በሃሳብ መለያየት ሞት አይደለም !!

ህገ መንግስታዊ ስርአቱ የሕዝብ አጀንዳ ላነገቡ የትኞቹም አይነት ሰላማዊ ሠልፎች  ዋስትናና ተገቢውን እውቅና ይሰጣል። የእንደነዚህ አይነት ሰልፎች መገለጫ ደግሞ  አላስፈላጊ የሆኑ፣ የተቋጠሩ ቂሞችና ጥላቻዎችን የሚያንጸባርቁ መፈክሮች የማይሰሙባቸው፤ ለውይይትና ለድርድር የሚረዱ ግብአቶች የሚገኙባቸው፤ በጥቅሉ ሰላማዊ ድባብ ያረበበባቸው ናቸው። በዚህ አግባብ ሃገር ለመገንባት የሚያስችሉና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰላማዊ ሰልፎች ለማካሄድ በመሰረቱ፤ ግና ከጅምሩ ከቂም በቀልና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አስተሳሰብ መውጣትና ለብሔራዊ መግባባት ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ያለውና የሚኖረው አካሄድ በሙሉ ጠብ አጫሪነት፤ ምናልባትም በቀለም አብዮት እንቅስቃሴ አንድን ስርአት የመገልበጥ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሰሞንኛ የነበሩ ሰልፎችን እና ጠባሳቸውን ከሃገር ግንባታና ውድመት አኳያ ወደኋሏ ተመልሶ እና ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ ተነስቶ የሚያሄስና ጀርባውን በመፈተሽ መፍትሄውንም የሚጠቁም ነው።
በየትኛውም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራትም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጽንሠ ሃሳብ መሠረት ከምርጫ ውጪ የሚደረግ የስልጣን ዘመቻ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሃገራችን በምትከተለው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራት እንደሚደረገው ሁሉ ሃሣብን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የመሠብሠብ እንዲሁም ሠላማዊ ሠልፎችን የማድረግ መብት የተፈቀደና ህገመንግስታዊ ዋስትናም የተሰጠው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ 
ግን ደግሞ ሃሣብን በነፃነት በመግለጽ መብት ሽፋን፣ በመሠብሠብና በመደራጀት መብት ስም፣ በሠላማዊ ሰልፍ ጥላ በመከለል የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ህገወጥ እንቅስቃሴ  የመመከትና በህግ አግባብ እርምጃ የመውሰድ መብት እንዲሁ በስልጣን ላይ ለሚገኘው መንግስት የተሠጠ ሃላፊነትና ይኸውም ሃላፊነት በህገመንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑንም ስለሂሳችን አጽንኦት መስጠትና በዚሁ ማእቀፍ ነጎሮቹን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ 
በዚህ ማእቀፍ ውስጥ ሆነን ነገሮችን ለማጤን እና ለመሟገት ከተስማማን ደግሞ በቀጣዩ ቅድመ ሁኔታም ላይ ያለአንዳች ማቅማማት ልንስማማ ግድ ይለናል ማለት ነው። ይኸውም የትኛውንም  አይነት ሠላማዊ ሠልፍ መፍቀድና መከልከል የመንግስት ሳይሆን የህገመንግስቱ መሆኑን የተመለከተው የመጀመሪያው ነው። 
ስለሆነም ባለቤት አልባ ስለሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል ገዢው ፓርቲ ይከለክላል የሚለውን ሥጋት ማራገፍ መጀመሪያ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጽንሠ-ሃሳብና በህገመንግስቱ መሠረት የስልጣን ምንጭ ህዝባዊ ምርጫ በሆነበት ሃገር በአብዮት ስልጣን ለመንጠቅና ትርምስ ለመፍጠር የሚደረግን ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ ማገድና እርምጃ መውሠድ የመንግስት ግብሩም ሃላፊነቱም መሆኑን መገንዘብ  ግድ የሚል ይሆናል ማለት ነው፡፡ 
ከዚህ ተነስተን ሰሞንኛ የነበሩትንም ሆነ ወደኋላ ተመልሰን በምርጫ ዋዜማዎችና ማግስቶች የተደረጉ ሰልፎችን ስናሄስ፤ በአገራችን የሚገኘውን ጨምሮ በውጭ ያለው የተቃውሞ ባነገበው አላማና በኪራይ ሰብሳቢ ባህሪው አንድ ሆኖ ታይቷል። አንድነቱም በቀለም አብዮት ሴራዎች ተገልጧል። ይህ ማለት ግን የአገሪቱን ህጎች አክብሮ ለመታገል ዝግጁ የሆነ አካል የለም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ ገዢው ፓርቲ በከፈታቸው ልዩ ልዩ የድርድር መድረኮች በመሳተፍ ሂደቱን በሚጠቅማቸው ወይም የጋራ ጥቅሞችን በሚያረጋግጥ አኳኋን ለመቃኘት ዝግጁ መሆናቸውን ማሳየት የጀመሩ ፓርቲዎች ስላሉ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ እነዚህ ፓርቲዎች የምርጫ ህጉን በማሻሻልና የምርጫ ቦርድን በጋራ ጥረት ከማዋቀር ጀምሮ የምርጫ ስነ-ምግባር ደንቡን ተደራድረው እስከማስፀደቅ፤ በእርሱም እስከመመራት የደረሰ የህግ አርቃቂነት አዝማሚያም አሳይተዋልና፡፡ 
ከነዚህ ባሻገር ያለወ ፅንፈኛ  የተቃዋሚ ክፍል ግን ከ97ቱ እና ከ2002ቱ ስህተት ካለመማሩም በላይ የለየለት ኪራይ ሰብሳቢ ፍላጎቱን ለማሳካት አመፅን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ ስልጣን ላይ መውጣት የሚሻ መሆኑን ከሰሞንኞቹ ሰልፎች ጀርባ ሆኖ ባደረጋቸው በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች በከፈታቸው ዘመቻዎች ተረጋግጧል፡፡ ከነዚህ ማረጋገጫዎች መካከልም ልክ እንደቀደመው እና የከሸፈው ስልቱ ችግር በሌለበት ችግር የተፈጠረ አስመስሎ ሰፊ የፈጠራ መረጃ በማቅረብ መጠመዱ እና ይኸው ሴራው አሁን ድረስ ያላቆመ መሆኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ለጋ ከመሆኑ በመነሳት ዴሞክራሲያዊ ስርአቱን ለመገንባት ከሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሾልከው የሚፈፀሙ የስነ-ምግባር ጥሰቶችን አጋኖና አባዝቶ በማቅረብ ህዝቡ በስርአቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ ሌት ተቀን በመፍጨርጨር ላይ መገኘቱም በገሃድ የታየና እየታየ የሚገኝ መሆኑም ተከታዩ ማረጋገጫ ነው፡፡ 
በገዢው ፓርቲና በመንግስት በኩል ስህተት ከታጣም በአንድ በኩል ሆን ብሎ ህግ በመጣስ በመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱ ላይ ፈተና እየደቀነ መንግሥት ህግ ለማስከበር ሲንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጣሰ በሚል የሚገለጸውም አቤቱታው ሌላኛው ማረጋገጫ ነው። መንግስት ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ ጠቧል የሚል ወቀሳ እንዳይቀርብ በመስጋት የህግ ጥሰቶችን አይቶ እንዳላየ ሲያልፍ ደግሞ ህግ የመጣስ መንፈስ እንዲበራከትና ወደ አመፅ ለመንደርደር የሚያመች ሁኔታ ለመፍጠር በሚያስችል እንቅስቃሴያቸውም አላማቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ የቀለም አብዮት ሃይሎች ጋር በፈጠሩት ጋብቻ ስርአቱን ጥላሸት የመቀባት ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻን በማካሄድ ላይ መሆናቸውም የሚታወቅና የሴራቸው ሁነኛ ማሳያ ነው።
ወደውጭው የቀለም አብዮት አቀጣጣይ ሃይል ስናመራ በዋናነት የምናገኘው አክራሪ የሆነውን የኒዮ ሊበራል ሃይል እና የሃገራችን ልማት እንቅልፍ የሚነሳቸውን የሻቢያ መንግስትና ግብረአበሮቻቸውን ነው፡፡ ይህ አክራሪ ሃይል ከራሡ መጽሃፍ በስተቀር ሌላ እንዳይነብና መመሪያ እንዲሆን የማይፈልግ፣ የራሡን መመሪያ በሌሎች ላይ በውድም በግድም መጫን የሚፈልግ ሲሆን ተከታዩ ደግሞ በተፈጥሮ ሃብቶቻችን ተጠቅመን ከስልጣኔ ማማ ላይ እንዳንወጣ ከሚሹ ሃይሎች ፍርፋሪ የሚለቃቅመው ሃይል ነው፡፡ 
ይህ አክራሪ ሃይል ዓለምን በራሡ አምሳል ለመቅረጽና ለእርሡ ብቻ የምትመች እንድትሆን ለማድረግ ሁሉንም ዓይነት  ማስገደጃ መሣሪያዎች መጠቀም የለመደ ነው፡፡ የማስገደጃ መሣሪያ ከመጠቀሙ በፊት በማባበል ከተሣካለት በዚሁ ተማምኖ የበላይነቱን ያረጋግጣል፡፡ ይህ አልሠራ ካለው ደግሞ ሃይልን ከዚህም አልፎ በጠላት የጎረቤት ሃገራት እና የተፈጥሮ ሃብቶች ጉዳይ ካላቸው ሃገራት ጋር አብሮ የቀለም አብዮትን እንደዋነኛ ማስፈፀሚያ ይጠቀምበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሠውና በ97 እና 2002 ምርጫ ዋዜማና ማግስት በሃገራችን ላይ ተሞክሮ የከሸፈው የቀለም አብዮትም ሃገራችን የራሷን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ በመከተሏና በአክራሪው ሃይል መመሪያ አልመራም፤ የራሤንም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ እንጂ የአክራሪ ሃይሉን መነባንብ መዋጥ ሲያልፍም አይነካካኝ  በማለቷ መሆኑን ያስታውሷል፡፡ አሁንም የሆነው በራሳችን መንገድ ለመሄድ ስንሞክር የገጠሙን ፈተናዎች በማጋነን እና ኪራይ ሰብሳቢ የሆነውን አመራር ተግባር በማጦዝ ለቀለም አብዮት ማመቻመች ነው።
በምርጫ 97 እና 2002 ከእነዚህ አክራሪ ሃይሎች በኩል ሲቀጣጠል የነበረው እና በተበታተነ ነገር ግን በእሩምታ መልክ ሲተኮስ የነበረው ጥይት ከነሂውማን ራይትስዎች፤ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሲፒጄ (የጋዜጠኞች መብት አስጠባቂ ነኝ ባይ) ወዘተ… እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ አሁንም ሰሞንኛ የነበሩ ባለቤት አልባ ሰልፎችን ተከትሎ የተኩሡ ባሩድ እየሸተተ የሚገኘው ከነዚሁ ወገኖች ነው።
ስለሆነም ቆም ብሎ ማሰብና በመንግስት ዝግጁነት እና በግምገማው ውጤቶች ላይ በመመስረት ሰላምና መረጋጋት በማስፈን በአገሪቱ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ላይ በግልጽነት ለመነጋገር መነሳት የግድ ይላል፡፡ አገሪቱን የሚመራው ገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች በአገሪቱ የፖቲካ ምኅዳር ውስጥ ያለውን የተበላሸ ግኙነት ህገ መንግስታዊ ስርአቱ በሚፈቅደው አግባብ ብቻ ሊያድሱ ይገባል እንጂ አመጽ በውጭ የሚገኘውን ተላላኪ ኪስ ካላሳበጠ በቀር ፋይዳው ውድመት መሆኑንም ሊረዱ ይገባል። የሕዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ ምላሽ የሚያገኙት ሁሉንም ወገን በጋራ የሚያስማማ መፍትሔ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኩፍኝ የተመታው ፖለቲካ እንዲፈወስ ተቃራኒ ሐሳቦች በነፃነት የሚፋተጉበት መድረክ ማመቻቸት እና ሰላማዊ ለሆኑ ተቃውሞዎችም ፈቃድ ሰጪው አካል ማፈግፈግና መታሸት የሌለበት መሆኑ ላይ ገዢው ፓርቲ ባደረገው ግምገማ አስምሮበታልና ብንጠቀምበት ይበጃል፡፡  
ከፖለቲካ ሥልጣንና ከሚሰጠው ጥቅም በላይ ሊያሳስብ የሚገባው የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ቅራኔው ገጽታውን እየቀያየረ በጦዘ ቁጥር የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ ከህገ መንግስታዊ ስርአቱ ውጭ የተደረጉና እየተደረጉ የሚገኙ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ካደረሱት ውድመት በተጨማሪ በአገሪቱም ሆነ በመላ ሕዝቧ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት መፍጠራቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ለውይይትና ለድርድር አልመች ያለውን ጨምሮ በውጭ የሚገኘው ተላላኪ ስለኪሱ እብጠት መሪ አልባ አመፆችን እየቀሰቀሰ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ እና ለሰላማዊ ውይይት የተከፈቱ በሮች እንዲዘጉ እያደረገ መሆኑንም ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
ባጠቃላይ፣ አሁን የሚታየውን ውጥረት በማርገብና ለሰላማዊ ውይይት አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ህዝቡም ጭምር መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ይህ የመንግሥት ኃላፊነት በሌሎች ወገኖች ካልተደገፈ የሚፈለገው ሰላም አይመጣም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ፀጋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ የጠቡንና የግጭቱን ጎዳና በሠለጠነ መንገድ ለማጽዳት ዝግጁ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አለባቸው፡፡ ለመፍትሔ የማይበጁና ጠላትነትን የበለጠ የሚያጋግሉ ፉከራዎችና ቀረርቶዎች ተወግደው ሥልጡን በሆነ መንገድ ልዩነትን ይዞ ለመነጋገር መትጋት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት አገሪቱ በደም እንድትጨቀይ የሚፈልጉ ኃይሎች ተነጥለው በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ፈጽሞ ሊቆጣጠሩት የማይችሉትን ግጭት አስነስተው አገሪቱን በደም ለመለወስ ጥረት ሲያደርጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች ግንባር ቀደም በመሆን ለሰላማዊ ውይይት  ፋና ወጊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም መባል አለበት፡፡ በሃሳብ መለያየትና ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ካልተቻለም ልዩነትን አክብሮ መቀጠል ዴሞግራሲያዊነት እና ለሃገር ልማትና እድገት ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። ሞት የሚሆነው ልዩነትን በአመጽ ለመፍታት መጣርና ለውጭ ሃይሎች ቀዳዳ መፍጠር ነው።