የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ የህዝብ ተወካዩችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ዓመታዊ ስብሰባ ሲከፍቱ ያሰሙት ንግግር፤ ያነሷቸው ሁሉም ጉዳዩች በቀጥታ ሀገራችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች ያመላከቱና መንግስታዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡ እንዲሁም ሀገራዊ ስሜትን ያጫሩ ጆሮ ገብ ሃሳቦች ነበሩ። እኔን ጨምሮ አብዛኛውን የሀገራችንን አድማጭ ያስደመመን ግን ፕሬዚዳንቱ የአሸባሪዎቹ የኦነግና የግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ማቀናበራቸውን የገለፁበት አግባብ ነው።
ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ዛሬም ድረስ በበርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጰያዊያን አዕምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ይገኛል። የሽብር ቡድኖቹን መሪዎች ባንዳዊ ስሌትንም እየኮነኑት ይገኛሉ። እኔም በዚህ ፅሑፌ ከሁለቱ ባንዳዎች ውስጥ የአሸባሪው ግንቦት ሰባት መሪን ስብዕና እቃኛለሁ—ግብፆች እንዲሰናከል ከሚፈልጉትና የሁሉም የሀገራችን ህዝቦች አሻራ ያረፈበት አንድ ማሳያ ከሆነው ከታላቁ የህዳሴ ግድብ አኳያ በመቃኘት።
እንደ እውነቱ ከሆነ የግንቦት ሰባትና የመሪው አሸባሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የትላንት ዳራ ሲበረበር ስብዕናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ በርከታ ሃቆች ይገኛሉ። በትረ ስልጣን የሚያስገኝልኝ ከሆነ ከዲያቢሎስ ጋርም በሸርክና የመስራት ችግር የለብኝም ብለው ነበር— አሜሪካ ቁጭ ብለው ስልጣን እንደ እህል ውሃ የሚርባቸውና የሚጠማቸው እኚሁ አሸባሪ ግለሰብ። ከትላንት እስከ ዛሬ ድረስ የኤርትራ መንግስት ተላላኪና በኢሳት አማካኝነት ቃል አቀባይ ብሎም የህዳሴውን ግድብ አሰናካይ በመሆን ተንቀሳቅሰው አንዳችም ፋይዳ አላስገኙም—ሰውዬውና ቡድናቸው።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቀቢፀ-ተስፋ ከካይሮ መንግስት ተቋማት ጋር ሆነው ሀገራዊ ክህደታቸውን ሊሳዩን እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ መሆናቸው እየተነገረን ነው። ሰውዬው እርግጥም ቃላቸውን አልበሉም። በአንድ ገፅታው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ መተማመንን ሊፈጥር የሚችል ውይይትን እያካሄደ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ትላንት ያልተሳካውን “የሆስኒ ሙባረክን መስመር” ለማስቀጠል እንደሚፈልግ ከሚነገርለት ከአዲሱ የአል-ሲሲ መንግስት ተቋማት ጋር በትብብር መስራታቸው ይፋ ሆኗል— ሀገራቸውን ለመሸጥ ተደራድረው።
ለነገሩ ሰውዬው ፍፁም ፀረ- ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ይህ አሳፋሪ ምግባራቸውም የተለመደ የባንዳነታቸው ተቀፅላ እንጂ አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ አሸባሪው ዶክተር ቀደም ሲልም ከዋህቢያና ከስደተኛው ሲኖዳስ ጋር በመሻረክ ኢትዮጵያዊያንን በሃይማኖት ሰበብ ለማበላላትና ኤኬልዳማ ለማድረግ ተወገርግረዋል። በህዝብና በመንግስት ቅንጅታዊ ተግባር ስዕለታቸው አልይዝ እያላቸው እንጂ፤ እንደ እርሳቸው የቀን ቅዠት ቢሆንማ ሀገራችን እንዳልነበረች በሆነች ነበር። ዛሬም በጥፋት ክለባቸው አማካኝነት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለመሸጥ ታጥቀው ተነስተዋል—የሚያስገኙት አንዳች ነገር ባይኖርም።
የግንቦት ሰባቱ መሪ በአስመራ መንግስት ድጋፍ በርካታ የሁከት ጥመኞችን አሰልጥነው (አሰይጥነው ቢባል ጥሩ ይመስለኛል) ሀገራችን ውስጥ ሁከት ለመፍጠር የአቅሚቲን ያህል መሯሯጣቸው አይዘነጋም—በሰላም ወዳዱ የሀገራችን ህዝብ አማካኝነት ጀሌዎቻቸው የንፀሃንን ደም ለማፍሰስ የመቋመጣቸውን ያህል፣ ደም ሳያፈሱ እየታፈሱ ወደ ማረሚያ ቤት ወረዱ እንጂ። የሽብር ቡድኑ አንድ ጊዜ ከሻዕቢያ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዋህቢያና ከስደተኛው ሲኖዶስ ጋር ለፀረ- ኢትዮጵያ ትግሉ አብረውት እንዲሰማሩና ታግለው እንዲያታግሉት በብልጣ ብልጥነት ሲክለበለብ የነበረ የጥፋት ኃይል ነው። ዛሬ ደግሞ የሃፍረተ ምግባሮቹን ቁጥር ከፍ ለማድረግና መቼም የማይሰበር የነውር ሪከርድ ለማስመዝገብ ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጋር አስረሽ ምቺው እያለ ነው።
ነገርዬው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” ሳይሆን አይቀርም። ታዲያ እዚህ ላይ የግብፅ መንግስት ጠላታችን ነው እያልኩ አለመሆኑ ይያዝልኝ። በእኔ እምነት የግብፅ መንግስት ከአል-ሲሲ በዓለ-ሲመት ጀምሮ ወደ አዲስ ምዕራፍ የውይይት መድረክና አስተሳሰብ ያመራ መስሎኝ ነበር። እርግጥ የግብፅ ህዝብ ተባብሮ በማደግ የሚያምን እንደሚሆን እገነዘባለሁ።
እነዚያ ህዝቦች ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን በየጊዜው ሲገልፁም አዳምጫለሁ። ሆኖም አንድ ያገጠጠ ሃቅ ይታየኛል። ይኸውም ግብፆች ከተለያዩ የሙባረክ ዘመን ቅሪት ባለስልጣኖቻቸውና በመንግስታዊ ተቋማቶቻቸው አማካኝነት ተዘዋዋሪና ቀጥተኛ አስተያየት እንደምንሰማው ነገር፤ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን ለመጋፋት ብቻ ሳይሆን እንድንተራመስና ግድቡን እንድናቆም የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ የቀድሞዎቹ የግብፅ ገዥዎች አመለካከት ነው— ትናንትና ተሞክሮ ያልሰራና ዛሬም ቢሆን ሊሰራ የማይችል መወያየትንና መደማመጥን ወደጎን ያደረገ እሳቤ።
ለነገሩ ዛሬ ትላንት ሊሆን አይችልም። በዛሬዋ ግብፅ እነ ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ፣ እነ ጋማል አብዱልናስር፣ እነ ሆስኒ ሙባረክ፣ እነ ሞሃመድ ሙርሲ የሉም። ከአሮጌ አስተሳሰባቸው ጋር ተሰናብተዋል። እነርሱ ግብፅ የአባይ ወንዝ ብቸኛ ባለ ይዞታና ተጠቃሚ መሆኗን አስለተው ለግብጽዊያን የሰበኩና ባሮጌው ዘመን አስተሳሰብ የተሰማሩ የትላንት ባላንጣዎቻችን ናቸው። ይህ ማለት ግን የፕሬዚዳንት አል-ሲሲ መንግስት የህዳሴውን ግድባችንን በፍጹም ደስታ ይቀበለዋል እያልኩ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ሁለት ጉዳዩችን በምክንያትነት አነሳለሁ። አንድም ለበርካታ ትውልድ የተሰበከን ጭፍን ፖለቲካ በቀላሉ መናድ ስለሚከበድ፣ ሁለትም የግብፅ መንግስት በይፋ በዓባይ የመጠቀም መብታችንን ባይቃወመም፤ ሰሞኑን በግልፅ እንደታየው በተቋማቱ አማካኝነት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር አዲስ የግንኙነት አቅጣጫ መመስረቱ የሚያመላክተን ዕውነታ ስላለ ነው።
እናም የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ደፋ ቀና ማለታችን የሚያስኩርፋቸው ወገኖች አይኖሩም መኖራቸው አይቀርም። አጋጣሚውን ተጠቅመው ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጉያ ስር በመወሸቅ የግል ጥቅማቸውን ለማጋበስ ሽር ጉድ የሚሉ እንደ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ዓይነት ሀገርን ለመሸጥ የተሰለፉ ግለሰቦች መኖራቸውን ማንም አይክድም። ይህ በፕሬዚዳንቱ አንደበት የተነገረው የእነ ግንቦት ሰባት ቅንጅትም ግብፆች የህዳሴውን ግድብ ለማደናቀፍ እንደሚሰሩ የሚያሳይ ሁነኛ ማስረጃ ነው።
ዳሩ ግን ግብፆች ካሻቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ለመስራት ቢጥሩም፣ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን የሚነፍግ አንዳች ህግም ይሁን ኃይል ከፀሃይ በታች ያለ አይመስለኝም። እንደሚታወቀው የህዳሴው ግድብ ግንባታ መላው ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን የደገፈው በሞራል ብቻ አይደለም። በጉልብቱም፣ በዕውቀቱም፣ በገንዘቡም በፀሎቱም ጭምር ነው። የሰው ስጋና ደም ለግንባታው የሚያገለግል ቢሆን ኖሮ፤ ይህን በመከወን ግድቡን ለማሳለጥ የተዘጋጁ እልፍ ናቸው ብል እንደ ማጋነን የሚቆጠርብኝ አይመስለኝም። የህዳሴው ግድብ ግንባታ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠበቀ ነው። መቻልን የቻልንበት፣ አንድ ከሆንንና ከተባበርን የማንወጣው ፈተና አለመኖሩን ያየንበትም ይሁን ያሳየንበት ጭምር ነው— ለወዳጆቻችንም፣ ለጠላቶቻችንም።
እንደ እውነቱ ከሆነ የሀገራችን ህዝቦች የውሃ ላይ ቋሚ ሃውልት የሆነው ይህ ግድብ በሥነ-ልቦናዊ ድል እሴትነት ብቻ ተመንዝሮ የሚለካ አይደለም። በዓባይ ወንዝ ዝንተ-ዓለም መጠቀም የማንችል አቅመ-ቢስ የበይ ተመልካች አድረገው የሚቆጥሩንን ሁሉ አፋቸውን ያሲያዝንበት ይመስለኛል። ይሀ ሁኔታ ደግሞ ለግብፆች ራስ ምታት፤ ለፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ደግሞ እንጀራ መሆኑ ግልፅ ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ተብዬው ባንዳ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ዓይነት። አዎ! ተስፋ ሰጪውን ጉዟችንን ሲያስተውሉ “ምነው ቀድሜ በሞትኩት” በማለት ዳግማዊ ሞታቸውን የሚመኙ የአስተሳሰብ አሮጌዎች ግብጽን እንደ ምቹ መደላድል አድርገው በመቁጠር ማማተራቸው አልቀረም— የሚያዋጣ ስሌት ባይሆንም።
ያም ሆነ ይህ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አስላለፍ የለየለት ባንዳነት ነው። ግለሰቡ ለካይሮ ያደሩት ግብፅ የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆነች አድርገው በመቀመር በመሆኑ ሰውዬው ሀገርን ሸጠዋል። ግና በሁለት ምክንያቶች ይህ እኩይ ባንዳዊ እሳቤያቸው የሚሰራላቸው አይመስለኝም። አንድም የዛሬይቷ ኢትዮጵያ የትላንቷ ባለመሆኗ፤ ሁለትም ዓለም በአንድ መንደር በምትመሰልበት በዘመነ ግሎባላይዜሽን አጥንቱንም ሆነ መረቁን ለእኔ ባይ ስግብግብነት ቦታ ስለሌለው ነው። ይህ የግንቦት ሰባት መሪ ነውረኛ ተግባርም “ሁሉንም ትመኛለህ፣ ሁሉንም ታጣለህ” የሚባለው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ስሌት በመሆኑም የሚሳካ አይደለም።
እናም ግብፅ በይፋ እንደ ጥንቱ ‘ዓባይ የብቻዬ ነው’ የሚል አቋምን በመንግስት ደረጃ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ባታንቀባርቅም ቅሉ፣ የአሸባሪው ዶክተር ቅዥት ግን ይፋዊ ሀገር ክህደት መሆኑ ሁሉንም የሀገራችን ህዝቦች የሚያስማማ ዕውነታ ነው። ለነገሩ ሀገሬን ክጄ ባንዳ በመሆን ልስራልህ የሚል ግለሰብና ቡድን፤ በባንዳነት የተሰለፈለትን አካል ያለመካዱ እርግጠኛ ሆኖ ስለማይቻል በሌላው ወገንም ቢሆን ተዓማኒ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። እናም በእኔ እምነት የሰውዬው አካሄድ ኢትዮጵያን በጥቁር ገበያ አውጥቶ ከመቸርቸር የማይተናነስ የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት ነው። በታሪክም በህግም ያስጠይቃል። ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ዘርግቶ የመሸጥ ያህል የሚቆጠር ነውና። ባህላችንን፣ እሴቶቻችንን እንዲሁም የአበውንና የእመውን የሀገር ፍቅር ታሪክን ብሎም ዛሬ ላይ በልዩነት ውስጥ ያለውን የአንድነታችንን ወርቃማ እውነት ያረከሰም ድርጊት ነው።
እርግጥ እነ ግንቦት ሰባት አቅመ ቢስ መሆናቸው በጀ እንጂ እንደ ልባቸው ሞኞት ቢሆን ኖሮ፤ በሽብር መርዛቸው ሀገራችንንና ህዝቦቿን ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ ግስጋሴያቸው ወደ ኋላ ባሰቀሯቸው ነበር። “እባብ የልቡን አይቶ እግር ነሳው” እንደሚባለው፤ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑን የልባቸውን መሰሪነት አይቶ አቅም ነሳቸው። ለጥቆም ስልጣንን ነጠቃቸው። ከዚያም የሽብር ዛር ሰፈረባቸው። ከሻዕቢያ ጋርም አቆራኛቸው። አሜሪካ ሆነው ኢሳትን በመፈብረክ የሽብር ሽምጥ ፈረስ ጋላቢ አደረጋቸው። ዛሬ ላይ ደግሞ ከግብፅ ተቋማት ጋር አብረው የሀገራችንን ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አንዱ ማሳያ የሆነውን የህዳሴውን ግድብ ሊያደናቅፉ እየሰሩ ነው።
አዎ! ሰውዬው ሃሳብ እኩይ ነው— ምግባረ ትንሽነት። በእኔ እምነት ሀገር ከመካድና ህዝብን ባንዳ ሆኖ ከመሸጥ የመረረ ስህተት የለም። ማንነትን መካድ ከመኖር በታች ይመስለኛል። አጉል መሆንም ጭምር ነው። ከሙታንም በላይ፣ ከህያው ፍጡራን በታች ሆኖ የመንቀሳቀስ ያህል የሚቆጠር። እናም እንዲህ ዓይነት የህዝብን ጥቅም ተፃርሮ የሚቆም ማናቸውም ኃይል በህዝብ ከመገለል ውጪ የሚያገኘው ነገር የሚኖር አይመስለኝም። በተለይም በግድቡ ግንባታ ዙሪያ አንድ የሆነንና ከጫፍ እስከ ጫፍ የተነቃነቀን ህዝብ እንኳንስ ባንዳ ቀርቶ ሌላም ሊፈታተነው አይችልም። ባንዳነት ኢትዮጵያዊ ባህል ባለመሆኑም የህዳሴው ግድብ በእነርሱ የተልዕኮ ሴራ አይደናቀፍም።