ታከለ አለሙ
ሀገርም ሆነ ህዝብ ካለመንግስት የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ በሚፈጠር ሁከትና ትርምስ መንግስት አልባ የሆኑ ሀገራት የገጠማቸውን ፈተናና መከራ መግለጽም መናገርም ከሚቻለው በላይ ነው፡፡ ህገወጥነትና ስርአት አልበኝነት ሲሰፍን፣ ህግና ስርአት የሚያስከብር ሲጠፋ፣ ለዜጎች ህይወትና ንብረት ዋስትና የሚሆን የለም፡፡ በየዘመኑ መንግስታት ነበሩን፤ ለዛውም ከማንም በፊት፡፡ ዛሬም መንግስት የለም ለሚሉት ወገኖች መንግስት አለ፡፡ መሰረታዊ የሆኑ ችግሮቹን መፍታትና የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይጠበቅበታል ማለት ነው እንጂ ተገቢው ጉዳይ መንግስትማ አለ፡፡
መንግስትን ማረምና ማስተካከል ሀላፊነቱ የህዝብ ነው፡፡ አዎን ህዝብን ያስመረሩና መንግስት የለም እስኪል ድረስ ያደረሱት ሙሰኞች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ መልካም አስተዳደርንና ፍትህን የረገጡ፣ የደፈጠጡ፣ ህዝብንም አምላክንም ምን ታመጣላችሁ የሚሉ፣ በግፍና በደል ጫንቃቸው የደነደነ ነውረኞች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ቢሆንም ከህዝብ ጋር ቆሞ ለማስተካከልና ስህተቱን ለማረም የሚችል ጠንካራ በህዝብ የተመረጠ መንግስት አለ፡፡
የህዝብን መብትና ስልጣን፣ ሀብትና ንብረት እንደ ግል ንብረታቸው ቆጥረው ጠያቂ የለንም ማነው የሚነካን በሚል የሰከሩ ዝንተ አለም እንኖራለን ብለው የሚያስቡ፣ አይነኬዎች ነን ብለው የሚታበዩ፣ ስልጣን የህዝብ መሆኑን ጭርሱን የረሱ ያሉ ቢሆንም ይህንን ሊያርም፣ ሊያስተካክልና ስርነቀል ለውጥ ማምጣት፣ አወቃቀሩንና አደረጃጀቱን በመለወጥ የህዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ ሊመልስ የሚችል መንግስት አለ፡፡ ካልመለሰም ህዝብ በምርጫ ካርዱ የሚሸኘው መሆኑን አሳምሮ የሚያውቅ መንግስት አለን፡፡
ህግና ስርአት መንግስት ከሌለ በሀገሪቱ ውስጥ በሚፈጠር አለመረጋጋትና ተቃውሞ አጋጣሚውን ለመጠቀም አሰፍስፎ የሚጠብቀው የተደራጀ የዘራፊና የቀማኛ ቡድን በሀይል በመታገዝ ይህ ቀረው የማይባል ድርጊት እንደሚፈጽም፣ ለምንም ነገር ርህራሄና ይቅርታ እንደሌለው ቀውስና ትርምስ የመፍረስና የመበተን አደጋ ገጥሟቸው ከነበሩ በርካታ የአፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ታይቷል፡፡ እኛም ዘንድ፣ ይህ እንዳይሆን መጠንቀቅ ለሀገርም ለህዝብም ይጠቅማል፡፡
ሶማሊያ መንግስት አልባ ሁናና ተበታትና ከ27 አመታት በላይ ስትዘልቅ ጉልበተኛ የመንደርና የጎበዝ አለቆች የራሳቸውን የታጠቀ ቡድን በየጎጡ አደራጅተው ሲዋጉ፣ አንዱ አንዱን ሲዘርፍ ከዚያም አልፎ የህዝቡ መደበኛና ሰላማዊ ህይወት ተናግቶ፣ መንግስታዊና ማሀበራዊ ተቋማት ፈርሰው ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጥፋትና ውድመት ተከስቶ አይተናል፡፡ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ቦስኒያ ሄርዞጎቢኒያ፣ ኢራቅን በቅርቡም ሊቢያን፣ ሶርያን፣ የመንንና ሌሎችንም በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በትርምስና በእርስ በእርስ መቋሰል ህዝብ የተላለቀበት፣ ህግና ስርአት የጠፋበት በእልህና ትንቅንቅ› ሀብትና ንብረት የወደመበትን አስከፊ ታሪክ በእኛው ዘመን አይተናል፡፡
ህዝቡ ውስጥ የሚነሳው ተበድያለሁ፣ መብቴ ተረግጦአል፣ አምባገነንነት ሰፍኖአል፣ ባለስልጣናት የሀገርና የህዝብ ሀብት ዘርፈዋል፣ በህዝብ ስልጣን ያለአግባብ ተጠቅመዋል፣ ከስልጣን ይውረዱ፣ ይልቀቁ ወዘተ ጥያቄዎች ህጉንና ስርአቱን ተከትሎ ተኪዎችን ሳያዘጋጅ የተደራጀና ማንኛውንም ሀላፊነት ለመውሰድ በሰላምና በስርአት ለመምራትና ለማስተዳደር የሚችል ሀይል በሌለበት ቢራመድ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ይሄንንም ሰክኖ ማሰብ ይጠይቃል፡፡
የብዙ ሀገራት የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የህዝብ እልቂትና ስደት መነሻውም ይሀው ነው፡፡ መንግስት የሌላት ሀገር ካፒቴን የሌላት መርከብ መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ ብዙ ሀይሎች አሉ፡፡ ሕዝብ ደግሞ አይቀበልም፡፡ መንግስትን የመረጠ ህዝብ መንግስት ስህተቱን አርሞ ከህዝብ ጋር ያቃቃረውን መሰረታዊ ችግር ፈትቶ ህግና ስርአቱ ህዝብን ባከበረና ባስከበረ መልኩ እንዲጠበቅለት ይፈልጋል፡፡
በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተአሚኒና ተደማጭ የሆነ ድርጅት ወይም ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ በህዝቡ ውስጥ በደሉንና ምሬቱን በመንተራስ ብቻ በስሜታዊነትና በጥላቻ ገንፍሎ የሚወጣ ተቃውሞ ሁሉም በመሰለውና በመረጠው መንገድ የሚሄድበት በመሆኑ የመጨረሻው ውጤት ተው የሚል መካሪ በሌለበት የከረረው ተቃውሞን፣ የሀገር መመሰቃቀልን፣ የህግና የስርአት መጥፋት የስርአተ አልበኝነት መስፈንን፣ የእርስ በእርስ ትርምስና ግጭትን ያስከትላል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግስትና ህዝብ በአንድ ቆመው ሊመክቱ ግድ ነው፡፡ ሁኔታው ህዝብን ለዘራፊዎችና ለቀማኞች ሲሳይ ከማድረጉም በላይ ማንም ሰው ለራሱም፣ ለቤተሰቡም የህይወትም ሆነ የንብረት ዋስትና የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም፡፡ ለእለት ፍጆታ የሆኑ ጉዳዪችን በተመከተ እንኳ ግብይት ማደረግ አይታሰብም፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ዋስትና የለውም፡፡ ይሄንን ነው ባለፉት 20 እና 30 አመታት በበርካታ ሀገራት ውስጥ ያየነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ዘግናኝና አስከፊ ሁኔታ በሀገራችን ተፈጥሮ ማየት ደግሞ የሚፈልግ ህዝብ የለም፡፡
ትርምስ፣ ሁከት ብጥብጥ፣ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር፣ ሰላም እንዲጠፋ በእጅጉ የሚሹ፣ ከነዚህ ሁሉ ማትረፍ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ሀይሎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የመንግስት መኖር የህግና ስርአት መከበር ለሀገርም ለህዝብም ወሳኝ ነውና መንግስት እያሰበበት ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡
በነዚህ ሁሉ ጠፖለቲካዊ፣ አዚኮኖሚዊና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች መሀል በሚሊዮን/ቢሊዮን የሚነግዱ፣ ሰላም እንዲደፈርስ ቀን ከሌሊት የሚሰሩ፣ ገበያቸው እንዲደራላቸው የሚሯሯጡ ሀይሎች በገፍ ስለመኖራቸው ማንም አይጠራጠርም፤ አሉ፡፡ በስክነት በሰላምና በመረጋጋት በመደማመጥ ማንኛውንም አይነት ችግርና አለመግባባትን የሚፈቱ የፖለቲካ አካሎች መንግስትም ሆነ ተቃዋሚው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ከታላቅ ጥፋትና ውድመት ይታደጋሉ፡፡ አስፈላጊም ናቸው፡፡
በእልህ፣ በከፋ ጥላቻ፣ በጀብደኝነት የተሞሉና ማን ምን ያመጣል የሚሉ፣ በሁለቱም ጎራ የሚገኙ እብሪተኞች መተላለቅና መጠፋፋትን በመምረጥ ሀገርንና ህዝብ ወደከፋ ጥፋትና ውድመት ይወስዳሉ፡፡ የነበረው ሁሉ እንዳልነበር ሁኖ ይጠፋል፡፡ በሁለቱም ጎራ ያሉ ጽንፈኞች ለሀገሪቱም ለህዝቡም፣ ሌላው ቀርቶ ለራሳቸውም አይበጁም፡፡
ህዝብ የሀገሩን ሰላም አጥብቆ ይፈልጋል፤ ለሰላሙም ይቆማል፡፡ መንግስትም ማረም ያለበትን እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ስህተቶቹን እንዲያርም፣ ጥገናዊ ሳይሆን ጥልቀት ያለው መሰረታዊ የተሀድሶ ለውጥ ያመጣ ዘንድ ይጠበቃል፡፡ በሌሎች ሀገራት እንዳየነው በመንግስት ሀይሎችና በተቃዋሚው መካከል በተፈጠሩ ትንቅንቆች የሰለጠኑ፣ ያደጉና የለሙ ከተሞች እንዳልነበሩ ሁነው ወድመዋል፡፡ በነዚሁ አካላት አለመግባባት ምክንያት የመሰረተ ልማት አውታሮች፣ ማህበራዊ ተቋማት፣ ቤተክርስትያኖች፣ መስጊዶች፣ ታሪካዊ ቅርሶች ወዘተ ሁሉ ወድመዋል፤ ህዝቡ ሞቷል፤ ተሰዶአል፤ አካለ ጎደሎ ሆኖአል፡፡
የሀገር ልማትና እድገት ከህዝብ ሰብአዊና መሰረታዊ መብቶች መከበር ጋር አብሮ ማደግ ካልቻለ አደጋ አለው፡፡ በየሀገራቱ በተደረገው ጦርነት የእርስ በእርስ ግጭት የትም ወድቆ የቀረውን ለማወቅ አይቻልም፤ ምግብም ሆነ ውሀ የለም፡፡ የከፋው ክፉ ቀን የሚባለው አይነት መሆኑ ነው፡፡ አርቆ ስለሀገርና ስለህዝብ አለማሰብ የሚያመጣው ጣጣና ጥፋት መመለሻም ማካካሻም የለውም፡፡
ምንግዜም፣ ስህተቶቹን እያረመ የህዝብን የበላይነት ተቀብሎ በህጋዊ የምርጫ ስርአት የሚያምን፣ የህዝብን ችግር የሚፈታ መንግስት መኖር ወሳኝ ነው፡፡ በመንግስት አለመኖር በሰላም መኖርና በሰላም መደፍረስ መሀል ስላለው ገደል ከሌሎች ሀገራት ልምድ ብዙ አይተናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ አክራሪና ጽንፈኛ እስላማዊ ሀይሎች በአንድ ወገን አለም አቀፉ ማፍያ በሌላ ወገን የደራ ገበያ ስለሚያገኙ ሰተት ብለው ይገባሉ፤ ያሻቸውን ይሰራሉ፡፡ የጦር መሳሪያ የሚያሰማራ የሰው ሀይል በብዛት ያገኛሉ፡፡ ህዝቡ አማራጭ ስለሌለው ያለማመንታት ጥያቄአቸውን ተቀብሎ ይሰለፋል፤ ይታጠቃል፣ አሰልጥነው ያሰማሩታል፡፡ እልቂቱ ውድመቱ ይከፋል፡፡
እነአልቃይዳ፣ እነአይሲስ፣ እስላሚክ ሌቫንትና ሌሎቹም በዚህ መልኩ ነው አቅምና ጉልበት አግኝተው አድማሳቸውን በማስፋት አለምን ያስጨነቀ ስውራዊ ሲላቸውም በገሀድ የሚዋጋ ሀይል ሁነው የወጡት፡፡ ዛሬ ሊቢያ እንዳልነበረች ሆና የአክራሪዎች መፈንጪያና መንግስት አልባ እስከመሆን በውድመት ውስጥ ስትራመድ ያ አምባገነን የተባለውና በግፍ እንዲጠፋ የተወሰነበትን ጋዳፊን ምእራባውያኑ ቢመኙትም የማይመለስ ነገር ሆነ፡፡ የመንግስት መኖር ለአንድ ሀገር ወሳኝ ነው፡፡
ምእራባውያኑ በኋላ ላይ የጥፋትና ውድመቱን መጠን አይተው ሊቆጣጠሩት እንደማይችሉም ከተረዱ በኋላ በሊቢያ፣ ኢራቅ ወዘተ የሰሩትን የገዘፈ ስህተት አምነው ቢቀበሉም ወደኋላ ማስተካከያ የሚደረግለት ነገር የለም፡፡ የጠፋው የሰው ህይወት ጠፍቶአል፡፡ የወደመው የሀገር ንብረትና ቅርስ ወድሞአል፡፡ የተዘረፈውም የሀገር ሀብት ድንበር ተሻግሮ ወጥቶአል፡፡ ቀድሞ የነበረውን የተረጋጋ ሰላም በምንም መልኩ ሊመልሱት አልቻሉም፡፡ ዋነኛው ተጎጂ የየሀገሩ ህዝብ ሆነ፡፡ መንግስት አልባ በመሆን እዳው ብዙ ነው፡፡
መንግስት አልባነት ሀገርና ህዝብን ታላቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ያለውን ጠብቀን ስህተቱን አርሞ የህዝብን ድምጽ አክብሮ እንዲሄድ የዲሞክራሲ በሩን አስፍቶ የተለያዩ ሀሳቦች በነጻነት እንዲንሸራሸሩ፣ እንዲሰሙ፣ እንዲደመጡ እንዲያደርግ፤ በቃህ ሲባልም የሚሰማ፣ ለተሻለ ሀገራዊ ተስፋዎችና አማራጮች እድልና በር እንዲከፍት ግፊት ማድረግ ከህዝቡ ይጠበቃል፡፡ ወደ መንግስት አልባነት ማምራት የለብንም፡፡ መንግስት አለን፤ ለዛውም ጠንካራ መንግስት፡፡
በየሀገሩ በተነሳው ሁከትና ትርምስ አመጹ ከመንገድ በመውጣቱ የፈረሰው የአረቡ ሀገራት ፕሮፌሽናል ሰራዊት በተለይ በኢራቅና በሊቢያ በአብዛኛው የተቀላቀለው አልቃይዳንና አይሲስን ነው፡፡ ታላቅ የጥፋት ሀይል ሁኖም ብቅ ያለው እሱው ነው፡፡
በአረቡ ሀገራት ተሞክሮ ስናይ መጀመሪያ ነበር ነገር ሳይበላሽ፣ ሰላም ሳይደፈርስ፣ ሀገርና መንግስት ሳይፈርስና ባዶ አወድማም ሳይሆን፣ አክራሪና ጽንፈኛ ተቀዋሚውም ሆነ ግትርና ስልጣን ወይም ሞት ያለው የወቅቱን ስልጣን ይዞ ይመራ የነበረው መንግስት ስለሀገርና ስለህዝብ ሲባል ሰክነው፣ ተረጋግተው፣ ተደማምጠው ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣት የነበረባቸው፡፡ ከረፈደ በኋላ ሰላማቸውን ለመመለስ አልቻሉም፡፡
በተለይ የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም የዘረፉትን ሀብትና ንብረት በሀይል የጠበቁና ያስጠበቁ እየመሰላቸው የህዝብን ሀያልነትና ወሳኝነት በመርገጥ በሀይል አንበርክከን ደፍቀን እየገደልን እንኖራለን በሚል ታንክ መድፍና የጦር ጀት ድረስ ያሰለፉት የኢራቅን፣ የሊቢያን፣ የየመን፣ የሶርያን ወዘተ መሪዎች እንዲሁም በውጭ ሀይሎች ቆስቋሽነት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየፈሰሰለት ህዝቡን አምርሮ፣ እንዲነሳ በከፋ ጥላቻ ተውጦ የገዛ ሀገሩን እንዲያወድም ያደረጉት ተቃዋሚዎች ሁለቱም ጭፍንና እብሪተኛ ሀይሎች ለየሀገራቸው ውድመትና ለህዝባቸው እልቂት በታሪክና በትውልድ ተጠያቂ ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው የሰለጠነ፣ የሰከነ፣ በሰላምና በመነጋገር የሚያምን የፖለቲካ ባህል ስለሌላቸው መሰረቱም ስላልነበረ ነው፡፡ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያምኑ የቱንም ያህል ህዝባዊ ተቃውሞ ቢኖር በህጉና በስርአቱ የሚያስተናግዱ የሚራመዱ ከሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ይችላሉ፡፡
የህዝቡ ተጽእኖ እጅግ የበረታ በሚሆንበትም አጋጣሚ በሰላማዊ ምርጫ ህዝብ አሸናፊ ሁኖ ሀገር ሳይጠፋና ሳይወድም እልቂት ውስጥ ሳይገባ ደም መፋሰስም ሳይከተል ህዝብ የመረጠው መንግስት ስልጣን እንዲይዝ ተደርጎ ሀገርም እንደ ሀገር ትቀጥላለች፡፡ ስልጡን እሳቤ፣ ስልጡን መሪዎች፣ ስልጡን ህዝብ የሚያደርገው ይሄንኑ ነው፡፡
የሰለጠኑትና የበለጸጉት ሀገራት በምርጫ ዘመን ለተወዳዳሪነት የሚቀርቡትን ፓርቲዎች አይተውና መዝነው የቱንም ያህል በመስመር ቢለያዩና ቢተናነቁም በመጨረሻው የህዝቡ ድምጽ ወሳኝ ሁኖ አሸናፊው በትረ ስልጣኑን ተረክቦ እስከተወሰነለት የአገልግሎት/ስልጣን ዘመን ድረስ ለሀገሬ ይበጃል የሚለውን ይሰራል፡፡ ህዝቡ ከፈቀደው ለሁለተኛ ግዜ ዳግም ሊመርጠውም ይችላል፡፡ ሀገሪትዋም ህዝቡም ሰላማቸው አይደፈርስም፡፡ ንብረታቸው አይወድምም፡፡
ዜጎች የህይወትና የንብረታቸው ዋስትና የሀገራቸውና የሰላማቸው ጠባቂ የሆነው መንግስት በሰላማዊ ምርጫ ህግና ደንብ መሰረት በአዲስ መንግስት ተተክቶ ይቀጥላል እንጂ አይፈርስም፡፡ በአፍሪካና በኤሽያ ይህ የሰለጠነ ሁኔታ ስለማይታይ ገዢ ፓርቲዎች አንድ ግዜ ስልጣኑን ከያዙ ስለማይለቁ በአብዛኛው ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ግጭትና የደም መፋሰስ ሲከሰት ይታያል፡፡ የሀገር ህልውና የህዝብ ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ወድቆ የሚታይበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ በህዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግስት መኖር ወሳኝነት አለው፡፡
መንግስት በህግና በስርአት ሊመራና ሊያስተዳድር ሳይችል ቀርቶ በአግባቡ ተተኪ የሆነ ሀላፊነቱን ወስዶ ሀገሪቱንና ህዝቡን ሊመራና ሊያስተዳድር የሚችል አካል በሌለበት ሁኔታ ከፈረሰ በሀገሪትዋና በህዝቡ ላይ የሚፈጠረው አደጋ ሊታሰብና ሊገመት ከሚችለው በላይ ይሄዳል፡፡ መንግስት ከሌለ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይቻልም፡፡ የህይወትም የንብረትም ዋስትና የለም፡፡ የመንግስት መኖር ለሀገርም ለህዝብም ይጠቅማል፡፡
በሰብአዊ መብት፣ በዲሞክራሲ፣ በመናገርና በፕሬስ፣ በመደራጀት ወዘተ ረገድ ገዢው ፓርቲ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ትችቶች ይቀርቡበታል፡፡ የገዢው ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ አባላት የህዝብን መብት በመርገጥ ህዝብ በምርጫ የሰጣቸውን የድጋፍ ድምጽ ቀልደውበታል፡፡ ሀላፊነትና አደራ ለመሸከም አይበቁም ሲል ተቃዋሚው ይከሳል፡፡ በዚህም ረገድ ከጥልቀታዊው ተሀድሶ መልስ ይጠበቃል፡፡
ትላንትም ዛሬም የነበረው ኢህአዴግ ሲሆን በውስጡ ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ሀይል የበላይነቱን ይዞ ሲፈነጭ ለምን በዝምታ ማየትን መረጠ የሚለውም የህዝብ ጥያቄ በሰፊው ይደመጣል (ይህ ማለት የጥልቀታዊው ተሀድሶ ምላሾች በጉጉት ይጠበቃሉ ማለት ነው)። በእስከዛሬው ቆይታ ኢህአዴግ ይህንን ለመለወጥ ያደረገው/የወሰደው እርምጃ ምንም የለም፡፡ የዛሬው ጥልቀታዊ ተሀድሶ እስከ ምን ይዘልቃል የሚለው ወሳኝ ጥያቄም ይነሳል፡፡
ጥልቀታዊው ተሀድሶ እስከምን ይራመዳል? ወይስ ተመሳሳይ ሰዎችን አንዱን አውርዶ ሌላውን በመተካት ለውጥ ይመጣል ብሎ ያምናል የሚለውም ጥያቄ በሰፊው ይነሳል፡፡ ጥልቀታዊው የኢህአዴግ ተሀድሶ ከተለመደው አካሄድ ውጪ በርቀት ተራምዶ ህዝብን የሚያረኩ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ይጠበቅበታል (ይህ ማለት ግን ግለሰቦችን መለዋወጥ ላይ ያተኮረ ነው ማለት አይደለም፤ ስርአቱን እንደ ስርአት፣ ፓርቲውን እንደ ፓርቲ ህመሙን ይመረምራል ማለት እምጂ)። መንግስትም መስራት ያለበትን በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡
ኢህአዴግ በተሀድሶ ስም የነበሩ ሰዎችን መልሶ ወደስልጣን ካመጣ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም አይነት መሆኑ ነው የሚለው ሰፊ የህዝብ አስተያየት ይደመጣል፡፡ ጥገናዊ ለውጥ የህዝብን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት አይችልም፡፡ ለቁስሉም መፍትሄ አይሆንም ሲል ህዝቡ ሳይቆጥብ ይናገራል፤ ስርነቀል ለውጥ መምጣት አለበት የሚለው ይህ የህዝብ አስተያየት ሚዛን ይደፋል፡፡ መንግስት አለ፡፡ ህዝብን ካስከፉና ካስመረሩ መሰረታዊ ስህተቶች የሚማር የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ የሚመልስ መሆን መቻል ይጠበቅበታል፤ መንግስት፡፡