የግብፆች ግልፅና ስውር እጆች

በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በአንዳንድ የውጭና የውስጥ ኃይሎች እዚህ ሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ሁከት ጠለቅ ብሎ የሚያስብ ሰው፤ የግብፆች ግልፅና ስውር እጅ ሊኖር እንደሚችል የሚጠራጠር አይመስለኝም። እኔም የተሰማኝ ይኸው ስሜት ነው። ለዚህም ለሌላውን ትተን በቅርቡ በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም ውስጥ የህዳሴው ግድብ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ተፅዕኖ እንዲያጠኑ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎችን ለመቅጠር ቀጠሮ ተይዞ መሰረዙና በግብፆች በኩል “ኩባንያዎቹ ከሱዳን መንግስት ቪዛ ስላላገኙ…ምንትስ’ በሚል የቀረበው ምክንያት እንዲሁም በእነርሱ በኩል ዛሬም ድረስ ፅኑ አቋም ሊያዝባቸው ያልተቻሉ የቅኝ ግዛት ውሎች፤ ግብፆች ዛሬም ሀገራችን ውስጥ ሁከት እንዲፈጠር ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አመላካች ይመስለኛል። አዎ! እርግጥም ለሀገራችን አለመረጋጋት የግብፅ ግልፅና ስውር እጆች መኖራቸውን ለመገንዘብ ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠይቅ አይመስለኝም።

እስቲ ከግልፁ እጆቻቸው እንነሳ። ግብፆች ከአንዋር ሳዳት እስከ ሙባረክ፣ ከሙባረክ እስከ ሙርሲ ብሎም እስከ አሁኑ ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ እስከሚመሩት መንግስት ድረስ በርካታ ገዥዎች የዘያችን ሀገር በትረ ስልጣኑን ተቆናጥጠዋል። ሆኖም በዓባይ ውኃ ላይ የሚያራምዱት አስተሳሰብ ግን ከመለሳለስ ውጪ ብዙ ልዩነት የተስተዋለበት ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም፡፡

እንዲያውም ግብፆች የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ወደ ጎን በማድረግ የዓባይ ጉዳይ የህዝባቸው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ ያለ ልዩነት ሲናገሩ እየተደመጡ ዛሬ ላይ መድረሳቸውን አስረጅ የሚያስፈልገው አይመስለኝም—ሲከውኑት የነበሩት ተግባሮቻቸው አፍ አውጥተው ይናገራሉና።

እርግጥ ነው— ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ አጠቃቀም ዙሪያ ለዘመናት ሳንግባባ ኖረናል፡፡ አለመግባባት ደግሞ የጠላትነት መለኪያ አይደለም፡፡ ግብፅ ለዘመናት ብቸኛ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን አሮጌውን የህግ ማዕቀፍ ደንግጋ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን መንፈጓ የትናንት ሃቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 85 በመቶ ያህሉን የናይል ወንዝ ድርሻ የምታበረክት ታላቅ ባለ ይዞታ ሀገር ብትሆንም ቅሉ፤ ከወንዙ ለዘመናት አንዳችም ጥቅም ጠብ ሳይልላት ትውልዶችን በበይ ተመልካችነት ተሻግራለች፡፡ ዓባይን እንዳሻቸው ሲበሉትም ሆነ ሲጠጡት የኖሩት ግብፆች ናቸው፡፡

እናም ግብፆች በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን በተለያዩ መንገዶች ስትጋፋ መኖሯ አይታበይም፡፡ ምንም እንኳን በታሪካችን ዓባይን ለመገደብ የተነሳ ትውልድ ኖሮ በግብፅ እምቢተኝነት ሳቢያ ከልማት ባይስተጓጎልም፤ በእጅ አዙር የሚደረጉ ጥረቶችን ታመክን እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

በወቅቱ እንደ ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግብፃውያን፤ እንኳንስ ዓባይን መገደብ ቀርቶ ስለ አባይ ማሰብ እንዳንችል ጉዳዩን በእሾህ ማጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ታዲያ ጊዜያት አልፈው ጊዜያት ሲተኩ ያንን እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተረቀቀን ያረጀ ያፈጀና ኢ- ፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ኢ- ሞራላዊ ህግን በመቀየር ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የውሃ ህግ ለመደንገግ የሀገራችን ድርሻ የአንበሳው ያህል ነው፡፡ ምስጋና ለገዥው ፓርቲና እርሱ ለሚመራው መንግስት ይሁንና ዛሬ እናም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አጀማመር የዚህ እልህ አስጨራሽ ጥረት ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይሁንና ሀገራችን ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ካላት ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት ግዕፆች ገና ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡትን ሃሳብ መተማመንን ለመፍጠር ስትል ብቻ በሆደ ሰፊነት ተቀብላዋለች። ሆኖም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለግብፅና ለሚዲያዎቿ ቋሚ አጀንዳቸው ከመሆን አላመለጠም። ‘ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ መገደብ ጀመረች፤ የግብፅ  ህዝብ  በውሃ እጦት ሊቸገር ጉሮሮው ሊዘጋ ነው’ በሚል በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ሰፊ ክፍተት እንደተፈጠረ ለማስመሰል ተንቀሳቀሰዋል። እናም ከግንባታው  መጀመር  ጋር ተያይዞ  የግብፅ ጩኸት አስካሁን መቋጫ አላገኘም።

በአንፃሩ ሀገራችን ዋነኛ አጀንዳዋን ድህነትን ማጥፋት አድርጋ እየሠራች ነው። የህዳሴው  ግድብ የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ደጋግማ ገልፃለች። ፕሮጀክቱ የግብፅ ሕዝብን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን በተለያየ መልክ ለግብጻውያን ወንድሞች ለማስገንዘብ ያልተቆጠበ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርጋለች። ይሁንና በግብፅ በኩል በየጊዜው የተለያዩ ግንባታውን ላለመቀበል ምክንያት ይሆኑኛል ያለቻቸውን ሃሳቦች እያቀረበች እስካሁን ድረስ ወደ ትክክለኛው መስመር መምጣት አልቻለችም።

ኢትዮጵያ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትል ከግብፅና ከሱዳን ታላቁ  የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ በርካታ ስብሰባዎችን አካሂዳለች። ግድቡ ጉዳት እንደሌለው ከሱዳንና ግብፅ ጋር ለመተማመን የሚያስችሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች ቀርበው ‘ጉዳት ያደርስብናል’ የሚሉት ግብፃውያንም ሆኑ የግድቡን ጠቀሜታ የተረዳችው ሱዳን የተለያዩ ሃሳቦችን አንሸራሽረዋል። ግብፆች ግን አሁንም ከቅኝ ግዛት ውሎች አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት የፈለጉ አይመስልም። እናም እንደ ትናንቱ ዛሬም ሀገራችን ግድቡን እንዳትገነባ የቻሉትን ሁሉ ከማድረግ የቦዘኑ አይመስለኝም። ስውር እጃቸውንም ከመዘርጋት ወደ ኋላ አላሉም።

እንደሚታወቀው የቀደሙት የግብፅ መንግሥታትም ኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ  አግኝታ በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት እንዳታካሂድ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ኖረዋል። በርካታ አለም አቀፍ  የልማት አጋሮች ፊታቸውን ከኢትዮጵያ እንዲያዞሩ አድርጋለች። እርግጥ ባለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ልማትንና ሰላምን የሚያሰፍን አመራር ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ዘመናት ተቆጥረዋል። የህዳሴው ግድብ ይጀመራል በተባለ ማግስት በተለያዩ አገራት የሚኖሩ  ዲፕሎማቶቿን በመጠቀምኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳታገኝ  ለማድረግ ተንቀሳቅሳለች።

ከዚህ አንፃር አልተሳካላትም ማለት ባይቻልም ግድቡ እንዳይገነባ ማድረግ ግን  አልቻለችም። ታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታው ገንዘብ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ ህዝብ  ስለሆነ ግድቡ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ አቅም የሚገነባ በመሆኑ ለዘመናት የተጠቀሙበት ስልት እንዳላዋጣቸው በመገነዘባቸው ወደ ድርድር መምጣት ግድ ሆኖባቸው ቢመጡም በድርድሩ ውጤታማነት ላይ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ አልቻሉም። 

በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ  በተያዩ ወቅቶች የተደረገው  ውይይት  ላይ መግባባት ሳይደረስባቸው ለሌላ ጊዜ የሚተላለፉበት ምስጢርም ይኸው ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ከሶስቱም ሀገራት የተውጣጣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያላቸው ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ማግስት በተካሄዱና ሀገራቱ በተስማሙበት መልኩ ጥናት አካሂዶ ውጤቱን አቅርቧል። ቡድኑ በዘርፉ በቂ ልምድና  እውቀት ያለው ሲሆን፤  የህዳሴው  ግድብ  በተገቢው  መንገድ  በማጥናት  ያገኘውን  ውጤት ለአገራቱ አስረክቧል። መፈጸም አለባቸው ያላቸውን አስተያየቶችንም አቅርቧል።

ግና በወቅቱ ከሶስቱ ሀገራት የሚጠበቀው ነገር የቀረበውን ሪፖርት አይቶ መፈጸም ሆኖ ሳለ፤ ግብፅ ግን ወትሮም ‘የውሃ ድርሻዬ ሊነካ አይገባም’ በሚል አሮጌ አስተሳሰብ የምትመራ በመሆኗ እንደገና ወደ ኋላ መጎተት መርጣለች። እናም ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በግልፅ በሶስቱ ሀገራት ኤክስፐርቶች ተጠንቶና ሪፖርቱም ጠረጴዛዋ ላይ ሳለ፤ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድን ይረጋገጥልኝ ስትል ሃሳብ አቀረበች። የኢትዮጵያ መንግስትም መተማመንን ለመፍጠር ሲል ብቻ አሁንም እሽታውን ሰጠ። ያም ሆኖ ግን አሁንም በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ዓይነት የተለያዩ የማዘግያ መንገዶች ግብፅ ‘የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ’ እያለች ነው።

በእኔ እምነት እነዚህ ሁሉ የግብፅ ግልፅና ስውር እጆች ዓላማቸው ሀገራችን ግድቡን እንዳትገነባ ማድረግ ነው። ምንም እንኳን የግብፅ መንግስት በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ግድቡን በመቃወም የሚሰጧቸውን ሃሳቦች እንኳን ሳይቀር ‘የመንግስታችን አቋም አይደለም’ እስከሚል አስገራሚ ዲፕሎማሲዎች ድረስ የደረሰ ቢሆንም፤ በተግባር ግን መተማመኛ በመፍጠሪያ ውይይቱ ወቅት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የእነዚህኑ ባለስልጣናት ሃሳቦችን ያራምዳል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እንዲህ ዓይነቱ ስውር መንገድ ጊዜ እስከሚገኝ ድረስ በውይይት የመግፋትና አመቺ ሁናቴ ሲፈጠር ደግሞ ግድቡ እንዳይሰራ ሀገራችን ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ‘ቤንዚን ለመጨመር’ መጠበቅ ነው።

እርግጥ ግብፆች በስውር የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ ያልተንቀሳቀሱበት ወቅት የለም። በናስር ወቅት ራሱን “ኦብነግ” የተሰኘ ቡድንን በማደራጀት ሀገራችን ከተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀምና ዓባይን እንዳትገድብ ጥረዋል። በቅርብ ጊዜም በሙባረክ የስልጣን ዘመን ወቅት የኤርትራን መንግስት እንደ መሳሪያ በመጠቀም የሀገራችንን አሸባሪዎችንና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን በማስታጠቅ ብርቱ ጥረት አድርጓል—ባይሳካለትም። በዘመነ መሐመድ ሙርሲም ወቅት ቢሆን በኤርትራ መንግስት አመቻችነት እንደ ግንቦት ሰባትና ኦነግ ዓይነት አሸባሪዎችን በመደገፍ ትርምስ ለመፍጠር ሞክረዋል። በፕሬዚዳንት አል-ሲሲ ወቅትም እነዚህ የትርምስ ስልቶች ገቢራዊ አለመሆናቸውን ማንም እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። በእኔ እምነት ግን አሁንም የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚመሩት እነ ግንቦት ሰባትና ኦነግ እንዲሁም የኤርትራ መንግስት በቀጥታ ዳረጎት የሚሰጣቸው አሸባሪዎች በመሆናቸው፤ ዛሬም ቢሆን ግብፆች በአንድ በኩል ድርድር እያደረጉ በሌላ በኩል ደግሞ ላላመረጋጋታችን ምክንያት እንደሚሆኑ መናገር የሚከብደኝ አይሆንም።  

ይሁንና ለግብፅ ስውርና ግልፅ እጅ በመንግስት በኩል ሊሰራ የሚችል ነገር እንደሚኖር ብገነዘብም፤ ዋነኛው መፍትሔ ግን የውስጥ ተጋላጭነታችንን በመቀነስ ላይ አትኩሮ መስራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የውስጥ ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ ዋነኛው መፍትሔ የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ትግል አጠናክሮ መቀጠል ነው። የፀረ-ድህነቱን ዘመቻ በሚፈለገው መጠን ማሳካት ከተቻለ ለብጥብጥና ለሁከት የሚነሳ ዜጋ ሊኖር አይችልም። ይህ ዕውን ከሆነም በግብፅም ይሁን በሌላ ወገን ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን መድፈን ይቻላል። እናም መንግስት አሁን የጀመረውን ድህነትን የመቀነስ ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል እላለሁ። ያኔም የግብፅም ሆነ የሌላው ወገን ግልፅና ስውር እጆች መሰብሰባቸው አይቀሬ ይሆናል።