የደኢህዴን በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረክ የአቋም መግለጫ

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራስያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ የከፍተኛ አመራሮች በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረክ የአቋም መግለጫ

ከመስከረም 18 ቀን እስከ 22 2009 ዓመተ ምህረት ድረስ ሲካሄድ የቆየው የደኢህዴን የከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረክ ትናንት ምሸት ላይ የሚከተለውን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቅቋል፡፡

1. የአንድ ድርጅት ጥንካሬው ከሚረጋገጥባቸው መለኪያዎች አንዱና ዋነኛው ተቋማዊ አቅሙ ነው፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ በጠራ አመለካከት፣ በፈጠረው አደረጃጀት፣ በዘረጋው የአሠራር ሥርዓትና በተሰማራው የሰው ኃይል የሚወሰን ይሆናል፡፡ ታዲያ ከዚህ አንፃር ድርጅታችን ደኢህዴን ላለፉት የትግልና የድል አመታት የተጓዘው ርቀት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ካለንበት መድረክ አንፃር ተቋማዊ አቅሙን የሚፈታተኑ ችግሮች መኖራቸው በጥልቅ ተሀድሶአችን አረጋግጠናል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ህዝባችንን በአጠቃላይና አባሎቻችንን በተለይ በተገቢው መንገድ ወደ ስምሪትና ውጤታማነት ሊያደርስ በሚያስችል ሁኔታ እንዳይመራው አድርጎት ከመቆየቱም በላይ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ባህሉ እየተሸራሸረ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንዲበራከቱ አድርጓል ፡፡ በመሆኑም እኛ ከፍተኛ አመራሮች በቀጣይ የተግባር እንቅስቃሴ ሂደታችን የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ለማስፈን በየደረጃ ያሉ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን አቅም በመገንባት አሰራሮችን ጠብቀን ለመስራትና ከአባላት ምልመላ እስከ ግንባታና ሥምሪት ያሉትን ችግሮች ቀርፈን ለውጤት ለማብቃት ከምን ጊዜውም በላይ ከአድርባይነት ተላቀን ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡

2. ከሀገራችንም ሆነ ከክልላችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ህዝቡን ያላሳተፈ ልማት የትም እንደማያደርሰን ተማምነን ያለፍነው ጉዳይ ነው ፡፡ ሥርዓታችን ልማታዊ ብቻም ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ካስገደዱን ምክንያቶች ውስጥ በሀገራችን ብሎም በክልላችን ብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነታችንና ይህን የምናጣጥምበት መንገድ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የጥልቀት ተሃድሶ ጉዞዓችን በተለያዩ ምክንያቶች ያመለጡ ዕድሎችንና መልካም አጋጣሚዎችን ለይተን በቀጣይ ሁሉንም የልማት ኃይሎች በተገቢው መንገድ አደራጅተን በየማህበራዊ መሠረቶቻቸው አንቀሳቀወሰን ፈጣን ብቻም ሳይሆን ቀጣይነት ያለውና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሁሉን አቀፍ ልማት በማረጋገጥ አለቃችን የሆነውን ህዝባችንን ለመካስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተግተን ለመሥራት ቆርጠን መነሳታችንን ለመላው ህዝባችንና አባላችን እናረጋግጣለን፡፡

3. ምንም እንኳን የጠራ መሥመር እና የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ ቢኖርም የልማት ሂደቱን የሚያቀላጥፉ መልካም አስተዳደር ካላረጋገጥን የህዳሴ ጉዞአችን መጨናገፉ አይቀርም፡፡ ስለሆነም እኛ የዴኢህዴን/ኢህዴግ/ ከፍተኛ አመራሮች ህዝባችን በተለያዩ መድረኮችና አጋጣሚዎች የሚያነሷቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች የመፍታቱ ጉዳይ ከቅንነት መጓደል እና የህዝብ አለቃነትን በውል ተረድተን በአደራ የተሰጠንን የትውሰት ሥልጣን የህዝቡን ጥቅሞች በሚያረጋግጥና የህዳሴ ጉዞአችንን በሚያረጋግጥ አኳኃን ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅም የመጠቀም አዝማሚያ እየሰፉ መምጣቱ አንስተን ገምግመናል ፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ለስልጣን ያለንን የተዛባ አረዳድ አስወግደን ህዝባችንን ለመካስ ቀልጣፋ ተደራሽ እና በውጤታማነት በመጠቀም የህዝባችንን እርካታ ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡

4. ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ የመሪነት አቅማችንን እየተፈታተነ የመጣውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ነቀርሳ እና የሥርዓቱ አደጋ የሆነውን የኪራይ ሰብሳብነት፣ ጠባብነትንና ጎሰኝነትን፣ ፀረ ዴሞክራሲን፣ የሃይማኖት አክራሪነትንና የብልሹ አሠራሮችን አመለካከቶችንና ተግባራትን በነቃ የህዝባችን ተሳትፎ ጠራርጎ በማስወገድ ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነቱን እንዲይዝ በማድረጉ ሂደት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሰላ ትግል የመሪነት ሚናችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

5. ሁሉንም የልማት አቅሞች ለማስተሳሰር የመሪነት ሚናውን የሚጫወተው የድርጅት ክንፍ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናት በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ከግብአት አቅርቦት እስከ ክህሎት ክፍተቶችን በመሙላት እና ከህዝቡ ዘላቂ ልማት አኳያ ወሳኝ በሆኑ፣ በተመረጡና ሰፊ የገበያ ጉድለት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ጣልቃ በመግባት የመሪነት ሚናውን የሚወጣውን መንግሥት የምንመራው እኛው በመሆናችን በቀጣይ በዚህ በጥልቅ የተሃድሶ መንፈስ እና ወኔ የሁሉም ተዋንያን ባለ ድርሻ አካላትን በተለይም የታችኛውን የወረዳና የቀበሌ አስተዳደር እርከኖች አቅም የመገንባቱን ጉዳይ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ በጠንካራ የሠራዊት ግንባታና የአመራር ዑደት ሥርዓት በቂ ተከታታይነት ያለውና ችግር ፈቺ ድጋፋዊ ክትትል በማድረግ ውጤታማ አመራር ለመሆን ከምንግዜውም በላይ ተግተን ለመሥራት ቆርጠን መነሳታችንን እናረጋግጣለን፡፡

6. ልማት የዴሞክራሲ ግንባታ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ሁሉ ዴሞክራሲም ለልማት መፋጠን አይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የማይነጣጠሉ አንድና ያው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እኛ ከፍተኛ አመራሮች ለልማት ተግባሮቻችን የሚሰጠውን የትኩረት አቅም እዛው እያለ ለዴሞክራሲ ግንባታ መጠቀም እንደሚገባን በተረዳነው ልክ በቀጣይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለትውልድ ባህል አድርጎ ለማቆየት ተቋማቶችን በተገቢው መገንባቱ የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ የህዝብ ምክር ቤቶችን፣ ብዙሃን ማህበራትን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሚዲያ ተቋማትን ከመደገፍና ከማብቃት አኳያ ያሉብንን ውስንነቶች በጥልቅ ተሃድሷችን ወቅት አንስተን በገመገምነው መጠን ምንም አይነት መንጠባጠቦች ሳይኖሩ በሙሉዕነት ለመደገፍ እና ውጤታማ ለማድረግ ተግተን ለመስራት ቃል እንገባለን ፡፡

7. በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከመንግሥትም በላይ ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን የመምራት ሀላፊነት የድርጅታችን ነው፡፡ ድርጅት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ ርዕዮተ ዓለማዊና ፖለቲካዊ መሪ ነው፡፡ ከልማታዊ መንግሥታት ባህሪይ እና ከእኛም ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስናይ መንግስት በብዙ የልማት ጉድለቶች ላይ ጣልቃ በመግባት ትልቁን ድርሻ የሚወስድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህንን ልማታዊ ጉዞ የሚመራው ድርጅትና መንግሥት ናቸው ካልን አብዛኛው የህዝብ ሀብት በእነዚህ አካላት እጅ ላይ መውደቁ የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ ድርጅትና መንግሥት ደግሞ ህዝቡ የኢኮኖሚ አቅሙ አድጎ የራሱን ካፒታል ራሱ በሚያስተዳደርበት ደረጃ ላይ እስክንደርስና የበላይነቱን እስኪያረጋግጥ ድረስ ሥልጣን በአደራ ወይንም በትውስት ወስደው ግን የበላይ ሆነው ሁሉንም የልማት ሥራዎች የመምራት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም እኛ ከፍተኛ አመራሮች የያዝነው ሥልጣን የህዝብ አደራ መሆኑን በጥልቅ ተሃድሷችን ውይይትና ግምገማ ወቅት በተግባባነው አግባብ ሥልጣን የግል ሀብትና የኑሮ መሠረት መገንቢያና የብልፅግና መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ ለህዝባችን እንደ ሻማ ቀልጠን የምናገለግልበት ይህንን ቁመና ይዞ መቀጠል የማይፈልግ አመራር ካለ ደግሞ የድርጅቱን ካባ በማውለቅ ልማታዊ በሆነ መንገድ የራሱን የግል ህይወቱን ማስቀጠል እንዲችል አማራጭ የተሰጠው መሆኑን በመገንዘብ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውና በመንታ መንገድ ቆሞ ህዝብንና መንግሥትን እየበደለ የሥርዓቱን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት እንደሌለብን ተረድተን በቀጣይ በተሰጠን ህዝባዊ ስልጣን በታማኝነት፣ በቅንነትና በትጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡

8. የስርዓቱ አደጋዎች ብለን የለየናቸውን ችግሮች ወይንም ጥገኛ ዝቅጠት አደጋዎች ለማስወገድ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ከሚሰጡ የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ጎን ለጎን እያንዳንዱ ከፍተኛ አመራር በተግባር እንቅስቃሴ ወቅት በተለያዩ አጋጣሚዎች እና በዕቅድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን በጥልቅ ተሃድሷችን በተግባባነው መንገድ የምንተገብረው ሆኖ ለቀጣይ የተግባር ጉዞአችን አስተማሪ ይሆን ዘንድ ችግሮቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎችና ግለሰቦች ላይ ተገቢ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ በማያዳግም ሁኔታ በመውሰዱ ሂደት ከራሳችን ጀምሮ የመሪነት ሚናችንን ለመወጣት ቃል እየገባን በዚህ አጋጣሚ ይህ የእርምጃ አወሳሰድ ትግል በእኛ በአመራሮች ብቻ ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል መላው የልማት ሀይሎች የሆነው ህዝባችንም ከትግሉ ጎን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

9. በክልላችን በኮንሶ አካባቢ በአንዳንድ አመራሮች የአያያዝ ስህተት እና ከውጪ ደግሞ በጸረ ሰላም ሀይሎች ግፊት በህዝባችን ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ህይወት ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡ የዚህ ዓይነቱ የፀጥታ ችግር በክልላችን ዳግም እንዳይከሰት እኛ ከፍተኛ አመራሮች አስቀድመን ሁኔታዎችን በመገምገም ፈጣን ምላሻችን በመስጠት ለመታደግ በቁርጠኝነት የመሪነት ሚናችንን ለመወጣት ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን፡፡
10. ፌዴራላዊ ሥርዓት ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያለሙትና እንዲያስተዳደሩ የሰው ስልጣን እንደ ሀገር አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው የትግል ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ ደግሞ ኢህአዴግ ከሥሩ አራት ብሔራዊ ድርጅቶችን በመያዝ ወጥ አመራር እየሰጠ የሚመራ አውራ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የአንዱ እህት ድርጅት ጥንካሬም ይሁን ድክመት በተዘዋዋሪ መንገድ በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ድርጅታችን ደኢህዴን በኢህአዴግ ሥር ካሉት እህት ድርጅቶች እና ክልሎች የሀገራችን አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ጉልህ ተሳታፊ በመሆን የበኩላችንን ታሪካዊ ድርሻ በመወጣቱ ሂደት እኛም ከፍተኛ አመራሮች በጥልቅ ተሃድሶ መንፈስ የሚጠበቅብንን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን!!

ህዝባችን አለቃችን ነው!
የሰማዕታትን አደራ ያለማመንታት እናከብራለን!!
ድል ለሰፊው ህዝባችን !!!
ድል ለአብዮታዊ ድርጅታችን!!!!
መስከረም 22 /2009 ዓ.ም 
ሀዋሳ