በአንድ ሀገር የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ (State of emergency) የሚታወጅበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ምላሹ ሰፊ ቢሆንም በተመጠነ መልኩም ቢሆን ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አንድ ሀገር እንደ ሀገር ተከብራና ሉአላዊነቷን አስጠብቃ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት፣ የኢንዱስትሪ ደህንነትዋ፣ የንግድ ልውውጡና የእለት ተእለት ሀገራዊ መስተጋብሯ በሰላም ውሎ የሚያድር የሚያድር ከሆነ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ አይታሰብም፡፡
ሆኖም ግን በመንግስት ደረጃ እጅግ አሳሳቢና አደገኛ አስቸኳይ የሆነ ብሄራዊ አደጋ በሀገሪትዋ ላይ መጋረጡ በተጨባጭ ማስረጃዎች ሲታመንበት የአደጋው ግዝፈት ተመዝኖ በፓርላማው ወይንም በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት በሀገሪቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይታወጃል፡፡ አዋጁ በብሄራዊ ደረጃ የሚታወጅበት የተለየ ምክንያት በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ በፍጥነት በመቀልበስ ወደተረጋጋ ሰላም ለመመመለስ ነው፡፡
እጅግ አስከፊ የሆነ የተፈጥሮ አደጋ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የውሀ መጥለቅለቅ፣ የሰደድ እሳት፣ ድርቅ፣ ያልተለመዱና የአደጋው መጠን በብሄራዊ ደረጃ አሳሳቢ የሆነ ተፈጥሮአዊ አደጋ ሲጋረጥ ለህዝብም ከፍተኛ የሆነ አደጋ የሚያስከትል መሆኑ ሲታመንበት ሀገራት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያውጃሉ፡፡ ያልተጠበቀ የጠላት ወረራ በአንድ ሀገር ላይ በድንገት ሲከሰት የተቃጣውን ወረራ ለመመከትና ለመቀልበስም አዋጁ ሊታወጅ ይችላል፡፡
በሀገር ውስጥ ከፍተኛ አለመረጋጋት ሲከሰትና የሀገሪቱ ሰላም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ተብሎ ሲታመን በተጨባጭ የመረጃ ትንተናዎች የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በሀገሪቱ ከፍተኛው መንግስታዊ አመራር በፓርላማው ወይንም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ይወጣል፡፡ ይህ ደግሞ በበርካታ ሀገራት ታይቶአል፡፡ የአዋጁ አፈጻጸም የግዜ ሰሌዳ በመሬት ላይ እንደተፈጠረው ክስተት የአደጋው ድርስነትና ክብደት እንደ ሀገሪቱም ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል፡፡
አደጋውን በአጭር ግዜ ውስጥ ለመቀልበስ የሚቻል ሁኖ ሲገመት ወይንም ሲታመን በቂ የመረጃ ትንተና በማድረግ የአዋጁን የቆይታ ግዜ አጭር ማድረግ ወይንም እንደ ሁኔታው ማራዘም ይችላል፡፡ 15 ቀን፣ አንድ ወር፣ ሶስት ወር፣ ስድስት ወር እያለ የቀኑ ገድብ ይቀመጣል፡፡ አደጋው በህዝቡ ውስጥ ካስከተለው ተጨባጭ የአደጋው መጠን ለህዝቡ ሰላምና የተረጋጋ ህይወት አሳሳቢ ሁኖ ከመገኘቱ አንጻር በየእለቱ ያሉት ለውጦች፣ መሻሻሎች ወይንም የሁኔታው ከነበረበት አለመለወጥ ወይንም እየባሰና እየከፋ መሄድ ለአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ማጠርና መርዘም ወሳኝነት አላቸው፡፡
ከአለም አቀፍ ተሞክሮም አንጻር ሲታይ የእስቸኳይ ግዜ አዋጆች ከመደበኛው ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት ባሻገር በተለይ የሚጥሉዋቸው የመብት ገደቦች አሉ፡፡ የመዘዋወር የመሰብሰብ፣ የመንቀሳቀስ፣ የሰአት ገደብ፣ በሚዲያው ላይ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ የሚጣል ገደብ በህብረተሰቡም ሆነ በግለሰብ መብትና ነጻነት ላይ የሚጥለው ገደብ አለ፡፡
እነዚህ ገደቦች የታወከውን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ወይንም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን ድርስ አደጋ በፍጥነት ለመቀልበስ ሲባል አጭር ግዜ የሚቆዩ እንጂ በዘላቂነት የሚቀጥሉ አይደሉም፡፡ የህብረተሰቡ ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት አደጋ ውስጥ መውደቁ በተጨባጭ ሲታይ፤ የህዝብና የሀገር ንብረት ውድመት፣ የዜጎች ህይወት በተለያዩ ቦታዎች መጥፋት ሲከሰት፤ በሰላም ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር አደገኛ ሁኔታዎች ሲከሰቱ፣ ዝርፊያ፣ ንጥቂያ፣ ግድያ፣ ውንብድና ሲበራከት ቀጣዩ ሁኔታ ሀገሪቱን ለባሰና ለከፋ አደጋ የሚያጋልጣት ሁኖ ሲገኝ አዋጁ ይደነገጋል፡፡
በተለይም የሀገሪቱን ሰላም ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት የሚጻረሩ የውጭ ሀይሎች ከጀርባ ሁነው የተለያዩ ቡድኖችን ድርጅቶችን በማደራጀት በማስታጠቅ የፋይናንስ እርዳታ በማድረግ ብሄራዊ ቀውስ ለመፍጠር በተለያዩ አካባቢዎች በምስጢር በዘረጉዋቸው መረቦችና መዋቅሮች ሰላም የማናጋትና የእለት ተእለት የህዝቡን ሰላማዊ ህይወት የማደፍረስ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸው በተጨባጭ ሲደረስበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና ሰላም የነበረውንም ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ሲባል አዋጁ ወሳኝ ጠቀሜታ አለው፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ወቅታዊው ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ገዢው ፓርቲ ህዝቡ ለመብቱ መከበር በየቦታው ያነሳውን የከረረ ተቃውሞ ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትህ ችግር፣ ከሙስና፣ መንግስታዊ ስልጣንን አለአግባብ ከመጠቀምና ከኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ጋር የተቆራኙትን በራሱ የውስጥ ግምገማ አስቀድሞ ለይቶ በማውጣት ጥልቀት ያለው ተሀድሶ በማድረግ ወሳኝ የመዋቅራዊና የአደረጃጀት ለውጦችን ለማምጣት ወስኖ እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህንን የህዝቦች ተገቢና ህጋዊ ጥያቄ በመጥለፍ ለራሳቸው ስውርና ድብቅ አላማ ማስፈጸሚያነት ለማዋል በህዝቡ ውስጥ ሰርገው በመግባት አመጹ እንዲስፋፋ፣ ከመንገድና ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ፣ ስርአተ አልበኛነት እንዲሰፍን፣ ህግና ስርአት እንዲጠፋ ለማድረግ የሚሰሩ ግልጽና ስውር ሀይሎችን ማየት ተችሎአል፡፡ ከድህነት ለመውጣት እየታገለች ያለችውን ሀገር ተስፋ ለመግደል በማቀድ ህዝቡ ሰርቶ የሚኖርባቸውን፣ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርባቸውን፣ በየቦታው የተገነቡ ፋብሪካዎች ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎችን፣ በኢንቨስተሮች የተገነቡ የተለያዩ የልማት ድርጅቶችን፣ የአበባ እርሻዎችን በእሳት የማጋየት፣ የማውደም የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት መዝረፍ፣ ማቃጠል የአክራሪና የአሸባሪ ሀይሎች ዋነኛ ተግባር መሆኑ በገህድ ይፋ ወጥቶአል፡፡
የመንግስትን ቢሮዎች፣ ድርጅቶች፣ ተሸከርካሪዎች ዶክመንቶች የማውደሙ የወንጀል ድርጊት በስፋት ተስፋፍቶ ህብረተሰቡንም ሽብርና ጭንቀት ውስጥ በመክተት እለታዊ ሰላማዊ ኑሮውንም ሆነ ማህበራዊ መስተጋብሩን፣ የንግድ ልውውጡን፣ የትምህርት ስርአትና ሂደቱን የማወክና የማስተጓጎል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ባሉ የተለያዩ ከተሞች ሰበታ፣ ቡራዩ፣ አርሲ፣ ሻሸመኔና በመሳሰሉት አካባቢዎች የታየው ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ልማቶችን፣ ተቋማትን የማፈራረሱ የወንጀል ድርጊት በኦነግና በግብጽ የተመራ ለመሆኑ በበቂና ተጨባጭ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ነው፡፡
ይህንን በውጭ ሀይሎች የበላይ መሪነት፣ በውስጥ ተላላኪዎች አስተባባሪነት በሀገሪቱ ላይ የተከፈተውን ልማቶችዋን የማውደም፣ ኢኮኖሚዋን የማንኮታኮት ጦርነት በማያሻማ ሁኔታ ማምከንና መቀልበስ ወሳኝ በመሆኑ የአዋጁ ጠቀሜታ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም፡፡
በየቦታው እየተስፋፋ የመጣው በኦነግ መሪነትና በግብጽ አስተባባሪነት የተከፈተው የኢትዮጵያን ልማትና የእድገት ጉዞ የመግታት፣ የአባይን ግድብ ግንባታም ሆነ ሌሎች ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የማሰናከል፣ የማውደም ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ ዘመቻ በአጭሩ ለመግታት የነበረውንም የተረጋጋ ሰላም ለማስቀጠል ህዝብና መንግስት በጋራ ይሰራሉ፤ የአዋጁ አስፈላጊነትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ እነኦነግ ሊከፍቱ በሞከሩት ቀዳዳ ሌሎች የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ልማትና እድገት የማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች ወኪሎቻቸውን በማሰማራት በየፊናቸው የየራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት እየተራወጡ መሆኑ በገሀድ ታይቶአል፡፡ ከዚሁ ጎራ ጋር ተዳብሎ እየተንቀሳቀሰ ያለው የቀለም አብዮት በኢትዮጵያ እናካሂዳለን የሚለው ከአረቡ አለም ሀገራት ውድቀት፣ ጥፋትና ውድመት ከኢኮኖሚያቸው መፍረስና መውደቅ፣ ከተቋሞቻቸው መፈረካከስ፣ ከህዝቡ እልቂትና ደም መፋሰስ ያልተማረው በጥላቻ የተሰነገው አክራሪ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይል ሀገሪቱ የማያባራ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ እየሰራ ይገኛል፡፡ የህ የሁከት ቡድን ይህንን ሲያደርግ ቀጣዩ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ለማሰብ እንኳ ያልበቃ ነው፡፡
በሌላም በኩል ኦነግን፣ ኦብነግን፣ ግንቦት ሰባትንና ሌሎችንም ጽንፈኛ ደርጅቶች ከአክራሪ እስላማዊ አረብ ሀገራት በሚያገኘው የተለየ የፋይናንስ እርዳታ እያደራጀ፣ እያስታጠቀ ስምሪት እየሰጠ፣ በአራቱም ማእዘናት ኢትዮጵያን እየወጋ የሚገኘው ሻእቢያ በሀገር ውስጥ የተነሳውን የህዝብ ጥያቄ የበለጠ ገንፍሎ እንዲፈስ፣ ከህግና ከስርአት ውጪ እንዲሆን በየቦታው ስርአተ አልበኝነት እንዲነግስ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ከግብጽ ጌቶቹ ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሄንንም ለማምከን አዋጁ አስፈላጊ ነው፡፡
ዋነኛ ግባቸው ኢትዮጵያን ማፈራረስ ሲሆን ምኞታቸው ሁሉ በህዝቡ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት እንዲነሳ ማድረግ፣ ይህንንም ተከትሎ መንግስት አልባ የሆነች፣ በየጎጡ የተከፋፈለች፣ የጎበዝ አለቆችና ሽፍቶች የሚፈነጩባት ልክ እንደ ቀድሞዋ ሶማሊያ ማእከላዊ መንግስት አልባ መሳቂያና መሳለቂያ ሀገር ሁና ማየትን ነው፡፡ ለሊት ከቀን የሚሰሩትም ለዚሁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያሰቡት ተሳክቶ አያዩም፤ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ አትበታተንምም፡፡
በህዝቡ ውስጥ የተነሳው የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ የሚፈታው በህግና በስርአት እንጂ ሀገር በማፍረስና በመበተን እንዳልሆነ ራሱ ህዝቡ ያውቃል፡፡ የውጭ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነትም አይቀበልም፤ አላማችውንም ጠንቅቆ ያውቃል፤ ከዚህም አንጻር የአዋጁ አስፈላጊነት ወሳኝ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የታየውን የህዝብ ተቃውሞ በመንተራስ ቀዳዳውን ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ በመሀል፣ በምስራቅ፣ በምእራብና በደቡብ ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በምስጢር ሲንቀሳቀሱና አድብተው የተመቸ ግዜ ሲጠብቁ የነበሩ አክራሪና ጽንፈኛ እስላማዊ ሀይሎችም አሉ፡፡ የእነዚህም ስውር እጅ አጋጣሚውን በመጠቀም ለአገር ጥፋት ተግባር የዋለበት ሁኔታም ተፈጥሮአል፡፡
እንዲህ አይነቱን የትርምስና የሁከት አጋጣሚ በመጠቀም በጭዱ ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ ሲሰሩ የነበሩ እንዲያውም አብዛኛዎቹ ከፋብሪካ፣ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን ማውደም ጀርባ እንደሚኖሩ የሚገመቱ፣ ከአልሻባብና ከአይሲስ ጋር ጥብቅ ቁርኝትና ትስስር እንደሚኖራቸው የሚታሰቡ፣ በግለሰብም ሆነ በአነስተኛ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱ አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ ደጋፊ መስሎ በመንቀሳቀስ የጥፋት ተልእኮዋቸውን ለመፈፀም እንደሚሯሯጡ ይታመናል፡፡ የዚህኛው ክፍል አዝማችና ፊትአውራሪ ደግሞ ጀዋር መሀመድ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያውና በኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ በመጠቀም ከባህር ማዶ በሚሰጠው ትእዛዝና መመሪያ አባላቱና ደጋፊዎቹ ተቃውሞ በተነሳበት ስፍራ ሁሉ ከህዝቡ ጋር እየተቀላቀሉ የጥፋት ተልእኮዋቸውን የሚፈጽሙ ናቸው፤ ፈጽመዋልም፡፡
ህዝቡ ንብረቱን፣ ሀብቱን፣ የሚሰራበትን፣ እንጀራው የሆነውን ፋብሪካ፣ በታመመ ግዜ ፈጥኖ የሚደርስለትን አምቡላንስ፣ የራሱ የሆነውንና የሚገለገልበትን መንግስታዊ ተቋም፣ ቢሮ ወዘተ የራሱ ንብረት ነውና አያፈርስም፤ አያወድምም፡፡ መንግስት ቢቀየር እንኳን ዛሬ እንዲወድሙ የተደረጉት ንብረቶች ሁሌም በአካባቢው ላለው ህብረተሰብ ለልጆቹ ጥቅም እንደሚውሉ ያውቃል፡፡ ለዚህም ነው ይሄንን እኩይ ተግባር ሆን ብለው የሚፈጽሙት አክራሪና ጽንፈኛ አቋም ያላቸው፣ በውጭ ሀይሎች የሚመሩ አሸባሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች ናቸው የምንለው፡፡
ከእነዚህ ሀይሎች ጀርባ ግብጽና ሻእቢያ እንዳሉ ለአፍታም ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ሀገርን ወደፊት ማራመድ የሚቻለው ሀብትዋን፣ ንብረትዋን፣ ልማትዋን ነቅቶ በመጠበቅ እንጂ የተሰራውን በማፍረስና በማውደም አይደለም፡፡ ከዚህም ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሀገርን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ በውጭ ሀይሎች ተላላኪነት በውስጥ ሰርገው በመግባት ለዚህ ሀገር የማውደም ተልእኮ አመራር በመስጠት የሚፈጽሙትን ሀይሎች ነጥሎ ለማውጣት ሌላም በስውር ያቀዱትን በሀገርና በህዝብ ላይ ያልታሰበ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሴራ ቀድሞ ለማምከን አዋጁ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ሰላም ከሌለ ልማት እድገት የለም፡፡ ሰላም ከሌለ በሰላም ወጥቶ ሰርቶ ለመመለስ አይቻልም፡፡ ሰላም ከሌለ የግለሰብም ሆነ የህብረተሰብ ህይወትና ኑሮ ሀብትና ንብረት ዋስትና የለውም፡፡ ከሁሉም በላይ ለአንድ ሀገርና ህዝብዋ ወሳኙና አስፈላጊው ነገር ሰላም ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ዙሪያ ገባዋን ውድቀቷንና መጥፋትዋን አጥብቀው በሚፈልጉ የቅርብና የሩቅ ሀገራት ኢላማ ውስጥ ያለች ሀገር ናት፡፡ ይህ በሁሉላችንም ዘንድ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡
የውስጥ ችግራችንን በውስጥ፣ በራሳችን የመፍታት የቆየ፣ ዘመናትን ያስቆጠረ ባህሉም ልምዱም አለን፡፡ መነጋገር፣ መወያየት፣ መደማመጥ፣ ልዩነትን አቻችሎ በጋራ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ጸንቶ መቆም፣ እርስ በእርስ ከመባላት፣ ከመናቆር ለሀገሪትዋ ጠላቶችም በር ከመክፈት ይልቅ ቀዳዳዎችን ማጥበብ፣ የሀገርን ሰላም ማስቀደም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
አዋጁ ሰፊ ክፍተት አለው፤ ዜግነትንና ሰብአዊ መብትን ይጥሳል፤ ለቂም በቀል መወጪያ ሰፊ በር ይከፍታል፤ በአዋጁ ሽፋን በመጠቀም ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሊካሄዱበት ይችላሉ፤ “ትፈለጋለህ” በሚል የህግ ሽፋን ንብረቶች በስፋት ሊዘረፉ ይችላሉ፤ “መተባበር ግዴታ ነው” በሚለው ድንጋጌ መሰረት “አልተባበረም” በሚል ሰበብ በግለሰቦች ላይ ኢሰብአዊ ተግባራት ሊፈጸሙ ይችላሉ የሚባሉ ሰፊ የህዝብ ስጋቶች ይሰማሉ፡፡ መንግስት በህዝቡ ውስጥ መከፋትና መመረር ያስከተሉትን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት ሰላምና መረጋጋቱን መመለስ ሲቻል የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዝርዝር ድንጋጌዎች አስደንጋጭ በመሆናቸው ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ የገደቡም ስለሆኑ የበለጠ የህዝብን መከፋትና መማረርን በማስከተል ሁኔታውን የበለጠ የከፋ እንዳያደርገው ያሰጋል ወዘተ የሚሉ የህዝብ አስተያየቶችም ይደመጣሉ፡፡
ይህንን ጉዳይ በባለቤትነት ይዞ የሚመራው ብሄራዊው ኮማንድ ፖስት ለህዝቡ መሰረታዊ ስጋቶች ሰፊ ምላሽ ይኖረዋል፡፡ ሁኔታውንም በቅርብ እየተከታተለ መታረምና መሻሻል ያለበትንም ሁኔታ እየፈተሸ ከህግ ውጪ ለሚንቀሳቀሱትና ለሚሰሩትም ከህዝብ ጥቆማ እየተቀበለ፣ እርምጃም እየወሰደ ሰላምና መረጋጋቱን ለመመለስ እንደሚሰራ ይታመናል፡፡ በእነዚህና ሌሎች በርካታ ምክንያቶችና የብሄራዊ የደህንነት ስጋቶች የተነሳ አዋጁን አስፈላጊና ወቅታዊም ተገቢም ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ሁላችንም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብል ልናደርግና ከኮማንድ ፖስቱ ጎን ልንቆም ይገባል።