ወጣቱን የልማት ኃይል ማድረግ ካልተቻለ የሁከት ኃይል መሆኑን ማስቀረት አይቻልም!

ያለፈውን ዓመት የሸኘነው በደብዛዛው ነበር። የመደብዘዙ ምክንያት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተወሰኑ ከተሞች ተቀስቅሶ ከነበረው ሁከት ጋር በተያያዘ የወጣቶች ህይወት በመጥፋቱ፤ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረው በነበሩ ተቋማት ላይ በደረሰ ውድመት በርካቶች የስራ ፈትነት እጣ ከፊታቸው በመደቀኑ፤ ማህበራዊ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማትና ፋሲሊቲዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው ምክንያት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዓመቱ ሊያበቃ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉ የአዲሱን ዓመት አቀባበልና አሸኛኘት ደብዘዝ አድርጎታል።

እነዚህ በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተቀሰቅሰው የነበሩ አውዳሚ ሁከቶች አሁን በርደው ህዝቡ ወደተረጋጋ ህይወቱ ተመልሷል። በሁከቱ ህይወታቸውን ያጡ ወጣቶችና የሰላም አስከባሪ አባላት ቤተሰቦችና ወዳጆች ግን ገና የሃዘን ሳግ አልለቀቃቸውም። በእሳት የወደመው የሕዝብና የግለሰቦች ንብረት ገና አመዱ ተግፎ አላበቃም። በዚህ ወደአመድነት በተቀየረ ንብረት ላይ ህይወታቸውን መስርተው የነበሩ ዜጎች መጪው ጊዜ እንደጨለመባቸው ነው።  በእነዚህ ሃብት በወደመባቸው አካባቢዎች የተፈጠረው ስጋት ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረጋቸው ባለሃብት ኢንቨስተሮችም ጉዳይ በአካባቢዎቹ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖም እንዲሁ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ይህ አስከፊ ሁኔታ የፈጠረው አስፈሪ ቅዠትም ገና አልገፈፈም። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዘረኝነት ጥላቻ በተፈጸሙ ድርጊቶች ሳቢያ የተፈጠረው መከፋትና ቁጭትም እንዲሁ አልገፈፈም። የዚህ ፀያፍ የዘረኝነት ድርጊት  ፈፃሚዎች ካሰከራቸው የጥላቻ ስሜት ሲባንኑ ህሊናቸው በወቀሳ እንደሚወቅራቸው ግልፅ ነው።

ያም ሆነ ይህ ይህ፤ አስከፊ አጋጣሚ ያለፈ ይመስላል። ከአሁን በኋላ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዳግም እንዳይቀሰቀስ ማድረግ ለሚያስችል ተግባር ነው። ይህ ደግሞ የሁከቱን እድገት ሂደት  (metamorphosis) ተንትኖ መረዳትን እንዲሁም ማስረዳትን ይሻል። በዚህ ረገድ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረግ ግልጽ ውይይት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። በተለይ በቀላሉ ስሜቱ የሚቀሰቀሰውንና ግብታዊ ርምጃ ለመወሰድ ቅርብ የሆነውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ቅሬታውንና ፍላጎቱን አውጥቶ እንዲናገር፤ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጮችንም በማቅረበ እንዲሳተፍ ማድረግ የሚያስችል ግልጽ ውይይት ማካሄድ ወይም አለማካሄድ ለዘለቄታው ሁከት ሊቀሰቀስ የሚችልበትን መንገድ የማጥበብ ወይም ያለማጥበብ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ከወጣቱ ጋር በሚካሄዱ ውይይቶች ወጣቱ ብሩህ ተሰፋ የሚታየውና የዘላቂ ህይወቱ ዋስትና  የተረጋገጠ ከሆነ አገሩን መገንባት የሚችል እምቅ አቅም ያለው እንጂ የሌሎች መናጆ  ሊሆን እንደማይችል ታሳቢ በማድረግ የወዲያኛው ወይም የወዲህኛው ቡድን ደጋፊ ነበርክ ከሚል ፍረጃ የጸዱ መሆን አለባቸው። ወጣቱ ከዚህ ቀደም የፈጸመው ድርጊት ወይም የተሰባሰበበት ጎራ ምንም ይሁን ምን በቀጣይ ሊሆን በሚገባው ላይ ባተኮረ መንፈስ መካሄድ አለበት። ፀረ ሰላም፤ ፀረ ልማት፤ የውጭ ተላላኪ፤ የአሸባሪ ተቀጥላ ወዘተ. የሚሉ ፍረጃዎች ወጣቱ መገፋት እንዲሰማውና እልህ ውስጥ እንዲገባ ከማድረግ ያለፈ የትም አያደርስም። ምክንያቱም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶች ከዚህ በፊት የፈፀሟቸው ወይም ያደሉባቸው እንቅስቃሴዎች ጥፋት መሆናቸውን አውቀው ጥፋት ለመፈፀም ሆን ብለው የገቡባቸው ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተትነቱ የሚያይል ሆኖ ይታየኛል። ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ፤ በሁከቱ ላይ የተሳተፉና በተለያየ መንገድ ሁከቱን የደገፉ ወጣቶች አገራቸው በእርስ በርስ ግጭት እንድትበታተን፤ እንድትወድም፤ የዓለም ውራ እንድትሆን፤ ድህነት፤ በሽታ፤ መሃይምነት፤ ስደት የገጽታዋ መገለጫ እንዲሆኑ . . . የማድረግ ፍላጎት የላቸውም ከሚል እምነት መነሳት ተገቢ ቅድመ ሁኔታ ነው። በዚህ መንፈስ የሚካሄድ የውይይት መድረክ ወጣቱ ቅሬታዎቹንና ፍላጎቶቹን መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉ በሚል ተስፋ እንዲናገር፤ የመፍትሄውም አካል እንዲሆን ማድረግ ያስችላል።

አሁን ደግሞ አጠቃላይ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎችና በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የወጣቱ ሚና ምን መሆን አለበት የሚለውን እንመለከት፤ እንግዲህ ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ አጠቃላይ የአገሪቱ ምርትና አገልገሎት እንዲጨምር ያደረገ፤ ማለትም ተጨማሪ ሃብት መፍጠር ያስቻለ እድገት ካፒታልንና መሳሪያን ብቻ በግብአትነት በመጠቀም የተገኘ አይደለም። የሰው ኃይልም ተጠቅሟል። በተለይ ለእድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የግብርናው ዘርፍ፤ እንዲሁም የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ተጠቅሟል። የኢንዱስትሪ ዘረፉም እንዲሁ፤ በዚህ ተጨማሪ ሃብት በመፍጠር ሂደት ላይ የተሳተፈ ሰፊ የሰው ኃይል የእድገቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሆኗል። በተለይ በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበው እድገት የተፈጠረውን ተጨማሪ የስራ እድልም ያመለክታል። በዚህ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ባስቻለ ሰፊ የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው።

የኢኮኖሚው እድገት ከፈጠረው በተቀጣሪነት የተገኘ የስራ እድል በተጨማሪ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የስራ ፈጠራ የአመለካከት ለውጥ ዘመቻ በርካታ ዜጎች ከመንግሥት የገንዘብ ብድር፤ የሞያና የምክር አገልግሎት፤ የመስሪያና የማሳያ ቦታ ድጋፍ እያገኙ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በግልና በቡድን የስራ እድል አግኝተዋል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅድ የትግበራ ዓመታት ብቻ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። በገጠር፤ ቀደም ሲል ለእርሻ ሥራ በማይሆኑ ተዳፋት መሬቶች ላይ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ተግባራት የፈጠሩት ተጨማሪ ቦታ ለበርካታ ወጣቶች ከተፈጥሮ አካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የንብ ማነብ፤ ከብት የማደለብና መሰል ሥራዎች ላይ የመሰማራት እድል ፈጥሮላቸዋል።

ይህ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ የስራ እድል ግን በአገሪቱ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረው ድህነት ከፈጠረው የስራ ፈላጊ ቁጥር አንጻር ሲታይ ከአናቱ የመጨለፍ ያህል የሚቆጠር ነው። በሌላ በኩል፤ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ  ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ይህ ሁኔታ የሕዝቡ አብላጫ ክፍል ወጣት መሆኑን ያመለከታል። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተወለደ አዲስ ትውልድ። ይህ በገጠርም በከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚታይ እውነታ ነው።

በገጠር ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረው 1 ነጥብ 2 ሄክታር ገደማ አማካይ አገራዊ የአባወራ የመሬት ይዞታ ግን አልተለወጠም። በዚያችው አንድ ሄክታር መሬት ላይ ጥገኛ የሆነው የቤተሰብ አባል ቁጥር ግን ቢያንስ እጥፍ ጨምሯል። አሁን እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ የሆኑ ተጨማሪ መሬት የሚፈልጉ የአርሶ አደር ልጆች ቁጥር መሬት ይዞ ካለው አርሶ አደር ጋር ሲነጻጸር ይበልጥ እንደሆን እንጂ አያንስም። ለዚህ የመሬት ፈላጊ ሊሸነሸን የሚችል በቂ ተጨማሪ ትርፍ መሬት ግን የለም።

እርግጥ፤ በገጠር ያለው ሁኔታ ከሃያ ዓመታት በፊት ከነበረው ተቀይሯል። አሁን ትምህርት በገጠር መንደሮች ድረስ ዘልቋል። የአርሶ አደሩ ልጆች ቢያንስ እስከአራተኛ ክፍል ተምረዋል። እስከ 8ኛና 10ኛ ክፍል የተማሩ የአርሶ አደር ልጆች በርካቶች ናቸው። ከቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛና ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የአርሶ አደር ልጆች ቁጥርም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። እነዚህ ቀለም የቀመሱና በአግባቡ የሰለጠኑ/የተማሩ የአርሶ አደር ልጆች ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የግብርና ስራ ላይ መሰማራት አይፈልጉም። ወይም አርሶ አደር እንሁን ቢሉም በቂ መሬት አያገኙም። እናም አብዛኞቹ የአርሶ አደር ልጆች ከተማ ሄደው ሰርተው መኖር የሚፈልጉ ናቸው።

ይህ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የጨመረው በከተማ የመኖር ፍላጎት ያለው መነሻው ገጠር የሆነ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ በከተማ ከተፈጠረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዲስ ትውልድ ጋር ተዳምሮ የከተማው የኢኮኖሚ እድገት የሚፈጥረው የስራ እድል ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የሆነበትን ሁኔታ ተፈጥሯል። እናም በከተማም ያለው የስራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ጊዜ ያለውን ስራ አጥ ቀደም ሲል ከነበረው የሚለየው አንድ ነገር አለ። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ከቴክኒክና ሞያ ተቋማት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቆ የወጣ መሆኑ ነው።

ቀደም ሲል እነደተገለጸው ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገትና የአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ፈጠራ ለበርካታ ዜጎች በተለየ ለወጣቶች የስራ እድል ያስገኘ ቢሆንም፤ ከላይ የተገለጠውን ተጨማሪ የሰው ኃይል ማስተናገድ ግን አልቻለም። ይህ ሁኔታ የሚያስብ አእምሮ፣ የሚሰራ አካል ያለውንና የአገሪቱን እድገት ወደፊት ገፍቶ ለራሱም መጠቀም የሚችለውን እምቅ የሰው ሃብት መጠቀም ያልተቻለበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም እድገቱ መሆን ከሚችለው በታች እያዘገመ እንደሆነ አመላካች ነው። የአገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድገው ካፒታልና ማሽን ሳይሆን የሚፈጥር አእምሮና ማሽን ማንቀሳቀስ የሚችል አካላዊ ብቃት ያለው ሰው ነው። ያለሰው ኃይል የኢኮኖሚ እድገት የሚባል ነገር የለም።

የሰው ኃይልን አለመጠቀም የእድገት አቅም መሆን ይችሉ የነበሩ ዜጎች ሸክም ሆነው የእድገት እንቅፋት የሚሆኑበትን፤ ራሳቸውን ችለው መኖር ባለመቻላቸው ወደተስፋ መቁረጥ የገቡ፤ መጪው ዘመን የደበዘዘባቸው፤ ከዚህ ተስፋ መቁረጥና የደበዘዘ መጪ ግዜ የሚያወጣቸውን ማንኛውንም አማራጭ (አደገኛውን አማራጮች ጭምር) የሚመርጡና የሚከተሉ ዜጎች/ ወጣቶች እንዲኖሩም አድርጓል። ይህ ሁኔታ የኢኮኖሚ አቅም መሆን ይችል የነበረውን የሰው ኃይል የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሰላም ስጋት ሰበብ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ አሁን በአገራችን የሚታይ ነባራዊ ሁኔታ ነው። ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት። አለበለዚያ ከምንም በላይ ሰላምና መረጋጋትን የሚሻው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃሉ። ከላይ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ የገለጽኩት በአማራና በኦሮሚያ ያጋጠመው ሁከት ዋነኛ መነሻ ምክንያት ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው።

ይህን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ወጣቱን በፍላጎቶቹ ዙሪያ ማወያያትና የመፍትሄው አካል እንዲሆን ማድረግን ይሻል። መንግሥት ወጣቱ ከተስፋ መቁረጥ ወጥቶ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያሳድግና ራሱንም የሚጠቅም ዜጋ እንዲሆን ለማድረግ በስብሰባዎች ከሚሰጥ ተሰፋ ተሻገሮ ተጨባጭ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ በተለይ ወጣቱ የስራና የእድገት ኃይል እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል በቂ በጀት መመደብን ይጠይቃል። ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ የሚመደብ በጀት እርዳታ ሳይሆን ወጣቱን በመጠቀም ሃብት መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ራሱን ከትርፍ ጋር የሚመልስ ነው። እርግጥ የበጀቱ አመዳደብና አጠቃቀም ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ መሆን ይኖርበታል።

በአጠቃላይ የኢኮኖሚውን እድገት ቀጣይነት ማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን የሚቻለው ወጣቱ የስራ ኃይል ሆኖ እድገቱን መግፋትና ራሱን መጥቀም የሚችልበት፤ በአገሩ ላይ የመኖር ዋስትናው የተረጋገጠበት ሁኔታ ሲኖር ብቻ መሆኑ ታውቆ፤ ለዚህ ርብርብ ሊደረግ ይገባል። ወጣቱን ወደእድገትና የልማት ኃይልነት ለመለወጥ የሚመደብ በጀት ለፍጆታ የሚውል ሳይሆን የሚረባ ካፒታል በመሆኑ መሰሰት  አያስፈልግም። በአንጻሩ፤ ወጣቱን የእድገትና የልማት ኃይል ማድረግ አለመቻል ደግሞ ኢኮኖሚው ማደግ ባለበት መጠን እንዳያድግ ማድረግ ከመሆኑ በተጨማሪ አገሪቱን ማተራመስና ደካማ ማድረግ ለሚፈልጉ ኃይሎች ተቀጣጣይ ሁኔታን ስለሚፈጥር ለአገሪቱም ህልውና አደገኛ ነው። ወጣቱን የልማትና የእድገት ኃይል ማድረግ ካልተቻለ የሁከት ኃይል መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።