የቋንቋ እና የባህል እኩልነት በኢትዮጵያ

ወ/ሪት አደይ አበባ ታምሩ

(ከየቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት)

 

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች አገር ናት፤ የብዙ ቋንቋዎች እና ባህል(ሎች) መገኛም፡፡ ሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች እኩል መሆናቸዉንም ህገመንግስቱ አረጋግጧል፤ የባህልና የቋንቋ እኩልነትንም አረጋግጧል፡፡ በዚህም ሁሉም ብሄሮችና  ብሄረሰቦች  ባህላቸዉን የሚያሳዉቁበትና  ቋንቋቸዉን ተጠቅመዉ እንዲማሩ እና እንዲዳኙበትም መደረጉ ለዚህ ማሳያ ነዉ፡፡

ቋንቋ መግባቢያ እንደመሆኑ  የሀገርንና የዜጎችን የሚገልፅ ሲሆን ባህል ደግሞ የሰዎችን ማንነት እና የአኗኗር ዘይቤ የምንለይበት ነው፤ ሁለቱም መሰረታዊ የማንነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የኢፌዲሪ ህገመንግስትም ማንኛዉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ህዝብ በቋንቋዉ የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለዉ በህገመንግስቱ መደንገጉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸዉን ለቀጣይ ትዉልድ ለማስተላለፍ እና በመከባበር ጸንቶ እንዲቆይ አንዱ የሌላዉን ተገንዝቦ በልዩነት ዉስጥ ተቻችለዉ እንዲኖሩ ያስችላል፡፡

የኢፌዲሪ ህገመንግስት ከመጽደቁ በፊት የቋንቋ  እና የባህል እኩልነትም ሆኑ ሌሎች መብቶች በህገመንግስቱ የተደነገጉ ቢሆንም እኩልነት በስፋት ሰፍኖ ይታይ እንዳልነበር አንዳንድ ጽሁፎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የተለያዩ እና ብዙ ሆነዉ አንድነት በመፍጠራቸዉ ዉበት የተላበሱ እና የሌሎችን ቀልብ የሳቡ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗንም በተለያዩ ክልሎች ላይ የሚከበሩ ብሄራዊ በአላት ምሳሌ ኢሬቻ-በኦሮሚያ፣ ጨምባላላ-በደቡብ፣ አሸንዳ-በትግራይ፣ ሻደይ-አማራ ክልል ሰቆጣ ወዘተ የሚከናወኑ መንፈሳዊ ክበረ በአላት ላይ የሚታደሙ የዉጭ ሀገር ዜጎች ምስክር ናቸዉ፡፡ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የጸደቀዉ የኢፌዴሪ ህገመንግስትም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄሮች እና ህዝቦች በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት ባጸደቁት ህገመንግስት ዋስትናቸዉን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ሁለቱን አቻችሎ አንዱ የሌላዉን ባህልና ቋንቋ  አክብሮ ለመጓዝ እንዲችል የሚረዳዉም ህዝቦች ልዩነታቸዉን እንደ ዉበት ቆጥረዉ መኖር ነዉ፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ‘ሀ’ ብሎ ህዳረ 29 ቀን መከበር የጀመረዉ የብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀንም በህገመንግስቱ የተገኘዉ የዲሞክራሲ ስርአት ዉጤት በህዝቦች መረጋገጡን ያሳያል፡፡ ህገመንግስቱ በሰጣቸዉ መብት መሰረትም ዴሞክራሲያዊ  መብታቸዉን፣ ቋንቋ እና ባህላቸዉን ጠብቀዉ ታሪካቸዉን እያቆዩ መሆኑን ያንጸባርቃል፡፡

በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 39/5 ላይ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ህዝብ ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያሏቸዉ፣ ሊግባቡ የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸዉ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልዉና አለን ብለዉ የሚያምኑ፣ የስነልቦና አንድነት ያላቸዉና በአብዛኛዉ በተያያዘ መልክአ ምድር የሚኖሩ መሆናቸዉን ያብራራል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከብሄር ብሄር የተለያዩ እና በርካታ ቋንቋ የሚነገርባት አገር ስትሆን  ከአባቶች ሲወርስ ሲዋረስ የመጣ የተለያየ ባህልና ልምዶች ያሏት አገር እንደመሆኗ ባህልን ለማስተዋወቅ ቋንቋ ትልቅ ሚና አለዉ፡፡ በአሁን ሰአትም ሁሉም ዜጋ እኩል ህገመንግስታዊ መብት ተሰጥቶት ባህሉን እና ቋንቋዉን በማሳደግ አለምአቀፍ እዉቅና የሚያገኝበት መንገድ መከፈቱን በUNESCO የተመዘገቡ ብሄራዊ በአላትን በምሳሌነት መዉሰድ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ የሲዳማ ብሄር የራሱ የሆነ አዲስ አመት አለዉ፤ ይህም ፊቼ ወይም ጨምባላላ በመባል የሚታወቅ የአዲስ አመት በአል አከባበር ሲሆን ክብረ በአሉ በየአመቱ በብሄረሰቡ ኮከብ ቆጣሪዎች በሚወስኑት ቀን መሰረት ይከበራል፤ ይህ በአልም በ2012 G.C UNESCO ተመዝግቧል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ባህልና ቋንቋቸዉን እያሳደጉ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ የአገራችነ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እስከአሁን ያከናወኗቸዉ የልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባተ ተግባረት ዋነኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያስቻለዉ የእኩልነታቸዉ ነጸብራቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በአልን ስናስብ ካለፈዉ የጋራ ታሪካችን የገነባነዉን አዎንታዊ እሴቶች በጋረ ለመጠበቅና ይበልጥ ለመገንባት ቢሆንና ለነዚህ አላማዎችና መርሆዎች እዉን መሆን የጸና  እምነት በመያዝ መሆን ይገባል፡፡