በፕሬስ ነፃነት ስም ህዝብን ማጋጨት አይቻልም!

ይህን ፅሑፍ ለማሰናዳት አነሳሽ ምክንያት የሆነኝ ሰሞኑን ፖሊስ የህዝቡን ሰላም በማወክ የግጭት መንስኤ ሆነዋል በማለት በአንዳንድ መፅሐፍ አዟሪዎች ላይ የወሰደውን ህጋዊ ርምጃ ተከትሎ፤ አንዳንድ ፅንፈኞች ጉዳዩን ከነፃ ፕሬስ ለማያያዝ መሞከራቸው ነው። እርግጥ የፖሊስ ርምጃ ከህግና ስርዓት አኳያ ጋር እንጂ ከፕሬሱ ነፃነት ጋር ሊያያዝ የሚችል አይደለም። ፅንፈኞቹ ግን ሁኔታውን ሆን ብለው በማጦዝ ጉዳዩን ከህገ መንግስት ጥሰትና ፕሬሱ ሊኖረው ከሚገባው ነፃነት ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል።

ዳሩ ግን መፅሐፍቶቹ የት እንደታተሙ የማይታወቁ፣ ከህትመቶቹ መንግስት ማግኘት የሚገባው የስራ ግብር ያልተከፈለባቸውና ደራሲዎቹም እዚህ ሀገር ውሰጥ የሌሉ እንዲሁም ዓላማቸው በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያያና በአማራ ክልሎች የተከሰቱትን ችግሮች ሆን ብሎ ለማባባስ የተዘጋጁ ናቸው። እናም ህግና ስርዓትን ከማስከበር አኳያ የሚመለከተው አካል ከእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ ተነስቶ ርምጃ መውሰዱ ተገቢ ይመስለኛል።

ከዴሞክራሲም አኳያ ቢሆን በመፅሐፍቶቹ አማካኝነት ሊተላለፉ የተፈለጉት ጉዳዩች  ዴሞክራሲን የሚያቀጭጩ በመሆናቸው ሊታረሙ የሚገባ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው በየትኛውም ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን ለመተግበር ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ክንዋኔውን የሚፈፅሙት በተናጠል ሳይሆን፤ በተለያዩ ደረጃ በጋራ በሚያከናውኑት ተግባር ነው። ይህ ይህ ይሆን ዘንድም ዜጎቹ ያሉባቸው ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ባህል ያላቸውን ግለሰቦች በተደራጀ አኳኋን ለማሰማራት የሚያስችሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች እንዲኖሩ መትጋታቸው አይቀሬ ነው። ታዲያ ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነው መፅሐፍ የሚገኝበት አንዱ የሚዲያ ዘርፍ ነው።

ሚዲያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። ሆኖም በማንኛውም ሀገር የሚገነባው ሚዲያ ከዚያ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንጂ፤ የምዕራቡን ዓለም አሰራር እንዳለ በመገልበጥ አይመስለኝም። የየሀገራቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አካሄድ የተለያየ ነውና። ሚዲያ በምዕራቡ ዓለም 4ኛው የመንግስት መዋቅርን ተመስሎ ተግባሩን ሊከውን ስለቻለ እዚህ ሀገር ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ መፈጠር አለበት ሊባል አይችልም። አፈጣጠራቸው፣ የክዋኔ አውዳቸውና የህብረተሰቡ ንቃተ-ህሊና ወሳኝ ጉዳዩች በመሆናቸው ሁሉንም የሚዲያ አሰራሮችን እንዳለ ገልብጦ ማምጣት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በአጭር አነጋገር ጉዳዩ አንድን ብሎን በማይገጥመው አቃፊው ውስጥ ደብድቦ በማስገባት ያህል ሊመሰል ይችላል። እናም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት አንድ የሚዲያ ውጤት ከሀገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲሁም ከህዝቡ እሴቶች አንፃር ሊመዘን መቻሉ የግድ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ያንን ሀገር እየመራ የሚገኘው መንግስት የስራ ድርሻ ነው።

መቼም አመፃንና ሁከትን የሚሰብኩ እንዲሁም እርስ በርሳቸው እንደ እፉኝት ተበላሉ እያሉ የሚሰብኩ የጥፋት ታምቡረኞችን አይቶ እንደላዩ ማለፍ ከአንድ ሃላፊነትና ሰብዓዊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅ አይመስለኝም። መንግስት ሁከትንን ሽብርን የሚነዙ አካላትን የህግ ተጠያቂ ማድረጉ ሥራውም፣ መብቱም፣ ግዴታውም መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህን በማድረጉም ሀገርንና ህዝብን ከጥፋት የመታደግ ተግባር በመሆኑ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ የሚገባው አይመስለኝም።

ነባራዊው ዓለምም ሆነ የሚዲያ ሙያ እንደሚነግረን ነፃ ኘሬስ ነፃ ውንብድና ማለት አይደለም። ግልፅ የከተማ ሽፍትነትም አይደለም። ነፃ ኘሬስ የግል ፍላጐታችን የበላይነት እንድንቀዳጅ ስንል ብቻ የሌለን ነገር በመፍጠርና ውሸትን በመደርደር፣ ከፍ ሲልም የሌሎችን መብትና ተቻችሎ የመኖር እሴቶችን ኢ-ስነ-ምግባራዊ በሆነ መንገድ በመናድ የምንነግድበት ሸቀጥም አይመስለኝም። እናም ሚዲያ እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ የዴሞክራሲ መብት የሚጎለብትበት የዜጎች በሰላም ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴት የሚደረጅበት እንዲሁም ህዝቡን በልማት ስራዎች ዙሪያ የማነሳሳትና ሀገራዊ ዕድገትን የማረጋገጥ ተልዕኮን ያነገበ መሆን ያለበት ይመስለኛል።

ከዚህ አኳያ ለልማት የሚተጋ የሚዲያ ሙያ በዴሞክራሲ ባልዳበሩ ህዝቦችና መንግስታት ዘንድ ቁልፍ የብልፅግና መሣሪያ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነቱ የሚዲያ አሰራር ህዝቦችን ለልማት ለማነሳሳትና የብልጽግና ከፍተኛው ማማ ላይ እንዲወጡ ያስችላል። በልማት ባልዳበሩና ድህነትን ሙሉ ለሙሉ ባልቀረፉ ሀገሮች ውስጥ የሚዲያው ሁከትና ሽብር ፈጠራ ከታከለበት ሀገራቱ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲቆዩ ማድረጉ አይቀርም።

በየዕለቱ ግጭትና ሁከት ካለ ስለ ልማት የሚያስብ ህዝብ ሊኖር አይችልም። ስለ ልማት የሚያስብ ህዝብ ከሌለ ደግሞ ሀገራዊ ዕድገት የሚባለው ነገር ከአባባልነት ሊያልፍ የሚችል አይመስለኝም። እናም ሚዲያው ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሰላምና ከእርሱ ሊገኝ ስለሚችለው ትሩፋት ማስተጋባት ይኖርበታል ባይ ነኝ። ይህን ዕውን የሚያደርግ ሚዲያ የህዝቦች አብሮነት የሚጠብቅበትን፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚዳብርበትን እንዲሁም የመተሳሰብና የጋራ ልዕልና የሚሰፍንበትን ቀመር በመስበክ ለሀገራዊ ዕድገቱ የበኩሉን ሚና ያበረክታል።

ይህ አሰራር ዛሬ በለፀጉ የምንላቸው ሀገራት ሳይቀሩ ያለፋበት ሃዲድ ነው። በጊዜ ዑደት ውስጥ የተራመዱበት መስመር ነው። በአንድ ሌሊት የተነገባ የዴሞክራሲ ስርዓትም ይሁን የኘሬስ ነፃነት አስተሳሰብ የትምና መቼም ኖሮ አያውቅም። በመሆኑም ችግሮች መኖራቸው የግድ ነው ባይባልም፤ በሥራ ሂደት እንከኖች ባጋጠሙ ቁጥር የተሰማሩበትን የፖለቲካ ነውጠኝነት ዕውን ለማድረግ በአስር ሺህ እጥፍ አባዝቶ ነገሮችን ለማወሳሰብና ህዝብና መንግስትን ለማምታታት የሚደረግ ተግባር አግባብነት ያለው አይመስለኝም።

ያም ሆነ ይህ በእኔ እምነት በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መካከል ፍፁም የማይፈታ ዝምድና በመኖሩ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያስታርቅና ሁለቱን እውነታዎች አግባብቶና አጣጥሞ የሚያራምድ የኘሬስ ፍልስፍና ማቋቋምና ምቹ አውድን መፍጠር ከማንኛውም ህዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት የሚጠበቅ ይመስለኛል።

ይህን ስል ግን ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ሲባል ኘሬስ መታፈን አለበት እያልኩ አይደለም። በሀገራችንም “ወንጀለኛ ጋዜጠኛ” እንጂ ነፃ ኘሬስ የታፈነ ባለመሆኑ ጉዳዩ ብዙ የሚያሟግት አይመስለኝም። ለነገሩ ሀገራችን ውስጥ በህግና ስርዓት የተጠየቀ እንጂ በፃፈው ፅሑፍ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም። ህግና ስርዓት ደግሞ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።

ህግና ስርዓትን የማስከበር ጉዳይ ከኘሬስ ነፃነት ጋር በየትኛውም መስፈርት የሚተሳሰር አይደለም። በአንፃሩም ህገ-ወጥ ዘገባዎችንና መፅሐፎችን የጥፋት ድርሣናትን አድርጎ በማቀጣጠል ዜጐችን ለማብላላት ጠዋት ማታ የሚወተረተሩ ግለሰቦች ተጠያቂ መሆናቸው እንደ ኘሬስ አፈና መቆጠር የለበትም—ጉዳዩ የህግ የበላይነትን ማስከበር ነውና።

እዚህ ላይ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሳለጥ የግድ ተደርጐ የሚጠቀሰው የአደባባይ ውይይትና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የሃሳብ ፍጭት ትክክለኛ አሰራር መሆኑን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል። ዜጐች በነፃነት ሲወያዩ፣ ሃሣብ ለሃሣብ ሲሟገቱ፣ ለልማት የሚበጁና ዴሞክራሲውን የሚያራምዱ የአስተሳሰብ ብልጭታዎች ሲፈልቁ፤ ዳብረው ለልማት ሊውሉ ይችላሉ።

ሆኖም ይህ ዓይነቱ ስናይ እሳቤ ስለተፈለገ ብቻ የሚመጣ የሰማይ መና አይደለም። ይልቁንም የበሰሉ ጋዜጠኞች በሌሉበትና ወደ የነፃ ኘሬሱ ባልገቡበት ሁኔታ አስተሳሰቡ የሚያመጣቸውን እውነቶች መናፍቅ ከቅዥትነት አያልፍም። እርግጥም አንዳንድ ጋዜጠኛ ተብዬዎች በነፃ ኘሬስ ስም የፖለቲካ ንግድን ለማጧጧፍ ሲራኮቱ በሚታይበት ሀገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ማለም አጋጣሚውን ለፅንፈኞች መፈንጫ መፍቀድ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የሚኖረው አይመስለኝም።

እናም በፕሬስ ነፃነት ስም ምንጫቸውና አከፋፋያቸው ማን እንደሆነ የማይታወቁ ብሎም ህዝብን ለማጋጨት የሚሰናዱ የህትመት ውጤቶችን ማገድ ተገቢነቱ አጠያያቂ የሚሆን አይመስለኝም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን የፕሬስ ውጤቶች ተግባራቸውን የሚያከናውኑት በህግ ማዕቀፍ እንጂ ህግን ተፃርረው ባለመሆኑ በመንግስት በኩል የህጉን አግባብ ተከትለው የሚወሰዱ ማናቸውም ርምጃዎች ከዚሁ አንፃር መታየት ያለባቸው ይመስለኛል።