ለማንቀሳቀሻ ፈንዱ ስኬት

 

የሰላም እጦት የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ከኢራቅ፣ ከሊቢያ፣ ከሶሪያ፣ እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል። በየሀገራቱ በተፈጠሩ ትርምሶችና ሁከቶች  ዜጎች ለዘመናት የለፉበትና የደከሙበትን ሃብትና ንብረት እንዲያጡ፣ ለዓይን ይስቡ የነበሩ ውብና ማራኪ ከተሞቻቸው በቀናት ውስጥ ወደፍርስራሽነት ሲለወጡ ለመመልከትና ውድ የሆነው የሰው ልጅ ህይወትም ድንገት ሆኖ ሲቀር ለመመልከት ግድ ብሏቸዋል።

በየሃገራቱ በተከሰተው መቋጫ የለሽ ቀውስም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ለአስከፊ ረሃብና ስደት፣ ጉስቁልና፣ ለአካል ጉዳትና ሞት ከመዳረግ ባለፈ ሌላ ያስገኘላቸው አንዳች ፋይዳ እንደሌለም አይተናል። እነዚህ ሀገራት በቀላሉ ሊወጡ ከማይችሉበት ዕልቂት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው መንግስቶቻቸው ለተፈጠሩ ችግሮች ፈጥነው ዕልባት ባለመስጠታቸው መሆኑ ይነገራል።

በእኛም ሃገር ከላይ የተመለከቱት ሃገራትን አይነት እንድንሆን የተለያዩና የሰው ህይወትን ጨምሮ በቢሊዮን በሚገመት የንብረት ውድመቶች በሚገለጽ ደረጃዎች ሙከራ ተደርጓል። እነዚህ ሙከራዎች በዚህ ብቻ ሳያበቁ አንፃራዊ  ለሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋትም ምክንያት ሆነዋል፡፡ የእኛውን ሃገር ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአብዛኛው ሁከቶችና ግጭቶች  ላይ ወጣቶች የተሳተፉበት መሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጐች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎቻችን ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል፡፡ በተጨማሪም የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሰርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጐች ለፈተናዎች ተዳርገዋል፡፡ ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት ወጣቶቹ አካባቢ ያልተሰራ እና ይልቁንም ለምሬት ያበቋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ያሏቸው መሆኑን ለመገመት አይከብድም ።

አብዛኞቹ ወጣቶች በዚህ ደረጃ በነዚህ አመጾች ላይ ተሳተፉ ማለት መንግስት ወጣቶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ባገናዘበና ለችግራቸውና ለጥያቄያቸው  በሚመጥን አግባብ ያልተንቀሳቀሰ መሆኑንም  ያመላክተናል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ወደ መቶ ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ የማያንሰው በወጣት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም በመንግስት በኩል በህብረተሰቡ ውስጥ የሚያካሂደው ማንኛውም አይነት የለውጥ እንቅስቃሴ ወጣት ተኮር እንዲሆን ግድ የሚለው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ዘግይቶም ቢሆን አብዛኛው የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የሌለው መሆኑን መንግስት መገንዘቡ ለመፍትሄው ቅርብ እንድንሆን ያስችለናል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ በአገራችን የተስፋፋው የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆኖ ከቆየ በኋላ የወላጆቹን ልማዳዊ የግብርና ስራ ሊቀጥልበት የማይፈልግ እየሆነ በመምጣቱ የገጠሩ ወጣት ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች በተለይ ደግሞ ወደገጠር ከተሞች እየጐረፈ መከማቸት የጀመረ መሆኑንም በተመሳሳይ፡፡

ስለምን ቢባል ወጣቱ ገጠሩን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የለቀቀ ቢሆንም፣ በከተሞቻችን አስተማማኝ የስራና የገቢ ሁኔታ ገና ባልተፈጠረበት አግባብ የሁከት ሰለባ መሆኑ አያጠያይቅምና፡፡ በየአካባቢያችን እንደሚስተዋለው ወጣቱ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው እና በዚህም ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት ከመቸውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር በተደጋጋሚ መጋለጧ እንደማይቀር በመገንዘብ አዲስ አይነት አሰራር ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡

በእርግጥ መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚህ ላይ በመመሰረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን በቶሎ ተገንዝቦ ተመጣጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤

ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና የተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአድልአዊ እና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት መደነቃቀፉ የፈጠረው የተስፋ ቢስነት ስሜት ለእንደዚህ አይነቱና ሃገርን ስጋት ላይ ለሚጥሉ የግጭትና የትርምስ አደጋዎች የሚያጋልጥ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች ራሱን ወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል የሚል ድምዳሜ ላይ በመንግስት በኩል መደረሱ ተገቢና ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ነኝ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ ነው፡፡

ይኸውም የወጣቶች ተንቀሳቀሽ ፈንድ ነው። ለዚሁ የማነቀሳቀሻ ፈንድ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ስነ ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከላይ የተመለከቱ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የ2009 ዓ.ም የመንግስት ትኩረት የአገሪቱን ወጣቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑም በንግግራቸው ተመልክቷል፡፡

ፈንዱ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆን መንግስት የገባው ቃል በብልሹ አሰራሮች እና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ተጠልፎ ወደባሰ ቀውስ እንዳይወስደን ደግሞ ወጣቱና ልማታዊው ሁሉ በአይነ ቁራኛ ተሳትፎ ማድረግና ሃብትና ንብረቱን ሊጠብቅ ይገባል። የሥራ ፈጠራው ሚያተኩርባቸው መስኮችም ላይ ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ይጠበቃል።

የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድን ተግባራዊ ለማድረግ የተያዘው እቅድ በአገሪቱ የሚስተዋሉ የስራ እድል ፈጠራና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ የሚያግዝ መሆኑም ይታወቃል። በዚህ አጋጣሚ ግን በመንግስት በኩል የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች በወጣቱ ዘንድ እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግና ማሳተፍም ለማንቀሳቀሻ ፈንዱ ስኬት አስፈላጊ ይሆናል። በተጨማሪም፣ መንግስት ወጣቱ ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ተከታታይነት ያላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም። የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በየደረጃው የሚገኙ ፈጻሚ አካላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከትም ይጠበቅባቸዋል። ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበው ተንቀሳቃሽ ፈንድ ወጣቶች በተማሩበት የትምህርት መስክም ተደራጅተው የስራ እድል የሚፈጥሩበትንና የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታም ማመቻቸት ይጠበቅበታል።