እነ ጃዋር እስከ መቼ በድሃው የኦሮሞ ህዝብ ይነግዳሉ?

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ እነ ጃዋር የራሳቸውን የፖለቲካ ንግድ ለማጧጧፍ ሲሉ በኢሬቻ በዓል ላይ ያስነሱትን ሁከት ተከትሎ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት፣ በመላው ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ያለው የኢሬቻ በዓል ለምን የእነ ጃዋር መጫወቻ እንደሆነና  በበማንኛውም ኦሮሞ የሚከበሩትን አባገዳዎች እነርሱ እንደማያዳምጧቸው እንዲሁም ከተፈጠረው ሁከት በስተጀርባ ያሉትን የውጭ እጆች ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በዚህኛው ክፍል ደግሞ ከሁከቱ በስተጀርባ ያሉትን ተጨማሪ እጆችን፣ እነ ጃዋር እስከ መቼ በኦሮሞ ህዝብ እንደሚነግዱ ብሎም ምን እንዳሰቡልንና እንደደገሱልን መረጃዎችን በማጣመር እንዲህ አጠናቅሬዋለሁ።… ተደማሪውና ቀሪው የውጭ ኃይሎች እጅ እንዲህ ይቀጥላል።…

ያኔም በሙባረክ ዘመን ልክ እንደ አሁኑ ዓይነት ፍላጎት በኤርትራ መንግስት ደላላነትና በግብፆች የገንዘብና የሎጀስቲክስ አቅራቢነት የተለያዩ የኢትዮጵያ ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች እንዲታጠቁና ድንበር አቋርጠው እንዲገቡ ተደርገዋል። ግን አልተሳካላቸውም። የተላኩትን መልዕክት ሳያደርሱ መንገድ ላይ ቀርተዋል። እናም ትናንት ያልሰራ ዘዴ ዛሬ ላይ ይሰራል ማለት በምንም ዓይነት አመክንዮ ሚዛን ላይ የሚቀመጥ አይደለም። ሀገራችን አሁን ያለችበት ቁመና ካለፉት አራት ዓመት ተኩል በፊት ከነበራት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተሻሻለ ነው። በመሆኑም በትናንት ስሌት ዛሬ ላይ መጓዝ ምናልባትም በፈጣን ለውጥ ውስጥ ያለውን ዘመን አለመገንዘብ ይሆናል።

ለነገሩ ግብፆች ሁሌም “ታሪካዊ የውሃ ድርሻ አለን” የሚል ያረጀና ያፈጀ እንዲሁም አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ-ዘመን ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለውን የቅኝ ግዛት የውሃ ስምምነቶችን በመጥቀስ ጊዜያቸውን የሚያባክኑ ስለሆነ የትናንት አስተሳሰብን አለመተዋቸው የሚገርም አይደለም። ያም ሆኖ ግን በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እስካሉ ድረስ፤ ለግብፆች “እኔ ብቻ ልብላ፣ እናንተ ጦም እደሩ” የሚል አሮጌ አስተሳሰብ ሲባል፣ ተቆራርሳ የምትዳከምና ዓባይን መገደብ የማትችል ለንቋሳ ኢትዮጵያ እንደሌለች ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል—ትናንት ዛሬ አይደለምና።

የኦነግን ካባ ደርቦ ኢስላሚክ ኦሮሚያን ለመፍጠር የሚሰራውና “ኦሮሞ ሁሉ እስላም ነው” የሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድን የሚከተለው ጃዋር መሐመድም ሌላኛው የባዕዳን ተላላኪ ነው። ጃዋር የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የዶክትሬት የማሟያ ፅሑፉን አሜሪካ ውስጥ የሚሰራ ተማሪ ነበር። የአንድ ተማሪ አቅም ደግሞ ይታወቃል። ይሁንና በተለያዩ ወቅቶች በአሜሪካ ድምፅ አማርኛው ክፍል “የፖለቲካ ተንታኝ” እየተባለ በመቅረብ በአንድ በኩል ኦነጋዊ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የእስላማዊ ኦሮሚያን አፅናፍ ሲሰብክ አዳምጠነዋል።

በዚህም “ሜጫውን” ትከሻው ላይ አድርጎ እየተንጎራደደ ስለ ኦሮሞነቱና ስለ እስልምናው ብዙ ማቅራራቱን አስታውሳለሁ። የግብፁን “የእስልምና ወንድማማቾች ቡድን”ን ይመሩ የነበሩትና ኋላ ላይ በአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት ፊልድ ማርሻል አልሲሲ መፈንቅለ መንግስት የተደረገባቸው መሐመድ ሙርሲ በይፋ ያራምዱት የነበረውን እሳቤ ጃዋርም አንድም ቃል ሳይጨምርና ሳይቀንስ “…ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዓባይ ላይ ግዙፍ የግድብ ግንባታ ማካሄድ አይደለም። የሚበጃት ያላትን ወንዞች በመጠቀም ትንንሽ ግድቦችን መገንባት ነው።…” የሚል አስተያየቱን ደጋግሞ ሰንዝሯል።

እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ሰውዬው “የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ” (OMN) የሚባል ጣቢያ ዳይሬክተር መሆኑን የሰማነው። በወቅቱ ‘እንደምን አንድ ተማሪ በየዕለቱ የሚተላለፍ ሚዲያ ሊያቋቁም ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን አስታውሳለሁ፤ እኔን ጨምሮ። ግና እኔን ጨምሮ እነዚህ ወገኖች ለምላሹ ብዙም ሩቅ አልተጓዙም። የጣቢያውን ፕሮግራሞች ከተከታተሉ በኋላ የግብፆች ኢትዮጵያን የማዳከም እጅ ሊኖርበት እንደሚችል ለመገንዘብ አልተቸገርንም። ይህ የጃዋር ተላላኪ እጅ በማህበራዊ ሚዲያ ኢትዮጵያን የማተራመስ ዓላማ ያነገበ መሆኑንም ለማወቅ እንዲሁ። እናም ከባዕዳን በገፍ የሚቀበለውን ገንዘብ በመጠቀምና ጥቂት የትርምስ ሃይሎችን በተለያዩ ድረ ገፆችና ፌስ ቡክ ላይ ሁከት የሚፈጥሩ አሉባልታዎችን ለ24 ሰዓት እንዲለጥፉ በመቅጠር የባንዳነት ተግባሩን በመከወን ላይ ይገኛል። በእኔ እምነት በአጭሩ ጃዋር የኤርትራ መንግስት ከግብፅ በደላላነት “ኮሚሽን” እየተቀበለ ወይም ግብፅ ራሷ የቀጠረችውና ሀገራችን ውስጥ ትርምስ እንዲፈጠር የሚሰራበት ሚዲያ ዳይሬክተር ነው። ሁለት ቀጣሪዎች ይኖሩታልም ብዬ አስባለሁ—ደላላው ሻዕቢያና የኢትዮጵያን ብልፅግና ማየት የማይፈልጉት ግብፆች። አዎ! ጃዋር የኤርትራ መንግስት በሚዲያ ዳይሬክተርነት ቀጥሮት፣ ክፍያውን ከግብፅ የሚቀበል ተላላኪ ነው። እናም የእርሱ ነገር “ሁለት እናት አለሽ፣ አንደኛዋ ብትሞትብሽ በሌላኛዋ ትምያለሽ” የሚሉት ነገር ዓይነት ይመስለኛል። ይህ ሰው ዛሬም እስከ ተከፈለው ድረስ በያዘው የትርምስ አጀንዳ የአሮሞ ህዝብን ባህላዊ ትውፊቶች በማወክ የህዝቦችን ህይወት በአደባባይ እየቀጠፈ ነው።

በእኔ እምነት ግብፆች በአንድ በኩል በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር እየተደራደሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነ ጃዋርንና ሌሎች የኢትዮጵያ አሸባሪዎችን እየደገፉ ሀገራችንን ለማተራመስና ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን “በሁለት ቢላዋ” የመብላት ፍላጎታቸውን መንግስት በተገቢው ሁኔታ ማጤን ያለበት ይመስለኛል። ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ከግብፅ ጋር በግድቡ ዙሪያ መተማመንን ለመፍጠርና የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያካሂደው ውይይት በሳልና የሰከነ መሆኑን ብገነዘብም፤ ግብፆች ከእነ ኦነግና ጃዋር ጋር እየፈጠሩ ያሉት የጥፋት ጋብቻ የህዝባችንን ህይወት እየቀጠፈ በመሆኑ ጉዳዩ ብርቱ ክትትል የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ ግን ይህ የእነ ጃዋር በንፁሃን ድሃ የኦሮሞ ህዝብ ስም የሚያካሂዱት የባዕዳን ተላላኪነት ንግድ አንድ ቦታ ላይ መቆም እንዳለበት ብዙዎቻችንን የሚያስማማን ይመስለኛል። 

እነ ጃዋር እስከ መቼ በድሃው የኦሮሞ ህዝብ ይነግዳሉ?

በኢሬቻው በዓል ላይ ለሞቱት ሰዎች እነ ጃዋር በተገላቢጦሽ የኦሮሞ ህዝብ ተቆርቋሪ መስለው በዲያስፖራው ውስጥ አሉባልታን እየነዙ ነው። ሰሞኑን በተመለከትኩት አንድ ቪዲዩ ላይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ዳይሬክተር ተብዬው ጃዋር መሐመድና የኢሳት (እሳት ቢባል ማንነቱን የሚገልፀው ይመስለኛል) ዳይሬክተር የተሰኘው አበበ ገላው የኢሬቻን በዓል መቋረጥ ተከትሎ ያሰሙትን ዲስኩር አዳመጥኩ።

እርግጥ የእነርሱን ንግግር እዚህ ላይ መድገም እነርሱን የሆንኩ ያህል ስለሚሰማኝ ልደግመው አልሻም። ሆኖም ሁለቱ “ዳይሬክተሮች” በኢሬቻ በዓል ላይ ሐይቅና ገደል ውስጥ ገብተው ህይወታቸውን ያጡት ንፁሃን ዜጎቻችንን መንግስት በጥይትና በኤሊኮፕተር እንደገደላቸው አስመስለው ላወሩት አስቂኝ የበሬ ወለደ ተረት ምላሽ መስጠት ተገቢ ይመስለኛል።

እዚህ ላይ ግን ውድ አንባቢዎቼ በቅድሚያ እንዲገነዘቡልኝ የምሻው አንድ ጉዳይ አለ። ይኸውም “ኢሳት” የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እርስ በርስ ለማባላት የኢትዮጵያን ዕድገት ማየት በማይፈልጉ ሀገሮች የተቋቋመ ጣቢያ መሆኑን ነው። ምንም እንኳን ጣቢያው ግንቦት ሰባት የተሰኘው የሽብር ቡድን ልሳን ቢሆንም ቅሉ፤ ባለቤቶቹ ሻዕቢያና ግብፅ ናቸው ማለት ይቻላል። በጣቢያው ላይ የሚነዛው አሉባልታ ሁሉ በግንቦት ሰባት ስም የእነዚህና የሌሎች ባዕዳን የትርምስና የተዳከመች ኢትዮጵያን የማየት አጀንዳ ነው። ግንቦት ሰባት እንደ ቱቦ ከማስተላለፍ ውጪ አንዳችም የራሱ አጀንዳ የለውም። እርግጥ ለዚህ አባባሌ አስረጅ ይሆን ዘንድም የሽብር ቡድኑ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ሳያስቡት አፈትልኮ በተቀረፁት የድምፅ ውይይት ላይ፤ የኤርትራ መንግስት ለስድስት ወራት “ስራ ማስኬጃ” ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እንደሰጣቸውና ከዚህም ውስጥ 200 ሺህ ዶላሩ የኢሳት ድርሻ መሆኑን ሲናገሩ በሚዲያዎች ላይ ተጭኖ በጆሮዬ ማድመጤን በእማኝነት አቀርባለሁ።

እርግጥ ከሻዕቢያ የደቀቀና እንደ ካሮት ቁልቁል የሚያድግ ምጣኔ ሃብት አኳያ ሲታይ፤ ዶላሩ የግብፆች መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ያው ሻዕቢያ በተለመደው የድለላ ስራው የራሱን ትልቅ “ኮሚሽን” ወስዶ ግማሽ ሚሊዮን ዶላሩን ለእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አልሷቸዋል ማለት ነው። እናም ኢሳት በግንቦት ሰባት ስም የተቋቋመ የኢትዮጵያን ብልፅግና የማይሹ የውጭ ኃይሎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሆኑን ማንም ሊጠራጠር የሚገባ አይመስለኝም። አበበ ገላው ደግሞ ልክ እንደ ጃዋር መሐመድ ሁሉ ሻዕቢያ የሚከፍለው የግብፆች ተቀጣሪ ነው። እናም በእኔ እምነት በድንገቴው ፖለቲከኛ በእነ ኮሜድያን ታማኝ በየነ አማካኝነት አሜሪካና አውሮፓ ለኢሳት ማጠናከሪያ እየተባለ የሚሰበሰበው ገንዘብ ሆን ተብሎ ለማደናገሪያ የሚካሄድ ነው። እናም በእነ ታማኝ ቅጥፈት ተታልለው ወይም ነገሩ ያልገባቸው አንዳንድ የዋህ ዲያስፖራዎች ላባቸውን አንጠፍጥፈው የሚያገኟትን ገንዘብ የሚያዋጡት የእነ ዶክተር ብርሃኑን ኪስ ለማደለብ ብቻ ነው። በቃ! ሌላ ዓላማ የለውም።

እንግዲህ እነዚህ ሁለት ተቀጣሪዎች (ጃዋርና አበበ) ናቸው— ሰሞኑን ቀደም ሲል የጠቀስኩትንና በኢሬቻ በዓል ላይ ራሳቸው በፈጠሩት ሁከት ሳቢያ በመፈተፋፈግና በመረጋገጥ ምክንያት ገደልና ሐይቅ ውስጥ እንዲገቡ የፈረዱባቸውን ወገኖቻችንን “መንግስት ገደላቸው” ለማለት የከጀሉት። አሪፍ የመገለባበጥ አክሮባት ይመስለኛል። ሆኖም ነገሩ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉት ዓይነት ነው። እርግጥ እነ ጃዋር በድሃው የኦሮሞ ስም ለመነገድ ማለት ያለባቸው ልክ በየሚዲያዎቻቸው እንደሚደረድሩት የውሸት መዓት እንዲህ ዓይነቱን የበሬ ወለደ ትረካን ነው። መንግስት እንኳንስ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ሊያስመዘግብ እየፈለገ ባለው የኢሬቻ በዓል ላይ በተገኙ ንፁሃን ታዳሚዎች ላይ ጥይት ሊተኩስ ቀርቶ፤ በዓሉን ለማክበር የክልሉ መንግስትና አባገዳዎች ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርጉ ድጋፍ ሲያደርግ መሰንበቱን ማንም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚገኝ ዜጋ የሚያውቀው ዕውነታ ነው።

እናም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት አንድም የየተኮሰ ጥይት የለም። ኤሊኮፕተሮች በአየር ላይ ያንዣበቡትም እንደተለመደው የ“እንኳን አደረሳችሁ” መልዕክቶችን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን ለመበተን እንጂ፣ በራሳቸው ህዝብ ላይ ጥይት ለመተኮስ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ከእነ ጃዋር የተላላኪነት አስተሳሰብ ውጭ፣ በንፁህ አዕምሮ ነገሮችን ለሚያጤን ማንኛውም ሰው መንግስት በአምልኮ ስፍራ በተገኙ ንፁሃን ላይ የሚተኩስበት አንዳችም ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል የሚገነዘብ ይመስለኛል።

እርግጥ በወቅቱ ህይወቱ ያለፈና ቆስሎ የተገኘ ማንኛውም ተጎጂ ወገን ወዲያውኑ በአምፑላንሶች ተጓጉዞ የተወሰደው ወደ ቢሾፍቱ ሪፈራል ሆስፒታል ነው። ከሆስፒታሉ ሐኪሞች ውጪ ስለ እውነታው ሊመሰክር የሚችል ሰው የለም። እናም ሰሞኑን የሆስፒታሉ ሐኪሞች እንደገለፁት ወደ ሆስፒታሉ በጥይት ተመትቶ የመጣ ሰው አለመኖሩን ገልፀዋል። ታዲያ እነ ጃዋር በውሸት ለኦሮሞዎች ተቆርቋሪ ሆነው እስከመቼ ሊዘልቁ ይችላሉ?…በእንዲህ ዓይነቱ የለየለት ቅጥፈትስ ውጭ ያለውን ዲያስፖራ እንጂ፤ ሃቁን የሚያውቀውን የሀገር ቤት ሰው ማታለል ይቻላልን?— በፍፁም።

በእኔ እምነት ይህን በድሃው ኦሮሞ የመነገድ ተግባርን ማስቆም ያለበት መላው የኦሮሞ ህዝብ ይመስለኛል። አዎ! የኦሮሞ ህዝብ በሞቱና በጉዳቱ ስማቸውን የሚያስጠሩትን፣ በሞቱና በጉዳቱ ውጭ ሀገር ሆነው በተላላኪነት ተንደላቀው የሚኖሩትን፣ በሞቱና በጉዳቱ ተደስተው ባህር ማዶ ሻምፓኝና ውስኪ የሚራጩትን፣ በሞቱና በጉዳቱ ኪሳቸውን የሚያደልቡትን፣ በሞቱና በጉዳቱ የባዕዳን ኪስ ማዳበሪያ የሆኑትን፣ በሞቱና በጉዳቱ ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የመጣውን ትውፊቱን ለመንጠቅ ያሰፈሰፉትን፣ በሞቱና በጉዳቱ በትግሉ ያመጣውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመንጠቅ ያሰፈሰፉትን፣ በሞቱና በጉዳቱ የጀመረውን ልማት በማቋረጥ ወደ ድሮው የሰቆቃ ዘመን እንዲመለስ ለማድረግ እየዶለቱበት ያሉትን…በሞቱና በጉዳቱ ሁሉንም ነገር ሊሆኑ የሚፈልጉትን ከሃዲ ባንዳዎች “በቃችሁ!” ሊላቸው ይገባል።

እነ ጃዋር ምን አስበውልን ይሆን?

በተቋረጠው የኢሬቻ በዓል ላይ እነ ጃዋር ያደራጇቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሁከቱን ሲፈጥሩ በእጃቸው የያዙት ባንዴራ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግስት አይደለም። የማንንም አይመስልም። ከእነ ጃዋር በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት የሁከት ኃይሎቹ ይዘውት የነበረው ባንዴራ በኦሮሚያ ህዝብ ውስጥ የሚታወቀውና በባንዴራው መሃል ላይ የሚገኘው ዋርካ (ኦዳ) የለም። ዋርካው (ኦዳው) የኦሮሞ ህዝብ የረጅም ጊዜ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ህዝብ መሆኑን የሚያመለክት ነው። የአስተዳደር ስርዓቱ ምክር ቤት የሚሰበሰበውም በዚሁ ዋርካ ስር ነው። ይህ የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነው ዋርካ ግን በእነ ጃዋር ዕውቅና ሊሰጠው አልተፈለገም። ጥቁር፣ ነጭና ቀይ ቀለም ያለውን ሌጣ ባንዴራ ብቻ ይዘው ነው የወጡት። እናም ይህ የእነ ጃዋር ፍላጎት “ምን አስበውልን ይሆን?” የሚል ጥያቄን የሚያጭር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

እናም በእኔ እምነት እነ ጃዋር ቢያንስ ለይስሙላም እንኳን ቢሆን ሁከት ፈጣሪ ጀሌዎቻቸውን የሀገሪቱን ባንዴራ በቅድሚያ፣ ለጥቆም የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ማስያዝ ነበረባቸው። ግን ይህ አልሆነም። ሊያደርጉትም አልፈቀዱም። እናም ሃሳባቸው ሁለት ነገሮችን መሆናቸውን ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም። አንደኛው፣ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ሆኖ በከፈለው መስዕዋትነት ያመጣውንና ላለፉት 25 ዓመታት ባህሉን፣ ወጉንና እምነቱን ያለ አንዳች ከልካይ እንዲከውን ያደረገውን ፌዴራላዊ ስርዓትን የማይቀበሉት መሆኑን ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ እነ ጃዋር የኦሮሞ ህዝብ የዘመናት ታሪኩና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫው የሆነውን ዋርካ ከባንዴራው ላይ ነቅሎ በማውጣት የህዝቡን ታሪክና የአስተዳደር ስርዓቱን እንደማይቀበሉ እየገለፁልን ነው። እርግጥ እነዚህ እሳቤዎቻቸውም የኦሮሞን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም—ሁለቱም ሃሳቦቻቸው የኦሮሞን ህዝብ ፍላጎትና እምነት መገለጫዎች ስላልሆኑ። እናም እነ ጃዋር ከጀርባው የተደበቀ ሌላ አጀንዳ ያነገቡ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት እነ ጃዋር የተላኩበትን ኢትዮጵያን የመበታተንና ደካማ ሆና እንድትቀር የማድረግ ስራን እየተወጡ ከመሆናቸውም በላይ፤ ምናልባትም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ግብፆች በሚያስገርም ሁኔታ ‘ጎረቤቶቻችን፣ አብረናችሁ ነን’ እያሏቸው ስለሆነ እነርሱን ለማስደሰት ሴራን እየሸረቡ ሊሆን ይችላል። እስቲ ለማንኛውም እንዲህ ብለን “የቢሆን” መላ ምቶችን እናንሳ።…እውን እነ ጃዋር ያሰቡልን የኦሮሚያ ክልል ባንዴራ መሃሉ ላይ የንስር (Eagle) ምልክት የሌለው ከመሆኑ በስተቀር ልክ እንደ ግብፆቹ ጥቁር፣ ነጭና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ፤ ዋርካውን የነቀሉት “ጎረቤቶቻችን” ስላሏቸው ንስሩን አስገብተው ‘ኦሮሚያ በፌዴሬሽን ከግብፅ ጋር ተቀላቅላለች’ ሊሉን አስበው ይሆን እንዴ?..ወይስ እነ ጃዋር ባለ “ሜጫዎቹ” አክራሪ ሙስሊም ስለሆኑ መሃሉ ላይ የግብፁን “የሙስሊም ወንድማማቾች” አርማን አሊያም ዜጎቻችንን በጠራራ ፀሃይ እንደ በግ ያረደውን “የእስላማዊ መንግስትን” (IS) አርማ ሊለጥፉበት አስበው ይሆን?…መቼም አጃኢብ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?!…

እርግጥ ወገኑንና ህዝቡን ለግል ጥቅሙ ሲል ለባዕዳን አሳልፎ በመስጠት እያስገደለ ካለ ቡድንና ግለሰብ እንዲህ ዓይነቱ የእብድ ሃሳብ ቢመነጭ የሚያስገርም አይመስለኝም። ያም ሆኖ እነ ጃዋር “አባ ሜጫ” በትክክል ምን እንዳሰቡልን ማወቅ ስለማንችል ከባንዴራው በስተጀርባ ያለውን ‘የዋርካ ነቀላ’ ምስጢራቸውን ቢገልፁልን በጄ ነበር። ግና እነ ጃዋር ቢገልፁልንም ባይገልፁልንም፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህይወታቸውን ሰውተው፣ ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያመጡት ፌዴራላዊ ስርዓትና መገለጫው የሆነው ሰንደቅ ዓላማው እነርሱ እስካሉ ድረስ የሚኖር መሆኑን ባለ “ሜጫው” ሰውዬና ጥቂት ግብረ-አሮቹ እንዲሁም ላኪዎቻቸው ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።

የኦሮሞ ህዝብን ዘመን የዘለቀውና ኢሬቻ ጭምር የሚከበርበትና የገዳው ስርዓት መገለጫ የሆነው ዋርካ በእነ ጃዋር የሴራና የሁከት ፖለቲካ ባንዴራ ውስጥ ባይኖርም፤ ሁሌም ኦሮሞዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ አብሮ ይኖራል። የኦሮሞ ህዝብ እስካለ ድረስ ዋርካውን (ኦዳውን) መለየት አይቻልምና። የእነ ጃዋር የኢሬቻ በዓል ብጥበጣም የክልሉ ህዝብና መንግስት የገዳ ስርዓትን በዓለም አቀፍ መድረክ በቅርስነት ለማስመዝገብ እያደረጉ ያሉትን ጥረት አያስተጓጉለውም—ህዝብንና መንግስትን ይበልጥ በማስተሳሰር በጉዳዩ ዙሪያ ጠንክረው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል እንጂ።

ማጠቃለያ

እነ ጃዋር በድሃው የኦሮሚያ ህዝብ ሞትና ጉዳት የሚነግዱበትን መንገድ ለመዝጋት መንግስት እንደ ሀገር መሪነቱ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ይህን በሰው ልጅ መተኪያ የሌለው ህይወት የመነገድና ለባዕዳን ተላላኪ ሆኖ በእጅ መንሻ ገፀ-በረከትነት የማቅረብ መስመርን መላው የኦሮሚያ ህዝብ በፅናት ሊታገለው ይገባል። እነ ጃዋር የመጡበት በትግሉ፣ በማንነቱና በባህላዊ የእምነት ትውፊቶቹ በመሆኑ የዚህን ተግባር ፈፃሚዎች ከውስጥ እያንጓለለ በማውጣት የሁከት ፈጣሪዎቹን ሴራ ባዶ ለማስቀረት በሚደረገው ማንኛውም ህጋዊ ርምጃ ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ የማይተካ ሚናውን ማበርከት ያለበት ይመስለኛል።

በመሆኑም በኢሬቻ በዓልም ላይ ይሁን እርሱን ተከትሎ በሁከት ፈጣሪ ኃይሎች አማካኝነት በተነዛው አሉባልታ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተማዎች እየተስተዋለ ያለውን የሰላም ማጣት ችግር ዋነኛው ምክንያት ህዝባዊ ፍላጎት ሳይሆን የጥቂት የሰላም ፀሮች የተልዕኮ እጅ ስራ መሆኑን በመገንዘብ ሰላም አዋኪዎቹን የሚፈጥሩትን ችግር በመፍታት ረገድ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

እርግጥ ሰላም ወዳዱና ከጥንት ጀምሮ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስተዳደርን የሚያውቀው መላው የኦሮሞ ህዝብ የሰላም ጠንቆችንና ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን የማይቀበሉትን እነ ጃዋርን እንደማይሰማቸው እሙን ነው። ሀገር ውስጥ ያሉት ጥቂት ልጆቹ የእነ ጃዋርን መሰሪና ህዝብን የሚያጠፋ አካሄድን ባለማወቅና በመታለል ሊከተሉ ይችላሉ። ይሁንና ህዝቡ ቢቻል የሰላምን ምንነትና የእነ ጃዋርን ሴራ በግልፅ በማስረዳት ልጆቹን ከጥፋት ተግባር ተባባሪነት የመመለስ፣ ይህ ካልሆነም በአጥፊዎች ላይ መንግስት ለሚወስደው ህጋዊ ርምጃ ድጋፉን በመስጠት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል እላለሁ።