ሕዝቡ ጠይቋል፤ መልስ እየጠበቀ ነው

በቅርቡ በፌደራል ደረጃ ከመምህራን፣ አልፎ አልፎም ከህብረተሰቡም ጋር በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና በክልሎች ሰፊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ለምን በህዝቡ ላይ በደልና እንግልት ይፈጸማል፤ ለምንስ ይሄ ተደረገ ወይም ይደረጋል? ብለው የሚጠይቁ ዜጎች አንገታቸውን እንዲደፉ ለማድረግ ያልተገባ ስም የመስጠትና የማሸማቀቅ ስራ እንደሚሰራ፣ ህዝቡ ጥያቄ እንዳያነሳ የስነልቡና ጫና እንደሚደረግ ህዝቡ በውይይቱ ወቅት አጋልጦአል፤ ስንነጋገር፣ ስንጠይቅ ኖረናል፤ መልስ ግን የላችሁም፡፡ መነጋገሩ ምን ፋይዳ አለው? ያሉም ብዙዎች ናቸው፡፡

ተሰብሳቢው በየቦታው በመንግስትና በህዝብ ሀብት ላይ ተፈጽሞአል ስለሚለው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ወዘተ ችግሮች ሁሉ ተነስተዋል፤ የመድረክ መሪዎችም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል መልሰዋል፤ የከበዳቸውን መዝግበው ይዘዋል፡፡ መልሱ የሚገኘው ከበላይ አለቆች ነው እናቀርባለን የሚል አካሄድም ነበር፡፡

ጥልቀታዊው ተሀድሶ የት ድረስ ይራመዳል፤ ምንስ ተጨባጭና ተግበራዊ ለውጥ ለህዝቡና ለሀገሪቱ ያመጣል፤ ተመሳሳይ ግለሰቦችን በመሾምና በመሻር፣ በማሰርና በመፍታት፣ በሙስና ከአንድ አካባቢ የተባረረን ግለሰብ ሌላ ቦታ ወስዶ በመሾም በህዝቡ ላይ ዳግም እንዲፈነጭበት በማድረግ የሚመጣ፣ የሚታይ ለውጥ አይኖርም፤ ይሄንንስ እንዴት ታዩታላችሁ? ሲል ተሰብሳቢው የማያባራ ጥያቄ መጠየቁን ማስተዋል ተችሏል፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሰጥበትም የማይሰጥበትም ሁኔታ በሰፊው ታይቶአል፡፡ መድረክ ሰብሳቢዎቹ በስፋት የአቅምና የብቃት ማነስ ችግሮች ታይተውባቸዋል ነው የሚለው ተሰብሳቢው፡፡

እንዴት ነው ጥልቀታዊው ተሀድሶ መሰረታዊ ስርነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው? በስርአቱ ውስጥ ተሸጉጦ የደረጀውን ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢ ሀይል በምን መልኩና እንዴትስ ነው በህግ ተጠያቂ ሊያደርገው  የሚችለው? በማለት ተሰብሳቢው ጠይቆአል፡፡ ጥያቄው በአወያዮቹ አቅም የሚመለስ ስላልሆነ  በጥያቄነቱ  ይያዛል፤ ወደበላይ አካል ይተላለፋል በሚል፡፡

ተግባራዊ መልስ ከመንግስት በመጠበቅ ተሰብሳቢው ሳያባራ ይጠይቃል፡፡ ውይይቶቹ ግልጽና ህዝቡ መሰረታዊ ችግሮቹን ይፋ ያወጣባቸው ነበሩ፡፡ በተሰጣቸው የህዝብ ወንበርና ሀላፊነት፣ ሽፋንና ከለላ በመጠቀም ሲዘርፉ ሲመዘብሩ የነበሩትን  በህዝቡም ላይ ሲሰሩት የነበረውን ግፍና በደል መንግስት አያውቅም አይባልም፡፡ ምን ለማድረግ አስቦ ይሆን? ተሰብሳቢው  ይጠይቃል፡፡ እናሳ ምን እየተደረገ ነው ያለው፤ እከክልኝ  ልከክልህ ነው፤ ማን በልቶ ማን ይቀራል ነው ተሸፍነው ተለባብሰው  ይቀጥሉ ነው? ምንድነው  የምትወስዱት ወሳኝ  እርምጃ  ይገለጽልን፤ ህዝብ በውይይቱ ላይ ይጠይቃል፡፡ መንግስት ሆነ በኢህአዴግ የዳጎሰ መረጃና ማስረጃ አለው ተብሎ ስለሚታመን ወሳኝ እርምትና እርምጃ ይወስዳል ተብሎ በህዝቡ ዘንድ  ይጠበቃል፡፡

የኢህአዴግ አባል የሆኑ ግለሰቦች በአመራር በተቀመጡበት ቦታ የእውቀት ማነስ፣ በራስ የመተማመንና የመወሰን ችሎታና ብቃት ማጣት  ከዚህም ባለፈ አይን ያወጣ ዘራፋ ውስጥ መሰማራታቸው ኢህአዴግ በህዝብ ግምት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ የምልመላ ስርአቱም ሰው በማግበስበስ ላይ የሚያተኩር ጥራትና ብቃትን የማይፈትሽ በመሆኑ ድርጅቱን ትዝብት ውስጥ ጥለውታል፡፡ ህዝብ እንዲመረር፣ እንዲከፋ፣ በስርአቱ እምነት እንዲያጣ  ያደረጉት የራሱ የኢህአዴግ አባላት ናቸው ባዩ ተሰብሳቢ ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ለዚህስ ምን መልስ አላችሁ ሲል ተሰብሳቢው ህዝብ መድረክ መሪውን ይጠይቃል፡፡ መልስ የለም፡፡ ጥያቄው ወደላይ ይሄድ ዘንድ ይመዘገባል፡፡  

ህዝብን ስለሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት መልካም አስተዳደር ለማስተማር የሚቀርቡት ካድሬዎች ራሳቸው በቂ ትርጉሙን አያውቁትም፤ ህጉንም ህገ መንግስቱንም በበቂ ሁኔታ አልተረዱትም፤ ሊማሩ እንጂ ሊያስተምሩ የሚገባቸውም አይደሉም፤ የዜጎች መብትና ነጻነት እስከምን ድረስ እንደሚሄድ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ተሰብሳቢው ይጠይቃል፡፡ የመድረኩ መሪ ማስታወሻ ይይዛል፡፡ መልስ የለም፡፡ መልስ አለ ከተባለም “ምላሽ ከላይኛው አመራር ይሰጣል” የሚል ነው፡፡ ካድሬዎች አለቆቻቸው ሲናገሩ የሰሙትን መልሰው ማስተጋባት፣ አዲስ ቃል ሲነገር ከሰሙ ቶሎ መቅለብና በተራቸው ያንን ማስተጋባት ብቻ ነው የሚችሉት የሚለው የህዝብ አስተያየትም ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ከህዝቡ ጋር ሰፊ መተላለፍ የተፈጠረው፡፡ ካድሬዎቹ አቅማቸውን የሚፈትን ያላቸውን  እውቀት የሚገዳደር ሰው ካጋጠማቸው ቶሎ ብለው ይሄ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ነው ሲሉ መወንጀልን ተክነውበታል ነው የተባለው፡፡

ራሳቸው ኪራይ ሰብሳቢነት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፡፡ ፈተናው ለኢህአዴግም ለህዝብም የከባድም ከባድ ነበር፡፡ ኢህአዴግ አባላቱን በማስተማርና የእውቀት ባለቤት በማድረግ በኩል ብዙ ሰርቶአል፡፡ እነሱ ግን የሚጠበቀውን ያህል መሆን አልቻሉም፡፡ እራሳቸውን በማንበብ የማብቃት የሰፊ እውቀት ባለቤት የማድረግ አመለካከታቸውን የማስፋት ነገር ብዙም የለም፡፡ በእውቀትና በአመራር ክሂሎት መብቃት ህዝብን ለመምራትና ለማስተዳደር የግድም ግድ ነው ሲል ተሰብሳቢው ህዝብ አስተያየቱን ሰጥቷል።        

ልማትና እድገትን ህዝብ አይጠላም፡፡ ችግሩ  የማልማቱ ተግባር እየተሄደበት ያለው አካሄድ የህዝቡን ህይወት ያላገናዘበ፣ ኑሮውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ፣ ከፍተኛ ህዝባዊ ቅሬታዎችን የፈጠረ፣ ከሀላፊዎች የግል ጥቅም ጋር የተቆራኘ ስራ የሚሰራበት መሆኑ ላይ ነው፡፡

ተሰብሳቢውም ሆነ ህዝቡ ግዜ ይፈታዋል በሚል ብሂሉ ዝምታን ቢመርጥም ፍጹም ደስተኛ አለመሆኑን በተገኘው መድረኩ ሁሉ ይገልጻል፡፡ የሚወጡት መመሪያዎች ወዲያው ወዲያው ስለሚሻሩ የህዝቡን ችግር የሚፈቱና ምላሽ የሚሰጡ ሁነው አልተገኙም፤ ጠብቁ አዲስ መመሪያና ደንብ ይወጣል ይባላል ይሄ ምን ማለት ነው? ሲል ህዝቡ ይጠይቃል፡፡ መልስ ግን  የለም፡፡ እነዚህ ሁሉ የህዝብን ቀየሜታና ቅሬታ እያሳደጉ የሄዱ አሰራሮች የግድ በመንግስት መመለስ አለባቸው፡፡

መንግስት ከተሞችን በማልማት ሰፊ ለውጥ ማምጣቱ የሚደነቅና የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ የሀገር ምሰሶ ዋልታና ማገሩ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ እንዲከፋ እንዲያለቅስ በመንግስት ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር ያደረጉት መንግስት ቦታና ክብር ሰጥቶ ያስቀመጣቸው የተጣለባቸውን አደራ ተላልፈው ለግል ጥቅማቸው በቆሙ በመንግስትም ስም ሲያስፈራሩ በኖሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ የጥልቀታዊው ተሀድሶ አቢይ ትኩረት መሆን ያለበት ስርአቱ በዚህ ደረጃ ተጋላጭ እንዲሆን በህዝብ አመኔታ እንዲያጣ እንዲማረር አስተዳደሩንም እንዲጠላ የማድረግ ስራ በመስራት ህዝብና መንግስትን ያናቆሩትን ለይቶ ማውጣት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ መቻል ላይ ነው፡፡

አመኔታን መልሶ በህዝቡ ውስጥ የመገንባትን ተጨባጭ ስራ መስራት ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ብዙ ችግሮችን ከህዝቡ ጋር በመቆም መቅረፍ ይቻላል ሲል የውይይቱ ተሳታፊ የሆነው ህዝብ ያሳስባል

የእያንዳንዱ ግለሰብ ዜጋ ብሶትና ምሬት በየቦታው ተጠራቅሞ ነው በድምሩ የህዝብ ብሶት ምሬትና ቁጣን የሚወልደው፡፡ እነዚህን አይነት ሰዎች ተሸክሞ አዝሎ በአካባቢም ሆነ በሀገር ደረጃ ምንም አይነት ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ህዝብም መንግስትም ያውቅሉ፡፡ ታደያስ?

ሀገርና ህዝብን ሳይሆን  እራሳቸውን የሚያስቀድሙ ግለሰቦች የመጨረሻው ደረጃቸው በህዝብ ፊት መዋረድ ነው፤ ቢሸፈኑም ከህዝብ እይታ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለዚህስ ምን ታስቦአል በማለት ህዝብ ይጠይቃል፡፡ አጣዳፊ መልስ ሊሰጠው የሚገባ ጥያቄ።

ባጠቃላይ ውይይት መደረጉ መልካም ነው። ህዝቡ መጠየቁ እሰየው የሚያሰኝ ነገር ነው። ዋናው ነገር ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘታቸው ነውና  በዚህ ጉዳይ መንግስት ሊፈጥን ይገባል።