የሠላም ጎዳና ያተርፋል

ሰርቶ ለመለወጥ፣አምርቶ ለመነገድ፣ነግዶ ለማትረፍ፣ተምሮ  ለማወቅ፣አውቆ ለመመራመር፣ ልማትን ለማፋጠን፣ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ የነገን ራዕይ ዕውን ሆኖ ለማየት…ብቻ የታሰበውን ዕውና ለማድረግና ሌላውን ለማለም ቁልፍ መሳሪያ ነው -ሠላም፡፡ ሠላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡

እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ከሠላም ውጭ ህልውና የላትም፡፡ ለዚህም ነው ቅድሚያ ለሠላም የሚባለው፡፡  በርካቶች ለሠላም መስፈን ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ተንገላተዋል፣ታግለዋል፡፡ ለሠላም መስፈን ላበረከቱት አስተዋፅዖም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከሠላም አምባሳደርነት እስከ የሠላም ኖቤል ሽልማት የተቀዳጁ ጥቂቶች አይደለም፡፡

ዜጋ ሰርቶ የሚለወጠው ሠላም ሲኖር ነው፡፡ የአገር ዕድገትም ከሠላም ውጭ የትም አይደርስም፡፡ እናም የሠላም መዝሙር ሁሌም እንደተዘመረ ነው፡፡ ሰንደቁ ከፍ ብሎ ይውለበለባል፡፡ ሁሉም ለሠላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ ይቀርባል፤ መልዕክቱ ይተላለፋል፡፡  

መንግስታት ሠላምን ማስፈን፣ዲሞክራሲን መገንባት፣የዜጎችን መብት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሊተገብሯቸው ከሚገቡ ጉዳዮችም እነዚህ ተግባራት በቀዳሚነት ይቀመጣሉ፡፡ አገራት በሚያፀድቋቸው ህገ መንግስቶችም እነዚህ የልማትና የዕድገት ግስጋሴ መሰረቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡

ዜጎች እነዚህ መሰረታዊ ዕሴቶች ሲጓደሉ የሚያስተዳድራቸውን አካል ይጠይቃሉ፤ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄ የቀረበለት አካልም ጉዳዩን ፈትሾና ገምግሞ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፡፡ ይህ አካሄድ ተገቢም ጤናማም ነው፡፡ ጠያቂው መብቱን፣የሚያስተዳድረው አካል ደግሞ ግዴታውን የመወጣት አካሄድ ነው፡፡ ይህን መሰሉ ሂደት ትናንትም ዛሬም አለ፡፡ ነገም ይኖራል፡፡

ዜጎች ለምን ጥያቄ አቀረቡ አይባልም፡፡የማቅረብ መብት አላቸውና፡፡ መንግስትም ለምን ተጠየቅሁ አይልም፡፡ የዜጎችን ጥያቄ መቀበልና ምላሽ መስጠት ኃላፊነቱም ግዴታውም ነውና፡፡ ይህ ግንኙነት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትም ሚናው እጅጉን የጎላ ነው፡፡ መንግስት ክፍተቱን የሚነግረው ህብረተሰብ በመኖሩ ይደሰታል እንጂ አይከፋውም፤ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ህዝቡ የልማቱ ዋልታና ማገር ነውና ሁሉም ሥራ ከህዝብ ጋር ለህዝብ ነው የሚሰራው፡፡

ህዝቡም አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለለውጥ የመትጋት ግዴታ አለበት፡፡ በመንግስት የታቀዱት ተግባራት ዕውን የሚሆኑት በህዝቡ የላቀ ተሳትፎ ነው፡፡ ህዝቡ በእኔነት ስሜት ልማቱን ዕውን ለማድረግ መትጋት ይኖርበታል፡፡ በዚህ መልኩ የተሳሰረው ጉዞ ውጤቱ ያማረ፤ፍሬውም የጎመራ ነው፡፡ ስኬቱም ፈጣንና ዘላቂ ነው፡፡ የሚፈለገው ልማት በሚፈለገው የጥራት ደረጃና በተቀመጠለት ጊዜ ዕውን ይሆን ዘንድ ህዝብ ዋናው ሞተር ነው፡፡

ህዝብ ልማቱን በጉልበትና ገንዝብ ይደግፋል፡፡ ሥራዎች ሲከናወኑ በቅርበት መከታተል ይችላል፡፡ ችግሮች ሲኖሩ ለሚመለከተው አካል የመጠቆም ዕድሉ በጣሙን ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ በቅርበት የሚገኘው ህዝብ ነውና፡፡ ስለሆነም ህዝብና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው፡፡

ማንኛውም ጥያቄ ለሚመለከተው አካል ሲቀርብ ታዲያ ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ከመልካም አስተዳደር እስከ የማንነት ጥያቄ ድረስ ያሉትን ያካትታል፡፡ ከዚህ እልፍ ሲልም ህገ መንግስቱ የመገንጠል ጥያቄ የሚያስተናግድበትን አግባብም አስቀምጧል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ እውነታና ተሞክሮ በስፋት የሚነሳው የመልካም አስተዳደር እጥረት ጥያቄ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄም አልፎ አልፎ መነሳቱ አልቀረም፡፡ በአገሪቱ ነባራዊ እውነታ እነዚህን ጥያቄዎች የማቅረብ ሙሉ መብትና ነፃነት አለ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ህዝቡ የማንነት ጥያቄን የሚያቀርብበት አግባብ በህገ መንግስቱ በግልፅ መቀመጡን ይናገራሉ፡፡

በዚህም መሰረት የማንነት ጥያቄ ጥያቄው ለቀረበበት የክልሉ መንግስት ይቀርባል፡፡ የክልሉ መንግስትም የቀረበለትን ጥያቄ አግባብነት ፈትሾና አጣርቶ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል፡፡ ይህም የራሱ ጊዜ ገደብ አለው(ከሁለት ዓመት ያልበለጠ)፡፡ የክልሉ መንግስት ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን ምለሽ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ መስጠት ይኖርበታል፡፡

ይህን ሳይሆን ቢቀር የጠያቂው አካል ጥያቄ ተንጠልጥሎ አይቀርም፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን እንደሚመለከተው ነው አቶ ያለው የገለፁት፡፡ በዚህም ጥያቄው ተገቢውን ምላሽ ያገኛል፡፡ ይህ አካሄድ እስከ አሁን ሲተገበር ቆይቷል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ጥያቄዎች በአግባቡ እየቀረቡ አግባብነት ያላቸው ምላሾችን ያገኛሉ፡፡

ለማሳያ ያህል በቅርቡ የተነሳ ጉዳይን እንመልከት፡፡ ስለወልቃይት የሚናፈሰውን መነሻ እናድርግ፡፡  ከወልቃይት ጋር በተያያዘ የማንነት ጥያቄ መቅረቡ ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ ጥያቄውን ሽፋን በማድረግ የታየው እንቅስቃሴ ነው ይላሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፡፡ የሚገርመው ታዲያ በወልቃይት ላይ የተነሳ የማንነት ጥያቄ የለም፡፡

ወልቃይት ላይ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ ካለ ጥያቄው መቅረብ ያለበት ለትግራይ ክልል ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ ክልሎች ሲዋቀሩ ወልቃይት በትግራይ ሥር ነው የተካለለው፡፡ ስለሆነም በህጉ መሰረት ወልቃይት ላይ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ በቀዳሚነት የሚቀርበው ለትግራይ ክልል ነው፡፡

ክልሉ ጥያቄ ቀርቦለት በተቀመጠው ቀነ ገደብ ምላሽ መስጠት ካልቻለ ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል፡፡ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ሰሞኑን እንደገለፁት ታዲያ ከወልቃይት ጋር በተያያዘ የቀረበ የምንነት ጥያቄ የለም፡፡ በቀጣይ ቢቀርብም ክልሉ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማተናገድ ቁርጠኛ አቋም ይዟል ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር የሚቀራረበውና በሌላ መልኩ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ የአማራና የትግራይ ክልሎች ወሰን የማካለል ሥራ ነው፡፡ ይህ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ተግባር እንደሆነ ኢህአዴግም በውሳኔው አስተላልፏል፡፡ እስከ አሁን ድረስ መዘግየቱም ተገቢነት እንደሌለው ነው አፅንዖት የሰጠው፡፡  

ለመዘግየቱም የህወኃትና የብአዴን አመራሮች ትኩረት አለመስጠት እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡ እናም የወሰን ማካለሉን ሥራ ሁለቱ ክልሎች በአፋጣኝ እንዲተገብሩ ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል፡፡ ለዚህም ክልሎቹ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ አንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡን ያሳተፈ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር እና የህወሃት ሊቀመንበር አቶ አባይ ወልዱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፣ የትግራይ እና አማራ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ወሰን የማካለሉ ሥራ በአፋጣኝ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ትናንት ደርግን ለመጣል፤ ዛሬ ደግሞ ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ የተዋጉና እየተዋጉ ያሉ ህዝቦች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ሁለቱን ህዝቦች ለማለያያት የያዙት አጀንዳ እንደማይሳካም በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡ ክልሎቹ ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩም ነው የተመለከተው፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው የወሰን ችግር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም መያዙን ገልፀዋል፡፡ የምክር ቤቱን ውሳኔ በአፋጣኝ ለመተግበር ክልሉ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ሁለቱም ክልሎች ችግሩን ለመፍታት እስካሁን መዘግየታቸው ተገቢ አለመሆኑን አቶ ንጉሡ ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ህወሃትና ብአዴን ችግሩን ለመፍታት በፍጥነት ወደ ተግባር ለመግባት መነሳታቸውን ነው የገለፁት፡፡ ችግሮችን ተቀራርቦ ለመፍታትም ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ የሚያገኙበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ አካሄዱም ይህንኑ ህጋዊ ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ፅንፈኛና ድብቅ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ህዝቡን ሽፋን በማድረግ መንቀሳቀሳቸው ግጭት እንዲነሳ ማድረጉ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡

በግጭት ደግሞ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይገኝም፡፡ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተነስተው በነበሩት ግጭቶች የሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሰው ሞቷል፤ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ በግለሰቦችና በህዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከእንቅስቃሴ ታግደዋል፡፡

አላስፈላጊው ግጭት የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አሳርፏል፡፡ በብዙዎች ላይም ጠባሳውን ጥሎ አልፏል፡፡ ይህ ድርጊት ለማንም የበጀውና የፈየደው ነገር የለም፡፡ እና ሠላማዊ መንገድን መከተሉ አዋጭነቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሠላምን መንገድ መከተሉ የሠላማዊነት መገለጫ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የስልጡንነት ማሳያ ነው፡፡

ጥያቄን የሠላምን መንገድ በመከተል ማቅረብና መሞገት ተገቢ ነው፡፡ ጥያቄ ሳይመለስ ሲቀር ደጋግሞ መሞገት ይቻላል፡፡ ይህ ባልተከለከለበት ሁኔታ ከሠላም ባፈነገጠ መልኩ መንቀሳቀስ አያዋጣም፡፡ የሰላምን በር መዝጋት አይገባም፡፡ ሁሌም የሠላምን በር መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ሠላም ከምንም በላይ አስፈላጊ ነውና ለሠላም ዘብ እንቁም፡፡

በሠላም ጎዳና የተራመድ ይጠቀማል፤ያተርፋል፡፡ በተቃራኒው የተጓዘ ውጤቱ ውድቀትና ኪሳራ ነው፡፡ የሠላምን በር የተጠቀመ ወደ ተሻለ ደረጃ ይደርሳል፤ያሰበውን ያሳካል፤ህልሙን ዕውን ያደርጋል፡፡ የተከፈተለትን የሠላም በር ከመጠቀም ይልቅ ለመዝጋት የሞከረ የትም ሳይደርስ ይቀራል፡፡ ሳይገባ ይወጣል፤ሳያሳካ ይወድቃል፡፡ 

እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ነገም የመልካም አስተዳደር እጥረት፣ የማንነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ይገባል፡፡ ስለሆነም ጥያቄዎቹን ማንሳትና ለምላሽ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መሆን ያለበት ታዲያ በሠለጠነውና በህጋዊው መንገድ መሆን አለበት-በሠላማዊ መንገድ፡፡ እና የሰላምን በር ዘግቶ ህገ ወጥነትን መከተል ትናንትም፣ዛሬም ነገም መቼም ቢሆን መፍትሔ አይሆንም፡፡

በየደረጃው የተቀመጡ አመራሮች ለግጭት በር ከሚከፍቱ ድርጊቶች ሊታቀቡ ይገባል፡፡ የመንግስትን ሥልጣን ለራስ ጥቅም የማዋል አባዜ የተጠናወታቸው አካላትም ከድርጊታቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ በሠላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ መስራትም ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሰሞኑን የኢህአዴግ ምክር ቤትም ይህን ነው አፅንዖት ሰጥቶ ያሳሰበው፡፡ መልካም አስተዳርን የማስፈን ዘመቻው ከምንግዜም በላይ ይጠናከራል፡፡ ግንባሩም ራሱን በጥብቅ የተሃድሶ ግምገማ ውስጥ በማሳለፍ የተያዘው የህዳሴ ጉዞ እውን እንዲሆን  እንደሚሰራ ነው የገለፀው፡፡