ወጣቱ ሊያመክናቸው የሚገቡ የአሉባልታ ጥሪዎች

በቅርቡ እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተመሩ ሁከቶች በአንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች ተከስተዋል። መቀመጫቸውን በውጭ ሀገር አድርገው እዚህ ሀገር ውስጥ ሁከት ለመፍጠር በመሹ ኃይሎች አማካኝነት ለተካሄዱት የማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳቱ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ በተለይም ወጣቱ ሰለባ መሆኑ አያጠያይቅም። እርግጥ ወጣቱ ለሁከት ኃይሎቹ ተገቢ ያልሆነ ምላሽ የሰጠው የመንግስት የተጠቃሚነት አሰራር ቅሬታ ስለፈጠረበት እንዲሁም መንግስት ሁኔታውን ለማስተካከል የወሰዳቸው ርምጃዎች ስለዘገዩበት ነው።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት መንግስት በየክልሉ ለሚገኙ የሀገራችን ወጣቶች ከስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። እርግጥም የሀገራችን ወጣት በውጭ የሚኖሩት ሁከት አቀጣጣይ ኃይሎች ከሞትና ከጥፋት ተግባር በስተቀር የፈየዱለት አንዳችም ነገር እንደሌለ ተገንዝቦ መፍትሔውን ከመንግስት ጋር ፊት ለፊት መነጋገር ያለበት ይመስለኛል። እዚህ ሀገር ያለውን የተጠቃሚነትና የመበልፀግ አጀንዳን የሚመራው መንግስት እንጂ እነዚህ ሃይሎች ባለመሆናቸው ወጣቱ የችግሩን ዕውነታ በሰከነ መንገድ ማጤን ያለበት ይመስለኛል።

እርግጥ እኔ እስከማውቀው ድረስ የሀገራችን ወጣት አመዛዛኝ፣ አስተዋይ፣ ፍትሃዊና በስሜት የማይጓዝ ነው። በተሳሳተ መንገድ አሊያም የችግሩን መንስኤ በውል ካለመገንዘብ ካልሆነ በስተቀር በሁከት ፈጣሪዎች የጥፋት ጎራ ይሰለፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ እናም ወጣቱ የውስጥና የውጭ የአመፅና የጥላቻ ጥሪዎችን በሁለት ምክንያቶች ማምከን ያለበት ይመስለኛል፡፡ አንደኛው፤ መንግሥት የሚከተለው ልማታዊ አቅጣጫ ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግሮች የመፍታት አቅም ያለው ስለሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የገነባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን ባለፉት ጊዜያት በተግባር ስለሚያውቀው ነው፡፡

ወጣቱ ሚዛናዊና ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ፤ በሁከት ፈጣሪ ሃይሎች አማካኝነት የሚቀርቡ “ጎስም ነጋሪት፣ ክተት ሰራዊት” ዓይነት የጥፋት እንዲሁም ፀረ-ልማት ጥሪዎችን አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ ይገባዋል፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው ወጣቱ ባለፉት 13 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግሥት እንደሚፈታው ማመን ያለበት ይመስለኛል። እናም ችግሩን በመቋቋም ወደ ዘላቂው መፍትሔ መግባት ያለበት ይመስለኛል—የሁከት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን የሚገኝ ነገር የለምና።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ የመንግሥትን የለውጥ ኃይልነት ስለሚያውቅ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን ይኖርበታል፡፡

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 25 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ከ25 ዓመት በፊት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው፡፡ ለአብነትም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። እናም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት አይፈልግም፡፡ ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ እናም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።

ወጣቱ ከሁከቱ ወዲህ ስለ እነዚህ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች የተገነዘበ ይመስለኛል። አዎ! ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት “እፈፅመዋለሁ” ብሎ ገቢራዊ ያላደረገው ምንም ዓይነት ነገር ያለ አይመስለኝም—በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ዕድገቱ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ካለማድረጉ በስተቀር፡፡

ያም ሆኖ ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባቸውን የተስፋ ቃላት ተፈፃሚ አድርጓቸዋል፡፡ አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም፡፡ እነዚህን ዕውነታዎች ወጣቱ አሳምሮ የሚያውቃቸው ይመስለኛል፡፡

ከእነዚህ ተጨባጭና የማይታጠፉ ቃሎቹ በመነሳትም፤ በቅርቡ ሀገራችን ውስጥ  የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር መንግሥት መስመር እንደሚያሲዘው ማመን ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ገዥው ፓርቲና መንግሥት የለውጥ አደራጅና ቀያሽ መሆናቸውን ወጣቱ በሚገባ ስለሚያውቅ፤ አሁን የተፈጠረው ችግር በመንግስት እንጂ በሁከት አቀንቃኞች ይፈታል ብሎ ያስባል ማለት አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን የሁከት ኃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ አያ ለማራገብ ቢሞክሩም እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ-ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ለማሳሳት ቢሞክሩም ወጣቱ ጆሮውን ሊሰጣቸው አይገባም፡፡

የማናቸውም ችግሮች መፍትሐሔ የሚመነጨው በሀገረቱ መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ኃይሎች ባለመሆኑ ሃቁን መገንዘብ ይኖርበታል። እናም መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቱ ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ ራሱን ማራቅ ያለበት ይመስለኛል። ወጣቱ እዚህ ሀገር ውስጥ ህይወቱን ለመለወጥ በተጨባጭ ለሚከናወኑ ተግባሮች እንጂ፤ ለሁከት አጋፋሪዎች የነውጥ ጥሪ በስሜታዊነት ጆሮውን ማዋስ አይኖርበትም፡፡ እነዚህ የሁከት ኃይሎች የሚፈጥሩለት ምንም ዓይነት ነገር ባለመኖሩ ከጀመረው በልማት ስራው ራሱን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ገለል እንዲሉ ሊነግራቸው የሚገባ ይመስለኛል። እናም በአዲሱ ዓመት ወጣቱ የመንግስትን ቃል በማመን ለሁከት ሊያሰልፉት የሚከጅሉ ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል እላለሁ።