በሕዝብ ልጆች መነገዱ ይቁም

 

                                                                                       

የእኛ ሀገር የዲያስፖራ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት ቆመናል፤ እንታገልለታለን እያሉ ሲርመጠመጡ የሚገኙት በጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ጉያ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ የኢትዮጵያን መበልፀግ መስማት በማይፈልጉ ሀይሎች ጉያ ውስጥ ተሸጉጠው የህዝብ ልጆችን በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመቀስቀስና ውዥንብር ውስጥ በመክተት ለእኩይ አላማቸው ሊማግዱዋቸው ይቅበዘበዛሉ፡፡

ጭፍንና በጥላቻ የተሞላው አክራሪ የተጀመረውን ሀገራዊ እድገትና ልማት እንዲገታ የአባይ ግድብንና ሌሎችንም ታላላቅ ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጁ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን አመጽ በመቆስቆስ ደም እንዲፋሰስም በማድረግ ለማስቆም ሀገራዊ ሰላም እንዲናጋ እንዲጠፋ በመጨረሻም ሀገሪቱን ለመበታተን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በህዝብ ልጆች እልቂት የፖለቲካ ስልጣን እንይዛለን ብለው ቢመኙም አይሳካላቸውም፡፡

ድሀ ቤተሰብ ለፍቶና ደክሞ ያስተማራቸውን ለሀገርም ለቤተሰብም ተስፋ ይሆናሉ ብሎ የሚጠብቃቸውን ወጣቶች በስሜታዊነት በመናጥ ትምህርታቸውን እንዲያቆሙ፣ የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ እንዲረብሹ ከጸጥታ ሀይሎች ጋር እንዲጋጩ የወጠኑት ሴራ ከህልምነት እንደማይዘል በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ በግብጽ እየተረዱና እየታገዙ ለኢትዮጵያ የተሻለ ለውጥ እናመጣለን የሚሉትን ፌዝ የኢትዮጵያ  ህዝብ  ዛሬ ላይ በውል ለይቶ  በመገንዘብ አንቅሮ  ተፍቷቸዋል፡፡

በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ የመንግስትም፣ የግል ስራም ሆነ የንግድ ልውውጥ እንዲቋረጥ፣ ትራንስፖርት እንዳይኖር በማድረግ የግለሰቦችንና የመንግስትን  ቤትና መኪና በእሳት በማንደድ ፋብሪካ በማቃጠል ህዝቡን ከሰራተኛነት ወደ ስራ አጥነት እየለወጡ የተገነባውን እያፈረሱ ለሀገር ቆመናል ማለት ከወንጀልም የከፋ ወንጀል፤ ከክህደትም የከፋ ክህደት  ነው፡፡ ህዝብን አታውቅም ላታልህ የማለት ያህል ድፍረት  ነው፡፡ ህዝብን መናቅም ጭምር ነው፡፡

በኦሮሚያ የተከሰተው አስደንጋጭና አሳዛኝ የጥፋትና የውድመት ድርጊት ብዙ  ይናገራል፡፡ የመጀመሪያው ተቃውሞ የተነሳው በኪራይ ሰብሳቢው፣ ሙሰኛውና ደላላው ህገወጥ ድርጊት  በመሬቱ ላይ በተፈጸመው ቅርምት ሽያጭና ዝርፊያ እንዲሁም ማስተር ፕላኑን በመቃወም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን ተገቢ የሆነ የህዝብ የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄና ተቃውሞ እንደ ክፍተት በመጠቀም የተለያዩ አክራሪና ጽንፈኛነትን የሚያራምዱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከጀርባ በውጭ ሀይሎች መሪነት በተለይም በግብጽ ገንዘብና አማካሪነት በመረዳት አጀንዳውን ወደራሳቸው መጠቀሚያነት ለማዞር በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች በማህበራዊ ድረገጾቻቸው የመጨረሻውን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ አቅራርተዋል፡፡ በእርስ በእርስ መተላለቅ በህዝብና በሀገር ሀብት ውድመት ጭርሱንም የከፋ ጨለማ ውስጥ ከመዘፈቅ ውጪ ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሰላም ለውጥና እድገት ልማት ለማምጣት እንደማይቻል ያውቃሉ፡፡ ይህንን ሀገራዊ አደጋ ማስተዋል ያልቻለ የማይችል በጥላቻና በስሜታዊነት የሚነዳ መናጆ የሆነ ተቃዋሚ ነው ያለው፡፡ ከእኩይ ሴራቸው አትራፊም ተጠቃሚም የለም፡፡ በህዝቡ ልጆችም በመነገድ ያለሙትን ጥፋት ለማሳካት የነበራቸው ቀመር ዛሬ ላይ መክኖአል፡፡

በህዝብ ልጅ መስዋእትነት መሸቀል የሚሻው አክራሪና ጵንፈኛው ስብስብ የሀሳብ ልዮነትን አያስተናግድም፡፡ ስክነት፣ ማስተዋል፣ ተረጋግቶ መደማመጥ፣ ስለሀገር አርቆ ማሰብ የሚባል ነገር የለውም፡፡ ስብስቡ እብደትና ስካር እያናወዘው ይገኛል፡፡ ለአንደበቱም ለከትና ጥግ የለውም፡፡  በማያባራ የቅዠት ዓለም ውስጥ ይዋኛል፡፡ በህዝብ ልጆች ትግልና ደም እሱ አሜሪካ ተቀምጦ በደስታና በፍስሀ እየኖረ ልጆቹን ምርጥ ትምህርት ቤት እያስተማረ ሀገር ቤት ያለው የሰፊው ህዝብ ልጅ እንዲሞትለት፣ እሳት ውስጥ እንዲማገድለት ይቀሰቅሳል፡፡

ሩቅ ሀገር ሁኖ ኢትዮጵያ ላይ መዓት እንዲወርድ ደም እንዲፈስስ ብጥብጥ እንዲነሳ ሀገር እንዲታመስ በማድረግ ሞት ይደግሳል፡፡ የሀገሩን ልቀትና ከፍታ ሳይሆን ጥፋት፣ ትርምስና ሁከት ደም መፋሰስ ውድቀት ለማየት ይቋምጣል፡፡ በህዝቡ ልጆች ደም ለመነገድ ቀን ከሌት ይታትራል፡፡

በምእራቡ አለም በሚኖርበት ነፃ ሀገራት መብት በተከበረበት እንደልቡ በየስብሰባውና በሬዲዮው፣ በየፓልቶኩ የሚጠይቀኝ ሕግና ደንብ የለም በሚል ወሰን የለሸ የጥላቻና የስድብ መዓት በሚጠላቸው ላይ እያወረደ አፋን ያለ ገደብ ይከፍታል፡፡ የድሀው ልጅ ኢትዮጵያ ላይ እንዲሞት ይሰብካል፡፡ ምን የሚሉት አስተሳሰብ እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡ እናንተ ሞታችሁ እኔን ለወንበር አብቁኝ የሚል ደፋር ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፓለቲካውን እየጋለበው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቅዠት ለሀገርም ለሕዝብም አይበጅም፡፡ መጨረሻው ውድቀት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በህዝብ ልጆች ሕይወት ሲራራ ነጋዴ መሆን ግዜው ረፍዶበታል ብቻ ሳይሆን መሽቶበታል ቢባል ይቀላል፡፡ የማንግባባቸው ልዩነቶች ቢኖሩንም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን ስለዚህም በሚያቀራርቡን ተቀራርበን በሚያለያዩን ተለያይተን ግን ደግሞ የጋራ ስለሆነችው ሀገር በጋራ መቆም አለብን የሚል አስተሳስብና እምነት የለውም፡፡ አያልፉ ይመስል በሞት የሚያሾፉ ናቸው፡፡ በማንቡዋለት ግዜና ዘመናቸው ሳይሰሩበት ከነፈ፡፡

አክራሪው ጵንፈኛ በአደባባይ ጀግናውን ጨዋና ትሁት አዛኝና ሩሁሩህ የሆነውን የሀገሩን  ሕዝብ አድርባይ እስስት ተገለባባጭ በሚል ዘልፎታል፤ አዋርዶታል፤ አላግጦበታል፡፡ ለምን እኔ የምለውን አይሰማም? ለምን አይበጠብጥም? ለምን ለእኔ ሲል አይሞትም? የሚል ነው መነሻው፡፡ በህዝብ ልጆች ስምና ደም ለመነገድ ያለው ፍላጎት ዛሬም አልታቀበም፡፡ ሊቆም ግን ግድ ይለዋል፡፡ እነሆ ዘመኑ የእውቀት ከሆነ ቆየ፡፡ ምክንያታዊ የሆነ፣ ለምን? እንዴት? ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ ተተክቶአል፤ በጅምላ መነዳቱም ሆነ መማገዱ ቀርቶአል፡፡

ሀገር የምትገነባው በጋራ ውይይት በመነጋገር በሀሳብ ልዩነት ቢሆንም ልዩነትን አጥብቦ ስለሀገር በመቆም እንጂ እንደ አረቦች እብደት ኢትዮጵያን የመሰለ ታላቅ ሀገር ከታሪካዊ  ጠላቶችዋ ጋር አብሮ በመቆም እንድትጠፋ በማድረግ  አይደለም፡፡ አገር ሰላለን ደህና “ጎበዝ ሲሞት በአገር ይለቀሳል አገር የሞተ እንዲሁ ወዴት ይደረሳል?” ይሉ ነበር የቀድሞ አባቶችና እናቶች፡፡

አክራሪውና ፅንፈኛው ተቃዋሚ ደግሞ እሱ በሰው ሀገር ደልቶት ተመችቶት ዶላር እየቆጠረ ስለሚኖር እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል እንሰሳዊ ሰሜት እኔ ያልኖርኩባት ኢትዮጵያ ለእኔ ምኔ ነች? ብትፈልግ ትጥፋ ትሙት እሳት ይንደድባት በደም ጎርፍ ትታጠብ የሚል ነው፡፡ ይህ ቡድብ አንድ ያላወቀው ጉዳይ አለ፤ እሱም ኢትዮጵያ ሊያጠፏት የሚሹትን የምታጠፋ እንጂ ልትጠፋ አለመቻሏን፡፡

ለምን አክራሪው ፅንፈኛና አሸባሪው የኢትዮጵያን ጥፋትና ውድቀት ተመኝ? ወልዳ ላሰደገች፣ ለቁም ነገር ላበቃች እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም፣ ወገን ሁና ለኖረች ለዚህ ብሩክ ሕዝብ እንዴት ውድቀትንና መፍረሷን ይመኙላታል? የመከራ ድግስስ ይደግሱለታል፤ ለልጆቿስ ሞትን ለምን?? መልካሙ ነገር ሀገርን ተባብሮ ተረዳድቶ መጠበቅ፣ ማሳደግ ከአንቺ በፊት ያድርገኝ ማለት ነበር እንደአባቶቻችንና እናቶቻችን፡፡ ይሄም ቢቀር ከጠላቶችዋ ጋር ማበርን  ምን አመጣው??

ኢትዮጵያ በልጆቿ ትኮራለች፡፡ እኛም ልጆቿ በእናታችን እንኮራለን፡፡ በችግሯም በደስታዋም በሀዘኗም የትም ጥለናት አልሄድንም፡፡ ስደትን አልመረጥንም፡፡ ፅንፈኛው ግን ስደት ላይ ሆኖ ኢትዮጵያ በደም ስትታጠብ ለማየት እንደሚመኘው እኛ የሀገራችንን ጥፋትና ውድመት መቼም ለማየት እንሻም፡፡ የትኛውም ጠላት ቢሰለፍ፣ ቢንጋጋ፣ ቢያሴር መመከቱን መመለሱን ሴራውን ማክሸፉን እናት  ሀገራችንን ኢትዮጵያን በአንድነት ጸንተን መጠበቁን ጥንትም ዛሬም እናውቅበታለን፡፡

የልጆችዋ ደምና ጉልበት ሀገር ለማልማት እንጂ  የራሳቸውን ሀገር ለማጥፋት አይውልም፡፡ የግንቦት 7፣ ኦነግና የግብጽ አላማ ማስፈጸሚያም አይሆንም፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ለሰንደቅ ዓላማችን በክብር መሞትና መስዋዕት መሆን ወትሮም የነበረ የእኛነታችን ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ ባንዳው ቡድንም በወገኖቹ ደም  መነገዱን ይተውና ለዚህ እድል እራሱን ያብቃ።