ዜሮ ድምር  . . . እጅግ የተከበረውን የገዳ ስርአት እስከመድፈር

የሃገራችን እና የህዝቦቿ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት ውስጥና ምናልባትም ጎረቤት ሃገራት በውስጣቸው ለሚፈጠር ቀውስና መከፋፈል መፍትሄውን ሲጀምሩ እንደምሳሌነት ከሚወስዷቸው፣ አለምንም ከሚያስጎመዡና የማይዳሰሱ ሃብቶቻችን መካከል ጨዋነታችን፣ አርቆ ማሰባችን፣ የመከባበር እና የመመካከር ባህላችን፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ልምድና ለሃገር ሽማግሌዎች የምንሰጠው የክብር ቦታ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ የማይዳሰሱ እና አኩሪ የሆኑቱ እሴቶች ለሌሎች ተምሳሌት ከሚሆኑባቸው እና ከሚያስጎመዡባቸው ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ ከምንም በላይ  ሃገራችንን በጋራ ለመጠበቅና  የሃገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ያገለገሉን ዋነኛ መሠረቶች ሆነው በማገልገላቸው ስለመሆኑ የሚጎመዡትም ሆነ አርአያነታችንን የሚወስዱ ሃገራት በሙሉ የመሰከሩት ነው፡፡ እንኳንስ ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ ይቅርና በርካታ መብቶቹም በተረገጡበትና መውጫ መግቢያ እንዲሁም መተንፈሻ እንኳ በታጣበት በዚያም ክፉ ዘመን ችግሮቹን ሁሉ ተቋቁሞ ያለፈው  የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከትና የመሳሰሉት ልዩነቶችን አክብሮ የመኖር የዘመናት ልምዱን ተጠቅሞ መሆኑም አይተባበልም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ አክብሮት ከሚያገኝባቸው ተምሳሌታዊ እሴቶቹ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው አገር ወዳድነቱ ነው፡፡ ይህ ለቅኝ አገዛዝ ያልተንበረከከ የአገር ፍቅር ፅናት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ ሕዝባችን ባሉት ለየት ያሉ እና ከላይ በተመለከቱት  ተምሳሌታዊ እሴቶቹ ስለመሆኑ አሁን እየተዘነጋ የመጣ ይመስላል ፡፡ መንግስትም ሆነ መንግስትን የሚመራው ፓርቲን ጨምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያስፈልጋል ሲሉ፣ በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች የመደራጀት መብታቸውን ተጠቅመው ፓርቲዎች በማቋቋም በምርጫ ብቻ የመንግሥት ሥልጣን መጨበጥ መቻልን ተቀብለው እና አምነው መሆኑ አያከራክርም፡፡ የሥልጣን ምንጭ የሆነው ሕዝብ የሚፈልጋቸውን ወኪሎች በነፃነት መርጦ ለሥልጣን የማብቃትን ብቸኛና ዴሞክራሲያዊ አማራጭ አምነውና ተቀብለው እንጂ በአመጻ ቆርበው እንዳልሆነም መገመት አይከብድም።
የሃገራችን ህዝቦች መንግስትንም ሆነ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና አክቲቪስቶችን፤ ይልቁንም ማህበራዊ ሚዲያውን እና ዴያስፖራ ተቃዋሚዎችን መዳኘትም ሆነ መስማት ያለባቸው በነዚሁ ህጋዊ ማእቀፎችና ከላይ በተመለከቱት አኩሪ እሴቶቹ ውስጥ ሊሆን ይገባዋል። ይህ ማለት ግን ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት ሲያጠፉ እና ይልቁንም አክብረው እንዲያስከብሩ የሚጠበቅባቸውን የህግ ማእቀፎች ሲጥሱ ህዝቡ ዝም ብሎ ሊመለከት ይገባዋል ማለት ሳይሆን ከላይ የተመለከቱ አኩሪ እሴቶቹን ይዞ በተቀመጠለት የህግ አግባብ የመጠየቅ፣ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ መብቶቹን በሙሉ አሟጦ የመጠቀምና ወጥሮ የመያዝ መብትና ሿሚም ሆነ ሻሪ እርሱ መሆኑን የሚያጠይቅ (Justify የሚያደርግ) ነው።
በመንግስትም ሆነ በመሪ ድርጅቱ በኩል በተለይ አሁን በየአጋጣሚው ለሚነሱ ቅሬታዎች እና ሮሮዎች ዋነኛው ምክንያት ‹‹የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲውል ከማድረግ ይልቅ፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጎ የመመልከት፤ በአንዳንዶቹም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ምንጭም ይኼው ያልተገባ ድርጊት የፈጠረው ችግር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ ለግል ኑሮ መሠረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌ መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዕርምጃዎችም መውሰድ እንደሚገባ ተወስኗል፤›› በማለትም በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅት ማዕቀፍ በማየት ይህንኑ የማስተካከያ ርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤›› የሚለውም ነጥብ ስለአጀንዳችን ሊታይ የሚገባው እና በቁልፍ አስረጅነት የሚያገለግል ነው፡፡
በዚህ ደረጃ  መንግስት እራሱን ፈትሾ ለማረም እና ለመታረም በእንቅስቃሴ ውስጥ በሚገኝበት አግባብ ላይ መታረሙ እና ለተሻለ ለውጥ መብቃቱ የአቋራጭ ስልጣን ፍላጎታቸውን፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳቸውን እና የጽንፈኛ አክራሪነት ግባቸውን መንገዶች እንደሚዘጋባቸው የተረዱ ሃይሎች ከህዝብ ተቃውሞ አደባባይ አልፈው የሃይማኖት መድረኮችን እና በአላትን ሳይቀር ጠልፈው በማራገብ ስለመሻታቸው ሲተጉ በዝምታ ማየት የዜግነት ግዴታን አለመወጣት ብቻ ሳይሆን ከላይ የተመለከቱ አኩሪ እሴቶችን ሳይቀር መሸምጠጥ ነው።
አሁንም መቃወምን መቃወሜ እንዳልሆነ በደማቁ ይሰመር። ምንም እንኳ ባለቤት አልባ ቢሆኑም  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመልካም አስተዳደር እጦት የተለበለበ ህብረተሰብ ያሰማቸው የተቃውሞ ድምጾች ሊሰሙ የሚገቡ መሆናቸው አያጠያይቅም። ያም ሆኖ ግን እነዚህን ጥያቄዎች ከላይ ለተመለከቱት እሴቶች ብንገዛ ኖሮ አደባባይ ሳይወጣ ሊመለስ አይቻልም ነበር?። እርሱም ይቅር አደባባይ ከተወጣ ኋላ የሉአላዊነታችን መገለጫ በሆነው ባንዲራችን ላይስ ባየናቸው መልኩ መዘባበት የተገባ ነበር?። ከላይ ከተመለከቱት እሴቶች አኳያ ይህም ይሁን እንኳ ባያስብል የመንግስን ንብረቶች አልፎና ይልቁንም “ድህነቱ ከአቅማችን በላይ ሆነ” ብሎ የወጣ ህዝብ የደሃ ንብረቶችን ማውደምና ለደሃው ህዝብ የለት ፍጆታ የሚሆኑ ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠልን ምን አመጣው?ምንስ ይሉታል???
ከሁሉ የሚልቀው ደግሞ አኩሪ የሆነው እና ሃገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይማኖታዊ እሴቱ በሚልቀው የእሬቻ በአል ላይ የሽብርተኛውን ባንዲራ ካልሰቀልን ብሎ መሟዘዝን እና ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆንን ምን አመጣው?። ከላይ ከተመለከቱት እሴቶች አኳያ ስራው እና ሴራው የህዝብ እንደማይሆን መገመት አይከብድም። በተለይ ለአባ ገዳዎች የኦሮሞ ህዝቦች ያላቸውን ቦታ ለምናውቀው ዜጎች። ያም ሆኖ ግን እንዲህ አይነቶችን የማይገልጹንና ክብራችንን የሚፈጠፍጡ ድርጊቶችን አለማውገዝና ሲሆን ቀድሞ ካልሆነም በኋላ ጸያፎቹን እና ጽንፈኞቹን አለማጋለጥ በራሱ ከላይ ከተመለከቱ ያኖሩን እና ወደፊትም እንደሚያኖሩን ከማያጠያይቁቱ እሴቶች ጋር አምርሮ መጣላት ነው።
በእሬቻ በአል ላይ የተፈጸመውን ደባ እና የአባ ገዳዎችን በረከት ያሳነሰ ምናልባትም በታሪክ የመጀመሪያ እንደሚሆን የማያጠያይቀው የወረደ ተግባር በማናቸውም መልክ ጨዋ ከሆነው የኦሮሞ ወጣት እና ህዝብ ሊሰነዘር የማይቻል እንደሆነ ለማጠየቅ ከድርጊቱ በኋላ ሲለቀቁ የነበሩ የዴያስፖራ ዘገባዎችን ጨምሮ ጽንፈኞቹ ያሰማሯቸው ሃይሎች በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያሰፈሯቸውን መመልከት ይበቃል።
የህግ አግባቦችን ጨምሮ በየትኛውም መመዘኛ ድርጊቱ ወንጀልና ሊያውም አሳፋሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቄጤማ በመጎዝጎዝ በአሉን ለማድመቅና ስለበአሉ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚረዱ ጽሁፎችን ለመበተን የወጣን ሄሊኮፕተር ቦንብ አዘነበች ብሎ ዘገባ ከድርጊቱ በስተጀርባ የኦሮሞ ህዝብ ሳይሆን እነማን እንዳሉበት የሚያረጋግጥ ነው። ያልሞተውን ሞተ፣ ያልተተኮሰውን ተተኮሰ ብሎ ወሬና ዘገባም በሞቱ ንጹሃን ውንድምና እህቶች ላይ መዘባበት እንጂ ህዝባዊነት አይደለም። ይህ አይነቱ አካሄድ ኢ-ሞራላዊና ህገወጥነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ምናልባትም ለእለት ትርፍ ጽንፈኞቹን፣ አክራሪዎቹን እና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎቹን ካልጠቀመ በቀር በማናቸውም መልክ ሃገርና ህዝብን የማይጠቅም ይልቁንም የሚያወድም መሆኑ ሊታወቅና በአጽንኦት ሊያዝ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ይሆናል።  
በዴሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ የመንግሥት ሥልጣን ከፓርቲዎች ወደ ፓርቲዎች የሚሸጋገርበት ብቸኛው አማራጭ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው። አገር ሰላም ሁሉም፤ ጤና የሚሆነውም በዚሁ ብቻ ነው ፡፡  
ከላይ የተመለከቱት ተምሳሌታዊ እና አስጎምዢ ስለመሆናቸው የተመሰከረላቸው የጋራ እሴቶች ልዩነታችንን በብልኃት እየፈታንና አንድነታችንን እያጠናከርን እንድንዘልቅ ያደረጉ መሆናቸውንም ማስታወስና ማስተዋል ከተገባን ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡ በውስጣችን የነበሩት እና ያሉት ጨዋነትና አርቆ አሳቢነት ልዩነትን ላከበረ አንድነት ምሰሶዎች ሆነው እንዲቆዩ እንጂ የማንም መቀለጃ እንዲሆኑ መፍቀድ አይገባም፡፡ እርስ በርሱ እየተከባበረና እየተመካከረ ልዩነቱን በአንድነት መንፈስ እያሸነፈ የኖረ ህዝብ ‹በልዩነት ውስጥ አንድነትን፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን› በተግባር ያፀናውን ሕዝብ ለሚመስል ምግባር ሊተጋ ይገባዋል እንጂ የጥቂቶች መቀለጃ መሆን በእርግጥም ያሳፍራል፡፡ 
በአሁኑ ጊዜ ከጨዋነት ጋር የማይመጋገቡና የሰዎችን መብት የሚዳፈሩ አሳሳቢ ድርጊቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ፈተና ውስጥ ከወደቀባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው በመንግሥት አማካይነት የሚፈጸመው መሆኑ ላይ መንግስት አምኖ ለመታረም ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ አግባቦች እያረጋገጠ ባለበት በዚህ ሰአት  በማኅበረሰባችን ውስጥ በግልጽ የሚታየው የተለየ ሐሳብን ያለማክበር ብሎም በጠላትነት  የመፈረጅ አባዜ በነፃነት ማሰብ የሚፈልጉ ዜጎችን እያሳቀቀ፤ ይልቁንም ከህግ ማእቀፍም በላይ ከላይ ከተመለከቱት እሴቶች ጋር የሚቃረን መሆኑንም የትኛውም ዜጋ ሊያጤነው የሚገባው ሰአት ላይ ደርሰናል፡፡
በሐሳብ መለያየት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር የተፈጥሮ ፀጋ መሆን ሲገባው ለምን ተቃራኒ ሐሳብ እንሰማለን የሚሉ አምባገነኖች በየቢሮው ሞልተዋል፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቡድን ድረስ ያሉ መብቶች ይከበሩ ብለው የሚጮሁ ሰዎች፣ እኛ ከምንለው ውጪ ሌላ ሐሳብ መደመጥ የለበትም ሲሉ መስማት ምን ማለት ነው? ማንም ሰው አዕምሮው ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ እንዳይናገር መከልከል ማለት ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑን እንዴት መገንዘብ ያቅታል? ሰዎች አዕምሮአቸው የነገራቸውን እንዲተነፍሱት ጋሬጣ መሆንስ ምን ይባላል? 
ሃሳብን ከመገደብ እና እነርሱ ያሉትን ያልሆኑት ላይ በየድረገጹ የሚጎርፈውን ናዳ ከመመልከት በላይ አሸማቃቂ ነገር የለም፡፡ ሰዎች በተናገሩ ቁጥር እንዲሸማቀቁ እየተደረገ በመሆኑ  የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች  ሰሞንኛዎቹን ሁካታዎች በተመለከተ አንተም ተው አንቺም ተይ ብለው ለመናገር እንኳ ሊደፍሩ አልቻሉም፡፡ የማህበራዊ ሚዲያዎቻችን “ጀግኖች” እንደምናያቸው፣ ሰዎች በተናገሩ ቁጥር ሀሳብን በሐሳብ ከመሞገት ይልቅ ማንነትንና ሰብዕናን በሚያዋርድ ስድብ እያሳቀቁ ሲሳደቡ እንጂ ሌላ ሲያደርጉ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት ገበያ ነው ሲባል እኮ፣ ከየትኛውም አካባቢ የሚነሱ ሐሳቦች በነፃነት እንዲሸራሸሩ ዕድል ይኑራቸው ማለት ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው ግን በተለይ በሶሻል ሚዲያ ያውም በፌስቡክ ‹ለምን ተናገራችሁ?› በሚያስብል ሁኔታ ዜጎች ሲወረፉ እና ሲዛትባቸው ነው፡፡ የሰዎች ሐሳብ በድጋፍና በተቃውሞ ውስጥ እየተቀረቀረ እንደ ስሜቱ ልክ ማሞገስና ማዋረድ ኢምክንያታዊ ከመሆኑም በላይ ከላይ ከተመለከቱት ምግባሮቻችን ያፈነገጠና ህገወጥነት ነው፡፡ ይህ የሕዝባችንን የጋራ እሴቶች የማይወክልና ከተራ የፖለቲካ ፍጆታ የማያልፍ አጓጉል ፍረጃ ለአገር የማይበጅ ከመሆኑም በላይ፣ ቅን ዜጎችን የአደባባይ ሰዎች እንዳይሆኑ በማድረጉ እና ሃይ ባይ እንዲሆኑ ባለማስቻሉ ይኸው ከተቃውሞው አደባባይ አልፎ የሃይማኖት መድረኮችም የጽንፈኞች እና የተላላኪዎች መፈንጫ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን ንጹሃንን በመቅጠፍ ሃገር እንዲያዝን አድርጓል፡፡ ደጋፊው ‹ነገረልኝ!› እያለ ጮቤ ሲረግጥ፣ ተቃዋሚው ‹ዓይንህ ላፈር!› ብሎ መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጣ በነፃነት ማሰብ ያከትምለታል፡፡ በነፃነት ማሰብ ሲያከትም የት ይደረሳል? አዎ መድረሻው ያው በእሬቻችን ላይ እንዳየነው የማንም መፈንጫና መዘባበቻ መሆንና ውርደት ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ የተመለከቱ አኩሪ ባህሎቻችንን ስንቅ፣ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ጋሻና መከታ አድርገን አደባባይ ልንወጣና ጥያቄያችንንም ልንጠይቅ፤ በጥያቄያችን ላይ የሚንጠላጠሉ ሃይሎችን ዞር በሉልን ልንል፣ ልናወግዝና ልናጋልጥ ይገባል። ያኔ የሰላም ፍላጎታችንና ጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ ያገኛል፤ ፊታችንም ሙሉ ለሙሉ ወደጀመርነው ፈጣን ልማታችን ይዞራል ማለት ነው።