ከእኛው እንጂ ከአድማስ ባሻገር የሚመጣ አንዳችም መፍትሄው የለም!

ብዙሃነትን መሰረት ያደረገው  ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለፉት 25 ዓመታት  አገራችን ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ እንድትችል አድርጓታል። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት  በአገራችን ለዘመናት የዘለቁ ችግሮቻች እልባት በመስጠት አገሪቱ የተረጋጋችና ሰላማዊ እንድትሆን አድርጓል። የአገራችን የፌዴራል ስርዓት የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ፣  ባህላቸውን እንዲያሳድጉ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲዳኙ፣ ህዝቦች ማንነታቸውን አውቀው እንዲኮሩ እድርጓል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአንድ ጀንበር ስራ አይደለም። ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ስራዎችን አከናውነናል። አለም የመሰከረው ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግበናል፤ በመመዝገብም ላይ  ነን።  አገራችን ለውጥ ጎዳና ላይ ትሁን እንጂ ያልተከናወኑ ነገር ግን ሊከናወኑ የሚገቡ  በርካታ ስራዎች የቀራሉ። አንድ ታዋቂ ሰው  ስማቸውን ባልጠቅሰው እወዳለሁ፣ በቅርቡ በአንድ መድረክ ሲናገሩ ከነበሩት ውስጥ አንድ አባባላቸውን ወደድኩላቸው። ለእናንተም እንደኔው አግርሞት ይጭርባችሁ እንደሆን ላካፍላችሁ።  ግለሰቡ  አባባሉንየተጠቀሙበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ  የአገራችን አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያሉ አካሎች  በመንግስት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለመግለጽ   በመንግስት፣  በግለሰቦችና በድርጅቶች  ንብረት ላይ እያደረሱ ያሉትን በደል ለመግለጽ ነው። “ግማሽ የደረሰን ጠርሙስ  ለመሙላት እውስጡ ያለውን አፍሶ እንደገና  ለመሙላት መነሳት በየትኛውም መስፈርት ኪሳራ ነው” ሲሉ እየተደረገ ያለውን የተሳሳተ አካሄድ ኮንነውታለ።

አሁን እያየን ያለነው ይህን ነው። መሙላት የጀመረውን ማፍሰስ።  ጥያቄን ለመንግስት ለማቅረብ ሲባል ወይም መንግስትን ለመቃወም  የግለሰቦችን፣ የማህበራዊ መገልገያዎችን፣ የመንግስት መስሪያቤቶችን፣ የኢንቨስተሮችን ንብረት ወዘተ  ላይ ጥቃት መሰንዘር በየትኛውም መስፈርት  ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው።   ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የዴሞክራሲ ስርዓታችን ገና ጅምር ነው። በርካታ ያልተፈቱ ነገር ግን ሊፈቱ የሚገባቸው ጠያቄዎች እንዳሉ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። እነዚህን ነቅሰን አውጥተን በሰለጠነ መልኩ ለመንግስት በማቅረብ መፍትሄ ማፈላለግ የተሻለ አማራጭ ነው።

መንግስት ድክመቱን አምኗል። ችግሮችንም ለመቅረፍ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው። ይሁንና እለቱን ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ሊገኝ እንደማይቻልም መታወቅ መቻል አለበት።  እንደኢትዮጵያ ያለ ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት ተከታይ አገር ይቅርና የሁለትና የሶስት መቶ ዓመታት የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ተሞክሮ አላቸው የሚባሉት ምዕራባዊያን ሳየቀሩ የዴሞክራሲ ስርዓታቸው ያለቀለትና የበቃ ነው ማለት አይቻልም።  የጸጥታ ሃይሎቻቸው በገዛ ዜጎቻቸው ላይ የሚፈጽሙተ ኢሰባዊ ድርጊት በራሳቸው ሚዲያዎች ሳይቀር  የምናየውና የምናደምጠው እውነታ ነው። ይሁንና በእነዚህ አገራት የሚደረጉ ተቃውሞዎች ንብረት በማውደምና  ህይወት በመቅጠፍ ላይ ያተኮረ አይደሉም። 

የሰላም ዋስትና ሁላችንም ልንሆን ይገባል። እኛ በተበጣበጥን፣ እኛ በውስጥ ጉዳያችን በተሻኮትን መጠን ለውጭ አካላት በር እንከፍታላን። ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን ላይ እንድናተኩር እንሆናለን። የተፈጥሮ ሃብታችንን  መጠቀም የሚፈልጉ አገራት በተለይ የግብጽ መንግስታት  የአገራችን መረጋጋት ከህልውናቸው ጋር ያገናኙ በመሆናቸው እንድንለማና አቅም እንዳንፈጥር ለዘመናት ሰርተዋል።  አሁን ላይ  ግብጽ  በአገራችን ጉዳይ ሰተት በላ በመግባት ላይ ነች።  ግብጻዊያን ሰሞኑን ምን እየዶለቱልን እንደሆነ የአደባባይ  ሚስጢር ነው። አንዳንድ ግብጻዊያን  የኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ለእነርሱ  የምስራች የሚሆንበት ነገር አይገባኝም።

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ እየተከተለች ያለችው አቋም ግብጻዊያን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ የውሃ አመንጪዋ አገር ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሰራር ነው። ከዚህም ባሻገር ግብጻዊያን መረዳት ያቃታቸው ጉዳይ በላይኞቹ የተፋሰስ አገራት በተለይ የውሃውን 85 በመቶ በምታመነጨው ኢትዮጵያ የተጠናከረ የተፋሰስ ልማት ማካሄድ ካልተቻለ የወንዙ ቀጣይ ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጥናቶች አረጋግጠዋል።  ኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አከናወነችም አላከናወነችም ከጋራ ሃብት ፍተሃዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም መብት እንዳላት በርካታ ግብጻዊያን  አሁን ድረስ በአግባብ የተረዱት አይመስሉም። ለዚህም የመስለኛል  ግብጻዊያን በተለያየ ጊዜ በውስጥ የአገራችን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚሯሯጡት።

ግብጻዊያን መልካም አጋጣሚዎች ተፈጠሩ ብለው ሲያምኑ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት  ሁከት በመፍጠር አቅመ ቢስ ማድረግ፤ ይህ አልሳካ ሲል ደግሞ  በድርድርና መነጋገር መብታቸውን ለማስከበር ሲሯሯጡ ማየት  እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው። እንዲህ ያለ ሚዛናዊነት የጎደለው አካሄድ መከተል አሳፋሪ ነው። የእኛው ወንድሞች፣ የእኛ ወገኖች የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በእንዲህ ያለ  አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ላይ ለተሰማሩ አካላት መጠቀሚያ መሆናቸው  ደግሞ  የበለጠ  አስነዋሪና አሳፋሪ ያደርገዋል።

ግብጻዊያን እየተሯሯጡ ያሉት ሰላማችንን ለመንጠቅ ነው።  አሁን አበክረው እየሰሩ ያሉት አንድነታችንን የሚያላላ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያጠፋ ድርጊትን በማስፋፋት ላይ ነው። ለኦሮሞና አማራ ህዝቦች ጥቅም  በየትኛውም መስፋርት ግብጻዊያን ሊቆረቆሩ አይችሉም።  እኛ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻችንን በመቀራረብና በመነጋጋር መፍታት እንጂ ከአድማስ ባሻገር የሚመጣ አንዳችም ነገር የለም። በሰላማችን ላይ ማንም ሊደራደር አይገባም።

ሰላም የሁሉም ዋስትና ነው። ሰላም ለልማት፣ ሰላም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት፣ ሰላም ለመድብለ ፓርቲ መጠናከር፣ ሰላም ለህዝቦች አብሮ መኖር፣ ሰላም ለአገር እድገት፣ ወዘተ ብቻ ሰላም የሁሉም ዋስትና ነው። ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የለም። በአገራችንን የውስጥ ጉዳይ እንዳሻቸው ጣልቃ በመግባት እንደፈለጋቸው መፈተት ለሚፈልጉ ሃይሎች ቦታ ልንሰጣቸው አይገባም። የአገራችን ሰላም ለድርድር የሚያቀርብ አይደለም። እንደነዚህ ያሉ  ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ወይም ፓርቲዎች ህብረተሰቡ ትዕግስት እንደሌለው ሊያውቁት ይገባል።

ባለፉት 25 ዓመታት የአገራችን ህዝቦች የሰላምን ዋጋ ከማንም በላይ ተገንዝበውታል። የሰላም እጦት ሞትን፣ አካል መጉደልን፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ረሃብን፣ መታረዝን  በአጠቃላይ ድህነትን አስክትሎብናል። ለሰላም ዘብ መቆም ለሰላም መዘመር ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰላም ወዳድ የህብረተሰብ ክፍል መሆን መቻል አለበት።  አሁን በሰፈነው ሰላም ተጠቃሚ መሆን ብቻ ሳይሆን  ለወደፊቱም የአገራችን ሰላም ዋስ ጠበቃ መሆን የምንችለው ከውጭም ሆነ ከውስጥ  ሰላማችንን ለሚያውኩ ሃይላት በራችንን ዝግ ማድረግ ስንችል። ማንም በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ የለብንም።

ልዩነትን በሃይል ማራመድ የሚቻልበት ወቅት አልፏል።  ህብረተሰቡ ጥያቄ እንዳለው መንግስትም አምኖ ተቀበሏል። ችግሮችንም ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እንኳን በታዳጊ አገር ይቅርና  በምዕራባዊያኖችም ዘንዳ ቢሆን ችግሮች በአንድ ጀንበረ አይፈቱም። የመንግስትን ጥረት በማገዝ ክፍተቶችን በመሙላት በመነጋገርና በመቀራረብ ለችግሮች መፍትሄ ማምጣት ይቻላል። በ21ኛው ክፍለዘመን በነውጥ መልካም ነገር ሊመጣ ከቶ መታሰብ የለበትም። በቅርቡ እያስተዋልን ያለነው ነውጥና ሁከት  ሶሪያን፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ ኢራቅን ወደ ውድመትና እልቂት  መርቷቸዋል። እጅግ በርካታ  የሶሪያ ዜጎች ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ  ጠፍቷል፣  ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ  አካል ጎድሏል፣ ማህበራዊ መገልገያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ወድመዋል፣ የግለሰቦች ንብረት ወድሟል። አሁንም ይህ ድርጊት አልቆመም።  ሁከትና ነውጥ የሚያመጣው ይህን ነው።  ምናልባትም ሶሪያ ዳግም እንደአገር ለመቀጠል በሚያዳግት መስመር  ላይ ትገኛለች።

ሰሞኑን በኢሬቻ ክብረ ባዓል ላይ በተፈጠረ ግርግር የንጹሃን ህይወት ጠፍቷል። ይህ በጣም የሚያሳዝን  መቼም የማንረሳው መጠፎ ክስተት ነው።  ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች በእንዲህ ያለ ሁኔታ የዜጎች ህይወት መጥፋት ሳያሳዝናቸው  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ናቸው። እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው። የእኛ አገር የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ  አመራሮች በወገኖቻችን  ሞትና የአካል ጉዳት ርካሽ ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረትን ስንመለከት እነዚህ ሰዎች ምን እያደረጉ ነው የሚያስብል ነው። መንግስት የሟቾችንና የተጎጂዎችን ቁጥር  ከአግባብ ምንጭ አጣርቶ ይፋ አድርጓል። ለተጎጂ ቤተሰቦችም የሚቻለውን እንደሚያደርግም ገልጿል። በነገራችን ላይ አንድ አልገባ ያለኝ ጉዳይ  መንግስት የሟቾችን ቁጥር በመቀነስም ሆነ በመጨመር የሚያገኘው የፖለቲካ ትርፍ  ለእኔ አይታየኝም።  አንድም ሰው ሞተ፣ ሃምሳም ሞተ፣ መቶም ሞተ  የዜጎቻችን ህይወት መጥፋት ሊያስቆጨን ሊያገበግበን ይገባል እንጂ በሟቾች ቁጥር ላይ እሰጣ ገባ መግባት ተገቢ አይመስለኝም።  ለክብረ በዓል የወጣ  ሰላማዊ ዜጋ ሳያስበው በእንዲህ ያለ ሁኔታ ህይወቱ ሲያልፍ እጅግ ያስቆጫል። ያንገበግባል። በሁላችንም ቤት የገባ ሃዘን ነው።

የህዝብ ሃዘንንና  ብሶቶትን በማራገብ የማይገባ ትርፍ መፈለግ የእኛ አገር የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የፖለቲካ አካሄድ ከሆነች ሰነባብታለች። ህብረተሰቡን በብሶቱና በሃዘኑ አስታኮ በመግባት የህዝቦችን  መልካም ግንኙነት እንዲሻክርና ወደማይገባ መንገድ እንዲያመራ መጣር የጤነኝነት አይደለም። አመጽ በማደራጀት፣ ህዝብን በማሸበር፣ ድንጋይ በመወርወር ወይም በማስወርወር፣ የልማት ተቋማትን በማፈራረስ፣ የግለሰብ ንብረት በመዝረፍና በማውደም  መንግስትን ከስልጣን  አወርዳለሁ ብሎ ማሰብ  የዋህነት ነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚመጣ ለውጥም አገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ያጠፋታል እንጂ አያለማትም።  

በሰላማዊ ውድድር ስልጣን መያዝ ሳይቻል ሲቀር በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መዘፈቅ፣ በህዝቦች መካካል   የጥላቻ ችቦ መለኮስ፣ የጥፋት እሣት ማቀጣጠል በዛሬዋ ኢትዮጵያ አንዳች ሥፍራ የለውም፡፡ ከሠላማዊና ህጋዊ የምርጫ መወዳደሪያ ሥርዓት ውጪ የስልጣን መወጣጫ  መሰላል እንደሌለ መታወቅ ይኖርበታል።