ለፓርላማችንም ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልጋል

    

 

በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት የተከሰተውን የበርካታ ወገኖቻችን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመፅ እያደረሰ ያለው የንብረት ውድመት ከመንግስት ጥበቃና ቁጥጥር ውጪ ሆኖ የነበረ መሆኑ  ታወቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች በተቀሰቀሰው አመፅ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ንብረት ወድሟል። ከነዚህም መካከል በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በአዋሽ መልካሳ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በአለምገና እና ሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች በተቀሰቀሰው አመጽ፣ በቢሊዮኖችና ሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ የተቋቋሙ ፋብሪካዎች፣ የህዝብና የጭነት ማመላለሻ መኪኖች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና የአበባ እርሻዎች ዋነኞቹ እና በቀዳሚነት የሚጠቀሱ የወደሙ ሃብቶች ናቸው፡፡

በላንጋኖ አካባቢ በ100ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነባው ቢሻን ጋሪ ሎጅ ባለፈው እሮብ በደረሰበት ዘረፋና ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ  የወደመ ሲሆን፤ በዚህ ዘረፋና ቃጠሎ የወደመው ንብረት ሲገመትም ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል አዋሽ መልካሳ በተቀሰቀሰ አመፅ በአካባቢው በሚገኘው ብስራት የጠጠር ማምረቻ ድርጅት ላይ የተከሰተው ቃጠሎም ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ አዳዲስ ማሽኖች ወድመዋል፡፡

ውድመቱ በደረሰባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ባለሃብቶች ሲናገሩ እንደተሰማውም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሥጋት ላይ እንደሚገኙና በማንኛውም ጊዜና ሰዓት በንብረታቸውም ሆነ በህይወታቸው ላይ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ገልፀው፤ ለደህንነታቸው ዋስትና እንደማይሰማቸው እና ሁኔታው ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱ ከፍተኛ ሥጋት ያሳደረባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዝዋይ ከተማ ውስጥ በአበባ እርሻ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ደግሞ  በአካባቢው በተቀሰቀሰው አመፅ ሳቢያ በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት እጅግ እንዳሳሰባቸው ጠቁመው፤ ዋስትና በሌለበትና ምን እንደሚከሰት መገመት በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ መሆን እጅግ አስፈሪ ነው ሲሉም ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ በሄደው ተቃውሞና አመፅ በርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የመንግስት ሴክተር መ/ቤቶች፣ የመንግስትና የግለሰቦች ተሽከርካሪዎች በእሳት ወድመዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሳምንቱ ውስጥ በርካታ የመንግስትና የግል ንብረቶች ወድመዋል፡፡ በሰበታ ከተማ ብቻ የኤሌክትሪክ ኬብል ማምረቻ፣ የጨርቃ ጨርቅና የፕላስቲክ ፋብሪካዎችን ጨምሮ 11 ልዩ ልዩ ፋብሪካዎች የተቃጠሉ ሲሆን ከ62 በላይ አውቶብሶችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ይታወቃል፡፡  

ይህ ደግሞ በተለመደው መልክ ስርአት ማስያዝና ህግ ማስከበር ያልተቻለ ስለመሆኑ የሚያመላክትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት ከነዚህና ለአብነት ከላይ ከተመለከቱት ውድመቶች በላይ ማረጋገጫ መጥቀስ የማይጠበቅ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው ።

አዋጁ ከላይ የተመለከቱ ባለሃብቶችን ጨምሮ በተመሳሳይም ሌሎች ባለሃብቶች ከስጋት ተላቀው ስራቸውን የሚሰሩበትን እና ሃገሪቱ ወደጀመረችው ልማት ተመልሳ ድህነትን የምትፋለምባቸውን ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ከሁሉ በላይ ደግሞ ዜጎች ያለአንዳች መሸማቀቅና መሳቀቅ ወጥተው እንዲገቡ ከማስቻልም በላይ ልማታችን እና እድገታችን የማይመቻቸው የውጭ ሃይሎችን ቀዳዳ ለማሳጣት የሚያስችል ይሆናል።

ይህ ማለት ግን ጉዳዩ በሙሉ በአዋጁ ይቀጫል ማለት ሳይሆን አዋጁ የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ለአመጻው ሃይል መንጠላጠያ ሆነው የነበሩ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ይገባል ማለት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።

አዋጁ በወጣበት ማግስት ፓርላማችን ስራውን ጀምሯል። የስራው መጀመሪያ ያደረገው ደግሞ እንደተለመደው እና በህገ መንግስቱ በተቀመጠው ልክ የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር አመታዊ የሆነውን የመንግስት እቅድና ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የተመለከተ ንግግር ማድመጥ ነው።

በመንግስት አስፈጻሚ እና ህግ አውጪ በሆነው ምክር ቤት በኩል በአመቱ ሊሰሩ ከተያዙ እቅዶች መካከል በዋናነትና የሚበዙት ለአመጻ ሃይሉ መንጠላጠያ ሆነው የነበሩ የህዝብ ቅሬታዎችን የተመለከቱ ሲሆን፣ ከነዚህም አብዛኞቹ አስፈጻሚ አካላትን የተመለከቱ ቢሆንም ያለህግ አውጪው ቁጥጥርና ክትትል ባሻገር ለመፈጸም አዳጋች ነውና በአስፈጻሚው ልክ ምክር ቤቱ ማድረግ ከሚገባው ተሃድሶ መካከል ይህ ጽሁፍ ዋነኛ የሆኑትን እና ከህዝቡ ቅሬታና ሮሮ ጋር የተያያዙትን ይጠቁማል።

የአምስተኛው ዙር ፓርላማ ሁለተኛው የሥራ ዘመን በህገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠለት አግባብ የወሩ መጨረሻ በሆነው መስከረም 30 2009 ሰኞ ሁለቱም ምክር ቤቶች በጋራ ባደረጉትና የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር እና ርእሰ መንግስት በታደሙበት ታላቅ ስነስርአት ተጀምሯል፡፡ በአገሪቷ አጠቃላይ ሕይወት ላይ የወሳኝነት ሚና ያለው ፓርላማ ከሥራ አስፈጻሚው ከሚቀርብለት ዕቅድና ሪፖርት በተጨማሪ፣ በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ያገኙ ዘንድ ከፍተኛው ሥልጣን ያለው ቢሆንም ሚናውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ለአመጽ ሃይሎች መንጠላጠያ ለሆኑት ቅሬታዎች ምክንያት በመሆን ከላይ ለተመለከቱት ውድመቶች ድርሻ የሚኖረው መሆኑን ስለተሃድሶው የተከበሩት አባላቱ መጀመሪያ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ይህና አባላቱ የዘነጉት ስልጣን ምንጩ ህገመንግስቱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበት ዕውነታ መሆኑንም  ስለተሃድሶው ማስመር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የፓርላማ አባላት ተጠሪነታቸውና ታማኝነታቸው ለወከላቸው ሕዝብ፣ ለሕገ መንግሥትና ለሕሊናቸው በመሆኑ ነው፡፡ የአንድ አገር የሥልጣን የመጨረሻ አካል የሆነው ፓርላማ በአገር አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ወሳኝነት የሚኖረውም ለዚህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የሁለተኛ የሥራ ዘመኑ ዋነኛ ተግባር ሊሆን የሚገባው እና ተሃድሶ ሊያደርግ የሚያሻው ላለፉት አሥር ወራት ለሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለንብረት ውድመትና ለአገሪቱ ህልውና ሥጋት ለሆኑ ችግሮች የእርሱም ጉድለት ያለበት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የክትትልና የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ ማከናወን፤ ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠለትን ሥልጣኑን አሟጦ እስካልተጠቀመ ድረስ ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት ባደረጉት ግምገማ በዋናነት ጎልቶ የወጣውና የችግሮቻችን ሁሉ መነሻና መድረሻ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ መስፋፋቱ ነው የተባለው የበለጠ ስር የሚሰድና ከዚህም ለከፋ ምሬት  የሚዳርግ መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስን የተመለከተ ተሃድሶ ነው፡፡

አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከሕዝብ ለተነሱ መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ በፓርላማ መክፈቻ ስነስርአቱም የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። ስለሆነም ፓርላማው በዚህ አግባብና ለእነዚህ አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳዮች ስኬታማነት በሚመጥን አግባብ ተሃድሶ ማድረግና ወደ ስራ መግባት ግድ ይለዋል ማለት ነው።

ሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች ዳግም የአመጽ ሃይሎች መንጠላጠያ እንዳይሆኑ አድርጎ ለመፍታት የህግ አውጪው ህገ መንግስታዊ ስልጣንና ድርሻ ከሁሉም ይልቃል። ለአመጽ ሃይሎች ቀዳዳ ከነበሩት መካከል ለብሄራዊ መግባባት  የሚረዱ የውይይት መድረኮች በስፋት አለመዘጋጀታቸው፤ የተዘጋጁትም ቢሆኑ አብዛኞቹ በኪራይ ሰብሳቢ አመራሮችና ጀሌዎቻቸው መሆኑ ይታወቃል፤ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ያደረጓቸውም ግምገማዎች አረጋግጠዋል። የህዝቡ ቅሬታዎች ከሆኑት መካከልም ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል አሳማኝ በሆነ መንገድ አለመስፈኑ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ስርአት መጥፋቱ፣ ሕገወጥነትና የኃይል ተግባር መበራከቱ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የመገናኛ ብዙኃን  የሁሉንም ድምፅ አለማስተናገዳቸው እና ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች ትልቅ ትኩረት አለመሰጠቱ መሆኑንም በሁለቱም በኩል የተደረጉት ግምገማዎች ማረጋገጣቸው በተዘዋዋሪ ፓርላማው እና አባላቱ ቁርጠኛ ያልነበሩ መሆናቸው ቀርቶ ለወከላቸው ህዝብ ታማኝ እንዳልነበሩና ቢያንስ እንኳ በህገ መንግስቱ ላይ የተሰጣቸውን ተግባርና ሃላፊነቶች አለመወጣታቸውን ነውና ጊዚያዊ መፍትሄ ከሚሆነው አዋጅ በላይ ዘላቂነት ለሚኖረው ሰላምና ልማት እነዚህን የተመለከተ ተሃድሶ ከፓርላማው ይጠበቃል ብንል ልክና ከመጠን በላይም ልክ ስለምንሆን ነው፡፡

በየትኛውም ዴሞክራሲ ባለበት ሃገር ላይ የህዝብ ውክልና ያለው እና የሃገሪቱ የበላይ የሆነ ስልጣን የተሰጠው ፓርላማ ሦስት መሠረታዊ ኃላፊነቶች ያሉበት መሆኑ ይታወቃል፡፡   አዳዲስ ሕግጋት መደንገግ፣ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን ማሻሻል ወይም መለወጥ፣ እንዲሁም የማያስፈልጉ ሕጎች ከተገኙ መሻርን የተመለከተው የመጀመሪያው ሃላፊነት ሲሆን፤ ሁለተኛው በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ የዜጎችን ፍላጎትና ምኞት ለማሟላት የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ መወጣት ነው፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ለሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ባለበት መንገድ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ብርቱ ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን፣ የመንግሥት አሠራርም ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የተመለከተው ደግሞ ሶስተኛው ሃላፊነት ነው ፡፡

ስለሆነም እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በብቃት ለመከታተልና በተለይም በ5ኛው ዙር ሁለተኛ የስራ ዘመን ይከናወናሉ ተብለው የተያዙትና በክቡር ፕሬዘዳንቱ የተመለከቱት፤ ይልቁንም ለአመጽ ሃይሎች መንጠላጠያ ሆነው የነበሩ ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለማጽዳት የተያዙ እቅዶችን ተግባር ላይ ለማዋል ፓርላማው ጠንካራ፣ ውጤታማና ብቁ መሆን ግድ ይለዋልና ጥልቅ የዚህ ወር ተግባሩ ይህንኑ የሚመጥን ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎች የሚሳኩት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ጥረት የሚቀላጠፈውና የሕዝብ ፍላጎት የሚሟላው በተያዘው እቅድ አግባብ ፓርላማው ጥልቅ ተሃድሶ አድርጎ በፊት የነበሩበትን ችግሮች ሲያራግፍ ብቻ ነው ። በተያዘው እቅድ ልክ ጥልቅ ተሃድሶ ያደረገ ፓርላማ የሕዝብ ተጠሪ እንደመሆኑ መጠን በፖሊሲዎችና በአፈጻጸሞች ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝቡን ጥቅም ለማስከበር ሥር ነቀል ዕርምጃ እስከ መውሰድ ድረስ የሚደርስ ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን ለመጠቀም የሚያዳግተው እና የሚያስፈራው አንዳች ሃይል አይገጥመውምና፡፡

በአገራችን ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ መጓደልና የሙስና ጉዳዮች በተደጋጋሚ ቢወሱም በጥልቀትና በዝርዝር ሲገባ የተከማቹ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በእነዚህ ችግሮች ላይ ከልብ መነጋገር ከተቻለ ሁሉንም ዜጎች ማዕከል ያደረገ ሰላማዊ መፍትሔ ማምጣት ከቶም አይከብድም፡፡ ከሥልጣን ጉጉት በላይ የአገርና የሕዝብ ህልውና ጉዳይ ቅድሚያ ከተሰጠው የማይፈታ ችግር የለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ባለድርሻ እና የስልጣን ብልግናን በቁንጥጫ እና በህዝባዊ ጡጫ ማረም የሚጠበቅበት ፓርላማው ነውና ለደረሱት እና ከላይ ለተመለከቱ ችግሮች ፓርላማውም ድርሻ የነበረው መሆኑን ያማከለ ተሃድሶ ሊያደርግ ይገባዋል ።

ባጠቃላይ፣ በጋራ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና የሕዝብን ፍላጎት ማርካት የሚቻለው ከኃይል ይልቅ ዴሞክራሲያዊው መንገድ ሲመረጥ ብቻ ነው፡፡ የመንገዱ ዋነኛ ባለቤት የነበረው ደግሞ የህዝብ ውክልና የተሰጠው ምክር ቤት ነውና ነው ከላይ ለተመለከቱት ውድመቶችም ድርሻ አለው የምንለው። የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን ቢሆንም የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያላደረገ ሥልጣን መቼም ቢሆን ተረጋግቶ አይቀጥልም፡፡ ይልቁንም አገርንና ሕዝብን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ፓርላማው እንዲህ ዓይነቱን ግንዛቤ የሚያሰርጽ ተሃድሶ በማድረግ ለህዝብና ለአገር የሚበጅ ውሳኔ እንዲሰጥ በዚህ አመት ዜጎች ሁሉ የሚጠብቁበት መሆኑን ሊያጤን ይገባል፡፡