የኤርትራ አካባቢያዊ ስጋትነት በኮንግረሱ ዕይታ  

ሰሞኑን የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አንድ ዐብይ ውይይት አካሂዶ ነበር፤ “ኤርትራ—ችላ የተባለች አካባቢያዊ ስጋት” በሚል ርዕስ። በመድረኩ ላይ ቀርበው ምስክርነታቸውን የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዩች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ አንዷ ናቸው። ረዳት ሚኒስትሯ ችላ የተባለችውን የቀጣናውን ስጋት አስመልክተው በሰጡት እማኝነት “ኤርትራ ራሷን እንደ ‘ዳዊት’፣ ዩናይትድ ስቴትስን ደግሞ እንደ ‘ጎልያድ’ ማየት ከፈለገች፤ የሚደርሱባት ቁስለቶች ሁሉ በራሷ፣ የምትወነጭፋቸው ጠጠሮችም የሚወርዱት በራሷ ህዝብ ላይ ነው” ብለዋል። በዚሁ የእማኝነት መድረክ ላይ ቀርበው የተናገሩ ሌሎች ምስክሮችም የአስመራው አስተዳደር የሚከተለውን የተሳሳተ አቅጣጫ በማቅረብ የመፍትሔ ሃሳቦችንም ለመጠቆም ሞክረዋል። 
እርግጥ ረዳት ሚኒስትር ግሪንፊልድ ሀገራቸውንና ሻዕቢያን ያመሳሰሉበት ‘የዳዊትና የጎልያድ’ ንፅፅር ተገቢ ነው ሊባል የሚችል ባይሆንም፤ እርሳቸው ያሉት “የዳዊት” ትንሽዬ ጠጠር ግን በተገቢው መንገድ ሻዕቢያን ያላቆሰለና ከከባቢያዊ የትርምስ ስጋትነቱ እንዲላቀቅ ያላደረገው ነው። እናም አሁንም ቢሆን የአስመራው አስተዳደር ቀጣናውን ከማመስ ባለመቆጠቡ የዋሽንግተን አስተዳደርና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሻዕቢያን ከህዝቡ ነጥሎ “ቆንጣጭ” የሆነ ቅጣት ሊያሳርፉበት የሚገባ ይመስለኛል። 
ረዳት ሚኒስትሯ ምንም እንኳን የሻዕቢያ ትንሽዬ ጠጠር ተመልሶ ህዝቡንም እንደሚጎዳ ቢገልፁም፤ የአስመራው መንግስት ግን ለህዝቡ ደንታ የለውም። የተመድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በየወሩ አምስት ሺህ ኤርትራዊያን ሻዕቢያ የሚፈፅምባቸውን ግፍ በመፍራት ወደ ጎረቤት ሀገሮች እየተሰደዱ ነው። ገሚሶቹም በባህር ላይ በሚያደርጉት ጉዞ የዓሳ ነባሪ እራት ይሆናሉ። እናም “የዳዊት ትንሽዬ ጠጠር” መወንጨፍ ያለበት በኤርትራ መንግስት ላይ እንጂ የሻዕቢያ የግፍ በትር ባጎበጠውና ወንድም በሆነው በዚያች ሀገር ህዝብ ላይ መሆን ያለበት አይመስለኝም። የኢትዮጵያ መንግስት ባልተገደበ ስደተኞችን የመቀበል ፖሊሲው ኤርትራዊያንን በተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ሲቀበል፤ የአስመራው የትርምስ ቡድን ደግሞ በገዛ ህዝቡ ላይ የስቃይ ቀንበርን በመጫን ለስደት ይዳርገዋል። ይህን ሁኔታ በተገቢው መንገድ የተረዳው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኤርትራ መንግስት ዜጎቹ ላይ በመፈፀም ላይ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጣራ ቡድን መድቦ፤ በዚያች ሀር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶችን ይፋ አድርጓል።
ሆኖም ይህን የመንግስታቱን ድርጅት ሪፖርት ለማጣጣል በሚመስል መልኩ ሻዕቢያ በውይይቱ ላይ ‘አትላንቲክ ካውንስል’ (Atlantic Council) የተሰኘው ቡድን አስገራሚ ሃሳብ አቅርቧል። ይህ ቡድን ኤርትራ ውስጥ ወጣቶች በነፃ ጉልበታቸውን እየተበዘበዙ “ቢሻ” በሚሰኘው የወርቅ ማዕድን ማውጫ ላይ በመሰማራት ከዚያች ሀገር ከሚያገኘው ገቢ በ‘ኔቭሰን ሪሶርስስ’ (Nevsun Resources) እንደሚደጎም መረጃዎች ያመለክታሉ። እናም ‘አትላንቲክ ካውንስል’ በውይይቱ ላይ አጀንዳውን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር ጥረት አድርጓል። ይህም የሻዕቢያ ባለስልጣናት በሰብዓዊና ዴሞክራሲ ጥሰታቸው እንዳይጠየቁ ኮንግረሱን ለማሳመን የተጠቀሙበት ዘዴ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይደለም።
ምንም እንኳን በ‘ኔቭሰን ርሶርስስ’ የሚደጎመው ‘አትላንቲክ ካውንስል’ አጀንዳው የኤርትራ ሆኖ ሳለ፤ በበላበት ለመጮህ ሲል በአስገራሚ ሁኔታ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳና ለዚህም በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከሰተው ችግር ምክንያት አስመራ የኢትዮጵያን ስደተኞች እየተቀበለች መሆኑን ለማሳየት ሞክሯል። አስቂኝ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ከመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዩች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህዘቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች እንደ ሻዕቢያና ተላላኪዎቹ ያሉ የውጭ ኃይሎች በመጥለፍ ችግሩን ለማባባስ መሞከራቸው ሳያንስ፤ የአስመራው አስተዳደር እንደምን በሌለው ባህሪው ለኢትዮጵያዊያን አስቦ ሊሰራ እንደሚችል ለማንም ግልፅ ሊሆን አይችልም። 
ለነገሩ ‘አትላንቲክ ካውንስል’ ተናገር የተባለውን ጉዳይ ከመናገር ውጭ እዚህ ሀገር ውስጥ ስላለው ሁኔታ የሚያውቀው ነገር የለም። ሆኖም ሃቁን በግልፅ ማስቀመጥ ይገባል። ይኸውም በሀገራችን በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወደ ሻዕቢያ የሄደ አንድም ዜጋ የለም። ችግሩ እዚሁ ሀገር ውስጥ የተፈታና በመፈታት ላይ ያለ ነው። ይልቁንም ሻዕቢያ የሚታወቀው ድንበር አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በኃይል አፍኖ በመውሰድ ነው። እናም የኤርይትራን መንግስት ማንነት አብጠርጥሮ ለሚያውቀው የአሜሪካ መንግስት እንዲህ ዓይነቱ በበሉበት የሚጮሁ ቡድኖች ቀልድ የሚያስገርም እንጂ፤ በአስመራው አስተዳደር ላይ የተጣሉትን ሁለት ማዕቀቦች እንዲሁም በቅርቡ የሻዕቢያን ቱባ ባለስልጣናት ተጠያቂ የሚያደርገውን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት የሚያላላ አይደለም። ለዚህም ይመስለኛል—የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዩች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ግሪንፊልድ ‘ትንሽዬው የኤርትራ መንግስት ጠጠር መልሶ የሚያቆስለው ራሱን ነው’ በማለት የተናገሩት። 
ያም ሆነ ይህ ግን በሻዕቢያ፣ በ‘ኔቭሰን ሪሶርስስ’ እና በጉዳይ አስፈፃሚው ‘አትላንቲክ ካውንስል’ መካከል ያለው የሶስትዮሽ ያልተቀደሰ ጋብቻ፤ የኤርትራ መንግስት ከተጣሉበት ማዕቀቦች ብሎም ባለስልጣናቱ ተጠያቂ ከሚሆኑበት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት የሚያድን አይደለም። ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት የትናንትና የዛሬ አካባቢያዊ ስጋትነቱ በሚገባ ስለሚታወቅ ነው። 
ሻዕቢያ ትናንት እንደ ተርብ ያልነደፈው ተጎራባች ሀገር የለም። ፀረ-ሰላም ኃይሎችንና አሸባሪዎችን ረድቷል። በአንድ ሴንቲ ሜትር እንኳ በማይጎራበታቸው በሶማሊያና በአዲሷ ሀገር ደቡብ ሱዳን የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር እጁን አስገብቷል። በዚህም ቀጣናውን የትርምስና የስጋት አካባቢ ለማድረግ ሳይታክት ተንቀሳቅሷል። ሻዕቢያ በ25 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት ጎረቤቶቹ ላይ ጦር መዝዟል—በየመን፣ በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲና በሱዳን ላይ። ጦር መምዘዙ አልሳካ ሲለውም የየሀገራቱን ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎችን በጉያው ሸጉጦ በማሰልጠን፣ በማስታጠቅና ወደየሀገራቱ አስርጎ ለማስገባት ያልሞከረበት ጊዜ የለም—ይህ ሙከራውም ከቀቢፀ ተስፋነት ሊዘል አልቻለም እንጂ። እነዚህ የትርምስ ተግባራቱም በአሜሪካ መንግስትም ይሁን ማዕቀቡን በጣለበት የመንግስታቱ  ድርጅት በሚገባ የሚታወቁ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ባህር ተሻግሮ ሶማሊያን ለማመስ የአልቃዒዳ የምስራቅ አፍሪካ ክንፍ የሆነውን አል-ሸባብን በየወሩ 80 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እየሰጠ ሲያግዘው እንዲሁም የጦር መሳሪያና የሎጀስቲክስ ድጋፍ ሲያደርግለት እንደነበር የመንግስታቱ ድርጅት የመደበው አጣሪ ቡድን ያጠናቀረው ሪፖርት እዛው የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ይገኛል። ይህን ሃቅ የማያውቅ የአሜሪካ ባለስልጣንም ይሁን የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገር የለም። በአዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ውስጥም የትርምስ እጁን ማስገባቱን የኢትዮጵያ መንግስት የተሟላ መረጃ እንዳለው ደጋግሞ ገልጿል። ይህን ሁኔታም የኢፌዴሪ መንግስትና ኢጋድ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ አካላት አሳውቀዋል። ጂቡቲንም ቢሆን ከመተናኮል አልቦዘነም። በወታደራዊ ጡንቻ የሚያምነው ሻዕቢያ የጂቡቲን ግዛት በኃይል በመውረሩ ሳቢያ የማዕቀብ ሰላባ እንደሆነ የማያውቀው ከኤርትራ ህዝብ ሃብት ከሆነው የወርቅ ሽያጭ በ‘ኔቭሰን ሪሶርስስ’ አማካኝነት የሚዘረፈውን ገንዘብ እየተቀበለ ለሻዕቢያ በየመድረኩ የሚጮህለት ‘አትላንቲክ ካውንስል’ የተባለው ተቋም ብቻ ይመስለኛል።
ያም ሆነ ይህ ግን የኤርትራ መንግስት ዛሬም የአካባቢው ስጋት የመሆን ፍላጎቱን አልገታም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አካባቢውን ለማመስ እየሞከረ ነው። ዛሬም እንደ ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ፣ ኦብነግና አርበኞች ግንባርን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች እዛው አስመራ ውስጥ ይገኛሉ። “ፈሩድ’ የተሰኘው የጂቡቲ አማፂም እዛው ነው። የሱዳንን መንግስት ላይ ‘የቤጃ እንቅስቃሴ’ የሚል ቡድን ፈጥሮም በማስፈራሪያነት እየተጠቀመበት ነው። ደቡብ ሱዳን ውስጥም “ቀይ ባህር ኮርፖሬሽን” በሚባለው ድርጅቱ አማካኝነት የተለያዩ የትርምስ ስራዎችን ይከውናል። 
እነዚህ አካባቢውን የማመስና ሀገራት በስጋት ቀጣና ውስጥ ሆነው ልማታቸውን እንዳያካሂዱ ለማድረግ የመሞከር ጥረት የኤርትራ መንግስት ሁነኛ መገለጫዎች ናቸው። እናም በእኔ እምነት የአስመራው አስተዳደር ከፈፀማቸውና እያደረገ ካለው ቀጣናዊ የሽብር ተግባር አኳያ አሜሪካም ሆነች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ ርምጃዎችን ወስደዋል ብሎ ለመናገር የሚከብድ ይመስለኛል። ከአሸባሪዎች አለቃነቱ ሊያስቆሙት የሚችሉ “ቆንጣጭ” ርምጃዎች የተወሰዱ አይመስለኝም። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባጣራው የዚያች ሀገር የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥሰት በሻዕቢያ ሹማምንቶች ላይ አፋጣኝ ርምጃ አልተወሰደም። 
በዚህም ሳቢያ የኤርትራ ሹማምንቶች በዓለም አቀፉ ህግ እንዳይመሩና ነባሪያዊ የትርምስ ባህሪያቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ረዳት ሚኒስትሯ ያሉት “የሻዕቢያ ትንሽዬ ጠጠር” የኤርትራን መንግስት በተገቢው መንገድ አላቆሰለውም። ይህ ሁኔታም ሻዕቢያ ዛሬም የአካባቢ ስጋት ሆኖ እንዲቀጥል ከማድረጉም በላይ፤ እንደ ‘አትላንቲክ ካውንስል’ (Atlantic Council) ዓይነት ወትዋቾችን እየገዛ የውሸት መድረክ ተዋናይ ሆኖ ሊቀጥል ችሏል። እናም የኤርትራ መንግስት የአካባቢው የሰላም ጋሬጣ በመሆኑ ራሱ የሚወነጭፋቸው ጠጠሮች በትክክል በሚያዳክሙት መንገድ ሊመቱት የሚገባ ይመስለኛል።