ፌስ ቡኩ  ይፍረደን

የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር የዘመናት ጥያቄ ምሉዕ በኩለሄ እንኳ ባይሆን በወሳኝ መልኩ በ1983 ማግስት ምላሽ ያገኘ መሆኑ አያከራክርም ። ምሉዕ በኩለሄ ስላለመሆኑም አልፎ አልፎ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና የተለየ ማንነት አለን ብለው የሚያምኑ ብሄሮች በየአካባቢው የሚያነሷቸውን ህጋዊና  ደሞክራሲያዊ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች አስረጅ ናቸው ።ይሁን እንጂ እኒህን ጥያቄዎችና አቤቱታዎች መንግስት ተቀብሎ ሲፈታ የቆየ ቢሆንም አንዳንዶቹ ወደግጭት አምርተው ደም ማፋሰሳቸው እሙን ነው።

ባለፉት የዴሞክራሲና የልማት አመታት የአገራችን ህዝቦች የምርጫ ተሳትፎ በየምርጫ ዘመኑ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ ቢሆንም በምርጫ ያልተሳካላቸው ሃይሎች የምርጫ ሂደትን ጨምሮ ከላይ በተመለከተው አግባብ የማንነትና መሰል ጥያቄዎች በተነሱ ጊዜ አጀንዳውን በመጠምዘዝ ወደቀለም አብዮት የመለወጥ ሙከራ ሲያደርጉ የቆዩ መሆኑም ይታወቃል ። ይህ ትርክትም በኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ከመልካም አስተዳደር እና ማንነት ጋር የተነሱ ጥያቄዎችን በመጠምዘዝ ለቀለም አብዮት እንዴት ሲያመቻምቹ እንደነበር ወደኋላ ተመልሶ በማስታወስ መረጃ በመስጠት ስለሃገር ሰላምና ልማት ቅኝታችነ በምን አግባብ መሆን እንዳለበት መጠነኛ ግንዛቤ እንዲሰጥ ታስቦ የተሰናዳ ነው ።

በተመሳሳይ መልኩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከነችግራቸውም ቢሆን በየወቅቱ እያደገ የመጣ መሆኑና በዚህም የመድበለ ፓርቲ ስርአቱ በመጠናከር ላይ የሚገኝ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። 

ወደ ጉዳያችን ሰምጠን ከመግባታችን አስቀድሞ ግን  ምንም እንኳ ጥቂት ቢሆኑም የህግ የበላይነትና የምርጫ ህጎችን አክብረው ለመንቀሳቀስ  እና የስልጣን ባለቤት ለመሆን የሚሹ ፓርቲዎች መኖራቸውን የዘነጋን እንዳልሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል።ይልቁንም በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመስራት የቆረጡ ፓርቲዎች መኖራቸው ለተጀመረው የመድበለ ፓርቲ ስርአት መጠናከርና የኢትዮጵያ ህዳሴ የፖለቲካ ቀጣይነት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ማስታወስና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።  

 

 

ሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ስትነሳ እና የህልውናችን አጀንዳ ነው ብላ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ስታደርግ የግጭትና የብጥብጥ ምንጭ የነበረውን ድህነትና ኋላቀርነት ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ የሚያስችሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ፕሮግራሞች በመንደፍ መሆኑን መጀመሪያ እና በዋናነት ስለአጀንዳችን ማስመር ያስፈልጋል። የዴሞክራሲ ጥያቄ በአገራችን ቁልፍ የትግል አጀንዳዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ማሳያው አሁንም ለቀለም አብዮት ማመቻቺያ የሚሆኑት ጥላሸቶች እዚሁ አጀንዳ ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ነው።

ይህ ስርአት ደግሞ በየአጋጣሚው ለማመቻመቺያ እንደሚለደፍበት ጭቃ ሳይሆን የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተለያየ ወቅት በተደራጀና ባልተደረጃ መልኩ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈሉበት ነው።ስለሆነም ከድል ማግስት ዜጎች ተነፍጓቸው የቆዩትን የመናገር፣ የመጻፍ የመሰብሰብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና ከቦታ ቦታ በነጻነት የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የህግ ጥበቃና እውቅና የተሰጣቸው ከመሆናቸውም በላይ የዴሞክራሲ ባህልና እሴት ግንባታ በዝቅተኛ ደረጃ ይገኝ ስለነበር ይህንኑ ክፍተት ለመሙላትና አስተሳሰቡ ስር እንዲሰድ የተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋማት ተደራጅተው ወደ ስራቸውን በመስራት ላይ ናቸው።

በአንፃሩ ተቃዋሚዎች በማንኛውም አማራጭ ይህንን ግስጋሴ ለመግታትና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ስርአቱ የወለዳቸውን  እና ቅሬታዎችን በአግባቡ ሊያስተናግዱ በሚችሉ ተቋማት ላይ  ሳይቀር አዳዲስ አጀንዳ በመፈብረክና በህጋዊ መንገድ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመጠምዘዝ የአደባባይ አብዮትን ሲያምጡ ስለመክረማቸው ሰሞንኛ የነበሩትና ይልቁንም መልስ የተሰጣቸውን እና መልስ ሊያገኙ የሚችሉባቸው ህጋዊ አግባቦችን ሁሉ በማራገብና በመጠምዘዝ የተከናወኑት ባለቤት አልባ ሰልፎች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

ሰሞንኛ የነበሩት ጥምዘዛዎች አስቀድመው የተሞከሩና የከሸፉ ስለመሆናቸው ወደፊትም ዜሮ ድምር አስተሳሰብ እስካልመከነና ህዝቡ እስካልነቃ ድረስ የመቀጠላቸው እድል የሰፋ መሆኑን ለማጠየቅ ወደኋላ ተመልሰን በተለይ ለቀለም አብዮት ምቹ መደላድል እንደሆኑ ጠበብቶቹ ከመሰከሩላቸው ምርጫዎች አኳያ መፈተሽ ግድ ይለናል።

ስለሆነም ህገ-መንግስታዊውን ስርዓት አጥብቀው የሚጠሉት እና ስልጣንን በአቋራጭ የሚሹ አክራሪ ፅንፈኞች በተለያየ ምክንያት ከስርዓቱ ጋር የተቃቃረውን በሙሉ ከጎናቸው በማሰለፍ የተንቀሳቀሱበት ምርጫ 97 ማስታወስ ስለፍተሻችን ተገቢ ይሆናል ፡፡

በብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ የፖለቲካ ስርዓት ኢትዮጵያን የሚያጠፋና እያጠፋ ያለ ነው ብለው የሚያምኑት ፅንፍ የወጣ የትምክህት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በአንድ በኩል፤ አገሪቱን ለመበታተንና በየብሄራቸው የጠባብ ቡድናቸውን ለማረጋገጥ ከተቻለ በሀገር አቀፍ ደረጃም አምባገነንነታቸውን ለመጫን የሚያልሙ ጠባቦች በሌላ በኩል ለመጨረሻው ፍልሚያ የተሰለፉበት የምርጫ 97 ሃይሎች ከሰሞንኞቹ በስተጀርባ የነበሩት ዋነኛ ሃይሎችም መሆናቸው ነው ወደኋላ ልንመለስ ያስገደደን ፡፡

ምርጫ 97 ላይ እነዚህ እርስ በርስ ቢነካኩ እሳት የሚጭሩ ፅንፍና ፅንፍ የቆሙ ተቃራኒ አቋም ያላቸው ኃይሎች ሕገ-መንግስታዊውን ስርዓት በመናድ የጋራ ተልዕኮ ጎን ለጎን ተሰልፈው የነበረ መሆኑ ይታወሳል ፡፡ ባለፈው ስርአት ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ አመራር የተሳተፉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የጥቅም ተጋሪ የነበሩ ሁሉ በነዚህ ዙሪያ ተሰባስበው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ ፡፡ የተሃድሶው ሂደት በየደረጃው ያንጠባጠባቸውና በተለያየ ምክንያት ከስርአቱ ጋር ሲሰሩ ቆይተው መንገድ ላይ የቀሩትና ተገፍተው የወጡትም የዚሁ ጎራ አጃቢ ሆነው መቀላቀላቸው ይታወሳል ፡፡ እንደዚህ እያለ የስብስቡን ቁጥር ያሰፋው የተቃዋሚ ጎራ  እጅጉን ነፃ በሆነው ዴሞክራሲያዊ የምርጫ መድረክ ህገ-ወጥነትንና ሕጋዊነትን ያደባለቀ ቅስቀሳቸውን በሰፊው ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በሁሉም ዘንድ እንደተስተዋለው የቅስቀሳቸው መነሻም መድረሻም ገዥውን ፓርቲ ማብጠልጠል እና ማብጠልጠል ብቻ ነበር፡፡ዛሬም ያለውና ከሰሞንኞቹ ግርግሮች በስተጀርባ ያየነው ይህንኑ አይነት በመሆኑ ነው ነገርየው የቀለም አብዮት ነው ብለን ለመደምደም ያስቻለን። ልክ  እንደ 97ቱ  በአዲሱ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መብትና ጥቅሙ የተጠበቀለት ምልአተ ህዝብ እንዳለ ሆኖ በየህብረተሰብ ክፍሉ የየራሱ ቅሬታና ብሶት የነበረው ዛሬም ያለ መሆኑ ሌላኛው የመደምደሚያችን መነሻ ነው፡፡

በወቅቱ በተሃድሶ የተቀመጠውን አርሶ አደሩን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ማስገባትና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማስቻል ምርታማነቱን አሳድጎ ፍላጎቱ እንዲያድግ የማድረግ አቅጣጫን ለማስፈፀም ሲባል ያለፈቃዱና ሳያምንበት ለማሰማራት በአንዳንድ አካባቢዎች የተደረገው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አዝማሚያ ያስከፋው አርሶ አደር ቁጥር ቀላል ያልነበረ መሆኑና ዛሬም አለመታረሙ ለሙከራው ምቹ መደላድል ፈጥሯል፡፡

በየአካባቢው የሚታዩ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተጨምረው ለቅሬታ የተጋለጠው የገጠር እና የከተማ አካባቢ ሕዝብ ትንሽ አለመሆኑም ልክ እንደ 97ቱ እድል የፈጠረላቸው እና አሁንም በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ችግሮች በፍጥነትና ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ካልተሄደ ግና እድላቸው እንደማይሟጠጥ አያከራክርም፡፡  

ሌላውና አሁንም እንደ 97ቱ ምክንያት ስለመሆኑ ገዢው ፓርቲ ባደረገው ግምገማ ያረጋገጠው የትምክህትና የጥበት ኃይሎች መናኸሪያ ሆኖ የቆየው የትምህርት ስርዓት እና የትምህርት ቤት አካባቢ ወጣቱን እንኳን በችግሮች ትንታኔ አፈታት ላይ በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ ማድረግ ቀርቶ ወደ ተንጋደደ አቅጣጫ እንዲያመራ ሲገፋ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የብሶተኝነት ስሜቱ እንዲባባስ ሲያደርግ የቆየ መሆኑና፤ የስራ አጥነት ችግሩም ሌላ የቅሬታ ዓይነተኛ ምንጭ የነበረ መሆኑ የሚያስማማና በቶሎ እዚህመ ጋር ያለው እሳት ካልጠፋ የአብዮተኞቹን እድል ማስፋት ይሆናል፡፡

እነዚህ በርካታ ችግሮች ድርጅቱ በተሃድሶ በገመገመው የማንጎላጀት ዓመታት የተፈጠሩና እየተከማቹ የመጡ ናቸው፡፡ በጥበትና በትምክህት ፅንፎች የተወጠረው የተቃውሞ ጎራ እነዚህን ቅሬታዎች ማባባስ፣ ማራገብና ማግለብለብ ዓይነተኛ ተግባሩ መሆኑ ላይ በተለያየ ቂምና ቁርሾ የተቀላቀሉትን በርካታ ግለሰቦች፣ በተለያየ ቅያሜና ብሶት ከስርዓቱ ጋር የተራራቁ ወጣቶችን አካቶና ከምንጊዜውም በላይ ቁጥሩን አስፍቶ የተሰማራው ተቃዋሚው ጎራ ዛሬም የተገለጠው  በተመሳሳይ መልከ መሆኑ ነው ነገርዬው የቀለም አብዮት ነው እንድንል ያስገደደን ።

ከሰሞኑ ተደርገው በነበሩት ባለቤት አልባ ሰልፎችና ከጀርባቸው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲራገቡ የነበሩ አስተሳሰቦችን እንዳየነው በምርጫ 97 ልክ  ብሶት መቀስቀስ፣ ስሜት ማጋጋል እና ሕዝብን ለሁከትና ለብጥብጥ ማነሳሳት መሆኑም ነው ሌላኛው የሙከራው ማጠየቂያ የሆነን፡፡ ውዥንብር መንዛት፣ የመንግስት ህልውና ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ የሚጋብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መፈፀም፣ የዘረኝነት ጉትጎታዎች ወዘተ በምርጫ 97  ቅስቀሳ ወቅት በታየው ልክ ሰሞኑን መታየቱም ተጨማሪው እና የድምዳሜያችንን ትክክለኝነት የሚያጠይቅልን አስረጅ ነው፡፡   

ጠባብ ብሄርተኞችም የለየላቸው የትምክህት ሃይሎችም በተለያዩ ፖርቲዎች የተወከሉበት ምርጫ 2002ትም ሌላኛው አስረጅ ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ መቀጠል የሚችሉት በአንድ ቋንቋና ባህል ስር ብቻ ነው ሌላው ሁሉ መደፍጠጥ አለበት” ከሚሉ ትምክህተኞች ይህንን ወይም ያኛውን ብሄር ወክለው “እኔ ብቻ ነኝ” እስከሚሉትና ሌላ የአፈና አገዛዝን በጠባብነት መንገድ ሕዝቦች ላይ ለመጫን እስከቋመጡት መንደርተኞች ድረስ በተሳተፉት ልክ ሰሞንኛ በነበሩት ግርግሮች ውስጥም አንድ መስለው ስለመቀላቀላቸው ፌስ ቡኩ ይዳኘን። ስለሆነም በሃገሪቱ ላይ የዴሞክራሲያዊ ስርአትን ከላይ በተመለከቱት አግባብ ለድርድር የምናበቃና በመንግስትም በኩል የህዝብ ቅሬታን በአፋጣኝ እየመለሱ መሄድ ካልተቻለ አደጋው ከባድና ምናልባትም ሃገሪቱን ወደኋላ ሞቶ አማታቶች የሚመልስ ሊሆን እንደሚችል ልብ ማለት ያሻል።

 

ማጠቃለያ

ፌስ ቡኩ ይፍረደን (ዮናስ)

እየተገነባ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርአት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ መሆኑን ያወሳል።የህዝብ ጥቅም ሁሉአቀፍ በሆነ መልክ እንዲረጋገጥም ማስቻያ የሆኑ ህግጋትን እና ተቋማትን ይጠቅሳል።ያም ሆኖ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሁሉንም ማርካት ባይቻልም ቅሬታዎች የሚስተናገዱባቸው ህጋዊና ሰላማዊ አግባቦች መኖራቸው ሊዘነጉ እንደማይገባና ከተዘነጉ ግን የአደጋውን ስፋትና ጥልቀት የተለያዩ አስረጂዎች በመጥቀስ ያስጠነቅቃል።ስለማስጠንቀቂያው ደግሞ ከምርጫ 2002 እና ከምርጫ 97 በስተጀርባ የነበሩ የቀለም አብዮት ሙከራዎችን ከሰሞኑ ሲነሱ ከነበሩ አጀንዳዎች መፈክሮችና አሰላለፎች ጋር ያላቸውን ተመሳሳይነት በማሳያነት ይጠቅስና በተለይም የጥበቱን እና የትምክህቱን አጀንዳና የጠላቴ ጠላት ግንኙነት ዛሬም ስለመደገሙ ፍርዱን ለፌስ ቡክ ሰበካና ሰባኪዎች በመተው የአደገኛነቱን ልክ በማሳየት ለህዝብና መንግስት ድርሻቸውን እንዲወጡ ያሳስባል።