የፖለቲካ ነውረኝነት

የዚህ ተረክ መነሻ በባህርዳር ተካሂዶ የነበረውን እና የሰው ህይወትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች የወደሙበትን ሰልፍ ባለቤት ነኝ ብለው ሲያበቁ በቪኦኤ የወጡበት፣ ስለውድመቱም በመንግስት በኩል የመጀመሪያው ተጠያቂ ስለመሆናቸው የተነገረላቸው የሰማያዊው ኢንጂነር ይልቃል ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ሰሞንኛዎቹን ሰልፎች በተመለከተ ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው። እዚህ ጋር ግን ኢንጂነሩ የፓርቲያቸው የኢንስፔክሽንና ኦዲት ኮሚቴ ያገዳቸው መሆኑ ይልቁንም ለፓርቲያቸው መተዳደሪያ ደንብ ሳይገዙ እንደሃገር መንግስትንም ሆነ መሪ ድርግቱን ለማሄስ የሞራልም ሆነ የህግ ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን መዘንጋት የማይገባና ምልከታቸው ሁሉ በዚህም መንፈስ መታየት ያለበት መሆኑን አንባቢያን ልብ ይሏል። በማውሳት ከቃለ ምልልሱም ለዚህ ተረክ መነሻ የሚሆኑትና በተለይ ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጋር የተያያዙትን ሂሳቸውን በመጠኑ እንመልከት።
እውነቱን ለመናገር ይህ ነገር ሰፋ ያለና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን ምልክቱ መታየት ጀመረ እንጂ የተከማቸ ችግር ነው፡፡ ችግሩ ተከማችቶ ተከማችቶ መገለጫዎቹ መታየት ጀመሩ፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ለተከታታይ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ የነበሩት ጥያቄዎች በሙሉ በአግባቡ ባለመያዛቸው አሁን እንደሚታየው የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ [. . . ] የችግሩ መሠረት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይኖር መደረጉ፣ የሲቪክ ማኅበራት አለመኖር፣ ዜጎች የፈለጉትን አመለካከትና አስተያየት በነፃነት ያለማራመድ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአታላይ አገዛዝ ወጥቶ የአገሩና የሥልጣን ባለቤት ባለመሆኑ ነው፡፡ [. . . ] አብዮት ሲባል በመሠረቱ ከፓርቲው አለፈ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ ፓርቲ ቀስቅሶ አብዮት አያስነሳም፡፡ አብዮት ማለት በድንገት የሚነሳና ጥያቄዎች ተከማችተው ተከማችተው ሰው ደመነፍሳዊ በሆነ ሁኔታ የሚያደርገው ነገር ማለት ነው፡፡ ተጠንቶ በየደረጃው እየተመራና እየሄደ ከሆነማ አብዮት አይደለም፣ አዝጋሚ ለውጥ ነው፡፡ አብዮት ቅፅበታዊ ነው፡፡ የታፈነ ጥያቄ ምላሸ የሚፈለግበት ነው፡፡ ምናልባትም ስትራቴጂ ተነድፎ ላይቀረፅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ካለመርካት የሚመነጭ ነው፡፡

እነዚህን እና የገዢው ፓርቲን ግምገማ የልጆች ጫወታ ነው እስከማለት የደረሱት የኢንጂነር ይልቃልን እይታዎች እና ክህደቶች በተለይም ከአብዮት ጋር ተያይዞ ከላይ በተመለከተው መልኩ እጃቸውን ስለታጠቡበት ጉዳይ እንኳንስ ባለቤት ነኝ ብለው የወጡበትን ሰልፍ ቀርቶ ኮሽታ ባለበት ሁሉ የነበራቸውን እጅ እርሳቸው የሉም ካሏቸው የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ ጉዳዮችና ተቋማት አኳያ ስለሃገራችን ሰላም ስንል በትኩረት እናያለን። ይህ ማለት ግን ገዢው ፓርቲ ቅዱስ ነው ለማለት እንዳልሆነና እራሱም በግምገማው ባመነው ልክ ብልሽት ውስጥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
በአንድ አገር ውስጥ የቀለም አብዮት እንዲኖርና አልፎ ተርፎም እንዲሳካ ከማድረግ አኳያ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ጠንካራ አንድነት ያለው የተቃዋሚ ጎራ መኖር እንዳለበት ስለቀለም አብዮት የተመራመሩ ልሂቃን ይገልፃሉ፡፡ 
በአገራችንም በ97 ዓ.ም ተሞክሮ የከሸፈው የቀለም አብዮት የተለያዩ ነገር ግን ከሞላ ጎደል በአንድ ተመሳሳይ የቀለም አብዮት ስትራተጅ የሚመሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች የመሩትና የተወኑበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት ጀምሮት በሂደት ቅንጅት ከተፈጠረ በኋላ መሪነቱን የተቆጣጠረው የ97ቱ የከሸፈ ሙከራ ከሞላ ጎደል በሁሉም ተቃዋሚዎች የታመነበትና የተደገፈ የቀለም አብዮት የነበረ መሆኑ በሚታወቅበት አግባብ ከአብዮት በስተጀርባ ፓርቲ ብሎ ነገር የለም የሚለው ከላይ የተመለከተ ትንታኔ ምናልባት ለፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃል ካልረዳቸው በቀር የፖለቲካ ሳይንሱን መርህና ግኝት ተጻራራ የሆነ ምልከታ ነው፡፡    
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚካሄድ አብዮት (ለስር ነቀል ለውጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ) ስኬታማ የሚሆነው በተጨባጭ ምክንያት የሚነሳ ሲሆንና በዚያው ልክ ለሚነሳው አብዮት ተመጣጣኝ የሆነ መሪና ተመሪ እንዲሁም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና ማህበራዊ መሰረት  መሰረት ያደረገ የአፈጻጸም ስትራተጂ ሲኖረው መሆኑ የመጀመሪያና በዋናነት የሚጠቀስ የአብዮት ተጠየቅ ነው።
አብዮት ስለ አብዮት ሲባል ብቻ የጥቂት አኩራፊ ወገኖችንና ምክንያት የለሾችን ስሜትና የከሰሩ ፖለቲከኞችን ድብቅ አጀንዳ መሰረት አድርጎ ልነሳ ቢል እንኳንስ ጥቂት ሊጓዝ ይቅርና ሳይፀነስ ሊጨነግፍ የሚችል መሆኑም ከላይ ከተመለከተው ጽንሰ ሃሳብ ጋር  ተመጋጋቢ የሆነ የአብዮት ተጠየቅ ነው።
በአፍሪካ የግብጽንና የቱኒዚያን አብዮት ተከትለው በአረቡ አለም የተነሱ አብዮቶች በከፊል የተሳኩ ቢመስልም መነሻቸውና መድረሻቸው የአብዮትን ህግጋት የተከተለ አልነበረምና፤ ሂደቱ ሁሉ በ”የጠላቴ ጠላት” የተደራጀ ነበርና አንጎበሩን መላቀቅ ተስኗቸው ወደከፋ መተላለቅ በመሸጋገር ላይ ስለመሆናቸው ግብጽን ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው።  
ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ . . . እንዲሉ ግብጽንና ቱንዚያን አርአያ በማድረግ በጥቂት ስሜታዊ ሃይሎች አብዮት ለማስነሳት የሞከሩና ሳይፀንሱት የጨነገፈባቸው የአረቡ አለም ሃገራትም ስለመኖራቸው የሚካድ አይሆንም።
በሀገሬ የተቃውሞ ፖለቲካ መድረክም በተመሳሳይ ከምርጫ 97 በኋላ ተስፋ የቆረጡና የከሰሩ ፖለቲከኞች ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ወደ አመጽና የቀለም አብዮት ለመለወጥ ያደረጉት ሙከራዎች በተደጋጋሚ ቢከሽፍባቸውም ሰሞንኛ ከነበሩት ሰልፎች ጀርባም ስለመኖራቸው የፓርቲዎቻቸውን ልሳን ጨምሮ “የመናገር ነጻነት፣ የሚዲያ አብዝሃነት . . . የሌለባት ሃገር” ሲሉ ኢንጂነር ይልቃል ለፈጸሙት ክህደት ዋቢ የሚሆኑትን ማህበራዊ ሚዲያዎች በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል። 
የአፈጻጸሙ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፤ ለእድገቱም ይሁን ለውድቀቱ ገዢው ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎችም ድርሻ ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ አለማቀፍ መለኪያዎችን ባሟላና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ በሚፈቅደው መልኩ በየአምስት አመቱ በሚደረጉ ብሄራዊና ክልልዊ ምርጫዎች ህዝቡ የህጋዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መንግስት የራሱን አዎንታዊ ሚና መጫወቱን መካድ በራሱ የአቋራጭ ስልጣን እና የቀለም አብዮትን ከመሻት የሚመነጭ መሆኑ አያጠያይቅም ። 
የፖለቲካ ስልጣን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ በህዝብ ድምጽና ከምርጫ ሳጥን ብቻ የሚረጋገጥ እንደሆነ በተከታታይ ምርጫዎቹ እንዲረጋገጥ በማድረግ ላይ መሆኑም ከነቀርነቱ ቢያንስ ሊካድ አይገባም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በነውጥና በውጭ ሃይል ድጋፍና ግርግር ስልጣን ሊያዝ እንደማይቻልና በጉልበት ስልጣን የመያዝ አማራጭ የተዘጋ መሆኑን  ሊያሳይ በሚያስችል መንገድ የተዘረጋው የምርጫ ስርአት ላይ በርካታ ጫናዎችና ስም የማጥፋት ዘመቻዎችን አስቀድሞ የቀለም አብዮትን መስበክ ከአቋራጭ ስልጣን ፈላጊዎች የተለመደና የማያከራክር በሆነበት አግባብ ከላይ በተመለከተው መልኩ መሸምጠጥ የፖለቲካ ነውረኝነት ነው።   
ባለፉት የዴሞክራሲና የልማት አመታት የአገራችን ህዝቦች የምርጫ ተሳትፎ በየምርጫ ዘመኑ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል። በተመሳሳይ መልኩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከነችግራቸውም ቢሆን በየወቅቱ እያደገ የመጣ ሲሆን የመድበለ ፓርቲ ስርአቱም በመጠናከር ላይ ስለመሆኑም ከጨቅላው ሰማያዊ በላይ ዋቢ የለም። 
ካለፉት ተከታታይ ምርጫዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ምንም እንኳ አሁንም የፅንፈኝነትና በአቋራጭ ስልጣን የመያዝ አባዜ ያልተላቀቁ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ፓርቲዎች የሚገኙ ቢሆንም ጥቂትም ቢሆኑ የህግ የበላይነትና የምርጫ ህጎቹን አክብረው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ ፓርቲዎችም መታየት ጀምረዋል። ከዚህ አንጻር በጠባቡም ቢሆን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመስራት የቆረጡ ፓርቲዎች መኖራቸው ለተጀመረው የመድበለ ፓርቲ ስርአት መጠናከርና የኢትዮጵያ ህዳሴ የፖለቲካ ቀጣይነት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ እንጂ ኢንጂነሩ በሸመጠጡት ልክ በነውረኝነት የሚታይ አይደለም።  
በሃገራችን ለመረጠው ህዝብና ለህግ ተጠያቂነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት ስለመጣሉም በርካታና ተጨባጭ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። በዴሞክራሲያዊ መንግስት የተቀረጹት ህጎች ሕገመንግስቱን እና ሌሎች ከሱ የሚቀዱትን ጨምሮ በማንኛውም ባለስልጣንን ወይም ህግ ወይም ልማዳዊ አሰራር እንዳይጣስ የሚከላከልና የሚጠብቅ የፍትህ ስርአት በአገራችን እየተገነባ መገኘቱንም በተመለከተ በተመሳሳይ።  
የመጨረሻው የስልጣን ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ በህዝቡ ይሁንታ የጸደቁትን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በጥቅሉ የህግ የበላይነት የነገሰባት አዲስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አንፃር፣ ከነቀርነቱም ቢሆን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። 
በህዝቦች የዘመናት ተጋድሎ እውን የሆነው የፌደራል ስርአታችን የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑና የእልቂትና የብተና ምንጭ የነበረውን የብዝሃንነት ችግር በመሰረቱ በመለወጥ አገራችን ቀጣይነት ባለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎች እንድታስመዘግብ ያስቻለ ያልተማከለ የፌዴራል ስርአት በመገንባት ላይ መሆኑንም መካድ የፖለቲካ ነውረኝነት ነው። 
ያልተማከለው የፌዴራል ስርአቱ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስርነቀል ለውጦችን አስከትሏል። ከሁሉ በፊት የዘመናት የአገራችን ጭቁን ህዝብች ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ተደርገዋል። ችግሩና ጥፋቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰማያዊ ፍጥረትና ለዚህ ተረክ መነሻ የሆነውን አስተያየት ጨምሮ ከሰሞንኞቹ ሰልፎች በላይ ለዚህ ዋቢ መሻት አይጠበቅብንም ።

ይህ ስርአት ህዝቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸው በጥብቅ እንዲከበር ከማድረጉም በላይ ህዝቦች በአካባቢያዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው በማድረግ የሚገለጽ እንጂ ከላይ በተመለከተው መልኩ ባይተዋርነትን በማንገስ ነውር የሚገለጽ አይደለም።
ይህች ሃገር ሰብእዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩባት፣ የዴሞከራሲ ባህልና ተቋሞች የሚያብቡባት፣ ህዝቡ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ህይወት የነቃ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥባት፣ በህዝቦች መብት መከበር፣ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ አንድነት የሚጎለብትባት፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ስርአት በመፍጠር ላይ እንጂ የፖለቲካ ነውር እንዲፈጸምባት ሆና አልተበጀችም።  
በትብብር ላይ የተመሰረተው የዴሞክራሲያዊ ፌዴራል ስርአቱ ሌላው ስኬታማ መገለጫ አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመፍጠር በህገመንግስቱ የተቀመጠውን የኢኮኖሚ አላማ እውን ከማድረግ አኳያ ባለፉት አመታት በክልሎች መካከል እየጎለበተና እየተጠናከረ በመጣው የእርስ በእርስ መደጋገፍና ትብብር እንጂ የሰማያዊው ኢንጂነር ባነወሩት ልክ አይደለም። 
ባጠቃላይ ስለሰማያዊው ኢንጂነርም ሆነ መሰል አስተያየቶች ማለት የሚቻለው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ ከነቀርነቱ እና በግምገማቸው ያረጋገጧቸው ብልሽቶች እንደተጠበቁ ሆነው ህዝቦች በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን ባላቸውና በምርጫ በሚቋቋሙ የህዝብ ስልጣን አካላት በእኩልነት እንዲወከሉ ማድረግ፣ እነዚህን መብቶች በተሟላ አኳኋን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲኖራቸው ድጋፍ ማድረጋቸውንም መሸምጠጥ የፖለቲካ ነውረኝነት እና የቀለም አብዮት ቁማር መሆኑን።