ነገረ—“ኢንፍሉዌንዛ”…(ክፍል አንድ)

ይህን ፅሑፍ ለማሰናዳት ምክንያት የሆነኝ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ላይ ያነጣጠረ ረቂቅ ውሳኔን አስመልክቶ መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም ለንባብ ለበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ምላሽ ነው። ሚኒስትሩ ክሪስ ስሚዝ በተባሉ የኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዩች ንዑስ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር መሪነት የተዘጋጀው “HR-2016” የተሰኘውን ረቂቅ ውሳኔን “ረቂቁ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ጊዜ እየጠበቀ የሚወጣ ነው” ብለዋል። 
እርግጥም ሚኒስትሩ ሁኔታውን በትክክል የገለፁት ይመስለኛል። የኢንፍሉዌንዛ ነገር ወቅትና ጊዜን እየጠበቀ የሚከሰት ወረርሽኝ ነው። መረጃዎች እንደሚገልፁት፤ ወረርሽኙ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ ብሎም በአንዳንድ አካባቢዎች በአዲስ መልክ እስከ 11 ዓመቱ ወይም ከዚያ በላይ ቆይቶ ሊቀሰቀስ ይችላል። ምርጫ 97ትን ተከትሎ በእኚሁ ግለሰብ የነበሩበት “HR-2003” የተሰኘ ረቂቅ ተዘጋጅቶ፣ ነገር ግን በመጨረሻው ላይ ሳይፀድቅ መቅረቱን እናስታውሳለን። አሁን ጊዜው 11 ወይም 12 ዓመታት ሳይሆነው የቀረ አይመስለኝም—አዲሱ ረቂቅ በኮንግረሱ ከተዘጋጀ። ይህም ነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” አመቺ ወቅት እየጠበቀ የሚነሳ በሽታ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። 
በእኔ እምነት ነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ህግ ሆኖ ለመፅደቅ በርካታ ደረጃዎችን የሚያልፍ ቢሆንም ቅሉ፤ በኮንግረሱ አባላት ወቅት እየተጠበቀ የሚረቀቀው የውሳኔ ሃሳብ ለኢትዮ-አሜሪካ ዘርፈ ብዙ ጠንካራ ግንኙነት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አላስብም። እናም የነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ”ን ረቂቅ እንደሚከተለው በመመልከት በዋና ዋና ጉዳዩች ላይ የግሌን ሃሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ። በቅድሚያ ግን በሀገራችን ውስጥ ስላለው ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ጉዳይ ማንሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይሀም የሀገራችን መንግስት ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያግዘን ከመሆኑም ባሻገር፤ የኮንግረሱ አባላት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሊገቡ እንደማይችሉ በግልፅ ያመላክታል ብዬ አምናለሁ።  
የኢትዮጵያ መንግስት ተጠሪነቱ ለማን ነው?
የዚህ ጥያቄ ምላሽ ቀላል ይመስለኛል። ምክንያቱም ምላሹ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ በግልፅ የተደነገገ በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው የህዝብ ሉዓላዊነትን አስመልክቶ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 8 ላይ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸው ተደንግጓል። ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዩቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መሆኑም በግልፅ ተጠቅሷል። ይህ ዕውነታም የሀገራችን ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸውን በሚያረጋግጡበት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፏቸው እንዲመራቸው የሚመርጡትን መንግስት የመሾምና የመሻር ስልጣን እንዳላቸው ያረጋግጣል። ይህን ደግሞ ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች እውን አድርገውታል፤ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ይህን የስልጣን ባለቤትነታቸውን ገቢራዊ ያደርጋሉ። በዚህም በየአምስት ዓመቱ የስልጣን ውክልና ኮንትራት በመስጠት የሚመሰርቱት መንግስት ተጠሪነቱ ለእነርሱ ብቻ እንዲሆን ያደርጋሉ። 
እናም የኢፌዴሪ መንግስት ተጠሪነቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ለሀገራችን ህዝብ እንጂ ለማንም አይደለም። በህዝቦች ሙሉ ፈቃድ ዕውን የሆነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አዛዡና ናዛዡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ሌላ የውጭ ኃይል ሊሆን አይችልም። እናም በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውን በሰብዓዊ መብት ተሟገችነት፣ በዴሞክራሲ አቀንቃኝነትና በፕሬስ ነፃነት ተሟጋችነት ስም ከልለው የርዕዩተ-ዓለም አጀንዳን የሚያራምዱ እንዲሁም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የእነርሱን አጀንዳ የሚያቀነቅኑ አንዳንድ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በዚህ ሀገር ውስጥ ለሚካሄዱ ጉዳዩች ምንም ዓይነት የማዘዝ ስልጣን ሊኖራቸው አይችልም። ሀገራችን ውስጥ ለሚፈፀሙ ማናቸውም ጉዳይ አዛዡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን መንግስት ደግሞ ታዛዥ ነው።
ይህ በመሆኑም የነገረ-“አንፍሉዌንዛ” ባለቤት የሆኑት አንዳንድ የኮንግረሰ አባላትም ይሁኑ የርዕዩተ-ዓለም ሲራራ ነጋዴ “መያዶች” የኢትዮጵያ መንግስት ለየትኛውም የውጭ ኃይል የማይታዘዝ፣ የህዝቦቹን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ የመያስጠብቅ፣ ከህዝቡ ውጪ ሌላ አዛዥና ናዛዥ የሌለው፣ ከየትኛውም ሀገር ጋር “የጌታና ሎሌ” ዓይነት ግንኙነትን የማይፈቅድ እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ የሰጥቶ መቀበል መርህ ብቻ የሚመራ ለህዝብ ፍላጎት ያደረ መንግስት መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። አዎ! የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገሩና ከህዝቡ ጥቅም ውጪ ለየትኛውም ወገን ፍላጎት የማያጎበድድ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ለሚዘወር የሁለትዮሽ ግንኙነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑን በቅጡ መረዳት ነገረ-“ኢንፍሉዌንዛን” በረቂቅነት ከማውጣት የሚያድን ይመስለኛል። ምንም እንኳን የዚህን ሀገር ውስጥ በህገ መንግስቱ መሰረት ዕውን እየሆኑ ያሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያስፈፅሙት የሀገራችን ህዝቦችና መንግስት ቢሆኑም፣ በነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ላይ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በማያመላክት መንገድ የቀረበውን ጥያቄ በድርበቡ መመልከቱ ተገቢ ይመስለኛል። 
በነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ላይ ምን ዓይነት ጉዳዩች ተነሱ?
ረቂቅ ውሳኔው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ነው። በአማራና በኦሮሚያ በፀጥታ ኃይሎች ስለተገደሉት ሰዎች ተዓማኒነት ያለው ምርመራ እንዲካሄድም ያሳስባል። ሆኖም ‘በረቂቅ ሃሳቡ ላይ የተገለፁት ጉዳዩች ሀገራችን ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክለኛ ገፅታው የሚያመላክት ነው ወይ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም በእኔ እምነት ሀገራችን ውስጥ የተከሰተው ችግር ትክክል ሆኖ፤ ችግሩ የተፈታበት የአፈፃፀም ሁኔታ ትክክለኛ፣ ገለልተኛና ሚዛናዊ በሆነ ዕይታ በረቂቁ ላይ ተመልክቷል ብዬ ስለማላስብ ነው። 
እንደሚታወቀው በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ስብዕና ጋር የተቆራኙና አንድ ሰው፣ ሰው ሆኖ ብቻ በመፈጠሩ ምክንያት የሚጎናፀፈው ተፈጥሯዊ መብቶች እንጂ፣ የዚያ ሀገር መንግስት ከፈለገ ለዜጎቹ የሚሰጣቸው ሳይፈልግ ደግሞ የሚነሳቸው ጉዳዩች አይደሉም። ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በረቂቁ ላይ የተሰነዘረውና “በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ” የሚለው ሃሳብ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኘሁትም። ምክንያቱም እነዚህ መብቶች ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ዕውን በሆነውና የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ባፀደቁት ህገ-መንግስት ላይ በግልፅ ከመስፈሩም በላይ፣ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ገቢራዊ እየሆኑ ስለመጡ ነው። በሀገራችን ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት አንዱ መነሻ የእነዚህ መብቶች አለመኖር በመሆኑ ዳግም ወደ ኋላ ተንሸራትቶ መብቶቹ የሚታጡበት ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። እናም እነ እነ ክሪስ ስሚዝ በደፈናው እንደሚሉት “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ” የሚያስብል ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም። 
እርግጥ ሀገራችን ለመብቶቹ ገና ጀማሪና አዲስ በመሆኗ በአፈፃፀም ደረጃ ‘ምንም ዓይነት እንከን የለም’ የሚል ሙግት ላነሳ አልሻም። እንኳንስ እንደ እኛ ዓይነት ለሰብዓዊ መብቶች ጀማሪ የሆነ ሀገር ቀርቶ፣ መብቶችን በማክበር ከሁለት ክፍለ-ዘመናት በላይ ያስቆጠረችው የእነ ሚስተር ስሚዝ ሀገር አሜሪካም ብትሆን፤ ዛሬ ላይ ያለ አንዳች እንከን መብቶቹን ገቢራዊ እያደረገችው ነው ተብሎ አይታሰብም። አይደለምም። 
ይህ ዕውነታም የዛሬ አራት ዓመት ገደማ አሜሪካ የሀገራትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ ሪፖርት አውጥታ ቻይና የሰጠችውን ምላሽ ያስታውሰኛል። ቻይና በወቅቱ “…አሜሪካ የራሷን ዜጎች ትሰልላለች፣ በሴቶችና በአናሳ ብሔሮች ላይ ጭቆና ታካሂዳለች እንዲሁም በመሳሪያ አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ ፈቅዳለች። እናም የዋሽንግተን አስተዳደር ‘የዓለም ዳኛ’ የመሆን ምንም ዓይነት መብት የለውም። ይልቁንም ራሱ የሚፈፅውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግር በተሻለ መንገድ መፍታት ይኖርበታል።…” ነበር ያለችው። 
በእኔ እምነት ይህ ማለት በደፈናው ‘አሜሪካ ውስጥ የሰብዓዊ መብት የለም’ ሊያስብል አይችልም። በአንፃሩም በመብቶች አፈፃፀም የዳበረ ልምድ ባለት አሜሪካ ውስጥ የአፈፃፀም ችግር መኖሩ ሊካድ የሚገባ አይመስለኝም። እናም ዕውነታው በእኛ ሀገር ውስጥም ከዚሁ አንፃር እንዲሁም ገና የመብቶች ጀማሪ መሆናችንም ታሳቢ መሆን ያለበት ይመስለኛል። እናም የደፈና ፍረጃ ለማንም የማይጠቅም መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።
እነ ሚስተር ስሚዝ በረቂቁ ላይ የታሰሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲሉም በረቂቁ ላይ አሳስበዋል፤ ኧረ እንዲያውም ‘አስጠንቅቀዋል’ ቢባል ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም። ያም ሆኖ ግን ይህኛውም የረቂቁ ሃሳብ ሚዛናዊና ህጋዊ አይመስለኝም። ምክንያቱም ‘ማስጠንቀቂያው’ ነባራዊውን ሃቅ የሚያንፀባርቅ ስላልሆነ ነው። እርግጥ ፖለቲከኛ አሊያም ጋዜጠኛ ሆኖ በሌላ የወንጀል ጉዳይ የታሰረ ሰው የለም ለማለት አይዳዳኝም። ሊኖር ይችላል፤ ይኖራልም። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ ግን በህግ ጥላና ከለላ ስር ያሉት ግለሰቦች ቢሆኑ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ተላልፈው የተገኙ ተጠርጣሪዎች አሊያም ፍርደኞች እንጂ ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ በመሆናቸው ምክንያት ስለታሰሩ አይደለም። 
እንደ እውነቱ ከሆነ እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ግለሰብ ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ስለሆነ ብቻ የሚታሰር ከሆነ፤ በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አስፈላጊ ባልሆኑ ነበር። ይሁን እንጂ በሰላማዊ ፖለቲከኝነት ሽፋን አሊያም በጋዜጠኝነት ክቡር ሙያ ጥላ ተከልሎ አንድ ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ወንጀል ከፈፀመና ከህግ አግባብ ውጪ የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ ከተንቀሳቀሰ አሊያም በሀገሪቱ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ከተንቀሳቀሰ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በህጉ መሰረት መጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም። አሜሪካም ውስጥም ቢሆን ማንኛም ሰው ቢሆን ከህግ በላይ እንዲሆን የሚፈቅድ አሰራር የለምና። 
እናም እነ ሚስተር ስሚዝ እዚህ ሀገር ውስጥ በፖለቲከኝነቱ አሊያም በጋዜጠኝነቱ ምክንያት ለእስር የተዳረገ ግለሰብ ለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ አይመስለኝም። ሆኖም እነርሱ የሚሉት ‘አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ ወንጀል ቢፈፅምም መታሰር የለበትም’ ከሆነ፤ እሳቤው የትኛውንም ወገን የሚያስማማ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው አደራ መሰረት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሰላለበት ነው። ይህን ደግሞ ለአሜሪካኖቹ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆንብኛል።
በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን እንዲሁም በቂሊንጦ እስር ቤት በተነሳው ቃጠሎ ሳቢያ የሞቱ ዜጎች ሁኔታ “በገለልተኛ አካል ይጣራ” የሚል ሃሳብም አቅርቧል—ረቂቅ ውሳኔው። ሆኖም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው መንግስት ህዝባዊ ኃላፊነት የሚሰማው በመሆኑ ረቂቁ እስከሚጠይቅ ድረስ የጠበቀ አይመስለኝም። መንግስት በቅድሚያ በእነዚህ አካባቢዎች ባለው የመልካም አስተዳደርና መሰል ጉዳዩች ምክንያት በህዝቡ ውስጥ የፈጠሩ ቅሬታዎችን ተንተርሰው አንዳንድ የኢትዮጵያን ዕድገትና መለወጥ በማይሹ የውጭና የውስጥ ኃይሎች አጀንዳውን በመንጠቅ በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ ህግና ስርዓትን ለማስከበር በተደረጉ ግጭቶች ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና የፀጥታ ኃይሎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል። ችግሩ የተፈጠረው መንግስት በአፈፃፀም ረገድ ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ባለመወጣቱ መሆኑን ገልፆ ይቅርታም ጠይቋል። ችግሩንም በገለልተኛ ወገን አጣርቶ ተገቢውን ርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። በአሁኑ ወቅትም በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በገለልተኝነት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አማካኝነት የማጣራት ስራው እንዲጀመር ተደርጓል።
ለሀገራችን ዜጎች ከኢትዮጵያ መንግስት በላይ ለማሰብ መሞከር በማንኛውም ሚዛን ቅቡል የሚሆን አይመስለኝም—ነገሩ “እኛ እናውቅላችኋለን፣ እናንተ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ” የማለት ያህል ይሆናልና። እናም “የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ” እንዲሉ አበው፣ ለዜጎቹ ከማንም በላይ የሚያስበውና የሚጨነቀው የኢፌዴሪ መንግስት፤ መብቶችን ለመጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አማካኝነት ማንም ሳይነግረው የማጣራት ተግባራትን ከህዝቡ ጋር በመሆን እያከናወነ ነው። ኮሚሽኑም  በገለልተኝነት ስራውን ይወጣል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራችን ውስጥ ማናቸውም ችግሮች በህገ መንግስቱ አግባብ የሚፈቱ መሆናቸውን የረቂቁ አዘጋጆች ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።
የሀገራችን ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኝነት የሚመነጨውም ከዚሁ ህገ መንግስት ነው። በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 54 ንዑስ አንቀፅ አራት ላይ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ህዝቦች ተወካዮች መሆናቸውንና ተገዥነታቸውም ለህገ-መንግስቱ፣ ለህዝቡና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑ ተደንግጓል። ተግባራቸውን የሚከውኑትም ከዚሁ ድንጋጌ አኳያ ይመስለኛል። እርግጥ የምክር ቤቱ አባላት ስራ አስፈፃሚውን የሚቆጣጠሩት፤ ስህተቶች ካሉ በወቅቱ ታውቀው በፍጥነት እንዲስተካከሉ፣ በህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ካልሆኑ ለማብራራት እንዲቻል፣ ተገቢ ከሆኑ ደግሞ በወቅቱ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ነው። 
እርግጥ ስራ አስፈፃሚው የራሱን ዕቅድ ለመገምገም የሚያስችለው አሰራርና ስርዓት ያለው መሆኑ አይካድም። ዳሩ ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱም ፈፃሚው አካል ምንም እንኳን ራሱን በራሱ ሲገመግም ትክክለኛ ግምገማ ሊያካሂድ ቢሞክርም፣ ሁኔታዎችን ከራሱ ምልከታ አንፃር ማየቱ ይቀራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። እናም በአፈፃፀሙ ላይ ያልነበሩ ወገኖች የራሳቸውን ነፃ ግምገማ እንዲያካሂዱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። እናም የፓርላማው አባላት ትልቅ የግምገማ አቅም ይመስሉኛል። ለነገሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉ ተቋማት ሲጀመር የተቋቋሙት ሥርዓቱ ራሱን በራሱ ለማረም እንዲያስችለው ታስቦ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ሳቢያም ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆኑ እንደ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት ተቋማት ገለልተኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ ስለ እኛ ሁኔታ ከእኛ ውጪ ማንም ሊቆረቆርልንና ሊያስብልን አይችልም። እንደ አሜሪካ ያሉ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አፈፃፀም የዳበሩ የውጭ ኃይሎች ድጋፍና እገዛ የማይጠላ ቢሆንም ቅሉ፣ በውስጥ ጉዳያችን ግን ጭልጥ ብለው ሊገቡ የሚችሉበት አመክንዩ ግን መኖር ያለበት አይመስለኝም። አይገባምም። የውጭ ኃይሎቹ ከዚህ በተቃራኒው የሚያስቡ ከሆነ ግን በውስጥ ጉዳያችን በግልፅ ጣልቃ መግባት ይሆናል። ምክንያቱም ልክ ላለፉት ዓመታት ‘ሆን ብለው ጥቁሮችን ማዕከል ያደረገ ግድያና ጥቃት ይፈፅማሉ’ የሚባሉት የአሜሪካ ፖሊሶች የሚዳኙት በሀገሪቱ ህገ መንግሰታዊ ስርዓት እንደመሆኑ መጠን፤ እኛ ሀገር ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ችግር በህገ መንግሰቱ አግባብ በመንግስትና ህዝብ የጋራ ምክክርና ውሳኔ ሰጪነት መፍትሔ የሚያገኝ በመሆኑ ነው። 
እናም እንኳንስ ግለሰቦች ቀርቶ አሜሪካም ብትሆን ቀደም ሲል የጠቀስኳት ቻይና እንዳለችው ‘የዓለም ዳኛ’ በመሆን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ የመግባት መብት ያላት አይመስለኝም። ምክንያቱም በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሀገራችንና የዋሽንግተን አስተዳደር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሲመሰርቱ፣ አንዱ በሌላኛው ላይ ፍላጎቱን በኃይል ለመጫን አስቦ አይመስለኝም። 
አሜሪካም ብትሆን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የጠበቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት በሀገራችን ላይ ፍላጎቷን በኃይል ለመጫን እንደማትችል የምታውቅ ይመስለኛል። ለዚህም የራሷ ምክንያቶች ይኖራታል ብዬ አስባለሁ። እነርሱም ሀገራችን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና በልማት ላይ ማተኮርዋን ዋሽንግተን ስለምትገነዘብ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታና ተባብሮ የመስራት አጋርነቷን ስለምታውቅ፣ ሀገራችን በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን የላቀ ሚና በሚገባ ስለምትረዳ እንዲሁም በዓለምና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ስለምታጤን መሆኑን በምክንያትነት መጥቀስ እችላለሁ። እርግጥ እነዚህ የሀገራችን መንግስትና ህዝብ የማንነት መገለጫዎችና ቁልፍ ተግባራት የአሜሪካ መንግስትም ፍላጎቶች እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት መናገር የምችል ይመስለኛል—ማንም የማይነቀንቃቸው የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት የማዕዘን ድንጋይ መሆናቸውንም ጭምር። 
ታዲያ እነዚህ የሁለትዮሽ ግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። አንዱ “ጌታ” ሌላው ደግሞ “ሎሌ” ሆኖ የሚከናወኑ ተግባራት አለመሆናቸውን የረቆቁ ባለቤቶች የሚገነዘቡት ይመስለኛል። ሀገራችን በአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ እጇን ለማስገባት እንደማትፈልግ ሁሉ፤ የአሜሪካ መንግስት አካላትም ከፖሊሲ አንፃር በውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን የሚያስገቡበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም። በመሆኑም የረቂቁ ባለቤቶች “በገለልተኛ ወገን ይጣራ” የሚል ጥያቄን እንደ ጥያቄ ሊያቀርቡ ቢችሉም፣ እንደ አዛዥ አሊያም በባለመብትነት ሁኔታ ሊሆን አይገባም። ያም ሆኖ ግን የ“ይጣራ” ፍላጎታቸው ‘እኛ ገለልተኛ የምንለው የውጭ ኃይሎችን ነው’ የሚል አንድምታ ያለው ከሆነ፤ እሳቤው የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትን በጠራራ ፀሐይ ለመንጠቅ መፈለግም ጭምር በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም። ይህን መሰሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ዕውን እንዲሆን የሚፈልጉት እንደ ሚስተር ስሚዝ ዓይነት ግለሰቦች እንጂ፤ ከዴሞክራሲ መርሆዎች አኳያ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምነው የአሜሪካ መንግስት ፍላጎት ይሆናል ብሎ ለመናገር የሚያስቸግር ይመስለኛል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም— የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዮኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ረቂቁን በመሪነት ያቀረቡት ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ረቂቆችን ለማቅረብ ሲጣጣሩ የቆዩ ናቸው በማለት የገለፁት። 
ውድ አንባቢያን በነገረ-“ኢንፍሉዌንዛ” ላይ በተሳሳተ መንገድ የሰፈሩትን አንኳር ጉዳዩች በዚህ አልቋጨኋቸውም። በክፍል ሁለት ፅሑፌ ላይ ቀሪዎቹንና በጉዳዩ ዙሪያ ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዩችን በማንሳት፤ የኮንግረስ አባላቱ ረቂቅ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገሩ ህዝብ እንጂ፣ ለየትኛውም ሀገር ወይም አካል ተጠሪ አለመሆኑን እንዲሁም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተገነባው የሚገኘው የዴሞክራሲ ባህል በህዝቦች ፈቃደኝነት ላይ የሚመሰረት እንጂ፣ በአሜሪካም ይሁን በሌላ የውጭ ኃይል በሚዘወር ዴሞክራሲ ሊገነባ እንደማይችል ለማሳየት እሞክራለሁ።