በረጅሙ የግብፅ እጅ አንጠምዘዝ፤ በኦነግ ባንዳዊ ስሌት አንታለል

በኦሮሞዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስረአት የሚከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በአል ታሪክ የማይረሳው አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሞታል። በመሆኑም፣ በአሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ሳይከናወን ቀርቷል። ይህ የሆነው ታላቁን የኢሬቻ በዓል ሁነት ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም ባሰቡ የሽብር ቡድን አባላት ነው። ይህ የኢሬቻን በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክንውን የጠለፈው ቡድን ኢሰብአዊ እርምጃን የወሰደው በድንገት ሳይሆን በከፍተኛ ምስጢር፣ ውስጥ ለውስጥ ሲዘጋጅ ቆይቶ በታቀደና በተደራጀ አኳኋን መሆኑ ግልፅ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አዋኪው ቡድን ሁለት አይነት እቅድ ነበረው። የመጀመሪያው የኢሬቻን ሁነት ሙሉ በሙሉ ጠልፎ አባገዳዎችን ተመልካች በማድረግ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራውን ቡድን የውዥንብር ፖለቲካ መስበኪያ መድረክ ማድረግ ሲሆን ይህ ካልተሳካ፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ የኢሬቻን በአል በመረበሽ እንዳይከበር ማሰናከል ነበር።

በተጓዳኝ ፎቶግራፍ እያነሱ የሚዲያን ስነምግባር ፍጹም በሚጥስ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ የደጋፊዎቻቸውን አይዟችሁ ባይነትና ረብጣ ዶላር የሚሸቅሉበትን አስከሬን ለማግኘት መልካም አጋጣሚ የመፍጠር ዓላማም ነበራቸው። የመጀመሪያው የበዓሉን ሁነት ሙሉ በሙሉ ጠልፎ በኦነግ አርማ ያሸበረቀ የነውጥ የቅስቀሳ መድረክ የማድረጉ ሙከራ አልተሳካም፤ ሁለተኛው ግን ከሞላ ጎደል ተሳክቶላቸዋል። በአሉ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሮ፣ በመልካ እናቶች (haadha malkaa) መሪነት፣ በአባገዳዎች ቀጣይነት በአርሰዲ ሃይቅ እርጥብ ሳር እየነከሩ ወደሰማይ በመርጨት የሚከናወነው ዋናው የምስጋና (irreeffannaa) ስርአት አብቅቶ በአባገዳዎች የሚከናወነው ስርአት ሲጀመር ነው ኦነግ አደናግሮ ያሰማራቸው የሁከት መልዕክተኞች የበአሉን ስነስርአት ማወክ የጀመሩት።

አዋኪዎቹ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ኦነግ ዓርማ ይዘው እየጨፈሩ ወደመድረክ በመውጣት አባገዳዎች የበአሉን ስረአት እንዳያከናውኑ ማይክራፎን እስከመቀማት የዘለቀ ነውረኛ ተግባር አከናወኑ። አባገዳዎቹ በኦሮሞ ባህል መሰረት በአዋኪዎቹ ጩኸት መናጋት የጀመረውን የበአሉን ታዳሚና ታዳሚው ውስጥ የተሰገሰገውን አዋኪ ቡድን ስርአት እንዲይዝና ህዝቡም እንዲረጋጋ “ጋዳን ነጋያ /gadan nagaayaa/፣ ኦሮሞዎች አድቡ! /oroomtich taa´ii !” የሚል ባህሉን የተከተለ ትእዛዝ ቢያስተላልፉም አዋኪዎቹ ሊሰሟቸው ፍቃደኞች አልሆኑም። በኦሮሞዎች ስርአት የአባ ገዳ ትእዛዝ ፍፁም የተከበረ ነው። በመሆኑም ታላቁን የኢሬቻ በአል በማደፍረስ የኦሮሞዎችን ባህልና ወግ መጣስ የጀመረው ኦነግ ያሰማራው አዋኪ ቡድን የአባገዳዎችን ትእዛዝ በመጣስ ሁለተኛውን የኦሮሞዎችን ባህል ያለማክበር ጥፋት ፈጸመ። ይህ ለኦሮሞዎች ስርአት – ባህልና ወግ የማይገዛ ቡድን ከአባገዳዎቹ አቅም በላይ ስለነበረ አባገዳዎቹ ስነስርአቱን ለማቋረጥ ተገደዱ።

ይህ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የተገኙበት ታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነት በሰላም እንዲከናወን የዜጎችን መብት ለመጠበቅ በስፍራው የተገኘው የክልሉ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል፣ አዋኪዎቹን በትእግስት ስርአት እንዲይዙ ቢለምንም አሻፈረኝ ብለዋወል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የኦነግ አርማ ይዘው ቡድኑን ከማወደስ ጥፋት በተጨማሪ የክልሉንና የኢፌዴሪ ሰንድቅ ዓላማን አውርደው ለማቃጠል ሙከራ አድርገዋል። የጸጥታ አስከባሪ ሃይሉ ይህንንም ቢሆን የወንጀሉ ድርጊት ፈፃሚዎች ላይ አንዳችም አካላዊ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ነበር የተከላከለው።

ይህ የጸጥታ አስከባሪውን ሃይል የሚፈታተን ድርጊት ሳያስቆጣው ሃይልን በሃይል የመከላከል ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበው የጸጥታ አስከባሪ ሃይል አካሄድ የሚሸጡት አስከሬንንና የተፈነከተ ሰው እንደሚያሳጣቸው የተገነዘቡት የኦነግ የሁከት ተላላኪዎች በታዳሚው ህዝብ እና በሰላም አስከባሪ ሃይል ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው ሰዉ ራሱን ከድንጋይ ለመከላከል እንዲሁም በድንጋይ ውርወራ ወደ ሃይል ጥቃት የተሸጋገረው ሁከት የሚያስከትለው ተመጣጣኝ ሃይል የመጠቀም የሰላም አስከባሪ ሃይል ርምጃ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በማሰብ ራሳቸውን ሊያድኑ በሚችሉበትና ክፍተት ወዳገኙበት አቅጣጫ በማፈግፈግ መሮጥ ጀመሩ።

ይህ አጋጣሚ አዋኪዎቹን አደራጅቶ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ደግፎ ያሰማራቸው ኦነግና አክቲቪስት የሚላቸው እነጃዋር የሚቸበችቡትን ሞት አስገኘላቸው። በሽሽትና በማፈግፈግ ላይ የነበሩት የበአሉ ታዳሚዎች በመውደቅና እርስ በርስ በመረጋገጥ እንዲሁም በሃይቁ አቅራቢያ የነበረ የውሃ መውረጃ ገደል  ውስጥ ገብተው በአሸዋና አፈር በመታፈን ህይወታቸው አለፈ።

የኦነግ፣ የኦነግ አክቲቪስት የሆነው ጃዋር መሃመድና የኤርትራ ማህበራዊ ሚዲያዎች  ገደል ውስጥ ወድቀው አሸዋና አፈር ተደምስሶባቸው የሞቱትን ሰዎች አስከሬን ተነስቶ እርዳታ ወደሚያገኙበት ስፍራ ተወስደው ሳያበቁ ነበር የአስከሬንና የቁስለኛ ገበያቸውን የጀመሩት። ይህ በራሱ በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት እንዲደርስ የነበራቸውን የረጅም ጊዜ እቅድ ያሳያል።

የግብፅ ቅጥረኛው ጃዋርና የኤርትራ ማህበራዊ ሚዲያዎች ህይወታቸው ካለፈውና ከተጎዱት ሰዎች ቁጥር በላይ እጅግ የተጋነነ የሟችና ቁስለኛ ቁጥር ነበር የሚናገሩት። በኦነግ፣ በጃዋርና በሻአቢያ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው እስከ 6 መቶ ሰው መሞቱንና ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መቁሰላቸው ነበር። በእርግጥ የሞቱት ሰዎች ግን 55 ነበሩ። (55 ሰው መሞቱ ትንሽ ነው እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እገልጋለሁ።) የቁስለኞችም ቁጥር 100 ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ አዋኪ ቡድኑ የሚወስደውን የሃይል ጥቃት ለመከላከል በምላሹ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ፣ በስፍራው በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመገኘታቸው ጋር ተዳምሮ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሟቾችና ቁስለኞች እንዲኖሩ ሊያደርግ ይችላል በሚል ግምት አቅደውት የነበረውን የሟቾችና የቁስለኞች አሃዝ ነው የነገሩን። የሞትና የመቁሰል ምክንያቱንም በተመለከተ አስቀድመው የገመቱትን ነው የተናገሩት። የሃኪም ማስረጃ እንዳመለከተው አንድም በጥይት ወይም በሌላ መሳሪያ ተመትቶ የሞተና የቆሰለ ሰው ባይኖርም፣ በጥይት ተደብድበው (በከባድ መሳሪያ ጭምር) እንደሞቱ አድርገው ነበር ያወሩት።

ሌላ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተነዛው ውሸት በተለይ የገዳ ስርአትን ምንም ሳይሸራረፍ ጠብቆ ያቆየው የጉጂ ጎሳ አባ ገዳ የሆኑት ኦቦ ጂሎ መልኦ ተገድለዋል የሚል ነው። ይህ በተለይ አባገዳቸውን እጅግ በሚያከብሩት የጎጂ ዞን ነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤንና ቁጣን ፈጥሯል። በሆሬ ቡላ ከተማ የተቀሰቀሰው ፖሊስ ጣቢያውን እንዲቃጠልና በቁጥጥር ስር የነበሩ ታራሚዎች እንዲያመልጡ ያደረገው ሁከት መነሻ ይህ አባ ገዳ ጂሎ መልኦ ሞተዋል የሚለው የሀሰት ወሬ ነው። ይህ ወሬ በተወራ ማግስት አባ ገዳ ጂሉ መልኦ በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ቀርበው እንዳልሞቱ ተናግረዋል። በእርሳቸው ምክንያት ሁከት የሚቀሰቅሱ ወጣቶችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል። በኢሬቻ በኣል ላይ የተፈጸመው የሁከት ድርጊት ተገቢ እንዳልነበረም አስረድተዋል።

በሌሎች የኦሮሚያ ዞኖችም እንዲሁ በኦነግና የኦነግ አክቲቪስቶች በሚያሰራጩት ነጭ ውሸት የተቆጡ ሰዎች ሁከት ተቀስቅሷል። በተለያዩ ዙኖች አንዳንድ ከተሞች የተቀሰቀሰው ሁከት ምንም አይነት የመብት ጥያቄ አልቀረበበትም። ከዚህ ይልቅ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ የግለሰብ ንብረቶችን፣ የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችንና ተንቀሳቃሽ ንብረታተቸውን በእሳት አጋይቶ በማውደም ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር የስራ እድል ማጣት ሆኖ ሳለ ለዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ተቋማትን ማውደም መድረሻው ምን እንደሆነ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። መድረሻው ማወደም ነው፤ የገዛ ሃገርን ማጥፋት። ይህ የሆነው የሁከቱ ጠንሳሾች ኢትዮጵያን በሁከት እንድትወድም ማድረግ የሚፈልጉ ግብጽን የመሳሳሉ ሃገራት የሚገኙ ቡድኖች መሆናቸው ነው። ሰሞኑን በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ይህን በተጨባጭ ያስረዳሉ። ግብጽ ኢትዮጵያን በእርስ በርስ ግጭት የማፍረስ ዓላማዋ መነሻ በአባይ ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን አይነኬ የባለቤትነት መብት ማስጠበቅና፤ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የመገንባት አቅም እንዳይኖራት ማድረግ፣ ከተቻለም በእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቱ ለዘለዓለም ፍትሃዊ የአባይ ወንዝ ውሃ ተጠቃሚነት መብቷን እንዳትጠይቅና በመብቷ እንዳትጠቀም ማድረግ ነው።

የኤርትራ መንግስት የግብጽን ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ ለማስፈጸም በተላላኪነት ያገለግላል። የኤርትራ መንግስት የግብጽ ኢትዮጵያን የማዳከም ከተቻለም የማጥፋት ተልእኮ ተቀብሎ የተላላኪነት ተግባሩን በእነግንቦት 7 በኩል ለማስፈጸም መወሰኑ ምንም አይገርም። የግብጽ ዓላማ የኤርትራ መንግስት ከያዘው ኢትዮጵያን ከማተራመስ ስትራቴጂ ጋር ስለሚጣጣም። ኢትዮጵያዊ የሆኑት ኦነግ፣ ግንቦት 7ና አክቲቪስቶቻቸው የግብጽን ኢትዮጵያን የማፍረስና በአባይ ውሃ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት እንዳይኖራት የማድረግ ስምምነት ግን አስገራሚም አሳዛኝም ነው። አስገራሚና አሳዛሽ ሆነም አልሆነም  ነገሩ እውነት ነው። ከሶስት ዓመት በፊት ከግንቦት 7 መስራችና መሪ ያፈተለከው በመነፈቅ የ500 ሺህ ዶላር እርዳታ በኤርትራ በኩል የተሰጠ ቢሆንም ምንጩ ግን ግብፅ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ እርዳታ በቋሚነት የሚሰጥ ነው። ለዚህም ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች የተለቀቀውን የግብጽና የኦነግን የወዳጀነት ጉባኤ በአስረጂነት ይጠቀሳል።

ኦነግ ከህዝብ ፍቃድ ውጭ ገንጥሎ የሚገዛው ሃገር የመመስረት እቅዱ በኢፌዴሪ ህገመንግስት መክኗል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ከሌሎች ጋር በመቻቻል፣ በመከባባርና በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት ኢትዮጵያን በፍቃዳቸው መስርተው፣ የዚህች ሉዓላዊ ሃገር የስልጣን ባለቤቶች ሆነው የመኖር መብታቸው በህገመንግስቱ ተረጋግጧል። ህገመንግስቱ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህ አልስማማ ካላቸው ጥያቄው የህዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥ ስርአትና ህዝበ ውሳኔ የመገንጠል መብታቸውን በዋስትናነት አስቀምጧል። ይህ ደግሞ የኦነግን ህልም አመከነው። በመሆኑም የሚገዛው ቁራጭ ሃገር የማግኘት፣ የህዝቡን ፍላጎትና ፍቃድ ያላገናዘበ ምኞቱን ለማሳካት የሃይልና የሽብር መንገድን መርጧል። ይህ በድብቅ የወሰነው ሳይሆን በይፋ ያሳወቀው ነው። በህዝብ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ሳያሳስበው በሽብርተኝነት፣ ከኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባባር ወዘተ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ከግብፅ ጋር የፈፀመው ያልተቀደሰ ጋብቻ መድረሻም ይሄው ነው።

ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ መፈጸም የሚያስችል እድል የሌላት ግብጽ ደግሞ ወደኢትዮጵያ ሰርጎ በመግባት ሃገሪቱን ለማፍረስ በጥላቻና በስልጣን ጥም የታወረ ቡድን ያስፈልጋታል። ይህን ዓላማ ለማስፈጸም ገበያ ላይ ኦነግንና ግንቦት 7ን አገኘች፤ በቀላሉም በገንዘብ ገዛቻቸው። ግንቦት 7ን ከኦነግ የሚለየው የአሃዳዊ ስርአት አቀንቃኝ መሆኑ ነው። በአሃዳዊ ስርአት ሊገዟት የምትችለውን ኢትዮጵያ መመለስ ካልተቻለ ትጥፋ የሚል አካሄድ እየተከተሉ ነው። ከኤርትራ መንግስት ጋር ተወዳጀተው ከግብጽ በሚላክ ገንዘብ ኢትዮጵያን በሽብር ለማተራመስ የሚጥሩት ለዚህ ነው። በአጠቃለይ ኦነግ የተገነጠለች ኦሮሚያ ተስፈኛ ስትሆን ግንቦት 7 ደግሞ ኦሮሞን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ቀልጠው በአንድ ማንነት የተጨፈለቁባት አሃዳዊ ኢትዮጵያ ተስፈኛ ነው። ይህን ማድረግ ካልቻሉ ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ነው የሚፈልጉት። ግብፅ ደግሞ ይህን አጥብቃ ትፈልጋዋለች።

ገዳዩን ከማጠቃለላችን በፊት አንድ ነገር እንበል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ማወቅ የሚገባው ነገር አለ፤ እሱም እነዚህን ጥቃቅ ሰበቦች መነሻ በማድረግ፣ ተገቢ የወጣቶችን ጥያቄዎች በመጥለፍ በተቀነባበረ አውዳሚ ሁከት እንዲፈነዳ የማድረግ ተግባር እየተለመደ ከመጣ ችግር ጀርባ፣ በተለይ ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ያለች መሆኑን። ግብጽ ይህን የምታደርገው ከተቻለ ኢትዮጵያን በማወደም፣ ካልሆነ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም አቅም የሌላት ደሃ እንድትሆን በማድረግ የአባይ ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን አይነኬ የባለቤትነት መብት ዋስትና ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ እንንቃ፤ አንታለል።   

በጋራ ጥረታችን ህዳሴያችን እውን ይሆናል!!!