ኢህአዴግ ተማሪ ነው፤ ተማሪ ደግሞ ይፈተናል

ይህን ፅሑፍ ለማሰናዳት ምክንያት የሆነኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ኢህአዴግ የተናገሩት ጉዳይ ነው— ኢህአዴግ በትግል ተፈትኖ ዛሬ ላይ የደረሰና ብቃቱም እንደ ንስር የሚታደስ ነው በማለት። የሚያጋጥሙትን ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅም ያለው ድርጅት እንደሆነም በስፋት ዘርዝረዋል። በዚህ ፅሑፌ ላይም ድርጅቱ ያገጠሙትን ችግሮች ከህዝብ ጋር ሆኖ የፈታበትን ሁኔታዎች ለማሳየት እሞክራለሁ—‘ኢህአዴግ ተማሪ ነው፤ ተማሪ ደግሞ ይፈተናል’ የሚል የመነሻ ጭብጥን በመያዝ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል። እናም በዚህ ፅሑፍ ከደርግ መውደቅ ማግስት፣ በተሃድሶው ወቅት፣ በምርጫ 97 እና በአሁን ወቅት ከመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዩች አንፃር ያጋጠሙትን ችግሮች በዋነኛነት በማንሳት ድርጅቱ የተጓዘባቸውን አባጣና ጎርባጣ መንገዶችን ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህ ምልከታዬም ገዥው ፓርቲ በትናንት ስህተቶቹ ዛሬን ማቃናት እንደሚችልና በዘወትር ተማሪነቱ እየተፈተነ የመጣ በመሆኑ፤ አሁን ያጋጠመውን ፈተና በሰከነና ህዝብን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የመፍታት ባህልና ብቃት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እስቲ ለማንኛውም በደርግ ውድቀት ማግስት ድርጅቱን ካጋጠመው ተግዳሮት ልነሳ። እንደሚታወቀው የአምባገነኑን ስርዓት መውደቅ ተከትሎ በ1983 ዓ.ም ከ17 የማያንሱ የታጠቁ የብሔር ቡድኖች ነበሩ። እነዚህ ቡድኖች የተለያዩ ዘውግ ያላቸው ናቸው። የተወሰኑት ጠባቦችና ትምክህተኞች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ በፅንፈኛ አክራሪነት የተሰለፉ ነበሩ። በወቅቱ ደርግን ገርስሶ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ እነዚህ ቡድኖች ለሀገራችን የጋራ መፍትሔ እንዲሹ ባቀረበላቸው ጥሪ መሰረት የሽግግር መንግስቱን ለመቀላለቀል ከያሉበት ቦታ ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው ይታወሳል። ለኢህአዴግ የእነዚህን የማይጣጣም ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች ፍላጎት ማቻቻል አንድ ተግዳሮት ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቡድኖቹን የተበታተነ ፍላጎት የተመለከቱ አንዳንድ ተንታኞች ‘ኢትዮጵያ ትበታተናለች’ የሚል ሟርትን ሲያቀርቡ ነበር። ይሁንና ኢህአዴግ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የራሱን መንገዶች ተከትሏል። በተለይም ድርጅቱ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዓመታት የተሸጋገረው በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሰላምና ማረጋጋት ስራዎችን ወደ ማከናወኑ ነበር።

በዚህም በውድ የህዝብ ልጆች አኩሪ መስዕዋትነት የተገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚሯሯጡ ፀረ ሰላም፣ ፀረ- ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ ኃይሎችን የማፅዳት ተግባሮችን ፈፅሟል። በወቅቱ ኢህአዴግና ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ለሀገራዊ ሰላም ሲሯሯጡ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አበው፤ ራሱን “ኦነግ” እያለ ይጠራ የነበረው የጠባቦች ቡድን ይህንን የተቀደሰ ዓላማ አልቀበልም በማለት የጦረኝነት አቅጣጫን በመምረጥ ማፈንገጡ የሚዘነጋ አይደለም።

ሆኖም ኢህአዴግ ከፍተኛ ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ ኦነግን ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ ከመለመን ባለፈ መስዋዕት እየሆነም ጭምር የሰላም እጁን ቢዘረጋም፤ ጠባቡ ቡድን ግን በእንቢተኝነቱ መፅናቱ የሚታወስ ነው። ኦነግ ለሰላም ሲታሰብ በየአካባቢው ሰው መግደልና ንብረት ማውደምን ስራዬ ብሎ ተያያዘው። ኢህአዴግ ለዚህ ሰላማዊ ተግባሩ በወቅቱ የተሰጠው ምላሽ ጦረኝነት መሆኑን በመገንዘቡ፤ ከብዙ ትዕግስትና ልመና በኋላ ሁሉም የሰላም መንገዶች ተሟጥጠው ሲያበቁ የኦነግ ሠራዊት በመረጠው መንገድ ርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል። ይህ ተግባሩም በህዝብ የተደገፈ በመሆኑ ኦነግ ያራምድ የነበረውን የእብሪት ጠብ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረግ ተችሏል።

የኢህአዴግ የሰላምና መረጋጋት ርምጃ ከመላው የሀገራችን ህዝብ ጋር ተቀናጅቶ አንድ ወሳኝ ምዕራፍ ሊከፈት ችሏል። ይኸውም የሀገሪቱን ለሰላምና መረጋጋት ዕውን በማድረግ  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያቀዷቸውና በሽግግር መንግስቱ የተቀመጡት ዓላማዎች ዕውን እንዲሆኑ ማስቻል ነው። የሀገሪቱ ህዝቦች ወደውና ፈቅደው አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመመስረት የሚያስችለውን የተመቻቸ ሰላማዊ ምህዳርም ተፈጥሯል። ይህ ሁኔታም ህገ- መንግስታቸውን በጋራ መክረው ዘክረው እንዲሁም አምነውበት እንዲያፅድቁት ከማድረጉም ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) እንዲመሰረት አስተማማኝ መሰረት ጥሏል። ይህም በደርግ ውድቀት ማግስት ‘ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው’ በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ተንታኝ ተብዬዎች ጥንቆላ መና እንዲቀር ያደረገ የሰላም መስመር ነው። እናም ኢህአዴግ ያኔ የተከተለው ትክክለኛ መስመር ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ ከብተናም እንድንድን ያደረገን ነው ማለት ይቻላል።

የሽግግር መንግሰቱን ተማሪነቱን ቀምሮ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ መንገዶች 10 ዓመታትን ከተሸጋገረ በኋላ፤ ድርጅቱ ሌላ አደጋ ገጠመው—በ1993 ዓ.ም። ይህ ወቅት ህወሓት ለሁለት የተከፈለበትና ኢህአዴግም እንደ ድርጅት የውስጠ-ድርጅት ትግሉ የጠነከረበት ጊዜ ነበር። ክፍፍሉ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንም ጭምር የነካካ በመሆኑ ድርጅቱ ሁለንተናዊ አቋሙን የፈተሸበት ነበር።

ነገሩ እንዲህ ነው።…ወቅቱ በሻዕቢያ የእብሪት ወረራ የተከፈተው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ፍፁም ድል አድራጊነት በተጠናቀቀበት ማግስት ነው። በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ብቅ…ብቅ ማለት ጀመሩ። እናም አመራሩ የውስጥ ችግሮቻችንን ፈትሸን እንፍታ የሚል የጋራ ድምዳሜ ላይ ይደርሳል። ውይይቱንም ሁሉም በየድርጅቱ እንዲያደርግና በስተመጨረሻም በኢህአዴግ ደረጃ ለመቀጠል ስምምነት ላይ ይደረሳል። በጠባብነት፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በትምክህት ጎራ የተሰለፉት እነ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ…ወዘተ የመሳሰሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሰራዊቱ ውስጥ የነበሩት ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው እነ ሌ/ጄኔራል ፃድቃንና ሜ/ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትን የመሳሰሉ የሰራዊት አባላት በአንድ ወገን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱንና ሀገሪቱን ከመበተን የሚያድን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን ያነገቡ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት በገሃድ መታየት ጀመረ። የውስጠ-ድርጅት ትግሉም ተጋጋመ።

በወቅቱ “አንጃው” ተብሎ የተሰየመው የጥገኝነት አቀንቃኝ ቡድን በማዕከላዊ ኮሚቴ 13 ለ15 በሆነ ድምፅ ሲሸነፍ ዴሞክራሲዊ መንገድን በመርገጥ አሻፈረኝ ብሎ ውይይቱን አቋርጦ ወጣ። በወቅቱም ተሰብሳቢው “በሰማዕታት አጥንትና ስጋ ይዘናችኋል እባካችሁ ተቀመጡና ተወያዩ” ቢባሉም፤ እምቢኝ፣ አሻፈረኝ በማለት ውይይቱን ረግጠው ወጡ። የድርጅቱን ህገ-ደንብም በግላጭ ጣሱ። ሆኖም ውይይቱ “አንጃውን” አግዶ ባሉት አባላት እንዲቀጥል ተደረገ። የ“አንጃው” አንዳንድ አባላት በወቅቱ በኦህዴድና በደህዴን ውስጥ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በሁለቱ ድርጅቶች ውስጥ ያልተገባ አካሄድን ለመከተል ሞከሩ። የ“አንጃው” አባላት ደቡብና ኦሮሚያ በእኛ ስር ስለሆኑ ምን ያመጣሉ ሲሉም ታበዩ። እንዲያውም የ“አንጃው” የዝቅጠት አስተሳሰብ በብአዴን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመመታቱ ሳቢያ ጥቂት አምሳያዎቹን በመያዝ በፓርላማ ውስጥ የራሱን መንግስት ለመመስረት ተሯሯጠ። ዳሩ ግን አብዛኛው ተወያይ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን በመደገፉ ምክንያት ይህ የ“አንጃው” ቀቢፀ-ተስፋ እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩ የበላይነትን በመያዙም ድርጅቱም ከብተና፣ ሀገራችንም የህዳሴዋን ጉዞ የምታሳልጥበት መንገድ ታያያዘችው።

በእኔ እምነት በደርግ ውድቀት ማግስት ከብተና እንዴት መዳን እንደሚቻል ትምህርት የቀሰመው ኢህአዴግ በተሃድሶው ወቅትም ይህን ፈተና ከተሞክሮው ማለፍ ችሏል። እንዲያውም የኪራይ ሰብሳቢነትንን የጥገኝነትን አደጋ መስቀረት በመቻሉ አሁን ላለንበት ሁለንተናዊ ዕድገት ልንበቃ የቻልንበት ምስጢር ይኸው ይመስለኛል።

በዚህ ሁኔታ እየተማረ የመጣው ኢህአዴግ፤ በሀገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት በተሃድሶው መስመር የተቀመጠውንና በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ካለው ፅኑ ፍላጎት ተነስቶ በህገ መንግስቱ መሰረት ምርጫ 97ትን አካሄደ። ምርጫውም ‘እንከን የለሽ’ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት ተንቀሳቀሰ።

ሆኖም የተቃውሞው ጎራ ይህን ‘እንከን የለሽ’ ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ ተጠቀመበት። ተቃዋሚዎች የህዝቡን ቅሬታዎችና ብሶቶች የማራገብ፣ ልክ እንደ አሁኑ ወቅት ‘ኢህአዴግ አብቅቶለታል’ የሚል ቀቢፀ-ተስፋዊ ስብከት እንዲሁም ፍፁም ዘረኛ በሆነ አስተሳሰብ ‘ወደ መጡበት እንመልሳቸዋለን…ምንትስ’…ወዘተ የሚሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችን እስከማራመድ ደረሱ። ባልተገባ ሁኔታም ምቹውን የምርጫ ምህዳር ዘመቱበት። የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በአንድነት ተቀናጅተውም የዘመቻው አካል ሆኑ። በዓለም ላይ የሚገኙ አክራሪ ኒዮ-ሊበራሎችና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ከያሉበት ዋሻ በፉጨት ተጠራርተው የዚሁ ዘግናኝ ቅስቀሳ አካል ሆኑ። የቀለም አብዮት ዘመቻም በውጭና በውስጥ ሃይሎች የጋራ ጊዜያዊ ግንባር አማካኝነት ተከፈተ።

ሻዕቢያም በበኩሉ በግንባር ላይ ያጣውን ድል በከተማ ውስጥ የጎዳና ላይ ነውጥ አገኛለሁ በሚል ቀቢፀ-ተስፋ ተንቀሳቀሰ። በስተመጨረሻም እነዚሁ ኃይሎች በፈጠሩት ሁኔታ ተቃዋሚዎች በጎዳና ላይ ነውጥ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድና ህገ-መንግስቱን ቦጫጭቀው ለመጣል በቀለም አብዩተኞች እየታገዙ ተንቀሳቀሱ። መንግስትና ኢህአዴግ ግን ይህን በሀገር ላይ የተጋረጠ ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድና በህጉ መሰረት ለመፍታት ተንቀሳቀሱ። በዚህም በጎዳና ላይ ነውጥ በህዝቡ ህይወትና ንብረት ላይ ለመዝመት የተጀመረው ጥረት ለማስቀረት ተችሏል። መንግስት የህዝቡን ሰላማዊ ህይወት መጠበቅ ያለበት አካል በመሆኑ በወቅቱ መወሰድ ያለበትን ርምጃ ሳይወድ በግድ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ጥረት ተደርጓል። 

በአንድ ወገን ሰላምን የማስከበር ስራ እየተከናወነ በሌላ በኩል ደግሞ ታዋሚዎች ባሸነፉበት አዲስ አበባ ያገኙትን ወንበር እንዲወስዱና በመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንዲለመኑ ተደረገ። ይህ የሆነበት ምክንያትም እነርሱን የመረጠውን ህዝብ በማክበርና ኢህአዴግ ለህዝብ ካለው አክብሮት የመነጨ ነበር። እነርሱ ግን በእምቢታቸው ፀኑ። በሚያስገርም ሁኔታ የመረጣቸው ህዝብ ፓርላማ ግቡ ብሏቸው የሰጣቸውን ድምፅም መልሰው ለውይይት አቀረቡት። በስተመጨረሻም አንዳንዶቹ ፓርላማ አንገባም በማለት የመረጣቸውን ህዝብ ድምፅ አሽቀንጥረው ጣሉት።…መንግስትም የህዝቡን ድምፅ አክብረው ፓርላማ ከገቡት ታዋሚዎች ጋር አብሮ መስራቱን ቀጠለ።

እንግዲህ በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገር ኢህአዴግ በሂደት ከችግሮች እየተማረና የሚያጋጥሙትንም ተግዳሮቶች ከህዝብ ጋር በመሆን እየፈታ መምጣቱን ነው። ከላይ በዋነኛነት የጠቀስኳቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት የተከተላቸው መንገዶች ድርጅቱ ከህዝብ ጋር በመሆን የማይፈታቸው ችግሮች አለመኖራቸውን የሚያመላክት ነው። ሆኖም እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉት የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና እነርሱን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ መገልገያነት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መኖሩ የግድ ነው።

እነዚህ ችግሮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለፉት 25 ዓመታት የተገኙት የልማት ትሩፋቶች የፈጠሯቸው አውዶች በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉኝም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ ማድረግ ይቻላል። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህን ማድረግ ይችላል። ለዚህም ይመስለኛል ሰሞኑን በስራ አስፈፃሚውና በምክር ቤቱ ባካሄዳቸው ስብሰባዎች ላይ በጥልቀት በመታደስ ተግዳሮቶቹን መፍታት እንደሚችል የገለፀው።

በእኔ እምነት ኢህአዴግ “እታደሳለሁ” ካለ ይታደሳል። ይህንንም በተለይም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ አሳይቶናል። በዚያ የተሃድሶ ወቅት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሀገራችንን የልማት ተምሳሌት አድርጓል። የኢህአዴግን መስመር ዛሬ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየወሰዱት ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል ነው።

እንደ ትናንቱ ከህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን በጥልቀት ይፈትሻል። በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማርገብ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊፈተን የሚችል ቢሆንም፤ ዋናው ቁም ነገር ፈተናውን ማለፉ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅሙም ይሁን ብቃቱ አለው። በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድርጅቱን በአዲስ ኃይል የመታደስ አቅም ባለው ንስር መመሰላቸውም ለዚህ ይመስለኛል።