መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል አጥፎ አያውቅም!

                                                   
ሽማግሌው ባዘቶ ጥጥ የመሰለ ፀጉራቸውን እያሻሹ “እጅ መንሻ ነው” አሉኝ። “ምኑ?” አልኳቸው። አካሄዳቸው የለመድኩት ስለሆነ ገብቶኛል። ወትሮም ቢሆን ወጋቸውን ከመሃል መጀመር ይወዳሉ። ግና ስረ-ነገሩን አይስቱም— አዛውንቱ ጎረቤቴ አባባ በቀለ ማንአህሎህ። ለጥቀውም “ዛሬ እናንተ ሙስና፣ ኪራይ መሰብሰብ፣ ጥገኝነት፣ በመንግስት ስልጣን የግል ኑሮን ማደላደል… ምንትስ እያላችሁ የምትጠሩት ‘ጉቦ’ ነዋ!” በማለት የጎንዮሽ እያዩኝ በእርጅና ምክንያት የተሸበሸበውን ፊታቸውን ፈገግ ለማድረግ እየሞከሩ ለጥያቄዬ ምላሽ ሰጡ። አባባ በቀለ ዕድሜያቸውን ባይነግሩኝም በግምት ወደ 80ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የሚሆን ይመስለኛል። ሰውዬው ዕድሜያቸው ቢገፋም ጨዋታ ወዳድና ስቆ አሳሳቂ ናቸው። በዚያ ላይ በዕድሜያቸው ብዙ ያዩ በመሆናቸው የሚሆነውንና የማይሆነውን በበሰለ ሁኔታ የሚያገናዝቡ ሰው ናቸው። 
ታዲያ የወጋችን መነሾ መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት በራሱ መዋቅር ውስጥ ሳይቀር በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና በተጠረጠሩ ባለሥልጣናቱ ላይ የወሰደው ርምጃ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ‘ዳግም እታደሳለሁ’ ማለቱን ተከትሎ የገባውን ቃል የማያጥፍ የመሆኑ ጉዳይ ነው። እናም ሰውዬው ጉሮሮአቸውን ሞረድ፣ ሞረድ አደረጉና “ምነው የዚህ ትውልድ ሰው ሆኜ በነበር?!” በማለት ትካዜ በተጫነው ቁጭት በሃሳብ ባህር የኋሊት ነጎዱ።…
እንዲህም አሉኝ።…“በኛ ዘመን እጅ መንሻ ለሹማምንቱና ለምስለኔው መብት ሲሆን፤ ለህዝቡ ደግሞ ግዴታው ነበር። ንጉሳዊው መንግሥትም ይህን ተግባር እንደ ነውር አይቆጥረውም። ደርግም ቢሆን ከጭፍጨፋው ባሻገር “ጉቦ” እያለ የውግዘት ዜማ አውጥቶ ቢዘፍንለትም፤ ድርጊቱ ግን የስርዓቱ ዋነኛ ስራ ማስኬጃ ሆኖ አልፏል። በተለይም ብሔራዊ ውትድርና በታወጀበት ወቅት በገንዘብ ኃይል የሃብታም ልጅ እናቱ ጉያ ውስጥ እንዲደበቅ ሲደረግ፣ የድሃው ልጅ ደግሞ የእሳት እራት የነበረበት ሁኔታ ሁሌም አይዘነጋኝም። ባለስልጣናቱም ቢሆኑ ‘ንጉስ አይከሰሰ፣ ሰማይ አይታረስ’ እንዲሉት ዓይነት በመሆናቸው ህግ የሚገዛቸው አልነበሩም። የዛሬው መንግስት ግን ይገርማል። ‘በሀገሬ ልማትን ለማምጣት ራሴን ማስተካከል አለብኝ፣ የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸው በሚያውሉት ላይ ርምጃ ወስዳለሁ፤ እኔም እንደ መንግስት እታደሳለሁ’ ብሎ ህዝቡን ያንገላቱትንና ሃብትና ንብረቱን ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትን ሹማምንቶቹን እየገመገመ ይከሳል፤ ያስፈርዳል፤ ይቀጣል፤ ያሳስራል። አሁን ደግሞ የህዝቡን ምሬት በማዳመጥ “አኔ ራሴ ዳግም እታደሳለሁ” እያለን ነው። ልጄ ተወኝ እስቲ! ዕድሜ የሰጠው ሰው ገና ብዙ ያያል።”…
ጎረቤታችን አባባ በቀለ ዕድሜ የተጫናቸው አዛውንት ቢሆኑም፤ የነገር አተያያቸው ግን ሁሌም እንደገረመኝ ነው። እርሳቸው “እጅ መንሻ” እያሉ የሚጠሩት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፤ በማህበረሰባችን ውስጥ ሲንቆለጳጰስ የኖረና ዛሬም ድረስ ተንከባሎ የመጣ ችግር መሆኑን አልሸሸጉኝም። የዛሬው መንግስትም በጥልቀት ዳግም ለመታደስ ምናልባትም ደንቃራ ሆኖ ሊያስቸግረው የሚችለውና በአተገባበሩ ላይ ዘለግ ያለ ጊዜ የሚወስድበት ነገር ካለም በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ይህን የተዛባ አስተሳሰብ የመቅረፍ ሁኔታ መሆኑንም ጠቁመውኛል። ሆኖም በእርሳቸው ዕድሜ ካዩዋቸው መንግስታት በእርሳቸው አጠራር “የኢአዴግ መንግስት” በእስካሁን አመጣጡ የገባውን ቃል አጥፎ የማያውቅ የህዝብ ዋስና ጠበቃ መሆኑን መታዘባቸውን ነግረውኛል። እናም የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል እንደ ትናንቱ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን በእርግጠኝነት ይናገራሉ። እርግጠኝነታቸውን “የትናንት ማንነትህን ንገረኝና የዛሬ አንተነትህን ልንገርህ” በሚል አባባል አጅበው።
እርግጥ አዛውንቱ ያጫወቱኝ ይህ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየው የተሳሳተ አስተሳሰብ በስነ-ቃል እስከመታጀብ የደረሰ ነው። ይህን ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለል የመጣ የተዛነፈ እሳቤን በጥቂቱ ለማንሳት ያህል፦   
      * በምስጋና የሚኖሩ የገነት መላዕክት ብቻ ናቸው፤
      * የተቆለፉ እጆች የሰውን ልብ አይከፍቱም፤
      * በምድራዊው ዓለም አንቀሳቃሽ ሞተሩ ገንዘብ ሲሆን፤ በሰማያዊው ዓለም    
       ደግሞ ፀሎት ነው፤
      * ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል፤ እና
      * የሚያበራይ በሬን አፉን አትሸብበው…የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
እርግጥ እነዚህ አባባሎች ከስልጣን ጋር ተያይዘው በተለያዩ ጊዜያት በህብረተሰቡ ውስጥ የተባሉና የተነገሩ ናቸው። አባባሎቹ የልማታዊ አስተሳሰብ ተምሳሌቶች አይደሉም። በአንድ ሀገር ውስጥ ልማትና ብልፅግና እንዲስፋፉ የተነገሩ ቀስቃሾችም አይደሉም—“በመንግስት ስልጣን ተጠቅመህ ብላና አብላኝ” ለማለት የተሰደሩ እንጂ። አንድ ሰው በልማታዊ ውጤቱ መጠን ሃብት ማፍራት የሚችል መሆኑንም አያመላክቱም። እሳቤያቸው በመንግስት ስልጣን ግላዊ ጥቅምን ማደላለደል በመሆኑም አጠቃላይ ማህበረሰቡን የሚወክሉ ናቸው ለማለትም አያስደፍርም። ይልቁኑም በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ያለን አላስፈላጊ ጥቅም የመሻትና ከፍ ሲልም የመንግስትን ጥቅም የግል መገልገያ አድርጎ የመጠቀም አስተሳሰብን የሚያሳዩ ናቸው። 
እንደ እውነቱ ከሆነ የእነዚህን አባባሎች አስተሳሰብ አስከፊነትንና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ለመረዳት ከእንደ እነ አባባ በቀለ ማንአህሎህ ዓይነት የዕድሜ ባለፀጋዎች የተሻለ አስረጅ ፈልጎ ማግኘት ላሳር ይመስለኛል። ምክንያቱም ባለፏቸው ስርዓቶች ውስጥ አንዱ በይ ሌላው ተመልካች፤ ጥቂቱ ተቀባይ አብዛኛው ህዝብ ሰጪ፣ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ፀረ-ዴሞራሲያዊነት እንዲሁም ለስልጣን ቀረቤታ ያለው ወገን ብቻ ተጠቃሚ እየሆነ የዜጎች ኑሮ እንደ ካሮት ቁልቁል ሲያድግ የትዕይንቱ ታዳሚ የነበሩ በመሆናቸው ነው። ለዚህም ይመስለኛል—አዛውንቱ ጎረቤቴ ሰሞኑን መንግሥት “ዳግም እታደሳለሁ” በማለቱ “አበጀ!፣ ጎሽ! እንዲያ ነው እንጂ የህዝብን ጥያቄ አድምጦ የሀገርን ዕድገት ለማሳለጥ ቃል መግባት! መቼም የዚህችን ሀገር ጅምር ዕድገት የኋሊት ለመቀልበስ የሚከጅሉ ኃይሎች ካልሆኑ በስተቀር፣ ይህን የመንግስትን የተቀደሰ ተግባር የሚፃረር ወገን ሊኖር የሚችል አይመስለኝም” ሲሉ ያጫወቱኝ።
እርግጥም የማንኛውም ሀገር ዴክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ባህሪ ራሱን በራሱ ማረሙና ያሉበትንም ችግሮች ማጥራት የሚችል መሆኑ ነው። ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያጠራም፤ በውስጡ ያለው ህዝብ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመምረጥ… ወዘተ. መብቶቹን ተጠቅሞ በስልጣን ላይ ያለውን ገዥ ፓርቲም ይሁን እርሱ የሚመራውን መንግስት በገሃድ ሂስ ማድረግ ሲችልና ገዥው ፓርቲም ይህን አድምጦ ማስተካከል ይኖርበታል። አሊያ ግን ህዝቡ የሰጠውን ውክልና በመሰረዝ ለሌላ ፓርቲ ሊሰጠው ይችላል። 
ታዲያ ይህ አሰራር በዴሞራሲያዊ ሀገራት ውስጥ ገቢራዊ የሚሆነውም፤ የትኛውም ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ከችግር የፀዳ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። እርግጥም የስርዓቱ ፈፃሚዎች ሰዎች በመሆናቸው ፍፁማዊ የሆነ አሰራር ሊጠበቅ አይገባም፤ አይችልምም። ዋናው ነገር መንግስት የህዝቡን አግባብ ያላቸውን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ አዳምጦ ምላሽ ለመስጠት ያለው ዝግጁነት ነው። ለዚህም ይመስለኛል—የኢፌዴሪ መንግስት ይህን በአሁኑ ወቅት ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዩች ዙሪያ ከህዝቡ እየቀረቡ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በጥልቅ ዳግም ተሃድሶ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን በመግለፅ ላይ የሚገኘው።
እርግጥም አዛውንቱ ጎረቤቴ እንዳሉት የኢፌዴሪ መንግስት በህብረተሰቡ ውስጥ ከስልጣን ጋር ተያይዘው ያሉት የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ለማረም ዘለግ ያለ ጊዜ ቢጠይቅም፤ መንግስት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ግን ዝግጁ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኛ ጭምር መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። የትናንት ተግባራቱ በገሃድ አፍ አውጥተው ይናገራሉና። እናም መንግስት ትናንት ‘አደርጋለሁ’ ብሎ ቃሉን እንዳላጠፈው ሁሉ፤ ዛሬም ለህዝቡ የገባውን ቃል ከቶ ሊያጥፍ አይችልም። እስካሁን ከተመለከትነው ባህሪው በመነሳትም ይህን ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። ምንም እንኳን ጉዳዩ “ዓባይን በጭልፋ” እንዲሉት ዓይነት ቢሆንም፤ እስቲ በምሳሌነት አራት ሁነቶችን ብቻ እንመልከት—በቀዳሚው ተሃድሶ፣ በምርጫ 97 እና 2002 እንዲሁም የዛሬ አምስት ዓመት የተፈጠረውን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ያከናወናቸውን ተግባራት በመጠቃቀስ።
ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ዕውን በሆነው ቀዳሚው ተሃድሶ፤ በሀገሪቱ ውስጥ አንዣቦ የነበረው የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርን ለመግታት በተደረገው ትግል፣ በድርጅቱ ውስጥ ለሁለት የተከፈለውን ጎራ በመለየት ለህዝቡ የተፈጠረውን ችግር እንደሚፈታና በሀገሪቱ ውስጥ ፈጣን ልማትን እንደሚያረጋግጥ ቃል ገብቶ ነበር። እናም በገባው ቃል መሰረት ለሀገረቲ ዕድገት መሰናክል የሆኑ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን በማቋቋም እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ወገኖች ለህግ የማቅረብ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰርቷል። የሀገሪቱን ኢኮኖሚም ለማሳደግ ጥሯል። በወቅቱ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያደቀቀው በመሆኑ፤ይህን በማሻሻልና ህዝቡ በየደረጃው ይብዛም ይነስ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። ዛሬ ለምንገኝበት የህዳሴ መስመርም መሰረት ጥሏል።
በምርጫ 97 ወቅትም ቅንጅት የተሰኘው ነውጠኛ ቡድን ከውስጥ የቀለም አብዮተኞች ደግሞ ከውጭ ተሳስረው በፈጠሩት ቀውስ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም በወቅቱ መንግስት ህዝቡን በማረጋጋትና የተፈጠረውን ችግር እንደሚቀለብስ ቃል ገብቶ ነበር። እናም ይህን ቃሉን ሳያጥፍም የሀገራችን ህዝቦች ከተፈጠረው ችግር እንዲያገግሙና ፊታቸውን አስከፊውን ድህነት ልመዋጋት እንዲያዞሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በዚህም ዓለም የመሰከረለትንና አፍሪካውያን እንደ ሞዴል እየወሰዱ ያሉትን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማስዝገብ ችሏል። 
በምርጫ 2002 ወቅትም ቢሆን ህዝቡ ለመንግስት የስልጣን ውክልናውን ሲሰጥ “ልማቱን አጠናክረህ እንድትቀጥልና ከድህነት አረንቋ እንድታወጣን አደራ ሰጥተንሃል” በማለት እንደነበር እናስታውሳለን። በወቅቱም ህዝቡ መንግሥት ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በግልፅ በመናገር ጭምር ነበር አደራውን የሰጠው። ታዲያ ምርጫው በተጠናቀቀ ማግስት መንግሥት የህዝቡን ሂስ ተቀብሎ ውስጡን በድጋሚ እንደሚፈትሽና ልማቱን እንደሚያሳልጥ ቃል ገብቶ ነበር። 
እናም ይህን ቃሉን ዕውን ለማድረግ የሀገሪቱን ህዳሴ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ ይፋ አድርጓል። በዚህም የህዝቡን ልማታዊ አደራ ከግብ ለማድረስ ጥሯል፤ ዕቅዱን ለማሳካትም ትላልቅ ስራዎችን በማከናወን ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል። ከዚያም በኋላ ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ምከንያት የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታለት ህዝቡ ሲጠይቀው ቃሉን ጠብቆ ምላሽ የሰጠ መንግስት ነው። 
መንግስት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ ርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሃዝ በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት በማከፋፈል እንዲሁም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበትን እንደ “አለ በጅምላ” ዓይነት የአቅርቦት ቦታዎችን በመክፈት የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግስት ነው። ይህም የኢፌዴሪ መንግስትን ህዝባዊነትና ሁሌም ቢሆን ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን የሚያመላክት ነው። እርግጥ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ምሳሌዎች እጅግ ከሚበዛው የመንግስት ተግባራት ውስጥ እፍኝ ያህሉን ነው። ምንም እንኳን እነዚህ መንግስታዊ ህዝባዊነት ምሳሌዎች ቢሆኑም፤ ዋናውንና መንግስት ለህዝቡ የሀገባውን ቃል የማያጥፍና ሁሌም ተግባሮቹን የሚያከናውነው ህዝቡን መሰረት ባደረገ አኳሃን መሆኑን ማሳያዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ይመስለኛል— ልክ የእኔው ዓይነት እምነት ያላቸውና በመግቢያዬ ላይ ለፅሑፌ መግቢያ ያደረግኳቸው  ጎረቤታችን አባባ በቀለ “የትናንት ማንነትህን ንገረኝና የዛሬ አንተነትህን ልንገርህ” ያሉት። አዎ! መንግስት ዛሬም “ዳግም በጥልቀት እታደሳለሁ” ሲል ቃሉን እንደማያጥፍ የትናንት ማንነቱ በገሃድ የሚነግረን በመሆኑ እምነታችንን በእርሱው ላይ መጣል ትክክለኛ አካሄድ ይመስለኛል።