ከትርምሱ ጀርባ!!

አገራችን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ቀድሞ ከነበሩት ሁኔታዎች የተለየ ነው፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ማዕዘናት ያሉና የሚኖሩ እንዲሁም በውጭ ያሉ ዜጎች የተፈጠረውን ቀውስ በውል ተረድተው ችግሮቹ በሠላማዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ መፍትሄም እንዲያገኙ አገሪቱ የተረጋጋ ሠላሟን ጠብቃ ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ የሁሉም ወገን የቅድሚያ ተግባር ነው፡፡ ከትርምሱ ባሻገር ማሰብ ይገባል፡፡

በእርግጠኝነት በአንድ ወቅት ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ችግር ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ድርጅቱ በስብሷል፤ ተሀድሶና ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል ብለው እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ያጋጠመው ችግርና ፈተና ከቀድሞው በባሰ ደረጃ ላይ መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ በውስጡ ያለውን የከፋ ችግር ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ ሊወጣው ይችላል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ህዝባዊ ወገናዊነት ይዞ ከግል ጥቅምና ሀብት አሳዳጅነት ርቆ ለህዝባዊ አገልግሎት ብቻ ይሰራ የነበረው ኃይሉ በአንድም ሆነ በሌላም ምክንያት ተመናምኖ በአመራሩ ዙሪያ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሰው ያለህ የሰው እያሰኘም ነው፡፡ እውነቱ ይኼ ነው፡፡

የአመራር ብቃትና ልምድ ማነስ ችግር የፖለቲካ እውቀት አስተሳሰብ ጥልቀትና አስፍቶ የማየት ድህነት የዴሞክራሲንና የብዝሀነትን ትርጉም በራስ ልክና መጠን እየሰፉ በጠባቡ ማየትና ሰፊ አድማስ አለመኖር የበቁ ሰዎችን የማጣት ችግር ህዝብን ከማገልገል ይልቅ የግለኝነትና ስግብግብ የአግበስባሽነት መንፈስ በደርጅቱ ሰዎች ውስጥ መስፈንና መግነን  እያየን ያለውን ችግር ወለደ፡፡ በዚህ አሳሳቢ አገራዊ ጉዳይ ላይ ስለመፍትሄው መነጋገር እንጂ መሸፋፈኑ አደባባይ ገፍቶ የወጣውን እውነት አይቀይረውም፤ ለውጥም አያመጣም፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት መንሰራፋት የፍትህ ሥርዓቱ መጣስ የመሬት ቅርምትና መክበር ዘልቆ የሄደና ሥር የሰደደ ችግር ከመሆኑ የተነሳ በኅብረተሰቡ ውሰጥ የነገሰውን ምሬት ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሄ አቅጣጫ በመስጠት መጓዝ አለመቻሉ ነው ሌላ ችግር የወለደው፡፡ በመንግሥት በኩል የተወሰዱት ርምጃዎች ችግሩን ማስተንፈሻ እንጂ መሠረታዊ ለውጥ እንዳላመጡ ህዝቡ ይናገራል፡፡ ህዝባዊ አደራን ረግጠው ህዝብ በምርጫ የሰጣቸውን ድምጽ ከቁም ነገር ባለመቁጠር ለግል ሀብትና ክብረት ብልጽግና በመጣደፍ የነበራቸው ህዝባዊ የአገልጋይነት ስሜት ጠፍቶ ራሳቸውን ወደከበርቴው መደብነት ወደ ቡርዣነት የለወጡ ቡድኖች ግለሰቦች የፈጠሩት ቅጥ ያጣ የሥልጣን ብልግናና አማሣኝነት ነው በየቦታው ያለውን የህዝብ ቁጣ የቀሰቀሰው፡፡ ኢህአዴግ ፈጥኖ ማጥራት ያለበትም ቁልፉ ችግር ይኸው ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ሊፈጠር ሊመጣ እንደሚችል ራሱ ኢህአዴግ አስቀድሞ የገመገመውና የገመተው በመሆኑ አዲስ ነገር የለውም፡፡ ችግሩን ያገዘፈው ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት ያለመቻሉ ነው፡፡ ህዝብ የአገሩ ባለቤት ነው፡፡ የአገሩ መሪም አሳዳሪም ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ የሚለውን አለመስማት ተገቢ ምላሽም አለመስጠት የህዝብ ቁጣን ይቀሰቅሳል፡፡ ምርጫም ቢመጣ በካርዱ የሚመርጠው የሚጥለውም ህዝብ ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የመጨረሻው ወሣኝ ኃይል ህዝብና ህዝብ ብቻ ነው፡፡ የሚበጀው ችግሩን ወደራስ ወስዶ መፍትሄ መፈለግ ነው፤ መፍትሄውም ህዝቡ ነው፡፡

በኢህአዴግ 10ኛ ጉባዔ ላይ አንድ የቀድሞ ነባር ታጋይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የሙስናና ምዝበራ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን አንስተው የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ህዝቡ በምርጫ ወቅት የተሰሩትን አገራዊ የልማት ሥራዎች እያየ እስቲ እንያቸው በሚል ከአንዴም ሁለት ጊዜ እድሉን እየሰጠን ልክ የሚወድቀውን ተማሪ መምህሩ ደግፎ ወደቀጣዩ ክፍል እንደሚያሳልፈው ሁሉ እኛም በዚህ መልኩ ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አጥብቀን ልናስብበት ይገባል፡፡

ቀጥለውም ወደአንድ ጠንካራ ፓርቲነት እንለወጥ የሚል ስምምነት ላይ ደርሰን ኮሚቴም ተዋቅሮ ነበር፤ ጊዜ ወስዷል፡፡ ብናደርገው መልካም ነው፡፡ ህዝቡ ራሳችንን ለውጠን ችግሮቻችንን ፈትተን የበለጠ ለመሥራት ካልቻልን ከዚህ በኋላ ሊታገሰን አይችልም ብለው ነበር፡፡ ለግለሰቡ ሀሳብ የሌሎች ድርጅቶች አመራሮች ገና ጠባብነትና ትምክህት ያልተሻገርናቸው ችግሮች ስለሆኑ በአሁን ደረጃ ይኼን ማድረግ አንችልም ጊዜ ይጠይቃል የሚል መልስ ሰጡ፡፡

አንድ የምሥራቅ ጎጃም ተወካይም በጉባዔው ላይ ረዥም ንግግር በማድረግ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስበው ሲገልጽ እንዴት በትግል ውስጥ አብረን ብዙ ያሳለፍን ጓዶች ሆነን በመግባባት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ይሳነናል ካለ በኋላ ለታላቁ መሪ መለስ የውጭ ጋዜጠኛ ምንድነው የሚያሳስብዎት ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ይህቺ አገር የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ያጋጥማት ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ ማለታቸውን በመጥቀስ እሱም ይኼ እንደሚያስጨንቀው ለጉባዔተኛው ገልጾ ነበር፡፡ ይህ ውይይት በቴሌቪዥን ተቀርጾ  የተቀመጠ ነው፡፡

ጉባዔው ከሚካሄድበት ወቅት በፊትም ሆነ በኋላ የተወሰነ ወር ድረስ በአገር ደረጃ ምንም ኮሽታ የህዝብ ተቃውሞና አመጽ አልነበረም፡፡ ጉባዔው ኅብረተሰቡን ባስመረሩት የመልካም አስተዳደርና የፍትህ አሠራር ችግሮች፣ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሞት የሽረት ትግል በማድረግ የኅብረተሰቡን ብሶትና ምሬት የሚቀርፉ የሚመልሱ ርምጃዎችን እንደሚወስድ ወስኖ ነበር ከጉባዔው መልስ ወደሥራ የገባው፡፡

በአገራዊ ደረጃ ኮንፈረንሶችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ተዘጋጅተው ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልሎችም ከህዝቡ ጋር በቀጥታ በመወያየትና በመደማመጥ የችግሩንም ግዝፈት በመረዳት በተለያየ ደረጃ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ኢህአዴግ በዕቅዱ መሠረት ብዙ መራመድ ቢፈልግም የተወሰዱት ርምጃዎች ማስታገሻ ከመሆን ባለፈ የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ የሚመልሱ ሆነው አለመገኘታቸውን ህዝቡ ይገልጻል፡፡

ሕዝቡ ሥርዓቱን ተብትበው ከላይ እስከታች ጠፍንገው ያሰሩት በኔት ወርክና በቡድን ተደራጅተው የመንግሥትና የህዝብን ሀብት ሲዘርፉ የነበሩት ጭራሽ ተደላድለው ማን ይነካናል ብለው ተቀመጡ እንጂ አልተነኩም፡፡ በመንግሥታዊ ወንበርና ሥልጣን ተጠቅመው አሁንም ያሻቸውን እየሰሩ ነው የሚል ብሶት ያሰማል፤ መላሹ መንግሥት ነው መሆን ያለበት፡፡

ገበሬውን ከእርሻ መሬቱ በልማት ስም አፈናቅለው ወይም አታለው በትንሽ ብር ገዝተው ሜዳ ላይ ከነቤተሰቡ የበተኑት እነሱ ከብረው ሚሊዬነር የሆኑት አልተነኩም፡፡ ዘረፋው ብሶበታል፤ ማስተር ፕላኑ ይቁም የሚለው ተቃውሞ በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ  ቀሰቀሰ፡፡ መንግሥት ውሣኔው እንዲቆም አደረገ፡፡ ህዝብን ማዳመጡ ተገቢም ትክክልም ነበር፡፡

የህዝቡ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጫናዎችን ፈጠረ፡፡ በኦሮሚያም በአማራውም ክልል ከመንግሥት ወታደሮችም ከህዝቡም መካከል በርካታ የሰው ህይወት ጠፋ፡፡ ንብረት ወደመ፡፡ ይህ ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር አለመፈታቱ ያስከተለው ድምር ውጤት ነው፡፡ ለምንና እንዴት ይህ ሆነ ሊከሰትስ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ኢህአዴግ በውስጡ በተንሰራፋው የኪራይ ሰብሳቢና የመልካም አስተዳደር የፍትህ ጠንቅ በሆነው የተሰጠውን መንግሥታዊ ሥልጣንና ኃላፊነት ለግል ጥቅሙ በማዋል የደለበ ትከሻ በገነባው መንግሥታዊ መዋቅሩን እንዳሻው በሚፈነጭበት ኃይል ተተብትቦ በመያዙ ፈጥኖም ርምጃ ለመውሰድ ባለመቻሉ የመጣ አገራዊ ችግር መሆኑን ህዝቡ በአብዛኛው ይናገራል፡፡ ብዙዎችም ይስማሙበታል፡፡

ይህ ክስትት በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በበርካታ አገራትም ውስጥ ያጋጠመ ፈተናና ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና ከሥሩ ለመፍታት የገዥውን ፓርቲ ቁርጠኛ የፖለቲካ ውሣኔ የህዝቡንም እገዛና ትብብር ይጠይቃል፡፡ ካለህዝብ ድጋፍ መቆም በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው፡፡

ፓርቲውም ሆነ በመንግሥት ጉያ ውስጥ ተሸጉጠው ህዝብና መንግሥትን የመዘበሩትንስ ለህግ ለማቅረብ ከኃላፊነታቸው ለማንሳት የከበደው ለምንድነው? ኢህአዴግ ይህንን ማድረግ ካልቻለ ራሱን ካላጠራ ህዝብን ያስመረሩ በዘረፋ የከበሩ ግለሰቦችን ሰብስቦ ስለዴሞክራሲ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለፍትህ፣ ስለልማትና ዕድገት ቢያወራ አንሰማም የሚለው ተቃውሞ መልስ ሊሰጠው ግድ ይላል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ ያሳለፈውም ውሣኔ ይህንኑ የሚያፀና ነው፡፡

መብታችን ተጥሷል፤ ዜግነታችን ተደፍሯል፡፡ በአገራችን ሰርቶ የማፍራትም ሆነ የማግኘት መብታችን ተገፏል፡፡ መሬታችን ተዘርፏል፡፡ ከቤትና ከመኖሪያችን እንድንፈናቀል እየተደረገ ቦታው ለሀብታሞች ተቸብችቧል፡፡ ህዝቡ ባለበት ማልማት ዘመናዊ መኖሪያውን መሥራት ሲቻል በአገር ልማት ስም ድሀው ዜጋ የትም እየተጣለ በኃይል እንዲነሳ እየተገደደ መንግሥት የድሀውን ህዝብ መብት በጉልበት ደፍሯል የሚሉት የተቃውሞ ድምጾች አዲስ ስላልሆኑ አስቀድሞ መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባ ነበር፡፡

አገር አለን ህግ አለ ብለን እንዳንል ህጉ የሚሰራው ለሀብታሞችና ጊዜ ለሰጣቸው ሹሞች ወይንም እነሱን ለተጠጉት ብቻ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ ብንጮህም በየደረጃው ያሉ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ለችግራችን መፍትሄ አልሰጡም፡፡ የተፈፀመብን ግፍና በደል በዜጎች ላይ ይፈፀማል ተብሎ የሚገመት የሚታመንም አይደለም ለሚለው የህዝብ  የተቃውሞ ድምጽ የህዝብን መብት ማክበር ማስከበር ለጥያቄዎቹ  ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅ የነበረውና የሚጠበቀውም ከኢህአዴግ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ መሠረታዊ ለውጥ እስኪያመጣ ድረስ ተቃውሟችን ይቀጥላል የሚለው ተቃውሞውን የማቀጣጠሉ ድርጊት አገርን፣ ህዝብን፣ ኢኮኖሚውን በእጅጉ የሚጎዳና የሚገል በመሆኑ ዛሬ ላይ ጎልቶ በየቦታው የሚታየውንና የሚሰማውን አለመረጋጋት ሁከትና አመጽ የህዝቡን ወሣኝ ጥያቄዎችን በመፍታት ወደነበረበት ሠላማዊ ሁኔታዎች መመለስ ይቻላል፡፡

የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ እንዲወጣ መሠረታዊ ምክንያት የሆኑትን የመልካም አስተዳደር በደል የፍትህ እጦት ሙሰኛነትንና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲንሰራፋ በመንግሥት ወንበር ላይ ሆነው ሲያራምዱ የነበሩትን ግለሰቦች በህዝብ ፊት በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተገቢ ርምጃ ነው የሚሆነው፡፡ የአሁኑ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሣኔ ወደዚሁ የሚያመራ ነው የሚመስለው፡፡

ሕዝቡ ለመብቱ ለመልካም አስተዳደር ለፍትህ መከበር ያደረገውን ትግል በአክብሮት እንመለከታለን ሲል ሰሞኑን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከግምገማው በኋላ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡ ኢህአዴግ እንደ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ታላላቅ አገራዊ የልማትና የዕድገት ተጨባጭ ለውጦችን ያስመዘገበ ድርጅት በመሆኑ ላይ ማንም አይከራከርም፡፡ ከትርምሱ ጀርባ ያለውን ዐቢይ ችግር በሠላም ከህዝቡ ጋር ተወያይቶ መፍታት ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን አጣዳፊ ተግባር መሆን ይገባዋል፡፡