ጠብ በሌለበት እርቅ የለም!

የባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የፖለቲካ  ሂደት ውስጥ  ቀደም ሲል ባለፍንባቸው ሥርዓቶች ያለነበሩ በርካታ አዳዲስ ነገሮች አይተናል። በዘውዳዊው የንጉሠ ነገሥቱ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓትና ይህን በተካው የወታደራዊ ቡድን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ሥርዓቶቹን በይፋ መቃወም፤ ተቃውሞው የቀረበው በንግግርም ይሁን በጽሁፍ የቀረበበት አኳኋን ምንም ያህል ምክንያታዊና ሰላማዊ ቢሆን ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ያሳስራል፤ ያስደበደባል፤ ያስገድላል።

በሁለቱም ሥርዓቶች ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በሕግ ነበር የተገደበው፤ ነጻ/የግል ሚዲያ የሚባል ነገር አልነበረም። ዜጎች ሃሳባቸውን ለመገለጽ የሚጠቀሙባቸው የኪነ ጥበብ ሥራዎች፤ መጻሕፍት፤ (የዘፈን ግጥሞችን ጨምሮ)፤ ቴአትሮችና ድራማዎች፤ . . . ለሕዝብ ከመለቀቃቸው በፊት በጥብቅ ሳንሱር ውስጥ የማለፍ ግዴታ ነበረባቸው።

 ብዙዎቹ የኪነ ጥበብ ውጤቶች የነጉሠ ነገሥቱንና የመሳፍንቱን ክብር ይነካሉ፤ የወታደራዊውን ደርግ ባለስልጣናት ይሸነቁጣሉ፤ የሥርዓቱን ርእዮተ ዓለም ይቃወማሉ፤ ወዘተ በሚል ሰበብ በሳንሱር ኃላፊዎች መክነው ቀርተዋል። አንዳንዶቹ በይፋ ከተገለጠው ውጭ “ይህን ለማለት የታሰበ ይመስላል” በሚል ጭምር ነበር እንዲመክኑ የሚደረገው፤ ለሕዝብ የቀረቡትም ቢሆኑ በሳንሱር መቀስ ተቆርጠውና ተቀጥለው  በሥርዓቶቹ ልክ የተከረከሙ ነበሩ።

እነዚህ ሁኔታዎች ከሥርዓቶቹ ጋር ታሪክ ሆነው ቀርተዋል። ዛሬ ሥርዓቱንና በሕዝብ ውክልና ሥልጣን የተረከበውን ፓርቲ በይፋ መቃወም በሕግ የተረጋገጠ የዜጎቸ መብት ነው። ይህ ሥርዓቱንና ገዢውን ፓርቲ የመቃወም መብት ለዘመናት ታፍኖ የኖረ ከመሆኑ የመነጨ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ባላውቅም፤ በአንዳንድ ሰዎችና ቡድኖች ዘንድ መቃወም በሃኪም የታዘዘላቸው እስኪመስል ድረስ ክፉውንም ደጉንም በጅምላ ሲቃወሙ መስማት የተለመደ ነው። እርግጥ ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ እስከተገለጸ ድረስ በሃኪም ሳይሆን በፈጣሪም የታዘዘ እስኪመስል ከአፍ ሳይነጥሉ መቃወምን የሚከለክል ሕጋዊ ሥርዓት የለም።

የመጨረሻው አሃዳዊ አምባ ገነናዊ ሥርዓት ወታደራዊው ደርግ ተወግዶ በወራት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦች፤ ሕዝቦችና ሌሎች የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች በመሰረቱት የሽግግር መንግሥት ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሬስ ነጻነት አዋጅ ጸደቀ። እርግጥ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት የሽግግር መንግሥቱ እንደ ሕገ መንግሥት ሲገለገልበት በነበረው ቻርተር የተረጋገጠ ነበር። 1984 ዓ/ም አጋማሽ ላይ ይህ በቻርተሩ የተረጋገጠው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ተግባራዊ የሚሆንበት የፕሬስ አዋጅ ጸደቀ።

ይህን ተከትሎ ለማንበብ የሚያታክቱ መጽሄቶች፤ ጋዜጦችና መጻሕፍት ወዘተ. ካለምንም የሳንሱር ምርመራ እየታተሙ መሰራጨት ያዙ። ሕዝቡ መጽሄቶቹን፣ ጋዜጦቹን እየገዛ፣ አየተዋዋሰ አነበባቸው። የመረጃና የመዝናናት ጥማቱን ተወጣ። ይሁን እንጂ፤ በወቅቱ ፕሬስ እንደሞያ ባለመጎልበቱና ባህሉም ባለመዳበሩ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠውን የፕሬስ ነጻነት የተጠቀሙት በአብዛኛው የአምባ ገነኑ ወታደራዊ ሥርዓት ካድሬዎችና ወታደራዊ መኮንኖች ስለነበሩ የሚዘጋጇቸው የፕሬስ ውጤቶች ተጨባጭና ሚዛናዊ መረጃ ከማቅረብ ይልቅ እንደፈለጉ የመጻፍና የመናገር መብታቸውን ያረጋገጠላቸውን ሥርዓት ለመናድ ዓላማ የተጠቀሙበት ሁኔታ በዝቶ ታይቷል። እስከ 1990 ዓ/ም የነበሩት ጋዜጦችና መፅሄቶች በራሳቸው በአዘጋጆቹ ተቃዋሚው ፕሬስ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ በመሠረቱ ተቃዋሚ የሚባል ፕሬስ የለም። ፕሬስ ነጻ ነው፤ ወይም የአንድ ፓለቲካ አመለካከት አራማጅ ልሳን ነው።

ታዲያ አሁን Horn TV በተባለው የኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰራጨውን ኢሳት የተሰኘ ቻናል መሰል ድረገፆችንና የፌስቡከ ገፆችን ስመለከት የመጀመሪያዎቹን “በለው፤ ውቃው፤ አገር ተዘረፈ፤ እከሌ የሚባለው ብሄር ተጨፈጨፈ፤ የእከሌ ጦር በዚህ በኩል እየገሰገሰ  ነው፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እደሜው አጥሯል፤ ምንትስ፤ ቅብጥርስ” ይሉ የነበሩ መርዶ ነጋሪ መጽሄቶችንና ባለ 8 ገጽ ታብሎይድ ጋዜጦችን ያስታውሱኛል። እርግጥ የኤርትራው ኢሳትና ሌሎች ድረገጾች ላይ የሚሰሩት የብጥብጥ ፖለቲካ አራማጆች በከፊል የያኔዎቹ ሳተናው፤ ክብሪት፤ እሳት፤ ጅራፍ . . . የተሰኙ ጋዜጦች አዘጋጆች ናቸው።

በዚህ አኳኋን የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሬስ አሁንም ከሁከት ናፍቆትና ከምጽአት ቀን ትንበያ ሙሉ በሙሉ ባይላቀቅም ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ፤ ከአገሪቱ የፕሬስ እድሜ አኳያ አንጋፋ ለመባል የበቁ የፕሬስ ውጤቶች ተፈጥረዋል። የፕሬስ ነጻነት ከህትመት ሚዲያም ተሻግሮ የግል ሬዲዮ ጣቢያዎችንም ከጨመረ አስር ዓመታት ገደማ ተቆጥሯል። በቅርቡ ደግሞ የቴሌቪዥኑም ጎራ ሊቀላቀለው ነው። ይህ ባለፉት ዓመታት የተመለከትነው አዲስ ነገር ነው።

ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አዳዲስ ነገሮች በርካቶች ናቸ።፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ማደራጀትና ለሥልጣን መፎካከር፤ ምርጫ፤ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ወዘተ። ስለሁሉም ማተት አንባቢ የሚያውቀውን ነገር እያወሱ ማሰልቸት ነው። ይሁን እንጂ፤ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ወደሆነው  ባለፉት ሃያአምስት ዓመታት ያለማቋረጥ፤ ከፍ ወይም ዝቅ ሳይል እንደጉንፋን አመቺ ወቅት እየጠበቀ ብቅ የሚል አንድ ጉዳይ ለመሸጋገር ያህል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሁኔታ በአጭሩ ለመመልከት ወድጃለሁ።

የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የሚለው እሳቤ ለኢትዮጵያ አዲስ ነበር። በ1960ዎቹ ማገባደጃ አንድ መሪ ኮሚኒስት ፓርቲ ለመመስረት በተለያየ መለያ ተደራጀተው ከነበሩትና በኋላ በውህደት ሳይሆን በጠመንጃ በመጠፋፋት ካከተሙት አምስት የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት (ኢማሌድህ) ፓርቲዎች ውጭ ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያያ አመለካከት የተደራጁና አመለካከታቸውን በይፋ እያራመዱ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን ለመረከብ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተናገዳ አታውቅም። ይህ ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ መገለጫ ነው።

አሁን በአገሪቱ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው በይፋ አቋማቸውን የሚያራምዱ ፓርቲዎቸ ከሰባ በላይ ናቸው። ብዙዎቹ በአመለካከት የማይለያዩ በመሆናቸው ቁጥራቸው መበራከቱ እንደመልካም ነገር ባይወሰድም፤ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠው በአመለካከት የመደራጀት መብት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል። እነዚህ ከ70 የማያንሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ የተካሄዱ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫዎች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል። እርግጥ በተለይ በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ በቂ እጩ ማቅረብ ባለመቻልና አካባቢያዊ ውክልናውን ዝቅ አድርጎ በመመልከት፤ በሌላም ምክንያት በዚህ ምርጫ ላይ ያልተሳተፉ ፓርቲዎች መኖራቸው አይካድም።

ከምርጫ ፉክክር ውጭ በሕገ መንግሥት በተረጋገጠው ሃሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት በመጠቀም በመንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እንዲሁም የራሳቸውን አቋም ያለምንም ክልከላ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። አሁንም ይህን እያደረጉ ነው። በዚህ ረገድ የሚያሳማ ነገር ካለ ተቃውሟቸውንና አቋማቸውን ማሰማት ባለመቻል ሳይሆን ከሰላማዊ የተቃውሞ ያፈነገጠ ከሕግ  አኳያም ወንጀል፤ ከፖለቲካ ሥነ ምግባር አኳያም ጸያፍ የሆኑ አካሄዶች መኖራቸው ነው። ይህ አንድም ከዴሞክራሲ ባህል አለመጎልበት፤ አሊያም ደግሞ ካለፉት አሃዳዊ አምባ ገነን ሥርዓቶች ከተላቀቅን ገና የአንድ ትውልድ እድሜ ሰላልተሻገርን ያለፉት አመለካከቶች አሁንም ያሉ በመሆኑ ነው። እናም በሂደት እየጠራ የማይሄድበት ምክንያት የለም።

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እነዚህንና ሌሎችንም አዳዲስ ነገሮች አይተናል ማለት ግን ሥርዓቱ ፍፁም ነው ማለት አይደለም። ብዙ ችግሮች አሉበት፤ በዙ ፈተናዎችም አሉበት። እንግዲህ ባለፉት ዓመታት አዳዲስ ነገሮች መመለከት ብንችልም፤ በዚሁ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ዘመን ውስጥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በእጅጉ እየተለዋወጡ ቢመጡም፤ ምንም ሳይለወጡ ቃናቸው እንኳን ሳይቀየር በአመዛኙ ሕጋዊ ሆነው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ አልፎ አልፎ ውጭ ባሉትና የኃይል መንገድ በመረጡ ቡድኖች ታጀቦ የሚቀረብ ጉዳይ አለ። ይህም ብሄራዊ እርቅ ይደረግ፤ ከአገር ሽማግሌ፤ ከምንትስ፤ ቅብጥርስ የተወጣጡ ሰዎች የተካተቱበት የሽግግር መንግሥት ወይም ባለአደራ መንግሥት ይመስረት ወዘተ. የሚል ነው። ይህ ጉዳይ አንዳንዴ ምርጫን፤ በአገሪቱ የተለያዩ  አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችንና መሰል አጋጣሚዎችን በማስታከክ ነው የሚቀርበው፤ ምንም አዲስ ነገር ሳይኖር፤ በተለይ በውጭ ሚዲያ የመናገር እድል ሲገኝ “ብሄራዊ እርቅ ካልተሰማ ሃገሪቱ ልትጠፋ ነው” የሚል ሟርት ይሁን ምኞት የማይታወቅ ወሬ የሚሰማበትም አጋጣሚ አለ። ሰሞኑንም ይህ ጉዳይ በአንዳንድ ሕጋዊ ሆነው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲነሳ ተደምጧል።

በመሆኑም፤ ይህን አደናጋሪና ሁሌም የሚነሳ የማይለማ ወይ የማይጠፋ ወሬ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ከሕገ መንግሥቱ አኳያ መመለከት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህ አጋጣሚን እየጠበቀ አንዳንዴም እንዲሁ እያፈተለከ በዋናነት ሕጋዊ እውቅና አግኝተው በምርጫ ላይም አየተፎካከሩ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሲቀርብ የሚደመጥ አስተያየት ሰጪዎች ችላ ያሏቸው ወይም ሊያስታውሱ ያልፈቀዷቸው መሰረታዊ እውነታዎች አሉ።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በብሄሮችና ብሄረሰቦች መካከል የነበረ የተዛባ ግንኙነት በማቃናት በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ በመካከላቸው የነበረውን የበታችነትና የበላይነት ስሜት፤ በጥርጣሬ መተያየት አስቀርቶ እንዲተማመኑ አድርጓል። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የቃልኪዳን ሰነድነት የጸናው መተማመን የሕዝቦች አንድነት ያላት አገር መመሰረት አስችሏል። ይህ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመተማመን በእኩልነት ለመኖር ተስማምተው የመሰረቱት የሕዝቦች አንድነት ያለው ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በአገሪቱ ሰላም አውርዷል። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የኖርንበት ሰላም በሕገ መንግሥቱ የተፈጠረ እርቅና መተማመን ውጤት ነው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖራቸው ተማምነው ቃል በተጋቡት ብሄሮችና ብሄረሰቦች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን፤ ይህ አለመግባባት ለግብታዊ ውሳኔ የተተወ ሳይሆን የሚፈታበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተበጅቷል። ይህም ጥያቄው የሕዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥና በሕዝብ በሚወሰን ሥርዓት እስከመገንጠል የዘለቀ መብትን የሚጨምር ነው። እናም ሽማግሌ ሰብስቦ ለእርቅ ለመቀመጥ የሚያስገድድ አንዳችም ነገር የለም።   

የብሄሮችና የብሄረሰቦች የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው። በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 8 ላይ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚል ርዕስ ስር፤

  • የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው።
  • ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው።
  • ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደረጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል።

ተብሎ ተደንግጓል።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዘጠኝ ክልሎችና ክልሎቹ በሚወከሉበት የፌዴራል መንግሥት የተዋቀረው የአገሪቱ የመንግሥት ሥርዓት ባለቤቶች ናቸው። በአገሪቱ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል አለመግባባት ቢፈጠር፤ የሚፈጠረው በእነዚህ በአመዛኙ በብሄርና ብሄረሰብ ማንነት ላይ ተመስርተው በተዋቀሩ የአገሪቱ ክልሎች መካከል ነው። ይህ ሲሆን ክልሎቹ ለብሄራዊ እርቅ አብረው ለመኖር የተሰማሙበትን ሕገ መንግሥት የመከለስ፤ በሁሉም ስምምነት ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ከዚህ ውጭ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠውን ዴሞክራሲና በብሄር ላይ በመመስረት የተዋቀረውን ፌዴራላዊ ሥርዓት አልፈልግም ብሎ አኩርፎ የሸሸ ሁሉ ብሄራዊ እርቅ የሚባል ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም። ይህ ጥያቄ ጠብ በሌለበት እርቅን ከመጠየቅ አይለይም።

የአገሪቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት የማስቀጠል አሊያም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እንዲፈርስ የማድረግ መብትም አቅምም ያላቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 መሰረት የአገሪቱ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የሆኑት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ ናቸው። ማንም ተነስቶ በአገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ የመወሰን፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አፍርሶ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ሥልጣን የለውም። ይህ ታዋቂ ሰዎች፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ ወዘተ. ሰብስቦ የሽግግር መንግሥት፤ የባለአደራ መንግሥት መመስረት የሚባለው ሃሳብ በራሱ ትርጉም የሌለው መሆኑን ያመለክታል። የአገሪቱ ሥልጣን ያለው በብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ነው።

እነዚህ ብሄራዊ እርቅ የሚል መሰረተ ቢስ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች በአገሪቱ ብዝሃነት ተጨፍልቆ አንድ የብሄራዊ ማንነትና አመለካከት ይኑር፤ ይህን ብዝሃነትን የመጨፍለቅ እርቅ እንመስርት እያሉ ከሆነም ጥያቄያቸው ትክክል አይደለም። ብዝሃነትን በማቅለጥ አንድነት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ኢሰብአዊና ኢዴሞክራሲያዊ ነው። ብዝሃነት ችግር ሳይሆን መቀጠል የሚችለው ለብዝሃነት እውቅና በመስጠት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማስተናገድ ነው። በኢትዮጵያ የብሄርም ሆነ የአመለካከት ብዝሃነት በሕገ መንግሥቱ ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አገር ናት። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ብዝሃነት ችግር ሳይሆን ሰላምን ማረጋገጥ የተቻለው ሕገ መንግሥቱ ብዝሃነትን ተቀብሎ ማስተናገድ በመቻሉ ነው።

አናም ይህ ሁከት በተቀሰቀሰ ቁጥር የሚቀርብ የብሄራዊ እርቅ ይደረግ፤ የሽግግር መንግ|ት ይመስረት፤ ወዘተ. የሚል ጥያቄ መነሻ በአገሪቱ በሕገ መንግሥት እርቅ መውረዱን ካለማወቅ፤ ምናልባትም ብሄራዊ እርቅ በሚል ሽፋን ከምርጫ ውጭ ወደሥልጣን ጠጋ ማለት የሚያስችል እድል ይገኛል የሚል ግምት ይመስለኛል። በአጠቃላይ፤ ለአገራዊ ወይም ለብሄራዊ እርቅ ልዩ ሸንጎ መጥራት የሚያስፈልገው አንድ፤*- በአገሪቱ ባለቤቶች መካከል ጠብ ሲኖር፤ ሁለት፤- ጠብ ሲነሳ የሚስተናገድበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይኖር ሲቀር ነው። በሕገ መንግሥቱ መሰረት የመስተናገድ መብት እያላቸው ከሥርዓቱ ያፈነገጡ ወገኖች አጋጣሚ እየጠበቁ የሚያቀርቡት “ብሔራዊ እርቅ” የሚል ጥያቄ የሞኝ ጥያቄ ነው። ጠብ በሌለበት እርቅ ትርጉም የለውምና!