ወሳኙ ሕዝብ ነው!!

ሕዝብ የሀገር ባላና ምሰሶ፣ ወጋግራና ማገር ነው፡፡ መንግስት ካለህዝብ ህዝብም ካለመንግስት መኖር አይችሉም፡፡ መንግስት ህዝብን ማዳመጥ አለበት፤ አዳምጦም ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ የመስጠት ግዴታም፣ ሀላፊነትም አለበት፡፡ ወሳኙ ትላንትም ዛሬም ወደፊትም ህዝብና ህዝብ ብቻ ነውና፡፡ በተለይም በህዝብ ምርጫና ድጋፍ የተመረጠ የፖለቲካ ድርጅት የሚመሰርተውም ሆነ የሚመራው መንግስት የሚሰየሙትም ሹሞች ቅድሚያ ተግባራቸው ህዝብን በቅንነት በታማኝነት ማገልገል ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከዚህ መስመር ሲተላለፉ የመረጣቸው ወሳኝ ህዝብ ድምጹን ከፍ አደርጎ በተቃውሞ ያሰማል፡፡

በመንግስትም ሆነ በድርጅቶቻቸው የኃላፊነት ወንበር ላይ የተቀመጡ ሹማምንት ከህዝብ ፍላጎትና እምነት ውጪ ሲራመዱ ከህዝብ አገልጋይነት ወጥተው በህዝብ መገልገልና መጠቀም ሲጀምሩ ስልጣናቸውን የግል ሀብትና ንብረት ማፍሪያ፣ ማከማቻ፣ መበልጸጊያ ሲያደርጉት፤ የሀገሪቱንም ሀብት የማትነጥፍና ሁሌም የምትታለብ የወተት ላም አድርገው በቃን በማይሉበት ምዝበራና ዘረፋ ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ወሳኙ ህዝብ አርሙ፣ አስተካክሉ፣ አካሄዳችሁ ከህግ ውጪ ነው የሚለውን ተቃውሞውን በተለያየ መልኩ ያሰማል፡፡ ሲያሰማም ቆይቶአል፡፡ የተሀድሶው ግምገማም ይሄንኑ አስምሮበታል፡፡

ሲነገረው የማያዳምጥ፣ ምን ታመጣለህ? ማነህ? በሚል እብሪት ልባቸው የተደፈነ መሪዎች ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀስ ዘንድ ምክንያቶች ናቸው፡፡ አመፅ ደግሞ የሚመራበት ስሌትና ቀመር የለውም፡፡ ጥፋትና ውድመት በንብረትም በሰው ህይወትም ላይ ያስከትላል፡፡ በሌሎች ሀገራትም ተቃውሞዎች ውስጥ ሲታይ የኖረው ይሄው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅልና ትርምስ ይልቅ ኢህአዴግ አስቀድሞ ማድረግ የነበረበትና አሁንም ያለበት ህዝብን ማዳመጥ፣ ለህዝብም መሰረታዊ ጥያቄዎች  ተገቢ መልስ መስጠት ነው፡፡ ከላይ እንዳልነው፣ ወሳኙ ህዝብ ነውና፡፡ እየተደረገ ያለው ተሀድሶም በዚህ አቅጣጫ ምን እንዳስቀመጠ ህዝቡ ለማየት ጓጉቷል፡፡

በመንግስት ሚዲያ አቀራረብም ረገድ በወቅታዊ ሁኔታዎች ዘገባም በህዝቡ በኩል ያለውን እውነት ችግርና መፍትሄውን ከማቅረብ ይልቅ አመራሩ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች የተለየ ፍላጎት በመከተል መልሶ ለህዝቡ ማቅረብ ምን ያህል ከህዝብ ጋር እንደሚያላትም፣ እንደሚያጋጭ፣ በህዝብ ዘንድም አመኔታን እንደሚያሳጣ የሚዲያዎቹንም ተአማኒነት አውርዶ እንደሚጥለው በተግባር የታየ ነው፡፡

ሚዲያው የህዝብ ነው፡፡ ይልቁንም ችግሩን በግልጽ አውጥቶ ሁሉም የጋራ መፍትሄ እንዲፈልግ በር መክፈት በሰለጠነ ግልጽ ውይይት ሰላማዊ መፍትሄ ማስገኘት ላይ ማተኮር ነበር የሚገባቸው፡፡ ህዝቡ ውስጥ ያለው ችግር ሌላ ሚዲያዎቻችን የሚያወሩት ሌላ ሆነ እንጂ፡፡ ህዝቡ ይሄ ድርጊት የህዝብን ድምጽ ማፈን ስለሆነ እውነትም ስለሌላቸው የመንግስትን ሚዲያ አናይም፤ አንከታተልም እስከማለት የደረሰበትም ምክንያት ይሄው ነው፡፡

ወሳኝ የሆነውን የህዝብ ድምጽ የራሱ የህዝብ በሆነው ሚዲያ እንዲሰማ የማይፈቅዱ ሹሞች ችግሩን ያባብሱት እንደሆነ እንጂ  መፍትሄ ሊያስገኙ አይችሉም፡፡ ሚዲያው በህዝብ ሀብትና ገንዘብ የሚተዳደር መሆኑን ረስተው የግላቸውና እንዳሻቸው የሚፈነጩበት የሚመስላቸውም ሀላፊዎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ለዚህ ነው የባህር ማዶዎቹ ከዚሁ የሚያገኙትን ዜና መልሰው ወደሀገር ቤት እንዲሰራጭ እያደረጉ ህዝቡ እነሱን ብቻ እንዲሰማ ለማድረግ የቻሉት፡፡ እውነትን በመደበቅ የህዝብን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡

የሀገር ውስጡ ፐብሊክ ሚዲያ እውነቱን ለማቅረብ ቢችል ኖሮ አመኔታን በሰፊው በመገንባት የህዝቡን ቀልብና ልቦና ለመሳብ በበቃ ነበር፡፡ ሀገር ቤት ውስጥ ስለሆነው ሀላፊዎች ምስጢር አድርገው የሚደብቁትን ዜና እነቢቢሲ እና ሌሎችም ከተጨባጭ ማስረጃው ጋር ከለንደን፣ ከአሜሪካ፣ ከጀርመን መልሰው ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሰሙታል፡፡ ህዝብ ማወቅ ያለበትን የማወቅ መብት አለው ይላሉ አለም አቀፎቹ የሚዲያና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተከራካሪዎች፤ ወሳኙ ህዝብ ስለሆነ፡፡

ጋዜጠኛው የመረጃ ነጻነትና የመገናኛ ብዙሀን ህጉ በሚፈቅደውና ህገመንግስታዊ ዋስትና ባገኘው የኢዲቶሪያል ነጻነት መብቱ አይጠቀምም፤ መብቱ ተረግጦአል፤ ነጸነት የለውም፤ በነጻነት አይዘግብም ማለት ነው፡፡ ይሄ ለስርአቱም ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሳንሱርና ቁጥጥሩን እያሰበ መስራት ለውጥና እድገት አያመጣም፡፡ ሚዛናዊ አድርጎ አመጣጥኖ የመስራት መብት እንኩዋን የለውም፡፡ ይሄም በተራው በመንግስት መገናኛ ብዙሀንና በህዝቡ መካከል ያለውን ክፍተት ያሰፋዋል፡፡

ሚዲያው የሚጠበቅበትን ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት የሙያ ነጻነቱን ተጠቅሞ መስራት ሲገባው ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች እጅ እየወደቀ የህዝቡን እውነተኛ ችግር ብሶት የመልካም አስተዳደር በደሎች የፍትህ እጦትና የኪራይ ሰብሳቢዎችን ምዝበራና ዘረፋ ለይቶ እንዳያጋልጥ ተጠፍንጎ ያለበትን ሁኔታ ነው እያየን ያለነው፡፡ ውጤታማ ስራ ቢሰራ ተጠቃሚው መንግስትም ወሳኙ ህዝብም ነው የሚሆነው፡፡

ጋዜጠኛው ህጉንና ስርአቱን አክብሮ መሰራቱ ተገቢ ነው፡፡ ሙያዊ ነጻነት በተገፈፈበት መልኩ ልክ እንደበቀቀን ወፍ በል ያሉትን እያለ ታዛዥነቱን አሳምሮ እንዲሰራ ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ መንግስትም ሊያገኝ የሚገባውን ውጤት አያገኝም፡፡ ይሄን ያህል አሽቆልቁለን ወርደናል፡፡ የቁልቁለቱን መንሸራተቻ በመያዝ ወደታች እየተምዘገዘግን ነው፡፡ ተሀድሶው ይሄንንም ጠልቆ ይፈትሸዋል የሚል እምነት አለ፡፡

የሚሰጡት የሚዲያ አቅጣጫዎች እውነተኛ ችግሩን ሳይደብቁ ችግሩን አፍረጥርጠው አውጥተው ለህዝብም ለመንግስትም ለሀገርም የሚበጁትን መፍትሄዎች የሚያስቀምጡ መሆን መቻል አለባቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የሚዲያ ስትራቴጂስቶች በፊት ነበሩ፤ ዛሬ ላይ ግን የሉንም ማለት ይቀላል፡፡

ለሁሉም አይነት ችግር መፍትሄና መድሀኒት ሁኖ ችግሩን ሊፈታ ህዝቡን አወያይቶ፣ ተሰሚና ተደማጭ ሰዎችንም አቅርቦ፣ ችግር አለብን የሚሉትንም አስደምጦ፣ አወያይቶ፣ ውዥንብርን አጥርቶ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት የሚችለው ሚዲያ በነጻነት የመስራት አቅሙ ስለተሸበበ ብቻ ማምጣት የሚችለውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡

ተደጋግሞ ሲነገር እንደሚሰማው፣ ለመንግስት ህልውና መቀጠልም ሆነ አለመቀጠል ህዝብ ወሳኝ ነው፡፡ ከህዝብ በላይ ያለ የሚኖር ምንም የለም፡፡ ወሳኙ ህዝብና ህዝብ ብቻ ነው፡፡

የአንድ ሀገር ባለቤት ወሳኙ መሪውና አሳዳሪው ህዝብ ሲሆን መንግስት በህዝብ ተመርጦ ወይንም ተወክሎ በኮንትራት ውል የተወሰነ ግዜ እንዲመራ እንዲያስተዳድር በስልጣን  ላይ የሚቀመጥ አካል እንጂ ዝንተ አለማዊ ሁኖ የሚቀጥል አይደለም፡፡ መንግስታት ይለዋወጣሉ፡፡ ይሄዳሉ ይመጣሉ፡፡ ሀገር ግን የመንግስት ሳይሆን የህዝብ ነች፡፡

ትልቁ ቁም ነገር መንግስታት በዘመናቸው ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ የሚጠቅም ዘመንና ትውልድ የሚሻገር ምን ስራ ሰሩ? ምንስ ለቀጣዩ ትውልድ አስቀመጡ የሚለው ነጥብ ነው በህዝብ  የሚመዘነው፡፡ ህዝብ ያያል፡፡ ይመዝናል፡፡ ፍርድም ይሰጣል፡፡

የሚጠበቀው ወይንም ይጠበቅ የነበረው ሹመኞች ለህዝብ እንዲሰሩ እንዲያገለግሉ እንጂ በጉልበትና በሀይል የተጫኑ ገዢዎች ሁነው መብቱን ሊረግጡ ሊገፉት በደልና ግፍ ሊፈጽሙበትም አልነበረም፡፡ የአሁን ጊዜ ምሬቱም ዋናው መነሻ ይሄው ነው፡፡

ህዝብ ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን አምርሮ ይጠላል፡፡ አይቀበለውም፡፡ አይደግፈውምም፡፡ የሀገር ሰላምና ደህንነት የአብሮነትም ጠንቅ መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ በመንግስት ወንበር ላይ ተቀምጦ ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን መስበክ ለዚህም ሳይታክቱ መስራት ከሁሉም የከፋው ነውረኛ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ በመሰረቱ ዘረኝነትና ጎጠኝነት በአለማችን ላይ እጅግ የከፋው መድሀኒትም የሌለው የካንሰር በሽታ ነው፡፡

ሁሉም ሰው የተፈጠረበትን ቤተሰብ ይወዳል፡፡ ያከብራል፡፡ ይህ ደግሞ መሆን ያለበት ለሁሉም ነው፡፡ በጋራ የምንኖርባት ሀገር ናትና፡፡ ህዝብ አትከፋፍሉን፤ አትለያዩን፤ ጥንትም ዛሬም አብረን የኖርን፣ ወደፊትም ሳንለያይ የምንኖር ነን እያለ ነው፡፡

በደስታውም በሀዘኑም ሁሉም አብሮ የሚካፈልባት የሚሳተፍባት ሀገር ነች፡፡ ይህ ከቀን በኋላ የመጣ የዘረኝነት በሽታ ስር እየሰደደ ከሄደ ሀገሪትዋ ሀገር አትሆንም፡፡ የውስጡም የውጩም ዘረኛና ጎጠኛ ሀይል በእብሪትና በማንአለብኝነት እሳት ለኩሰው ከዳር ሁነው ለመሞቅ አይቻላቸውም፡፡ እሳቱ መልሶ እነሱንም አንድዶና አቃጥሎ ወደአመድነት እንደሚለውጣቸው ለአፍታ ሊጠራጠሩ አይገባም፡፡ ትንሽ ፈሪኀ አምላክ መሆንም እኮ ጥሩ ነው፡፡ ስንት ዘመን ይኖራል ብሎ ማሰብም ደግ ነው፡፡ ህዝብ አይለያይም፡፡ እንለይህ ቢባልም አይሆንም፤ ተሳካ ቢባል እንኳን ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡

ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም ወደፊትም የሚኖረው ከህዝብና ከህዝብ ጋር ነው፡፡ ክፉውንም ደጉንም ማሳለፍ የሚቻለው በሀገር ከህዝብ ጋር ነው፡፡ ነገ ምን ይመጣል ብለው የማያስቡ ስለህዝብም ሆነ ስለሀገር ቀጣይነት የማይጨነቁ ከሰለጠነ አስተሳሰብ የተፋቱ፤ ዲሞክራሲ ምን እንደሆነ ለይተው የማያውቁ የከፋ ጸረ ህዝብ አቋምና እምነትን የሚያራምዱ ሰዎች በሁለቱም ጎራ አሉ፡፡ በመሆኑም ነው ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊና ምሁራዊ አመራር አጥቶአል የሚባለው፡፡ እነዚህ ወገኖች ግን ለምንም አይበጁም፡፡ ከጥፋትና ከውድቀት ውጪ የሚያመጡት ለህዝብ የሚጠቅም  አንዳች ነገር የለውም፡፡ ዞሮ ዞሮ ተጎጂዋ ሀገርና ህዝብ ስለሆኑ ስህተቶቹን ፈጥኖ ማረም ወሳኝነት አለው፡፡

ይህንን የአመራር ውድቀት ያመጡትን አለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ላይ ጥቁር ነጥብ እንዲያርፍ ያደረጉትን፣ ሀገሪትዋንና ህዝቡን ያዋረዱትን ከአፍንጫቸው አርቀው ለማሰብ ያልበቁ ሰዎችን እንደ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ከውስጡ መንጥሮ ሊያወጣቸው ካልቻለ የጥልቀቱ ተሀድሶ አብዛኛው ህዝብ እንደሚለው ግዜ መግዣና ማለዘቢያ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ችግሩንም አይፈታውም፡፡ እናም ጥልቀቱ የምር ሊሆን ይገባል።

ሀገሪቱ የ100 ሚለዮን ህዝቦች ቤት እንጂ ጥቂቶች የሚፈነጩባት የግል ንብረት አይደለችም፡፡ ከህዝብ ተጣልቶ ከህዝብ ተጋጭቶ ህዝብን አስለቅሶ በአመራሩ በሰላም የቀጠለ መንግስትም ፓርቲም በአለም ታሪክ አልታየም፤ የለምም፡፡

ሌላው ትልቁ ነጥብ ህዝብ ካመረረ በቃኝ ካለ የትኛውም ምድራዊ ሀይል ቢሰለፍ ሊያንበረክከው አይችልም፡፡ ይሄን እውነት የቀድሞው መሪ መለስ ዜናዊ አሳምረው ተናግረውታል፡፡ በሀይልና በሰራዊት በመሳሪያ ብዛት በቴክኖሎጂ ምጥቀትም በመጠቀም ህዝብን ካለፍላጎቱ ማንበርከክ አይቻልም ነው ያሉት፡፡

ምድራዊ ሀያላን የተባሉት ሁሉ በተለያየ ዘመናት ታሪካቸው በውርደትና በውድቀት የተደመደመው ከህዝብ ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው ነው፡፡ ይሄ እሳቤ ጭርሱንም አያዋጣም፡፡ ህዝብ ምን ያመጣል አይባልም፡፡ ሀገር የህዝብ እንጂ ወቅት የፈጠራቸው ሹማምንቶች የግል ንብረትና እንዳሻቸው የሚፈነጩባት መድረክ አይደለችም፡፡ ሊሆንም  አይችልም፡፡ መንግስት ያለህዝብ ከባህሩ ውስጥ የወጣ አሳ ማለት ነው፡፡

ህዝብ ከሌለ ህዝብ እምቢተኛ ከሆነ መንግስት ማንን ነው የሚመራው የሚያስተዳድረው ብሎ መጠየቅም የአባት ነው፤ የህዝቡ ጥያቄ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሙስና፣ ከኪራይ ሰብሳቢ፣ ምዝበራ፣ ዘረፋ፣ ነጠቃና ምሬትም በላይ ያልፋል፡፡ ፍትሀዊ የስልጣን ውክልናና የሀብት ክፍፍል የለም፤ በገዛ ሀገራችን ባዳ ሆነናል፤ ዜግነታችን ተረግጦአል፤ የብሄረሰቦች እኩልነት ቢባልም በተግባር ያለው ሁኔታ ይሄንን አያሳይም፤ እኩልነት የለም እያለ ነው፡፡ ለዚህ መልስ መስጠት ያለበት፤ ማስተካከል የሚገባው ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ነው፡፡

የኢህአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ ይሄንን ሲባል፣ ሲነገር፣ አዝወትሮም ሲሰማው የኖረውን ችግር እንዴት ይፈታዋል? ይመለከተዋልስ?? ጥልቀታዊው የኢህአዴግ ተሀድሶ እነዚህን ቁልፍ ችግሮቸ ሊፈታና ሊያስወግድ ካልቻለ አሁንም ውሀ ቢወቅጡት መልሶ እንቦጭ እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ሀገርን የሚጠብቃት የሚፈጥራት የሚለውጣት የሚያሳድጋት ህዝብ መሆኑም ሊሰመርበት የግድ ነው፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ ንጉስ፣ ፕሬዚደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ጀነራሎች ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፡፡ ተተክለው ዘላለማዊ ሁነው አይኖሩም፤ ያልፋሉ፡፡ ቁም ነገሩ ለሀገር፣ ለህዝብ የሚበጅ ዘመንና ትውልድ የሚሻገር ምን ስራ ሰሩ? በምንስ ይዘከራሉ? የሚለው ነው፡፡ ዘለአለማዊ ስልጣንና ወንበር የለም፡፡ አይኖርምም፡፡

ብዙ ታሪክ የሰሩ፣ ለሀገርና ለህዝብ የለፉ፣ የደከሙ መስዋእትነትም የከፈሉ ታላላቅ ሰዎችም  ይህቺን ሀገር ይዘዋት አላለፉም፤ ጥለዋት ነው የሄዱት፡፡ አንዲት እስፒል ይዘው አልሄዱም፡፡ ሀገርና ህዝብ  ትውልድም ምንም ሆነ ምን ይቀጥላል እንጂ አይቆምም፡፡

ለሀገር ስለደከምኩ መስዋእትንት ስለከፈልኩ ልዝረፍ፤ ልመዝብር፤ ላግበስብስ ሲባል ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ያውም በመሪነት ወንበር ተቀምጦ መዝረፍ በስልጣን መባለግ አደባባይ ህዝብ እስኪያውቀው ድረስ በጣም ያሳፍራል፡፡ አንገትም የሚያስደፋ ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ ታሪክንም በሌብነት ማቆሸሽ፣ ማሳደፍ፣ ጭቃ መለወስ ውርደት እንጂ አያኮራም፡፡ ተሀድሶው እስከየት ይዘልቃል ብሎ መጠየቅ  ተገቢ ነው፡፡

መለስ ዜናዊ እንዳሉት በህዝብ ላይ የተፈጸመ ግፍና በደል በዝቶ ጽዋው ሲሞላ ማቆሚያ መገደቢያ ማብረጂያ ሲያጣ ገንፍሎ ሞልቶ ተርፎ ይፈሳል፡፡ ህጋዊ ፈቃድ ሳታገኝ ሰልፍ አትውጣ እርምጃ ይወሰዳል ሲባል ብትገለኝም ግድለኝ መብቴ ተደፍሮ ሰውነቴ ተረግጦ መሬቴ ተዘርፎ ሰውነቴን አጥቼ ከምኖር ሞቴን እመርጣለሁ ብሎ እየተመመ አደባባይ ሲወጣ ጥያቄው የጥቂት ጸረ ሰላም ሀይሎች ነው ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ የተሀድሶው ጥልቀት የወሳኙን ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች የተመረኮዘ መሆን ይገባዋል፡፡

አዎን ችግር አለ፡፡ በደል አለ፡፡ መከፋት አለ፡፡ ምሬት አለ፡፡ የሰፋ ቅያሜም አለ፡፡ የጋራ ሀገራችን ስለሆነች ቁጭ ብለን ተነጋግረን ሰላማችንና ልማታችን እንዳይታወክ የሀገሪትዋ ጠላቶችም መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኙ በገዛ እጃችን በእልህና በንዴት በስሜታዊነት ተሞልተን ቤታችንን እንዳናፈርስ ሰላማዊ መፍተሄ እናብጅለት ማለት ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ ትልቅነትም ነው፡፡

እዚህ ደረጃ ድረስ ህዝቡ በምሬት እንዲዋጥ እንዲሞላ ያደረገው ችግር ምንድነው? ብሎ መጠየቅ መፍትሄውንም ከህዝብ ጋር በመመካከር ማምጣት ሀላፊነቱ የመንግስትና የኢህአዴግ ነው የሚሆነው፡፡ የጥልቀት ተሀድሶው እስከ ምን ድረስ ነው የሚጠልቀው የሚለውን ለማየት ህዝቡ በጉጉት የሚጠብቀውም በብዙ መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ስርነቀል ለውጥ ወሳኝ ለሆነው ህዝብ ይበጃል፡፡