላማዊ ኃይሎች እንዳሉ በሚገባ ይታወቃል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የኤርትራ መንግሥት ከዋኸቢ እስላማዊ አክራሪ መንግሥታት ጋር ውል በመፈራረም በየመን ላይ ለከፈቱት ጦርነት የአሰብ ወደብን የጦር ኃይላቸውና የጦር መርከቦቻቸው እንዲሁም ተዋጊ የጦር ጄቶቻቸው ማረፊያና መነሻ አድርጎ ሲሰጣቸው ከዚሁ ቦታ እየተነሱ ነው የመንን እየደበደቡ እያፈራረሷት ያሉት፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፤ በረዥም ጊዜ ሂደት አክራሪውን ጦረኛ የዋኸቢ እስላማዊ ኃይል አሰብ  ቀድሞ የኢትዮጵያ መሬት በነበረው ቦታ እንዲሰፍር ሲደረግ ዋነኛ ኢላማዋም ኢትዮጵያ መሆንዋን ለአፍታ መጠራጠር አይገባም፡፡

የዋኸቢን አክራሪ እስላማዊ እምነት በስፋትና በቅርበት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስገባት፣ ለማሰራጨት፣ ለማስፋፋት፣ በሂደትም በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ መሠረት በመጣል በኢትዮጵያ በሸሪአ ህግ የሚመራና የሚተዳደር መንግሥት እንመሰርታለን የሚለው የረዥም ጊዜ ዓላማና ግባቸው መሆኑም ይታወቃል፡፡

ለዚህም መንደርደሪና መወንጨፊያ ያደረጉት የኤርትራን መሬትና የኤርትራን መንግሥት ነው፡፡ አደጋው ግዙፍ መሆኑ ቢታወቅም በጊዜ ሂደት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መመርመሩ ወሣኝ ነው፡፡ ይህን በመሰለ አስጊና አደገኛ ቀጠና ውስጥ የምትገኝ አገር ናት – ኢትዮጵያ፡፡

ዙሪያ ገባዋን የአገሪቱን መጥፋትና መዳከም በሚሹ ኃይሎች ተከባ ያለች አገር ብትሆንም በእስካሁኑ ሁኔታ በጥንካሬ መክታ ቆይታለች፡፡ ወደፊትም በበለጠ ብርታት ትመክታለች፡፡ በሌላው በኩል ያደረጉት ሙከራ አልሳካ ሲላቸው አሁን ደግሞ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን የመልካም አስተዳደር የፍትህ ሙስና የኪራይ ሰብሳቢነት ህዝቡን ያስመረረና ሥር የሰደደ መንግሥትም አምኖ የተቀበለውንና ለመፍታት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝበትን ችግር መነሻ ምክንያት በማድረግ ይህን ክፍተትና ቀዳዳ በመጠቀም አገሪቱን ቀውስና ትርምስ ውስጥ ለመክተት በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

በወኪሎቻቸው አማካይነት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የታየው የህዝብ አመጽ ቀጣይነት ኖሮት ጭርሱንም ከቁጥጥር ውጪ እንዲወጣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን አጠቃላይ አገራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ሠላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ይህን ቀዳዳና ወርቃማ አጋጣሚ መጠቀም አለብን በሚል በመራወጥ ላይ ናቸው፡፡

ለዚህም የግብጽ መንግሥት መሀመድ ሙርሲ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከደጋፊዎቹና ከታዋቂ ምሁራን ጋር በቀጥታ የቴሌቪዥን ውይይት በተላለፈ ሥርጭት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስቆም መወሰድ ባለባቸው የተለያዩ አማራጭ እርምጃዎች ላይ ሲወያዩ ከወታደራዊ አማራጮች ይልቅ ለተለያዩ የኢትዮጵያ  ተቃዋሚ ኃይሎች ከፍተኛ የግብጽ መንግሥትን በጀት በመመደብ በኤርትራና በግብጽ ደህንነት በኩል አገር ውስጥ ቀውስ ለመፍጠር መወሰናቸው ይታወቃል፡፡

የዚህ ዓላማና ዕቅድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር የእርስ በርስ የጎሳና የብሄር ግጭቶች እንዲፈጠሩ፣ ኢኮኖሚው እንዲሽመደመድ፣ የተጀመሩ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች የታላቁን ህዳሴ ግድብ በዋነኛነት እንዲቋረጡ አገሪቱ የማትወጣው ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ሲሆን ሥራውን ከጀመሩት ሰነባብተዋል፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ፡፡

ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሰው አክራሪ እስላማዊ ኃይል ኦብነግ፣ ኦነግ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ነጻ አውጪ፣ የአፋር ንቅናቄና ግንቦት ሰባት እነዚህ ሁሉ የሚረዱት ኢትዮጵያን ለመበታተን ተግተው በሚሰሩት የኤርትራና የግብጽ መንግሥታት ነው፡፡

ሰሞኑን በአገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠረው የህዝብ ተቃውሞ በመነሳት የኤርትራና የግብጽ መገናኛ ብዙኃን በተለይ በሶሻል ሚዲያዎቻቸው ጭምር የሰጡት ተከታታይ ሽፋን ያላቸውን ዕቅድና ፍላጎት በግልጽ ያሳየና የመሰከረ ነበር፡፡

በአገር ውስጥ የተፈጠረው ከመልካም አስተዳደር ከፍትህ እጦት ከሙሰኛነትና ኪራይ ሰብሳቢነት በሥልጣን አለአግባብ በመጠቀም የህዝብና የመንግሥትን ሀብት በመዝረፍ የከበሩ በመሬት ወረራና ቅርምት ላይ የተሰማሩ ሹሞችና አጋሮቻቸው በህዝቡ ላይ በፈጠሩት ምሬትና መከፋት ህዝቡ ተቃውሞውን ወደአደባባይ በመውጣት ማሰማቱንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ሁኔታው ወደከፋ ደረጃ እንዲያድግ ቀውስ እንዲነግስ በወኪሎቻቸው አማካይነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

እዚህ ላይ በህዝቡ በመንግሥት በእውነተኛ አገር ወዳድ ዜጎችም ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ከሁሉም ቅድሚያ ተሰጥቶት የውስጡን ችግር ማለትም የህዝቡን ጥያቄ ፈጥኖ ለመፍታት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ወሣኝ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

ከህዝቡ ጋር ፊት ለፊት መወያየት ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት መንግሥት ህዝብ ያልፈቀደውንና ያላመነበትን ማንኛውንም ነገር ከማድረግ መቆጠብ የህዝብ ይሁንታ የሌለውን ተቀባይነት ያላገኘውን ነገር በኃይል በመጠቀም አስፈጽማለሁ ከሚል እንቅስቃሴ መታቀብ ለህዝቡ ምሬት ዋነኛ ምክንያት የሆኑትን መሠረታዊ  ችግሮች  ለይቶ መፍታት የህዝቡን ቅሬታ በማስወገድ የተረጋጋ ሠላምን ለማስፈን የሚያስችል ሲሆን የሁሉም  ዜጋ የጋራ ርብርብም መታከል መቻል አለበት፡፡

በተከፈተው ቀደዳ በህዝብ ቁስልና የመከፋት ስሜት በመጠቀም አጠቃላይ አገሪቱን የቀውስ አዙሪት ውስጥ ለመክተት የሚጣደፉትን የውጭ ኃይሎች በዚህ መልኩ ጥረታቸውን በማምከን የአገሪቱን ሠላማዊ ጉዞና ደህንነት የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች የማሳካቱን  ተግባር ሳያሰልስ ማስቀጠል ይቻላል፡፡

አገሪቱ እንድትበታተንና እንድትፈርስ ለሊት ከቀን የሚሰሩትን የውጭ እኩይ ኃይሎች ከንቱ ምኞት ለማክሸፍ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ስለአገራቸው ሠላምና ደህንነት ሲሉ በጎ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መድረክ ማመቻቸትም ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ህዝብን መስማት ማዳመጥ ከህዝብም ጋር ሆኖ ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ ማበጀት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የአገሪቷ ዋነኛ ባለቤት ወሣኙ ኃይል ህዝብ ነውና፡፡

ህዝቡ መንግሥት ያቀረብኩትን ጥያቄ በህጉ መሠረት ይመልስልኝ ነው ጥያቄው፡፡ እንቅስቃሴውም የራሱ የህዝቡ እንጂ በፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም ፓርቲዎች አልተመራም፡፡ እንዲያውም እጃችሁን አንሱ፡፡ በሌላችሁበት ያላችሁ በማስመሰል ለፕሮፓጋንዳችሁ መጠቀሚያ አታድርጉን የሚል መልዕክትም አስተላልፏል፡፡ ህዝቡ ከፖለቲካ ድርጅቶችም ቀድሞ መራመዱን ያሳየበት ሁኔታም ነው የተፈጠረው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት የምትፈርስ የምትበታተን አገር አይደለችም፤ አትፈርስምም!!