በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ከተቀመጡት መሰረታዊ መርሆዎች ውስጥ አንዱ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት ነው፡፡ መርሁ በህገ- መንግስቱ አንቀጽ 11፣ 25 አና 27 ላይ በማያሻማ ሁኔታ ተመልክቷል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ይህን መርህ መንግስት የጣሰው በማስመሰል ያልተገባ ምስል ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ፍፁም የተሳሳተ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ከራስ ፖለቲካዊ ዕይታ አንፃር መቃኘት በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማም መርሁንና ትክክለኛ አተገባበሩን ብሎም አሁን የሚገኝበትን ደረጃ ማሳየት ነው፡፡ ሆኖም ትናንት ከሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት አኳያ የነበረውን ሁኔታ በማሳየት፣ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የከፈሉትን መስዋዕትነት እንዲሁም መርሁን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም የተካሄዱ ያልተገቡ ተግባራትን መመልከት የተሟላ ምስል ስለሚሰጠን እነዚህን ሃቆች በቅድሚያ መቃኘቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖቶችና እምነቶች ባለሃብት እንዲሁም የተለያዮ እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት የሃይማኖት ብዙሃነት መገለጫ ሀገር ናት፡፡ መነሻቸው መካከለኛው ምሥራቅ እንደሆነ የሚነገርላቸው የክርስትና፣ እስልምና፣ የአይሁድና ሌሎች ሃይማኖቶች ብሎም ሀገር በቀል የሆኑ እምነቶችን ህዝቦቿ ተቀብለው በሰላም እምነታቸውን የሚፈፅሙባት ሀገርም ናት፡፡
ሆኖም ይህ የሃይማኖት ብዝሃነት በእኩልነት ላይ ከመመስረት ይልቅ፤ የአንድ የሃይማኖት የበላይነትን የማስፈኑ ጉዳይ የመንግስትነት ስልጣኑን ከተጨበጠው ገዥ መደቦች ጋር ዘመናትን ሲሸጋገር ቆይቷል፡፡ በዚህም የሀገራችን የሃይማኖት ብዝሃነት ከመለያነት የዘለለ ፋይዳ ሳይኖረው ዘመናትን ከማስቆጠር ባሻገር፣ የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን በተለያዩ ወቅቶች ለንባብ የበቁ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከሀገራችን የሃይማኖት ታሪክ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበራቸው ቀደምት መንግስታት ሃይማኖታዊ ብዝሃነቱን በአስተዳደራዊ መንገድ ለመጨፍለቅና ወደ አንድ ለማምጣት ያልጣሩበት ጊዜ አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡
በዚህም በአንድ በኩል “የክርስቲያን ደሴት” አስተሳሰብ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “የሙስሊም እምነት ተከታዮች የበላይነታቸውን መጎናፀፍ አለባቸው” የሚል እሳቤን ሰንቀው የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ገዥዎቹ የተከተሉት አቅጣጫ የሃይማኖት ብዝሃነት ባለባት ሀገር ውስጥ በመሆኑ፤ የአንድ ሃይማኖትን የበላይነት የማስፈን ፍላጎታቸውን እስከ መጨረሻው ሊያሳኩ አልቻሉም። ከዚህ በተጨማሪ የሃይማኖት የበላይነትን የማስፈኑ የገዥዎች ጥረት የግጭት መንስዔ ለመሆን በቅቶ፤ በተለያዩ የእምነት ተከታዮች መካከል ጥላቻና ብጥብጥ ሲያነግስ መቆየቱ የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሀገራችን የሃይማኖት ብዝሃነትን የምታንፀባርቅ ብትሆንም፤ በተጨባጭ ግን ብዝሃነቱን ማስተናገድ ተስኗት ዘመናትን ለመሻገር በቅታለች፡፡
ይህም ቀደምት ገዥዎች በተለያዩ ጊዜያት የተከተሏቸው መንገዶች በራሳቸው ዛቢያ ላይ የሚሽከረከሩና የሌላውን ሃይማኖት በእኩልነት የማየት አቅጣጫን የተከተሉ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው። በዚህም ሳቢያ ሃይማኖታዊ ጭቆናና በደል ያንገፈገፋቸው ዜጎቿ መብታቸውን ለማስከበር በየጊዜው ተንቀሳቀስዋል፡፡ ረጅም ዓመታትን ያሰቆጠረው ይህ የሃይማኖት እኩልነትንና ነፃነትን የማስፈን ትግል፤ በእኩልነትና በመቻቻል የመኖርን ራዕይ ሰንቆ ትክክለኛው አቅጣጫን በመከተል ለፍሬ ከበቃና ህጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ስራ ላይ ከዋለ እነሆ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሃይማኖታቸውና እምነታቸው ተከብሮ በእኩልነትና በመቻቻል መርህ የተመሰረተች አዲሲቷን ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ችለዋል፡፡ በመሆኑም ህዝቦች ከዘመናት የሃይማኖትና የእምነት ጭቆና ተላቀው ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩበትን፣ መንግስታዊ ሃይማኖት የሌለባትን ብሎም የማይታሰብባትን ሀገርን እየገነቡ ነው፡፡ የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው የኢፈዴሪ ህገ- መንግስት የሃይማኖት እኩልነትንና የእምነት ነፃነትን በማስፈርና በተግባር በመተርጎምም የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመቻላቸው፤ የሃይማኖት ብዝሃነት የምታስተናግድ ሀገርን መፍጠር ችለዋል፡፡
ዛሬ ከትናንቱ የተለየ ነው። የሃይማኖት ብዝሃነት በሚስተናገድባት ኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለ አንዳች ቅድሚያ ሁኔታ የማምለክ ብሎም የመከተልና የማስፋፋት መብቱን ማጣጣም ችሏል። በሃይማኖቱና በእምነቱ ጣልቃ የሚገባ ማንኛውንም ሃይል የማስቆም መብቱን መጠቀም የመቻሉ ጉዳይንም በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡ ይህም ማንኛውም የሀገራችን ህዝብ የሃይማኖት እኩልነት አጀንዳ በማይሆንበት ዘመን ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡
ሆኖም በእነዚህ የሃይማኖትን ብዝሃነት የማስተናገድ ዓመታት ውስጥ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አልነበረም። ህገ-መንግስታዊ መርሁን ተገቢ ባልሆነና ፅንፈኝነትን በሚያበረታታ ሁኔታ ላይ የተሰለፉ ወገኖች መኖራቸው የሂደቱ አንድ አካል ነበር፡፡ በተለይም የአክራሪነት አስተሳሰብና ተግባር ብዝሃነትን የሚቃረን ከመሆኑም በላይ፤ በልማታዊው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ ያንዣበበው አደጋም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት እንደነበር ብዙዎችን የምናስታውሰው ሃቅ ይመስለኛል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 11፣ 25 እና 27 ላይ ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን እምነት የመከተል መብቱ የተረጋገጠና እየተተገበረ ያለ ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ፤ እነዚህ የሃይማኖትን ጭንብል ያጠለቁ ጥቂት ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት የተነሳሱ ሃይሎች ግን ሃይማኖትን እንደ ምክንያት በመጠቀም ወደ ተግባር መሸጋገራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነዚህ ሃይሎች የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው። ዳሩ ግን የሀገራችን ኪራይ ሰብሳቢዎች ያለፉት ስርዓቶች ያደረሱትን በደልና ጭቆናን በመቆስቆስ ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም ህዝቡን ለማደናገር የሞከሩበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር።
ምንም እንኳን አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ብዝሃነትን በማወቅ ብቻ ሳትወሰን፣ ብዝሃነትን በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር መሆኗን በማስመስከሯ፤ የፈጣንና ተከታታይ ልማት ባለቤት እንዲሁም የአስተማማኝ ሰላምና የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቷ በስኬት ጉዞ ላይ ቢገኝም ቅሉ፤ በሃይማኖት ካባ ስር የተጠለሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችና በህገዋነት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች በዋነኛነት የብዝሃነትን መርህ ለመጣስና በዚሀም ሁከትነናብጥብጥን ለማንገስ መንቀሳቀሳቸውን የዚህ ፅሑፍ አንባቢ የሚያስታውሰው ይመስለኛል፡፡ ሁለቱንም ለግንዛቤ ያህል መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡
እርግጥ ሃይማኖትን በመጠለያነት መርጦ በአነሳሽነት ተሰልፎ የነበረው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል ሁለት ገፅታዎችን የተላበሰ ነው ማለት ይቻላል። እነርሱም ሃይማኖትን ለኪራይ ሰብሳቢነት ማስፈፀሚያ መንገድ በመምረጥ ህገ ወጥ ተግባራቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ ወገኖች ያሉበት በአንድ ወገን፣ በሌላኛው ዘውግ ደግሞ ከሃይማኖት አጥባቂነታቸው በመነሳት ንቃተ ህሊናቸው በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ምዕመናን ሃይማኖታቸውን የሌላው ሃይማኖት የበላይ እንዲሆን ከመመኘት በሚመነጭ ፍላጎትን ያነገቡ ኃይሎችን ያቀፈ ነበር፡፡
ሌላኛው በማነሳሳት ተግባር ላይ ተጠምዶ የነበረውና የህጋዊነትን ለምድ ለብሶ ለመንቀሳቀስ የነበረው ብሎም በህገ ወጥ መንገድ ስልጣንን ለመጨበጥ የሚንቀሳቀሰው የፖለቲካ ኃይል ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ኃይል የደረሰበትን ኪሳራ ለማወራረድ “የሃይማኖትን ጭንብል” ማጥለቅ በዋነኛ አማራጭነት የሚከተል የተቃዋሚ ሃይል ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ጭምብሉ የወለቀ አይመስለኝም፡፡ ይህ ኃይልም ልክ እንደ ኪራይ ሰብሳቢው በሁለት መልኩ ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል በአሸባሪነት የተሰለፈው እንደ ግንቦት ሰባት ዓይነቱ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በህጋዊነት ስም ህገ ወጥ ተግባር ሲያከናውን የተስተዋለው ሰማያዊ ፓርቲን የመሳሰሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ነው፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ ሃይሎች ሃይማኖትን ከለላ በማድረግ ያራመዱት ፅንፈኝነትን የማስፈን ጥረት ረጅም ርቀት ባይችልም፣ ሀገራችን የምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሲፈታተን በግልፅ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ሃይማኖትን በመጠለያ ታዛነት ለመጠቀም መርጠው የእስልምና እና የክርስትና ምዕመናንን ለማደናገር ሞክረዋል፡፡ የኋላ ኋላ ግን በህዝቡና በመንግስት ሰላምን የማስከበር የተቀናጀ ጥረት ሃሳባቸውን ዕውን ሳያደርጉ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ሥርዓቱ በውስጡ የሚፈጠሩትን ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅምና ብቃት ያለው በመሆኑ የሃይማኖት ብዝሃነትን በመቃረን የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን ከህዝቡ ጋር በመሆን ፈትቷል፤ በመፍታት ላይም ይገኛል፡፡
እርግጥ ዛሬ የምንገኝበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ለምንገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ መፈጠር መንግስትና ህዝብ የሃይማኖት ፅንፈኝነት በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ላይ የጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ በከፍተኛ እልህና ወኔ በመረባረባቸው ነው፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት የአብሮነታችን ተግዳሮት ሆኖ ብቅ ያለውን የሃይማኖት ፅንፈኝነትን ከስር መሰረቱ ለማድረቅ ሰፋፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማካሄዱን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ተግባሩም በአንድ በኩል የችግሩን ምንጭ በማጋለጥ ፣በሌላ በኩል ደግሞ በተሳሳተ መንገድ የተሰለፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስ አስችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር ችግሩ ከሃይማኖት ጋር የማይያያዝ መሆኑን ለማሳየት በማስረጃ ላይ ተመሰረቶ ባካሄደው የማጋለጥ ስራ በችግሩ ምንጮች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ተችሏል። ይህም በሃይማኖት አክራሪ ፖለቲከኞቹ ላይ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣን በማስከተሉ እነዚህ ሃይሎች በብዙ መልኩ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ የተገደዱበትን ድርጊት አስከትሏል ማለት ይቻላል፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉትን የሃይማኖት ፅንፈኝነት ችግርን የመቅረፍ ጥረት በዋናነት መሠረት ያደረገው ምንጩን በማድረቅ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያ ታጋሽነትና አርቆ አስተዋይነትን በማስቀደም ለሃይማኖት አክራሪነት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ በማጥናት መፍትሄዎችን የማስቀመጥ ሂደትን ተከትሏል። ከዚህ አኳያም ሀገራዊው የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታን የተመለከተ ሲሆን፤ በእኩልነትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተው የእምነት እኩልነትና ነፃነት በኪራይ ሰብሳቢ አመለካከት እንዳይበረዝ የማድረጉን ተግባር በሰፋፊ የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች መመከት ችሏል፡፡
በመሆኑም የሃይማኖትና የመንግስት መለያየትን በተግባር በማረጋገጥ መላው ህብረተሰብን የመብቱ ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለው የዘመናት ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብሎም የሃይማኖና የእምነት ኢ-ህገ መንግስታዊ አጀንዳ ቀስ በቀስ ተቀባይነት የማያገኝበትን ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህም ሥርዓቱ በአንድ በኩል ፅንፈኝነትን እየመከተ የብዝሃነት መሰረትን እያጠናከረ መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ይመስለኛል፡፡