አገርን መታደግ!!

 

                               ይነበብ ይግለጡ

ኢትዮጵያ ጥንትም ታሪካዊና ትልቅ አገር የነበረች ነች፡፡ ዛሬም የቱንም ያህል የውስጥ ችግር ቢኖር በመወያየት በሠላም ሊፈታ የሚችል ሆኖ እያለ ወደ አገር ጥፋትና ውድመት እንዲያመራ ለውጭ ኃይሎችም መፈንጪያ በር እንዲከፈት ዜጎቿ በዝምታ ሊያዩ ሊፈቅዱም አይችሉም፡፡

በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በኩል ችግሮች አሉ? አዎን ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ራሱ አምኖ የተቀበላቸውም ሆኑ ካመነባቸው በላይ የሆኑ መጠነ ሰፊ ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን በመፍታት ወደ ውጤት መድረስ የሚቻለው ተቻችሎ ተከባብሮ ተደማምጦ የጋራ ስለሆነችው አገር በማሰብ በመወያየት እንጂ አገርን ሊያፈርስ የሚችል ውልና አቅጣጫ በሌለው ትርምስና ተቃውሞ አይደለም፡፡

እርስ በርስ በመጠፋፋት አገር አይገነባም፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ዳርቻው ጥፋትና ውድመት  ነው፡፡ ከዚህ የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ አገር ደግሞ ከጥፋቱም በኋላ ቢሆን በሌላ ትውልድ ትቀጥላለች፡፡ ጥያቄው አገርም ህዝብም አላስፈላጊ መስዋዕትነት መክፈል የለባቸውም ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢና ሠላማዊ መልስ መስጠት መንግሥታዊ ግዴታው መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት ይሄዳል መንግሥት ይመጣል፡፡ ህዝብና ትውልድ ደግሞ እንደ ጅረት ይቀጥላል፡፡ ፍሰቱ አይቋረጥም፡፡ አገሪቷ የትልልቆችና የአዛውንቶች አገር ነበረች፡፡ ምክራቸው ጥፋትን የሚመልሱ ፍቅርንና መከባበርን የሚያስተምሩ እጅግ ብዙ አባቶች እናቶች የነበሩባት ያሉባትም አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይህንንም ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

ህዝብን ከህዝብ የሚያቃርኑ የሚያጋጩ አስተያየቶችና አባባሎች የመንግሥት ወገን ነኝ ከሚሉም ሆነ ከተቃዋሚው ጎራ ካሉት ጽንፈኞች ሊሰማም ሊደመጥም አይገባም፡፡ ነውርም ነው፡፡ ግለሰቦች ሊያጠፉ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡

በብሄር ስም ሊነግዱ ጥላቻ እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ይኼ ክስተት በዓለም ዙሪያ የታየ ነው፡፡ ሆኖም ተደርጎም ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት የክፉ ቀን ጥንስሶች በመላው ዓለም በየቦታው ሞልተው ተርፈዋል፡፡ የሉም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ ህዝብን ግን አይወክሉም፡፡

ህዝብ ደግሞ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ ፈጣሪ እናት ነች፡፡ ሁሉም ተፀንሶ የተወለደው ያደገው የተገኘው የበቀለው እዚህችው ጥቁር አፈሯ ላይ ነው፡፡ ልጆቿ እንዲተላለቁ አትሻም፡፡ አትፈቅድምም፡፡ ከዚህ የውጭ ጠላቶቿ ከደገሱላት የጥፋት አዙሪት አገሪቷን የእርስ በርስ የጦርነት አውድማ ለማድረግ ከሚያቅራራው ሻዕቢያና ከጌታው ግብጽ መሰሪ ደባና ተንኮል ኢትዮጵያን ልጆቿ ይታደጓታል፡፡

ሰሞኑን ሞቶ ለመቀበር ትንሽ የቀረው ሻዕቢያ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያዎቹ ጮቤ እየረገጠ ይገኛል፡፡ ይሳለቃል፡፡ ይንጫጫል፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ሁኔታ ሠላም መደፍረሱ በእጅጉ አስፈንድቆታል፡፡ ያላወቀው እውነት ግን አለ፡፡ ይህ ሁኔታ የተከሰተው በውስጥ ችግር፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፍትህ እጦት፣ በሙስናና ምዝበራ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በሀብት ክፍፍልና በይዞታ ጥያቄ እንጂ ይህን ያመጣው ግንቦት ሰባትና ሻዕቢያ አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡

ችግሩ የቱንም ያህል ቢሆን መንግሥትና ህዝብ መክረውና ዘክረው በጋራ ህዝባዊ መድረክ ይፈቱታል፡፡ እልባትም ያገኛል፡፡ ህዝቡ ያቀረበው ጥያቄ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ህዝብ በመንግሥታዊ አስተዳደሩ ሳይረካ ሲቀር ኢፍትሃዊነት አለ ብሎ ሲያምን ከሚያነሳው ጥያቄ የተለየ አይደለም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ህዝብና መንግሥት አብረው በጋራ በመሥራት እልባት ይሰጡታል እንጂ ሻዕቢያ የሚፈነጭባት ወይም በሻዕቢያ የሚረዳ ተላላኪ ኢትዮጵያው ውስጥ መቼም ሆነ መቼ እግሩን አይተክልም፡፡

ህዝቡም ደጋግሞ ገልጾታል፡፡ ጥያቄያችን በህጉና በአግባቡ መሠረት መልስ ይሰጠን ጥያቄውም ሆነ ተቃውሞው የእኛ እንጂ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አይደለም ነው ያለው፡፡ በሻዕቢያ የሚረዳ የሚታገዝ የትኛውም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ፓርቲ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድም ምንም ተቀባይነትም እምነትም የለውም፡፡ አያገኝምም፡፡

ህዝቡ ሻዕቢያን ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ዛሬ ጮቤ እየረገጠ ያለው ሻዕቢያ ኢትዮጵያን አፈራርሳታለሁ ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ይህ ደግሞ እንደማይሆን ህዝብና መንግሥት ደጋግመው ያረጋግጣሉ፡፡ አንድነታቸውንም አጽንተው ይቆማሉ፡፡ መንግሥት በሻዕቢያ ላይ የተመጠነ እርምጃ እያለ የሚለውን ውጤት ዛሬ ላይ እያየው ያለ ይመስላል፡፡ አንዱም መሠረታዊ ድክመቱም ይኸው ነው፡፡ ፈጥኖ ለችግሮች ሁሉ እልባት አለመስጠት፡፡

በውጤቶች መኩራራት ዘወትር ደግሞ ደጋግሞ የተሰሩትን ሥራዎች አግዝፎ ማሳየት ለትናንት እውቅና ያለመስጠት ችግር አገርንም ህዝብንም ይጎዳል፡፡ አገር በትውልድ ፈረቃ በየዘመኑ በነበሩ ሰዎች ደረጃ በደረጃ እየተገነባች የመጣች ወደፊትም በትውልድ ፈረቃ የምትገነባ የምታድግ የቀደመው ሲያልፍ ተተኪው ክፍተቱን እየሞላ የሚሄድባት እንጂ ሁሉን እኛው ሰርተን ጨረስን የሚባልበት አይደለም፡፡

ይኼን የሰለጠነ አተያይ የሚከተል እውነቱን የሚቀበል ባህልን ባለማዳበራችን ሁልጊዜም ትናንትን በመኮነን ሥራ ተጠምደን ትላልቅ ሥራ የሚከወንባቸው ጊዜዎች ያልፋሉ፡፡ ስለራሳችን ብቻ መናገር ስለምንወድ ለተተኪውም ትውልድ ስልጡን ባህል ስላላወርስነው ሌላው ባለተራ ሲመጣ ደግሞ ዛሬ የተሰራውን አፈራርሶ ጠረጴዛና ወንበሩን ሳይቀር ቀይሮ  ወይም ሰባብሮ ለአገር የሚበጀውን ሁሉ እየጣለና እያወደመ እያፈራረሰ አዲስ ጉዞ ነው ብሎ የሚያስበውን ይጀምራል፡፡

በሌላው ዓለም እንዲህ አይደረግም፡፡ በዚህ ረገድ የሰለጠኑት የዓለም አገራት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የነበረውን ጠብቀው አዲስ የመጨመር የማሳደግ ሥራን ይከውናሉ እንጂ በታሪክነት የሚዘከረውን የትናንት ሥራ እንዳልነበረ አድርገው አያፈርሱም፡፡ አንድም የትናንት ታሪክ ነው፤ ሌላም የቱሪስት መስህብና የገቢ ማስገኛ ነው፡፡

ተተኪ ሆኖ የሚመጣውም ትውልድ ትናንት የተማረው ያየው የወረሰው ይህንኑ መንገድ ስለሆነ  እሱም እንደ አዲስ አገሪቷን ወለድኳት ፈጠርኳት ለማለት የማይሄድበት መንገድ የለም፡፡ ይህቺ አገር እንዲህ ታሳዝናለች፡፡ ልብንም ትነካለች፡፡ ለሁሉም በመንግሥታዊ አመራር ላይ ላሉትም ለጽንፈኛ ተቃዋሚውም ሰክኖ ማሰብን ይላበሱ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የጋራ አገር ናትና፡፡

በተቃዋሚውም ሆነ በመንግሥት በኩል ከግትርነት ከእኛ በላይ ለአገር አዋቂና መድኃኒት የለም እኛና እኛ ብቻ ነን ሁሌም ትክክል ከሚል ዘመን የሻረው እሳቤ ሌላው አያውቅም አይነቃብንም ከሚል የጅል አስተሳሰብና እብሪት በመውጣት ስለአገር ሠላም ስለህዝብ ፍቅርና አንድነት በልዩነትም ውስጥም በጋራ ተከባብሮ ስለመኖር በጥንቃቄ ማሰብ ይገባል፡፡

በትልቅ አገራዊ መንበር የተቀመጡ ግለሰቦች የመረጣቸውን ህዝብ ፍላጎት ጠብቀው ለመሥራት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ትልቅ ብሄራዊ ራዕይ ሊኖራቸውም ይገባል፡፡ ወደመንደርና ጎጥ አስተሳሰብ ከወረዱ ሌላውን በእኩልነት ዓይን ማየትና መሥራት ካልቻሉ ችግሩ ሥር ይሰዳል፡፡ እልባትም ያጣል ማለት ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንን ለውድቀት ያበቃት ብዙ አገራትን ያመሳቀለው በስተመጨረሻው መሪ ነን የሚሉትንም አፈራርሶ አፈር ያስገባቸው ይኸው የዚሁ የጎጥ አስተሳሰብ ክፉ ደዌ ካንሰር በሽታ ሥር የመስደዱ ውጤት ነው፡፡

ጊዜ የፈቀደላቸውን አጋጣሚና መንግሥታዊ ሥልጣን በመጠቀም ከሚገባቸው በላይ ያግበሰበሱ የዘረፉ ግለሰቦችን ኢህአዴግ መንጥሮ ሊያስወግዳቸው ለህዝብ ፍርድ በማቅረብ በዘረፋ የተገኘውንም ሀብትና ንብረት ማስመለስ ካልቻለ አሁንም ሥርዓቱ ታላቅ አደጋ ውስጥ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡

ታላቁ መሪ መለስ እንዳሉት ህዝብ ካመፀ ህዝብ ከተነሳ የትኛውም ሠራዊት አይመክተውም፡፡ መልዕክቱ ህዝብን አክብሩ ነው፡፡ ከመንግሥትና ህዝብ  ተሰርቆ የተከበረበት በስግብግብነት ያግበሰበሱት ሀብት ወንበር ሥልጣን ቅንጦት ድሎትና ምቾት ሁሉ በነበረ ታሪክ የሚቀር ነው የሚሆነው፡፡

እኛ ብቻችንን ከምንጠፋ አገርና ህዝብ ይዘን መጥፋት አለብን የሚሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞችም እነሱ እንጂ አገርና ህዝብ እንደማይጠፋ የተረዱት አይመስልም፡፡ አገርና ሀዝብ እንደገና ዳዴ ብለው አቧራ አራግፈው እንደሚነሱ በብዙ አገራት ታሪክ ታይቷል፡፡

ትውልድም ዘመንም ይቀጥላል፡፡ ክፉዎቹም በመጥፎ ምግባራቸው ሲነሱ ይኖራሉ፡፡ ይህንንም ማስተዋል የተገባ ነው፡፡ ከእብሪትና ምን ይመጣብኛል ከሚል መታበይ መቆጠብ ለራስም ለአገርም ለትውልድም ይበጃል፡፡

በሁሉም ጎራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰክኖ በእርጋታና በአስተውሎት ማሰብ የሚገባን ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ፡፡ ሁኔታዎች ከእጅ ካመለጡ ከወጡ አንመልሳቸውም፡፡ መንግሥትም ካለህዝብ መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡ መካር የሌለው ንጉስ እንደሚሉት እንዳይሆን ኢህአዴግም ባዶ ተስፋ ከመስጠት ወደ ተግባራዊ ሥር ነቀል ለውጥ ፈጥኖ መግባት ለህዝቡም ማሳየት አለበት፡፡

ልማት ህዝብን ባለበት ማልማት እንጂ ከኖረበት ቀዬ አፈናቅሎ ቦታውን ለሀብታም በመሸጥ ህዝብን በማፈናቀል ያለመጠለያ ሜዳ ላይ በመተው ማህበራዊ ትስስሩን ማፈራረስ የህዝባዊነት መገለጫ መቼም አይሆንም የሚለውም የከረረ የህዝብ ተቃውሞ በመንግሥት በኩል ሊደመጥ ተቀባይነትም ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ህዝብ ነው የአገሩም የመሬቱም ባለቤት። የሚለውና የሚናገረው ሊሰማም ሊከበርም ይገባዋል፡፡

አገሪቷ የመላው ህዝቧ እንጂ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች ወይም ፓርቲዎች የግል ንብረት አይደለችም፡፡ ልትሆንም አትችልም፡፡ የተከሰተውን ችግር ከጣራ በላይ እያወጣው ያለውም ይኸው መሆኑን ነው ህዝቡ የሚናገረው፡፡ በሠላማዊ መንገድ የተለዩና የሚታወቁ ችግሮችን በመፍታት ለህዝቡ ጥያቄ መልስ መስጠት ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም፡፡

የተለያዩ አስተሳሰቦችን አመለካከቶችን ብዝሀነትን የሚያቅፍ የሚያከብር ዴሞክራሲ እንዲያድግ ነው መሰራት ያለበት። ህዝብ ተቆጣ ተቀየመ ማለት ያለአንዳች ክርክር ፈጣሪ ተቆጣ ማለት ነው፡፡ ህዘብ ከተቀየመ ከተቆጣ ካመፀ መንግሥት ማንን ነው የሚመራው የሚያስተዳድረው ብለንም መጠየቅ ይገባናል፡፡ የችግሩ ግዝፈት የትየለሌ ነው፡፡

ማጣፊያው እንዳያጥር ተማምኖ በጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ ግድ ነው፡፡ ሸፋፍነን እንለፈው ቢባልም አይሆንም፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ዓይነት ነው የሚሆነው፡፡ ከህዝብ የተደበቀ ሊደበቅ የሚችልም ምንም ነገር የለም፡፡

የዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ ምንነት፣ የህዝብ ወሣኝነት፣ የመንግሥት አገልጋይነት መሠረታዊ ትርጉሙ እየተዛባ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ ለማረምና ለማስተካከል ግልጽነቱ ካለ ይቻላል፡፡ በመሪው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚው በኩል በእልህ በግትርነት በኃይል የሚኬድበት መንገድ ሁሉ መጨረሻው ለአገርም ለህዝብም ውድቀትን ነው የሚያመጣው፡፡ ከዚህ መታቀብ ይገባል፡፡

ሁሉም ወገን ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በጽሞና ሊያየው ይገባል፡፡ የአገር ሠላምና መረጋጋት የአገር ልማትና ዕድገት የሚገኘው አንድም አገርና ህዝብ ሲኖሩ ሌላም የተረጋጋና ዋስትና ያለው ሠላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ የለም፡፡ አገርን ከጥፋትና ትርምስ ከውጭ ኃይሎች የጥፋት ሴራ አገርን መታደግ የመንግሥትም የህዝብም የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡