በኢሬቻ በዓል ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

መንግስት የህዝቡን ባህል ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ ሲሲራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ መንግስትና ሕዝብ ልዩ ትኩረት ሰጥተውት ሲሰሩባቸው ከነበሩት ታላላቅ የኦሮሞ ሕዝብ ባህሎች አንዱ በየአመቱ በሆራ አርሰዴ ቢሾፈቱ ሕዝባችን ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ሚሊዮኖችን በመታደም የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ በኃይማኖት፣ በፆታና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ በጋራ የሚያከብሩት የአንድነት መገለጫ ነው፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የገዳ ሰርዓትን በአለም የማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ እና ባህላችን በአለምአቀፍ መድረክ ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ መንግስታችን ከፍተኛ ጥረት ሰዲያደርግ ቆይቷል፡፡

የክልላችን ህዝብ በዓሉን ለአለም አምረው እና ደምቀው በሚገባ ለማሳየት ከፍተኛ ጉጉት እና ምኞት የነበረው በመሆኑም በዚሁ ምክንያት በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች እና የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም የተለያዩ አለምአቀፍ እንግዶች የታደሙበት ሆኖ ሳለ ለባህላችን እና ለህዝባችን ምንም ደንታ የሌላቸው ኃይሎች በጠነሰሱት እኩይ ሴራ ምክንያት ሁከት እና ብጥብጥ ሊፈጠር ችሏል፡፡

መንግስት ከፍተኛ ትግስት እና ጥንቃቄ ያደረገ ሲሆን እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይፈፀም ለህዝቡ እና ለአባገዳዎች ምንም አይነት እክብሮት ሳይሰጡ እንዲስተጓጎል አድርገውታል፡፡

በዚህም በተፈጠረ መገፋፋት እና መረጋገጥ ምክንያት የ52 ያክል ዜጎቻችንን ውድ ህይወት አሳጥቷል፡፡

ይህም ሁኔታ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ምክንያት እንጂ በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ-ገፆች የሚሰራጨው የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ምክንያት እንዳልሆነ በአካባቢው የተገኘው ህዝባችን ምስክር ነው፡፡

በመሆኑም መላው የክልላችን እና የሀገራችን ህዝቦች ይህንን በግልፅ ሊረዱት ይገባል፡፡
በነዚህ የጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባር ህይወታቸውን ላጡት ዜጎቻችን መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የክልላችን ህዝቦች መፅናናትን ይመኛል፡፡

ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን በመቆምም አስፋላጊ ሆኖ የተገኘውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል፡፡

መንግስት እንደትላንቱ ሁሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን ዛሬም የገዳ ስርዓታችን በአለም ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ይህንን የህዝባችንን ጥቅም የሚጎዳ እና ከባህላችን ውጪ የሆነ አሳዛኝ ድርጊት ህዝቡ አምርሮ እንዲያወግዘው ክልላዊ መንግስቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መስከረም 22/2009
ፊንፊኔ