መጣመርን የማያውቁ “ጥምረቶች”

እነሆ በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ህዝባዊ ጥያቄ ተከትሎ፤ ኢዴፓን ጨምሮ 16 የሚሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሀገር ቤት ውስጥ “ተጣምረናል” ብለውናል። መቼም እንኳንስ የብዙ ሰዎች ፍላጎት ይኖርበታል ተብለው የሚታሰቡ ፓርቲዎችን ቀርቶ፤ የሁለት ግለሰቦችንም “መጣመር” ጆሯችንን አቅንተን መስማታችን የሚቀር አይመስለኝም። “ተጣምረናል” እስካሉን ድረስ ‘መስሚያችን ጥጥ ነው’ ብለን ዝም ልንላቸው እንችልም። አዎ! ሀገራዊ ወግና ባህል ነውና ‘መልካም ጥምረት ይሁንላችሁ፤ ጥምረታችሁን የአብርሃምና የሳራ ያድርግላችሁ’ ብለን መመረቃችንም ይቀራል ብዬ አላስብም። መርቀን ግን ዝም አንልም። ‘ለምን ተጣመራችሁ?፣ ከዚህ በፊትስ የመጣመር ባህል ነበራችሁ?፣ ተጣምራችሁስ ምን ዓይነት ፍሬ አፈራችሁ? ዛሬስ ተጣምራችሁ ምን አላችሁ?’ ብለን መጠየቃችን የግድ ነው—ከምርቃታችን መሳ ለመሳ።

ለጥያቄዎቻችን ግን ምላሽ የምንሻው “ከጥምረቶቹ” ብቻ አይደለም። የሀገራችን ተቃውሞ ጎራን የትናንት የመቀናጀት፣ የመሰባሰብ፣ የአንድነት፣ ግንባር የመፍጠር…ወዘተርፈ. ዳራዎችን መፈተሽ ያለብን ይመስለኛል። ይህን ስናደርግም ጎራው ጥምረትን የማያውቅ “ተጣማሪ” መሆኑን ራሱ እጅ አውጥቶ ሲናገር እናገኘዋለን። እስቲ በቅድሚያ 16ቱንም “ተጣማሪዎች” ‘ለምን ተጣመራችሁ?’ ብለን እንጠይቃቸው። ለምላሹም ‘ተጣምረናል’ ባሉበት ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ማብራሪያ እንነሳ።…“ጥምረቱ” የመጣመሩን ምስጢር ሲለልጥ “በሀገሪቱ ያለው ውጥረት ይረግብ ዘንድ ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጠር”      ነበር ያለው።

እርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ ችግር ካለ፣ ያ ችግር እንዲፈታ መጠየቅ ክፋት የለውም። እንዲያውም በቀና መንፈስ ጥያቄው ከቀረበ ‘አሰየው’ ማስባሉ አይቀርም። ሆኖም “ጥምረቱ” እንዳለው በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር እንዲፈታ “ብሔራዊ እርቅ” መፈጠር ያለበት አይመስለኝም። ጥያቄውም “ብሔራዊ እርቅን” የመፍጠር አይደለም። ህዝቡ በግልፅ ያነሳው ጥያቄ ከመልካም አስተዳደርና በተፈለገው መንገድ በቂ የስራ ዕድል አለመፈጠሩና ሌሎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያላረጋገጡ ጉዳዩችን እንጂ ብሔራዊ እርቅን አይደለም። ባይሆን እዚህ ላይ ‘መንግስት ብሔራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማስፈን መስራት አለበት’ የሚል አስተያየት ቢቀርብ የተቃውሞ ወጉ ይመስለኛል። እርግጥ ባለፉት 25 ዓመታት በሀገራችን ውስጥ ብሔራዊ መግባባን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል።

ለነገሩ አንዳንድ ወገኖች ብሔራዊ መግባባትን በተሳሳተ መንገድ ሲመለከቱት ይስተዋላል—ሁሉም ዜጋ በሁሉም ጉዳዩች ላይ መግባባት አለበት ከሚል አተያይ ተነስተው። ሆኖም በዓለም ላይ ያለ ማንኛውም ህዝብ በሁሉም ጉዳዩች ላይ ሊግባባ አይችልም። እንኳንስ ህዝብን የሚያክል ትልቅ የማህበረሰብ ስብስብ ቀርቶ፤ በቤተሰብ ውስጥም ቢሆን ባልና ሚስት፣ ወንድምና እህትም ቢሆኑ በሁሉም ጉዳዩች ሊግባቡ አይችሉም። በማህበረሰብም ይሁን በቤተሰብ ውስጥ ልዩነት ያለና የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው። እናም ብሔራዊ መግባባት ማለት አብዛኛው ህዝብ በአብዛኛው ጉዳይ የጋራ አተያይን እንዲያዳብር ማድረግ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በዚህም ከሀገር ሉዓላዊነትና ዕድገት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ማከናወን የተቻለ ይመስለኛል። ለዚህም የኤርትራ መንግስት ድንበራችን ውስጥ ዘልቆ በመግባት ወረራ በፈፀመብን ወቅት መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀፎው እንደተነካበት ንብ “ሆ!” ብለው በነቂስ በመውጣት እስከ ህይወት መስጠት ድረስ ያደረጉት ቀናዒ የሀገር ፍቅር እንዲሁም ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ዕውን በሆነውና ዛሬም እየተገነባ ላለው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ እንዲሁም ቦንድ በመግዛት እያከናወነ ያለው ሀገራዊ ተግባር ሁነኛ ማሳያዎች ይመስሉኛል። የተቃውሞው ጎራ ግን እነዚህን መሰሎች ተግባራት እንዲጎሉና ሀገራዊ ፋይዳቸው እየጨመረ እንዲሄድ ከመጠየቅ ይልቅ፣ በሌለ ምህዳር ውስጥ ሆኖ ስለ ብሔራዊ እርቅ ያወራል።

እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ “ጥምረት” ለሀገር ከማሰብና ከመቆርቆር የመነጨ ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ይመስለኛል። ምክንያቱም የተቃውሞው ጎራ ትናንትም ቢሆን የሚጣመረው የራሱን የስልጣን መወጣጫ መሰላል ለማደላደል እንጂ የህዝቡን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ባለመሆኑ ነው። ይህ ሁኔታም የጎራውን የተቃውሞ “ትናንትነት” መለስ ብለን እንድንመለከተው ያደርገናል።

በምርጫ 97 ወቅት የቅንጅት ተጣማሪ የነበሩት ፓርቲዎች ሲያደርጉ የነበረውን የሜዳ ላይ ትዕይንት የዚህ ፅሑፍ አንባቢ የሚዘነጋው አይመስለኝም። ተጣማሪዎቹ ለአንድ ዓላማ ነው ይምንቀሳቀሰው ብለው ሲያበቁ፤ ለስልጣን ካላቸው ጉጉት የተነሳ አንዱ ሌላውን በመወንጀልና በየግል ሚዲያው ስም በማጥፋት የመቦጫጫቅ ስራን ሲያከናውኑ ነበር። እነዚህ ህዝብን ወክለን ነው የተጣመርነው የሚሉ ተቃዋሚዎች ገሚሳቸው በየሜዳው አጠናና ዘነዘና ይዘው እርስ በርሳቸው ሲናረቱም ተመልክተናል። በምርጫ 2002 ወቅትም ቢሆን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የነበሩ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዓይነት ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ከዘራቸውን ይዘው ሲባረሩ አይተናል። በወቅቱ መኢአድ የተሰኘው ሌላኛው ተቃዋሚ ደግሞ እንደ ገና ዳቦ አራት ቦታ ተቆራርሶ እርስ በእርሱ ሲፋተግ ተመልክተናል። ሌላ ሌላም።…ይህ ዕውነታም የተቃውሞው ጎራ ተጣማሪዎች ጥምረትን የማያውቁ መሆናቸውን ከማሳየት ውጪ፤ በህዝቡ ልብ ውስጥ እንዳይገቡና በመርጫ ተወዳድረው እንዳያሸንፉ ያደረጋቸው ይመስለኛል። እናም በመጣመራቸው ያገኙት ነገር አለ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።

ያም ሆኖ መጣመርን የማያውቁት እነዚህ “ተጣማሪዎች” ወትሮም ቢሆን አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ወይም “ኮሽ” የሚል ነገር ሲሰሙ ፈጥነው ግንባር መፍጠርን አሊያም ልክ እንዳሁኑ ተጣምሮ አጀንዳን የመጠምዘዝ ተግባር ማከናወን ልማዳቸው እየሆነ የመጣ ይመስላል። “የጥምረቱ” ዋነኛ ግብም በአቋራጭ ስልጣን ለመቆናጠጥ ያለመ ነው። ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ አንዱ ሌላኛውን መወንጀል ይከጅላል፤ አንደኛው አለቃ ሌላኛው ደግሞ ምንዝር የሆነ እየመሰለው የጎሪጥ ይተያያል። በል ሲለውም ከተጣማሪው አንደኛው በሌላኛው ላይ ወይም በዋናው ጥምረት ላይ ጥናት ካላካሄድኩ ሞቼ እገኛለሁ ይላል።

በአንድ ወቅት መድረክ በተባለው ፓርቲ ውስጥ በአባልነት ታቅፎ የነበረው “አንድነት” ይሰኝ የነበረው ድርጅት መድረክን ካላጠናሁህ ብሎ በማስቸገር እስር በርሳቸው ይፋተጉ እንደነበር እናስታውሳለን። ‘አታጠናኝም’ ያለው መድረክም አንድነትን ከተጣማሪ አባልነቱ አሰናብቶታል። ይህም ወትሮም መቧደኑ ወደ ስልጣን ደጅ የሚያደርስን ጥርጊያ መንገድ ለማመቻቸት እንጂ፣ ስብስቡ የእሳትና ጭድ ክምር በመሆኑ ለመበተን ጊዜ የማይወስድበት መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እርግጥም ለመቧደን ከየጥሻው የተጠራራውን ያህል፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ የነገር ካራውን ስሎ ለመበተን ጊዜ አይወስድበትም። እናም “ተጣማሪዎቹ” በእስከዛሬው የተቃውሞ ቆይታቸው አንዳችም ረብ ያለው ነገር ለህዝቡ ሳያከናውኑ አሁንም “ተጣምረናል” እያሉን ነው።

እንግዲህ በእንዲህ ዓይነት በ“ጥምረት” ውጥረት ማዕበል ግራና ቀኝ ሲናውዝ የነበረ የሀገራችን ተቃዋሚ ነው “ውጥረት ይርገብ” በማለት በመጠየቅ እግረ-መንገዱን መንግስት ከየትኛውም ተቃዋሚ ጋር እርቅ እንዲያደርግ ያሳሰበውና ይህ ካልሆነም ሀገሪቱ ዋጋ እንደሚያስፈልጋት የጠቆመው። እርግጥም “በልጅ አመካኝቶ ይበሏል አንጉቶ” የሚባለው ብሂል የሚመጣው እዚህ ላይ ይመስለኛል። ሃቁ ግን ተቃዋሚው “ጥምረት” እንደሚለው አይደለም። የተቃውሞው ጎራ “የበሬ ምንትስ ይወድቃል ብላ ስትከተል ዋለች” እንደምትባለው እንስሳ ዓይነት በ‘ስልጣን አገኝ ይሆን?’ ምናልባታዊ ስሌት ተመርቶ እንዳለው አይደለም። እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የቀረቡት ጥያቄዎች ትክክለኛና ተገቢ ናቸው። ሆኖም ጥያቄዎቹን አንዳንድ የውጭ ፅንፈኞችና የሀገራችንን ዕድገት ማየት የማይሹ የውጭ ሃይሎችና “የውስጥ አርበኞቻቸው” በመንጠቅ የራሳቸው አጀንዳ ማራመጃ አድርገውታል። ይህ ትስስርም በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ አመፅ የሚደርስ ሁኔታን ፈጥሯል።

ያም ሆኖ ግን መንግስትና ገዥው ፓርቲ ችግሩን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ ነው። ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ውይይት እያደረጉ ነው። ከውይይቱም መንግስትም ይሁን ህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ እያገኙ ነው። ይህ ሁኔታም ተፈጥሮ የነበረውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ወትሮም ጥያቄው የህዝቡ በመሆኑ ህዝቡ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ችግሮች በተጨባጭ እያወቃቸው በመምጣቱና የመረጠው መንግስት ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ የሚያምን በመሆኑ ለችግሩ እልባት ማግኘት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው። እናም ይህ ነባራዊ ሃቅ ባለበት ቦታ ውስጥ “ብሔራዊ እርቅ” የሚባለው ነገር ለማንም ግልፅ አይደለም። የዚህ ሀገር ባለቤት የሆኑት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደመሆናቸው መጠን፤ እነርሱ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር ችግሩን ለመፍታት እየተወያዩ በመሆናቸው የሚከፍሉት ሀገራዊ ዋጋ አለመኖሩን “ጥምረቱ” ይገነዘበዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ያም ሆነ ይህ ግን “ጥምረቱ” ምን ዓይነት ግንዛቤ ኖሮት መግለጫውን ለመስጠት እንደበቃ ባላውቅም፤ ገዥው ፓርቲ አሁን በጀመረው መንገድ ግጭቶች አይፈቱም ማለቱ ከዴሞክራሲያዊ አግባብነት የተለየ ይመስለኛል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ገዥው ፓርቲ ራሱን በመፈተሽ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ላይ መሆኑን ገልጿል። ገና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ህዝብን የማክበር ባህል ስላለው የህዝቡን ትክክለኛ ጥያቄዎች ለመፍታት እየሰራ ነው። ይህ ደግሞ የህዝብን የበላይነት ከማመን የመነጨ እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የፍርሃት መገለጫ አይደለም። እናም ህዝብን በማክበርና የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ መልሶ ከህዝቡ ጋር እየሰራ ያለውን ገዥ ፓርቲ፤ ‘በጀመረው መንገድ ግጭቶች አይፈቱም’ ማለት ምን እንደሆነ ለማንም ግልፅ አይመስለኝም።

ሆኖም ጥምረትን የማያውቁት “ተጣማሪዎች” ለማለት የፈለጉት በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩት ችግሮች ሳቢያ በዜጎችና በፀጥታ ሃይሎች ላይ የደረሰውን የህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ከሆነ፤ ይህ ሁኔታ ገና በመጣራት ላይ ያለ በመሆኑና መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ እጅግ ማዘኑን በመግለፅ የተፈጠረውን ሁኔታ በገለልተኛ ቡድን አጣርቶ ተገቢውን የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወስድ ቃል በመግባቱ ጊዜው ገና ይመስለኛል።

ምንም እንኳን የሀገራችን ተቃዋሚዎች ባህል በአስቀድሞ ፍረጃ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ይህ ሁኔታ ቢያንስ በአዲሱ ዓመት ሊስተካከል የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ዓይነት አካሄድ ከዴሞክራሲ አኳያ ያለው ጠቀሜታ ትርጉም የሌለው በመሆኑ ነው። እንዲያውም ነገሮችን በማባባስ ሌላ ችግር ከመፍጠር በስተቀር ለህዝቡ የሚፈይድለት ምንም ነገር የለም። እናም ጥምረትን የማያውቁት “ተጣማሪዎች” በአንድ ጉዳይ ላይ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ጉዳዩን ከራሳቸው ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኛነት በዘለለ፣ ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ መፈተሽ ያለባቸው ይመስለኛል—እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ከዝም ብሎ ተጣማሪነት ወደ “ተቃዋሚነት” ከፍ የሚያደርግ ነውና።