ሰክኖ ማሰብ…!!

 

                                                           ይነበብ ይግለጡ

                                                                      ኢትዮጵያ ጥንታዊ የመንግሥትነት ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ እንደ ቀደምትነቷና  ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትነትዋ ቀድማ ማደግ አልቻለችም፡፡ ለዚህም ዐቢይ ምክንያቱ በውስጥ የነበረው የእርስ በእርስ ትርምስና ግጭት እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ጫናም የራሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የሀገሪቷን ዕድገት ቁልቁል እንደካሮት ሰቅዞ ይዞ የጦርነት አውድማ ሆናም ኖራለች፡፡ ዳግም የተመሰቃቀለ ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ሰክኖ ማሰብ ከመሪዎችም ከዜጎችም ይጠበቃል፡፡

ከፖለቲካዊ አመለካከት መግረር በእልህ በከፋ ጥላቻና በስሜታዊነት የሚኬድበት መንገድ መቼም ቢሆን ለሀገርም ለህዝብም አይጠቅምም፡፡ ከውድመትና ከእልቂት በስተቀር የሚያስገኘው ወጤት የለም፡፡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ አበው በማነህ ማነህ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅና ፉክክር ሀገሪቱን ለውጭ ኃይሎች በሯን ከፍቶ አሳልፎ መስጠትም ሊከተል ይችላል፡፡ አሁን ላይ እየታየ ያለው ምስቅልቅልና ትርምስ የሚነግረን ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡

አክራሪ ዲያስፖራው 14 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ ለችግሩ መፍትሄ ሳይሆን እያሰበ ያለው ወትሮም በቋፍ ነበርና ይህን የትርምስ አጋጣሚ ልጠቀምበት ባይ ሆኖ አሰፍስፏል፡፡ የማይለው ነገር የለውም፡፡ በሀገር ቤት ላለው ሁኔታ ዋናው መነሻ የመልካም አስተዳደር እጦት የፍትህ ሥርዓቱ መዛባት የገነነው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ህዝቡን አስመርሮ ማስከፋቱ ሲሆን ኢህአዴግ ይህንን ፈጥኖ ለመንቀል አለመቻሉ ያስከተለው ችግር ነው በህዝቡ ተቃውሞ ውስጥ ያለው፡፡

የትኛውንም ዓይነት የህዝብ ጥያቄ በተረጋጋና በሠላማዊ መንገድ በሠላምና በውይይት በመተማመንም ጭምር ፈጥኖ ያለመፍታት ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ነው አሁን ያለውን ሁኔታ የወለደው፡፡ ኢህአዴግ አደረጃጀቱንም መመርመር መፈተሽ ግድ ይለዋል፡፡ ከዘመኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ሊራመድና አብሮ ሊጓዝ የሚችል የሰለጠነ ፖለቲካን ማየትም ይገባዋል፡፡

የሄደበት መንገድ ከልማት ስኬቶቹ ውጪ ያሉት ችግሮች እንዳሉት ህዝብ ሲነግረው ደምጹን አጉልቶ ሲያሰማ ማዳመጥና መፍትሄ መሻትም አለበት፡፡ የማይለወጥ የማይሻሻል ምንም ነገር የለምና፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቴን ሞቴ ያድርገው በሚል ግትር መስመርም መዝለቅ አይቻለውም፡፡ በተፈጥሮ በዲያሌክትክሱ ህግ መሠረት ሁሉም ነገር በለውጥ ሂደትና ህግጋት ብቻ ነው የሚመራው፡፡ ይህንንም ማጤን ይገባዋል፡፡ ተቸክሎ የሚኖር ካለበት የማይንቀሳቀስ ለውጥ የማያመጣ በለውጥ ሂደት ውስጥ የማያልፍ ምንም አንድም ነገር የለም፡፡

ህዝብ አልቀበልም የሚለውን በግዴታ መጫን የግድ ተግባራዊ ማድረግ ከህዝብ ጋር እስከወዲያኛው ያለያያል፡፡ ተቀባይነትም ያሳጣል፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ስለዴሞክራሲ መንግሥት ሊናገር የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም የሚሉት ሞጋቾች በህዝብ የተመረጠ መንግሥት የህዝብን ችግር ሰምቶና ተቀብሎ መፍትሄ ይሰጣል እንጂ በመረጠው ህዝብ ላይ ኃይል አይጠቀምም የሚል የሰላ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡

ይህ የሚያሳየው በኢህአዴግ ውስጥ በሀሳብ ፍጭትና ክርክር ያምን የነበረው ክፍል ከውስጡ ተመናምኖ የጠፋበት በበሳል ፖለቲከኞች ድርቅ የተመታበት ደረጃ ላይ መድረሱን ነው በሚልም የሚገልጹት አሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ያሳስባል፡፡ ያስጨንቃልም፡፡

አሁን እየታየ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩም ብዙዎች ናቸው፡፡ የህዝብ ጥያቄዎችን በወቅቱ በሠላማዊ መንገድ ለመመለስ አለመቻል የሚያስከትለውን ውጤት በገሀድ እያየነው ነው፡፡ ለዚህ ተወቃሹ መንግሥት እንጂ ሌላ አካል ሊሆን አይችልም፡፡ አሁንም ስህተቱን ለማረም ይችል ይሆን የሚለውም ጥያቄ ራሱን ችሎ ጥያቄ ውስጥ ነው ያለው፡፡

መከራከሪያቸው ሙስናው የመልካም አስተዳደር የፍትህ ችግሩ ሌላውም ሌላውም ሲፈጠርና እግር አውጥቶ ሲራመድ የነበረው በኃላፊነትም ላይ ሆኖ ለውጥና መፍትሄ ሊያመጣ ያልቻለው አመራር ነው አሁንም በኃላፊነት ወንበር ቁልፍ ቦታዎችን ይዞ ያለው፡፡ እያስጠበቀ ያለው የራሱን ወንበር እንጂ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት አይደለም የሚሉት ወገኖች እልፍ ናቸው፡፡

እነዚህ ክፍሎች ኢህአዴግ በሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ተጠልፎ መሥራትና መንቀሳቀስ ለውጥ ማምጣትም አልቻለም፡፡ ደጋግሞ ቢናገርም ወደተግባር ለመግባት አልተሳካለትም፡፡ በዚህ መልኩ የህዝቡን እምነት ማሸነፍ አልቻለም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡

ይህ የህዝብ ጥያቄያችን አልተመለሰም ተቃውሞው በፖለቲካ ድርጅቶች አልተመራም፡፡ ዲያስፖራ ሆነው አለን የሚሉትም ጽንፈኞች አጋጣሚውን እንጠቀምበት ከሚለው መወራጨት ሊታቀቡ ይገባል፡፡ የሀገሪቷ ሠላምና መረጋጋት መደፍረስ እነሱን ሳይሆን የሚጎዳው በአገር ውስጥ ያለውን ዜጋ ነው። እነሱ ምን አለባቸው? ምን ይሆናሉ? ምን ችግር ይገጥማቸዋል? ቢባል መልሱ ምንም ነው፡፡

ይልቁንም ለአገራችንና ለህዝባችን የተሻለ እናስባለን የሚሉ ከሆነ በመጀመሪያ ራሳቸውን ይፈትሹ፡፡ አዎ! የወገናቸው ቁስል ቁስላቸው፤ ደስታው ደስታቸው፤ ሞቱም ሞታቸው ነው፡፡ በዚህ እንስማማለን፡፡ ግን ደግሞ የተሻለ ሀሳብ ማፍለቅ ችግሮች ተባብሰው መስመራቸውን ስተው ምላሽ አጥተው አገርን እስከማጥፋት ከመረማመዳቸው በፊት ሰክኖ ማሰብ ቤንዚን ከማርከፍከፍና ክብሪት ከመለከስ ከጥላቻ ፖለቲካ ተቆጥቦ አስተዋይነት በተመላበት መንገድ ችግሮች ሁሉ አገርንና ህዝብን ሳይጎዱ ጥፋትም ሳያስከትሉ በሠላም፣ በውይይትና በአብሮነት እንዲፈቱ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

 

ሶሪያን እንደ አገር ቀድሞ የሚያውቃትና ያየ በአገር አንድነትና አብሮነት ላይ ሊያላግጥ አይችልም፡፡ አሁን ያለው ተተኪው አዲስ ትውልድ በፈተናና በመከራ ውስጥ ያለፈ አይደለም፡፡ ገና አፍላ በሆነ ትኩስ ስሜት ውስጥ ሆኖ የመጣው ይምጣ የወደመው ይውደም ባይ ነው፡፡ ይኼ የቀድሞዎቹን የአገሪቱን ታሪክና ያለፈችባቸውን ውጣ ውረዶች ካለማወቅ ካለመረዳትም የሚመነጭ ነው፡፡

 

ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም የሚለው የአባቶች ተረት የራሱ ምክንያት ያለው በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያ የአዛውንትና ትላልቅ አባቶቹና እናቶቹ አገር መሆኗን በየጊዜው በፖለቲከኞች የሚፈጠሩ ችግሮች አገርን ሳይበትን ህዝብን ሳይጎዳ እልቂትም ሳያስከትል በምክር በውይይት በቆየው የአገር ባህልና ወግ በቤተ እምነት ጭምር እየፈቱ አገራቸውን ጠብቀው ዛሬ ያለው ዘመን ላይ እንድንደርስ ማድረጋቸውን ደግሞ ደጋግሞ ሊያጤነው ግድ ይለዋል፡፡

 

የሰለጠነውና የተማረው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ደግሞ ከአባቶቹ የተሻለ አድርጎ አገሩን ሠላሙን የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ ትውልድና ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድም ከወንድሙ መጋጨትና ወደ ደም መፋሰስ ማምራት የለበትም፡፡ ጥንት የነበረው ፍቅርና ወንድማማችነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ህዝብ የማይቀበላቸውን የማያምንባቸውን ነገሮች ሁሉ ማስተካከል ማረም ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ ለሁሉም ሠሰላም ይበጃል፡፡

 

በገዥው ፓርቲ በኩል አሉ የተባሉትን ችግሮች ሁሉ አምኖ የተቀበለውንም ሆነ ያልተቀበለውን በሰፊ ህዝባዊ ውይይት በሠላማዊ ምክክር ግትርነትና እኔ ብቻ ነኝ ለዚህች አገር መድህንና አዋቂ ከሚለው ኋላ ቀር አስተሳሰብ ተወጥቶ ሁሉም በአገሩ ጉዳይ ያገባዋል ይመለከተዋል ባለጉዳይ ባለቤትም ነው በሚለው መሠረታዊ እምነት መፍታትና ስለጋራ አገር ማሰቡ መጨነቁ ተገቢ ነው፡፡

 

አንዱ ለአገር አሳቢ ሌላው ጠላት ተደርጎ የሚወሰድበት እሳቤ ተነቅሎ ሁሉም በባለቤትነት መንገድ ለአገር ሠላምና ደህንነት በሚበጀው ላይ አተኩሮ ቢሰራ ያንዣበበውን አደጋና ችግር በቁርጠኝነት መፍታት ይቻላል፡፡ አገርንና ህዝብንም መታደግ ይቻላል፡፡

 

መንግሥትም ሆነ ጽንፈኛው አክራሪ ፖለቲከኛ ግትር ከሆነ የትንቅንቅ ፖለቲካዊ አመለካከት አቋም በመላቀቅ ዘመናዊና ለመቀራረብ በሚያበቃ በጋራ ለአሀገር መሥራትና መቆም አገርንም ከጥፋትና አደጋ ለመታደግ የሚያስችል መንገድን መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጎሣና ዘር የጥላቻ ፖለቲካ ማራመድ መቼውንም ቢሆን ለአገር አብሮነትና ቀጣይነት አደጋ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በውጭ ያሉ አክራሪ ፖለቲከኞች የጽንፈኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ የማይበጅ አፍራሽ መሆኑን በመረዳት ስለአገርና ስለህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በስክነት ሊያስቡበት የሚገባው ጊዜ አሁን መሆኑን ደግመው ደጋግመው ሊያዩት ይገባቸዋል፡፡

አንዳንዶችም ጽንፈኞች በውጭ አገራት የራሳቸውን ምቾትና ደህንነት ጠብቀው ቤተሰብና ዘር ማንዘራቸውን አግዘው አውጥተው እየሰሩ እየኖሩ በድሎትም እየተቀማጠሉ በአገር ቤት የድኸውን ልጅ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳቸውን በፌስ ቡክና በሶሻል ሚዲያው ጎጠኛና የጥላቻ ፖለቲካና የዘር ቅስቀሳ እያደረጉ ህዝብ ከህዝብ እንዲናጭ፣ እንዲጋጭ፣ እንዲባላ፣ አጠቃላይ አገራዊ ቀውስና ትርምስ እንዲፈጠር የሚያደርገውን አካሄዳቸውን መልሰው መላልሰው ሊፈትሹት ግድ ይላል፡፡ መንግሥት ይመጣል፡፡ መንግሥት ይሄዳል፡፡ ህዝብና ህዝብ ግን አብሮነቱ ይቀጥላል እንጂ አይለያይም፡፡

ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ መሪዎች ሰዎች ናቸውና ሊሳሳቱ ከመንገድ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ሆኗል፡፡ ይሆናልም፡፡ ህዝብ ግን እንደ ህዝብ ሊወነጀል፣ ሊከሰስ፣ ሊሰደብና ሊነቀፍ አይገባውም፡፡ የፖለቲካ ሥርዓትም ሆነ ግለሰቦች ኖረው ያልፋሉ፡፡ ህዝብ ግን በየትውልዱ ፈረቃ እየተተካካ ይቀጥላል፡፡ አብሮነቱም እንደዚያው፡፡

ከተራ ስድብ ከአሉባልታ ዘመን ከማይሽረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ስብዕናን የማቆሸሽና የመግደል ካንሰር በሽታው ሊፈወስ ያልቻለው በእርስ በርስ መጠላለፍና መወነጃጀል መካካድ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መናናቅና ፉክክር ወንድም ወንድሙን እየጣለና አንዱ በሌላው ውድቀት እየተመፃደቀ እስከዛሬ የዘለቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃዋሚዎችም ትግል ዛሬም ወደተሻለ ምዕራፍና የላቀ እይታ አልተሸጋገረም፡፡ ከውድቀቱ አልተማረም፡፡ ስህተቱን ከግትር ፖለቲካው በመነሳት አምኖ ለመቀበልም አይፈቅድም፡፡ ዛሬም እዚያው የዛሬ 40 ዓመት የነበረበት ከበሮ ድለቃው ጥላቻው ስም ማጥፋቱ መወነጃጀሉ መናቆሩ ላይ ነው ያለው፡፡ እርግማን ይሆን? ይሆንም ያሰኛል፡፡

አብዛኛው የአገሪቷ ፖለቲካዊ ውድቀትም ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከእነሱው የተወረሰው ኋላ ቀር የመናቆር የመበላላት የስም ማጥፋት ለአገርና ለህዝብ ከእኛ በላይ አሳቢና ተቆርቋሪ የለም ሊኖርም አይችልም የሚለው ግለኛ እሳቤ ሌላውን የመኮነንና የመወንጀል አባዜ ያመጣው ያስከተለው ድምር ውጤት ነው ሀገሪቷን አዙሪት ውስጥ ደፍቋት የኖረው፡፡ ለብዙዎችም መጥፋትና መገለል ምክንያት የሆነውም ይኸው ዘመንና ትውልድ ሊሽረው  ያልቻለ በሽታ ነው፡፡

በስድብ፣ በአሉባልታ፣ በውቃው፣ ደብልቀው፣ አተረማምሰው ፖለቲካ አገርንና ህዝብን የሚያህል ታላቅ ጉዳይ እንደዘበት ማየት ከሰከኑ ግለሰቦችም ቡድን ነን ከሚሉትም መስማት አገራዊ ሠላማዊ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ውኃ ሲወስድ አሳስቆ እንዲሉ ሶሪያም ይህንኑ ዓይነት ጽንፈኛ አመለካከት በሚከተሉ ልጆቿ ነው የወደመችው፡፡ ልጆቿም ብቻ አይደሉም የዚያችን አገር መጥፋትና መውደም ያፋጠኑት፡፡ የአገሪቷን መፈረካከስ መበታተን የሚሹ የውጭ ኃይሎችም ሰፊ ሚናና ድርሻቸውን ተወጥተዋል።

የመጨረሻ…መጨረሻ ሁሉም የሶሪያ የአገርነት የክብር የሉዓላዊነት ጥንታዊ ታሪክ እንዳልነበረ ሆኖ በጥፋትና በውድመት ተደመደመ፡፡ ፍርስርሷ ወጣ፡፡ ዜጎቿ ሰክኖ ማሰብና አርቆ መመልከት በተሳናቸው ግትር ፖለቲከኞቿ የተነሳ አገርና ሠላም አጥተው ለቀው ተሰደዱ፡፡ ብዙ ሺህዎች ሞቱ፡፡ ረገፉ፡፡ ያቺ ትልቅ የነበረች አገር ዛሬ የዓለም አቀፉ እስላማዊ አክራሪ ኃይል መፈንጪያ ሆነች፡፡ የምዕራቡ ዓለም ዘመናዊ ወታደራዊ ጦር መሣሪያም መፈተሻ ለመሆን በቃች፡፡

የነበረውን የቀድሞዋን ሁኔታ በፍጹም መመለስ አልተቻለም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በራሷ ልጆች ሰክኖና ተደማምጦ ተወያይቶ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ችግር ሠላማዊ መፍትሄና እልባት ለማምጣት ለማበጀት ባለመቻላቸው ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በተቃዋሚው እንዲሁም በህዝቡ በኩል ሁሉም ሰክኖ ማሰብ ወደሠላማዊ መፍትሄ መምጣት አገርንም ህዝብንም ከጥፋትና ከውድቀት ለመታደግ ይበጃል፡፡ ደግሞና ደጋግሞ ሰክኖ ማሰብ ይጠበቃል፡፡

ሁሉንም ከማጣጣል ቢያንስ የተሰሩትን አገራዊ ግዙፍ የልማትና የዕድገት ሥራዎችን ከትናንቱ የተሻሉትን ለአገር የሚበጁ የበጁ ዕድገቶችንም ከጭፍን ጥላቻ ወጥቶ መቀበል በጎደለው ላይ ደግሞ አጥብቆ መከራከር መሞገት ተገቢነትም አግባብነትም አለው፡፡

በጠመንጃ የመጣ በጠመንጃ ይወርዳል ለሚለው የቆየ ፖለቲካዊ አባባል ይህቺ አገር ስንትና ስንት ዘመን በጦርነት ውስጥ የኖረች ከመሆኗ አንጻር ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ ከመግባት የሰለጠነ ትውልድና አገርን ለአደጋ አሳልፎ የማይሰጥ ሠላማዊ መንገድን መምረጡ የሚበጅ ነው የሚሆነው፡፡

አገር ከፈረሰ ውሉ ከተበጠሰ መልሶ አንድ ለማድረግ የሌላ አዲስ ትውልድ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ችግሮች በሠላምና በተረጋጋ ሁኔታ ሊፈቱ መልስ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ነው ማሰብ የሚገባው፡፡ አሁን በተያዘው አካሄድ ሁኔታው በእጅጉ ያሳስባል፡፡

ኃላፊነት የጎደላቸው ፖለቲከኞች ማስተዋል የተሳናቸው በእልህና በጥላቻ የተሞሉ ወገኖች በንግግርም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያው በሚቆሰቁሱት ተንኳሽ ሁኔታ ለግጭት ምክንያት በመሆን አገሪቷ ወደከፋ የሲቪል ጦርነት ውስጥ ገብታ አንድነቷ ፈርሶ ለሌሎች ውድቀቷን ለሚሹ መፈራረሷን ለሚመኙ ኃይሎች ሰፊ በር ከመክፈት ውጭ ለአገር ሠላምና መረጋጋት የሚያስገኙት ፋይዳ የለም፡፡

በጽንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግትርና ጭፍን አቋም የተነሳ ብዙ አገራት እንዳልነበሩ ሆነው ጠፍተዋል፡፡ ህዝባቸው በእርስ በርስ ጦርነት ተላልቋል፡፡ ኢኮኖሚያቸው ወድሟል፡፡ በአንድ ዘመን ኃያልና ዓለም አቀፍ እውቅናና ታሪካዊነት የነበራቸው ጥንታዊ ከተሞች ህንጻዎች ሁሉ በጦርነት ፈራርሰው ወደአቧራነት ተለውጠው ሙት ከተማ ሆነው ሰው የሚባል አይኖርባቸውም፡፡ ህዝቦቻቸው አገር ጥለው ተሰደዋል፡፡

ህጻናት ወጣቶች አሮጊት ሽማግሌዎች ሴቶች በሚዘገንን ሁኔታ አልቀዋል፡፡ ምግብ ውኃ፣ መብራት መጠለያ የለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሊያዩት ቀርቶ ሊሰሙት የሚዘገንን ነገር ማንም እውነተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአገሩ ምድር ላይ ተከስቶ ማየትም መስማትም አይፈቅድም፤ አይፈልግምም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚገባትም ይኼ አይደለም፡፡ ሰክኖ ማሰብ ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡