የኢህአዴግ ምክር ቤት ግምገማ የት ያደርሳል?

በኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች ላይ የተነሱትን ሕዝባዊ አመፆችና ተቃውሞዎች አስመልክቶ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ  ኮሚቴና ምክር ቤት በተከታታይ ባደረጉት ግምገማ የተቃውሞዎቹ ዋነኛ መነሻ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ በዋናነትም የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል የፈጠረው ቁጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከስራ አስፈጻሚው በኋላ ግምገማ ያደረገው ምክር ቤት በተለይ በአማራ ክልል ለተነሳው ተቃውሞ እና ግጭት ‹‹በአማራ ክልል በሰሜን ጐንደርና በአጐራባች የትግራይ ወረዳ መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ በተነሳው ጉዳይ በሕወሓትና በብአዴን አመራሮች በኩል መፍትሔ ከመስጠት አኳያ የተከሰተው መዘግየት ተገቢ እንዳልሆነ በመገምገም፣ ሁለቱ ድርጅቶች ከዚህ ድክመት ተላቀው ፈጣንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ መፍትሔ እንዲሰጡ፤›› ሲል መፍትሄውን የተመለከተ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በማከልም ‹‹በትግራይ ክልል ከወልቃይት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲታይ፣ እነዚህና ለግጭት መንስዔ የሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮችም ከሕዝብ ጋር በመመካከርና በመግባባት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት በተከበረበት አኳኋን እንዲፈታ መደረግ አለበት፤›› ሲል በውሳኔው ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ ለመላ አገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰላም ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሉም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ አሁንም አፍራሽ እና ለስርአት አልበኞች እድሉን የሚያሰፉ ትችቶች እየተሰጡ ነውና እንደሃገር ለመቀጠልና ስለሰላማዊ እንቅስቃሴያችን  የምክር ቤቱን ውሳኔ ከግምባሩ ፖለቲካዊ ዲሲፕሊን እና ከተጨባጩ ሃገራዊ እውነታ አኳያ ይህ ትርክት ፍተሻ ያደርጋል ።

የስርአቱ  ርእዮተ አለማዊ ሰነዶችን ጨምሮ በፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ላይ ሁሉ  በግልጽ እንደተቀመጠው ልማትንም ሆነ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሆኑ ተመልክቷል።

የጋራችን የሆነችው ይህች አገር ቀጣይነት የሚኖራት እነዚህን ሁለቱን የህልውናዋን መሠረቶች ጠብቃ መቆየት ስትችል ብቻ መሆኑን ዛሬ ሳይሆን አስቀድሞም ከላይ በተመለከተው አግባብ በግልጽ ያስቀመጠው ስርአት በአንፃሩ ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል እነዚህን የህልውና መሠረቶች እንዳይረጋገጡ ተግቶ እንደሚሰራና ይህም ሃይል  በህዝቦች ጥቅሞችና ፍላጎቶች ላይ  እየተረማመደ  ወደ ትርምስ ለማምራት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ በተፈጠሩት ላይ ደግሞ የማባባስን ስልት መከተል መሆኑን ባመለከተው ልክ ለሰሞንኛዎቹ ቀውሶችም በዋናነት ጎልቶ የወጣው ምክንያት ይኸው እንደሆነ ባደረገው ግምገማ ማረጋገጡና ማመኑ የመፍትሄው መጀመሪያ እና  ተስፋን የሚያለመልም  እንጂ ተስፋችንን በምንም መልክ የሚያጨልም አይሆንም ።

የመልካም አስተዳደር ጉደለት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ፈተና ሆኖ የተደቀነው አንድም መንግስታዊ አገልግሎትን ለሁሉም ወገን በፍትሃዊነት፣ በጥራትና በብቃት ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት የአቅም፣ የክሂሎትና የህዝባዊ ውግንና ጉድለቶች በፈፃሚው አካል ላይ ጎልቶ መንፀባረቁ መሆኑን ባደረገው ግምገማ ማረጋገጡና ይህንንም ይፋ አድርጎ ከላይ የተመለከቱ ጥሪዎችን ማቅረቡ የህዝባዊነቱና የዴሞክራሲያዊነቱ መገለጫ እንጂ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰለባዎች እንደሚያራግቡት አይደለም።

ሌላው እና ምክር ቤቱ በግምገማው አረጋግጦ የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠበትና ተስፋ ሰጪው ጉዳይ ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችሉ በተሃድሶ መስመሩ አማካይነት የተነደፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርሞች፣ አሠራሮችና አደረጃጀቶችን በቁርጠኝነትና በብቃት መፈፀም የሚችል የአመራር ሃይል በበቂ አለመፈጠሩን የተመለከተው አጀንዳ ነው ።

መልካም አስተዳደርን ማስፈን የመስመሩን ቀጣይነት ከማረጋገጥ ባለፈ በዜጎች ውስጥ የባይተዋርነት መንፈስ እንዳይፈጠር፣ ዜጎች በአገራቸው እጣ ፋንታ ላይ የመወሰን አቅማቸው እንዳይነጠቅ እና በማያቋርጥ የእድገት ጉዞ ውስጥ እየተመመች ያለች አገር ግስጋሴ እንዳይስተጓጎል ግድ የሚል መሆኑንም ከሁከቶቹ በስተጀርባ የተማረበት ሃቅ መሆኑንም አምኖ መቀበሉ የመፍትሄውን ግማሽ መንገድ ስለመጓዙ የሚያረጋግጥ እንጂ በምንም መልክ ተስፋ የሚያሳጣ አይሆንም።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር ቁርጠኝነት መጓደል፣ ከህዝባዊ ውግንና መንሸራተትና ከህዝብ ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም ባህል እየሆነ መምጣቱን፤ በተወሰነው የአመራር ክፍል በኩል የሚታየው ዳተኝነት፣ ከችግሮቹ ተቆራርጦ አለመገኘትና በአድርባይነት አዙሪት ውስጥ መዳከርም አምኖ መቀበል ስለመፍትሄው ወሳኙን ምእራፍ እንደመሻገር ነው። ከኔ ጥቅም በፊት የህዝባችን ጥቅሞችና መብቶች መቅደም  አለበት ብሎ ለዚህ መታገልና ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንደሚገባና ለዚህ ዝግጁ የሆነ አመራር ከታች እስከ ላይ የግምባሩ አባል ያልሆኑትን ጭምር ለማካተት መወሰንም  ላየናቸው ቀውሶች ምክንያት የሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ብሎ መውሰድ እንደሚቻል የሚያመላክት እንጂ የሚያፈዝ አይሆንም።

ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የተፈጠረው የአመራር አቅም ትልቅና ሃገሪቱን እና ህዝቧን ገና ብዙ ርቀት ሊወስድ የሚችል  መሆኑንም መዘንጋት አይገባም። የአመራሩ ስብጥር ደግሞ  ሁለቱንም ትውልዶች ያስተሳሰረና ከፖለቲካዊ አቋም በላይም ተሻግሮ ብቃትን መሰረት ካደረገ ቅብብሎሹ  በአግባቡ እንዲመራ የሚያስችል በመሆኑ የህዳሴው ጉዞ በታቀደለት ልክና መጠን መጓዙ የማይቀር ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለና ምክር ቤቱም እንዳሰመረበት የውግና ጉዳይ  ቀጠሮ የሚሰጠው አለመሆኑ ላይ ከመግባባት መደረሱ ሌላኛው ተስፋችንን የሚያለመልም ነጥብ ነው።

ከህዝብ ያልወገነ አመራር የተሃድሶን መስመር ታምር ፈጣሪነት እየሰበከ፣ የህዝብ መሬት የሚዘርፍ፣ አርሶ-አደሩን በልማት ስም ከመሬቱ  እያፈናቀለ ከኪራይ ሰብሳቢው ሃይል ጋር የሚዘምር፣ ልማታዊ ባለሃብቱን እየደቆሰ ጥገኛውን የሚያጀግን፣ ኪራይ ሰብሳቢውን ሃይል የሚታገል አመራርንም ሆነ ፈፃሚ ሃይል እንዲሁም የህበረተሰብ ክፍል ነጥሎ እየመታ ትግሉን የሚያቀዘቅዝ እና ሰልፉን ከጥገኛው ሃይል ጋር አስማምቶ ስርአቱን ከውስጥ የሚንድ ሃይል ያበቃለት መሆኑም ላይ አቋም መያዙ ሊጠቀስ የሚገባው እና የአደፍራሾችን አሉባልታ የሚያከሽፍ  የግምገማው ትሩፋት ነው ።

እዚህ ሰልፍ ውስጥ የገባን አመራር ማጥራትና ማስወገድ፣ የተሃድሶ መስመሩ ማነቆ መሆኑንና ይህን ሊፈታ በሚችል መንገድ ተመጣጣኝ ርምጃ መውሰድ ግድ የሚል መሆኑም ላይ ምክር ቤቱ ያለአንዳች ልዩነት አቋም ይዞ መውጣቱ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመለክት እንጂ ከቶም መበስበስን የሚያጠይቅ አይደለም።

ምክር ቤቱ ስለዚህና ከላይ ስለተመለከቱት አቋሞቹ በሊቀመንበሩ በኩል ምክንያቱን ሲያጠይቅ እዚህም እዚያም ቅሬታዎች በበዙና መፍትሄዎች የሌሉ በመሰሉ ቁጥር ቅሬታ የሚይዘው ሃይል እየበዛ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ወደለየለት ሁከትና ብጥብጥ መሄዱ እንደማይቀር ከሰሞንኞቹ ሁከቶች በመማሩ መሆኑን የተመለከተው የመጀመሪያው ነው።

ሌላው ቀርቶ የተሃድሶ መስመሩ መሠረት የሆነው አርሶ-አደር በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንደታየው አመራሩና መዋቅሩ ሲያስከፋውና መፍትሄ ሲነፍገው በትግሉና በጥረቱ ያረጋገጣቸው መብቶቹና ጥቅሞቹ ላይ ከመዝመት አለመመለሱን መመልከቱም ስላሳለፋቸው ውሳኔዎች መጠቀስ የሚገባው ሁነኛ መነሻ ነው ።

ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል ከህዝባዊ ውግንናው የተነሸራተተው የአመራር ሃይልን አጥብቆ በመያዝ፣ እሱ ላይም ተከታታይ ስራ በመስራት፣ ከመስመሩ እየራቀ እንዲሄድና በመጨረሻም መስመሩን ለመግታት ከሚሰሩ ሃይሎች ጋር እንዲሰለፍ የማደረግ አቅጣጫ ማስያዙን፣ አልፎ አልፎ ከመልካም አስተዳደር ጋር በቀጥታም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ ግኑኝነት ያላቸው ጥያቄዎች  ሲነሱ ጥያቄዎችን የማራገብ ወይም ሆን ብሎ የማዳፈንና ሁከትና አመጽ ሆኖ እንዲወለድ የማድረግ ስራ ውስጥ እጁን ያስገባ አመራር እዚህም እዚያም መታየቱን አምኖ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው ለሚገኙ ዜጎች ጥሪ ማቅረቡ የህዝባዊነቱን ልክና ለመታረም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም፣ ቅን ዜጎች ሁሉ ከጎኑ ልንቆም ይገባል።