ዳግም ጥልቅ ተሃድሶውና አንዳንድ የሚነሱ ብዥታዎች

                                          

ገዥው ፓርቲና መንግስት በተለያዩ ወቅቶች በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ “ዳግም በጥልቀት እንታደሳለን” ማለታቸው አይዘነጋም። ይህን የመንግስትንና እርሱን የሚመራው የኢህአዴግን አቋም ተንተርሰው ግን አንዳንድ ኃይሎች የጥልቀት ዳግም ተሃድሶውን ከመንግስት ፍርሃትና ማርጀት እንዲሁም ውሳኔ ካለመስጠት ብሎም ጥልቁን ተሃድሶ ከሰዎች ሹም ሽር ጋር ሊያገናኙት ይሞክራሉ። በዚህም የተለያዩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመበተን ህዝቡን ለማደናገር ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ማረም ስለሚገባም እኔም በበኩሌ ብዕሬን እንዲህ አንስቻለሁ።

እንደሚታወቀው ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ያለፉ 15 ዓመታትን የተሃድሶ ጎዞን በሚገባ ገምግመዋል። በግምገማቸውም መላው የሀገራችን ህዝቦችበልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተሰባስበው በገጠርና ከተማ በልማት፣ በዴሞክራሲና ሰላም አንፀባራቂ ድሎችን በማስመዘገብ የተሃድሶ መሰመሩን ህያው ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው የተሃድሶ መስመር በገጠር ብቻ ሳይወሰን በጥቃቅና አነስተኛ ስትራቴጂ የከተማ ህዝብ ኑሮ ለመቀየር ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ ማስመዘገብ መጀመሩንም ገልፀዋል። በዚህም ብዙ የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም በርካታ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ገቢራዊ መሆናቸው ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይም በትምህርትና በጤና የዕድገቱን መሰረት ለመጣል የሚያስችል ስራ መከናወኑም ተወስቷል።

ሆኖም ገዥው ፓርቲና መንግስት የነበሩትን ችግሮች ከመግለፅም አልተቆጠቡም። ሀገራችን እየተከተለች ባለችው ልማታዊና ዴሞክራሰያዊ መስመር በህዝቡ ተሳትፎ እነዚህ ድሎች ቢመዘገቡም፤ የተጀመረውን ለውጥ ወደ ኋላ የሚመልሱ፣ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የአመራር ጉድለት መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል። እነዚህ ችግሮች በህዝቡ ውስጥ ተስፋ ቆራጭነት እንዲያቆጠቁጥ ከማድረግ ባሻገር እስከ አመፅ የሚያደርስ ሁኔታን መፍጠራቸውንም አልካዱም።

የችግሮቹ መንስኤ ናቸው በማለትም ባለፉት 15 ዓመታት  የተመዘገበው ድል የፈጠራቸው ተጨማሪ ፍላጎቶችን በአግባቡ መልስ መስጠት አለመቻሉ፣ በመጀመሪያው በተሃድሶው ወቅት የተለዩትና የሥርዓቱ አደጋዎች መሆናቸው በግልፅ የተቀመጡት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በፅናት በመመከት ከምንጩ ለማድረቅ የተከናወኑት ስራዎች አናሳ መሆናቸውን ለይቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግስት ስልጣንን የግል ኑሮ ማደላደያ የማድረግ ፍላጎትና ተግባር መከሰቱ የችግሩ መንስኤ መሆኑ ተወስቷል። በዚህም ሳቢያ ገዥው ፓርተና መንግስት “ዳግም በጥልቀት እንታደሳለን” በማለት የተለያዩ ስራዎችን ጀምረዋል። ይህ ስራቸውም የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝብ እስከታች ድረስ ወርዶ ማወያየትን ያካተተ ነው።

እርግጥ ገዥው ፓርቲ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የሚያካሂደው ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ ጉያ ውስጥ ያደገ፣ የህዝቡን ጥያቄዎችን የሚያዳምጥና የመፍታት ባህልን ያዳበረ እንዲሁም የህዝብን ፍፁም የበላይነት ከመገንዘብ መንፈስ እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የተፈጠረውን ችግር ፈርቶ አይመስለኝም።

ለነገሩ ገዥው ፓርቲ የህዝብን አመኔታ ተቀብሎ ሀገሪቱን የማስተዳደር ኮንትራት የወሰደው ከህዝቡ በመሆኑ ህዝቡን ቢፈራው ምንም የሚደንቅ ነገር ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ህዝቡ የሰጠውን የኮንትራት ውል በፈለገው ጊዜ ሊነጥቀው ስለሚችል ነው። እናም መንግስት ህዝቡን የሚፈራው ለራሱ ሲል ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ውጪ መንግስት አንዳንድ በተቃውሞው መስመር የተሰለፉ ኃይሎች እንደሚሉት የህዝቡን ወሳኝነት በመከላከል ደረጃ አይደለም። ላድርገውም ቢል ፈፅሞ የሚችለው አይሆንም—አስተሳሰቡም ሆነ ድርጊቱ ከሚከተለው ዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ጋር ፈፅሞ የሚሄድ አይደለምና።

ይህ የገዥው ፓርቲ ትክክለኛ ለህዝቡ ምላሽ የመስጠት የዳግም ተሃድሶ ሂደት ከማርጀቱ ጋርም የሚያገናኘው ነገር ያለ አይመስለኝም። ከዓለም የፖለቲካ ሂደት ጋርም ፈፅሞ የሚቃረን ነው። አንድ ፓርቲ በዕድሜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ልምዶችንና ተሞክሮዎችን እያካበተ በዚያው ልክም ተተኪዎችን እያፈራ ብሎም ለሀገሪቱ የሚሻሉ መንገዶችን በብቃት የመቀየስ ስልትን ሲያሳድግ እንጂ በረጅም ጊዜው ምክንያት በመሸምገሉ ጥያቄዎችን የማይመልስ አይሆንም።

ለነገሩ 25 ዓመት ማለት በፖለቲካ ሂደት ረጅም ዕድሜ ተብሎ የሚጠቀስ አይደለም። ፓርቲው ራሱን እያጠናከረ የሚመራውን ሀገር ወደ ላቀ ደረጃ መምራት የሚችልበት አፍላ ጊዜ ይመስለኛል። እነዚህ ወገኖች ኢህአዴግን ‘ስላረጀ ምላሽ አይሰጥም’ የሚሉ ከሆነ በዓለማችን ላይ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩት የእነ ኮሪያን፣ ማሌዥያን፣ ጃፓንንና ደቡብ አፍሪካን ብሎም የአሜሪካ ፓርቲዎችን ምን ሊሏቸው ይሆን—ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ እስከ ሁለት ክፍለ ዘመኖች ድረስ ዕድሜን አስቆጥረዋልና። እናም ክርክራቸው ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኘሁትም። ይልቁንም በእኔ እምነት ኢህአዴግ በተግባር እየተፈተነ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ችግሮችን በተገቢው የመፍታት ቁመና እና አቅም አለው።

ከዳግም ጥልቅ ተሃድሶው ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ብዥታ መንግስት በያዝነው ወር መጨረሻ የሚደረገው የስልጣን ሽግሽግ የሁሉም ነገር ‘አልፋና ኦሜጋ’ አድርጎ የማየት ሁኔታ ነው። እርግጥ ‘በፓርቲ ኮፍያ ሹመት የለም’ የሚለው አባባል ማንኛውም የፓርቲውን እምነቶችንን አሰራሮችን የሚያስፈፅሙ ምሁራን ወደ መንግስት የስራ ኃላፊነት ይገባሉ የሚል ቢሆንም፤ የፓርቲው አባል ሆነው ብቃቱና አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ቦታ የላቸውም የሚል አንድምታን የያዘ አይደለም። የህዝቡንና የፓርቲውን አመኔታ የተጎናፀፉና የመስራት አቅሙ ያላቸው ምሁራንም ይሁኑ የፓርቲው አባላት ለሚፈለጉበት ቦታ ሊታጩ እንደሚችሉ ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በያዝነው መስከረም ወር መጨረሻ መንግስት ሁሉንም ባለስልጣናት ከስራቸው በማሰናበት እንደ አዲስ የሚዋቀር አስመስለው ሲናገሩ ይደመጣል። በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ትክክል አይደለም። ሁሉንም ነገር በአንድ ጀንበር መከወን አይቻልምና። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በግልፅ የሚታወቁና የአቅም ችግር ያለባቸው አመራሮች ትናንትም ይሁን ዛሬ መነሳታቸው አዲስ አይደለም። ነገም በገዥው ፓርቲና በመንግስት እንዲሁም በህዝቡ አመኔታ ካልተጣለባቸው ሊነሱ ይችላሉ። የመንግስት ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ የኪራይ መፈልፈያ ቦታ ባለመሆኑ ከዚህ አኳያ የሚታዩና በአፈፃፀም ረገድ ችግር ያለባቸው አመራሮች ተገምግመው በሌላ ሊተኩና መጠየቅ ካለባቸው ሊጠየቁ የግድ ነው።

ሆኖም ይህን ለማከናወን ጊዜ የሚጠይቅ ይመስለኛል። ሁሉም ነገር በ“የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት…” ዓይነት ቀመር ሊከናወን አይችልም። ከኢህአዴግ የግምገማ ባህል በመነሳት ሁሉም ችግሮች በያዝነው ወር መጨረሻ ይጠናቀቃሉ ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም። ግምገማው ከላይ ወደ ታችና ከታች ወደ ላይ እንዲሁም የጎንዩሽ አካሄዶች ያሉበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ነገሮች ለይስሙላ ሲባል ማፋጠን አይቻልም። ተገቢም አይደለም። በሚደረጉት የአሰራር ለውጦች ውስጥ ህዝቡ በየደረጃው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል። እናም ጊዜ የወሳኝነቱን ቦታ ይወስዳል ማለት ነው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢህአዴግ የሚያደርገው ማናቸውም ግመገማዎች የተጀመረውን መስመር የማጠናከርነና ይበልጥ በፅኑ መሰረት ላይ የማኖር እንጂ መስመር የማጥራት ጉዳይ አይደለም። እናም ሹም ሽር በሚኖርበት ወቅት ‘የትኛው አመራር የድርጅቱን መስመር ለማጠናከር ያግዛል? የትኛውስ ከድርጅቱ መርሆዎች ውጪ እየሰራ የህዝቡን ምሬት እያናረው ነው?’ የሚል ጥያቄ የሚኖር ይመስለኛል። ይህን ጥያቄ ለመመለስም ሁሉንም አመራር ማሰናበት የሚጠበቅበት አይመስለኝም። በኢህአዴግ ውስጥ ሁሉም አመራሮች መስመሩን የማያጠናክሩ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉምና።

እንደሚታወቀው ኢህአዴግና መንግስት የሚከተሉት መስመር ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ነው። ሀገራችን በዚህ መስመር ስር ተጉዛ ላለፉት 13 ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግባለች። ህዝቧም ከዕድገቱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው—ከተገኘው ዕድገት ጋር የተፈጠሩ ፍላጎቶችን በማርካት ረገድ የሚቀር ነገር ቢኖርም። እናም ሁሉም የኢህአዴግ አመራሮች ለመስመሩ እንቅፋት ቢሆኑ ኖሮ ይህ ዓለም የመሰከረለት ዕድገትና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ምሳሌ መሆን የቻለ ዕድገት ባልተመዘገበ ነበር። በመሆኑም አስተሳሰቡ ከነባራዊው ዕውነታ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

በአጠቃላይ በአንዳንድ ወገኖችና የመንገስትን ህዝባዊ ባህሪ በመጠምዘዝ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት በሚሯሯጡ ወገኖች አማካኝነት የሚነሳው የዳግም ጥልቅ ተሃድሶ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ከዚህ አኳያ መታየት ይኖርበታል። ዳግም ተሃድሶው ገዥው ፓርቲና መንግስት በውስጣቸው የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብንና ተግባርን ከምንጩ ለማድረቅ እንዲሁም ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንጂ የግል ጥቅም ማስፈፀሚያ እንዳይሆን የሚረዳ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ይህን ለመፈፀምም ስር ነቀል በሆነ መንገድ በየደረጃው የሚከናወን ተግባር በመሆኑ የጊዜ ዑደትንና ተግባራዊ ሂደትን ይጠይቃል። ስለሆነም ህብረተሰቡ በዳግም ጥልቅ ተሃድሶው ላይ ሆን ተብለውና የመንግስትን ጥረት ለማኮሰስ በማለም የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተሳሰቦችን ሳያዳምጥ፤ ገዥው ፓርቲና መንግስት በየደረጃው የሚያካሂዱትን የአሰራር በመደገፍ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ የሚጠበቅበት ይመስለኛል።