የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሴኮንድም አይስተጓጎል!!

 

 

 

ከፍተኛ ሙቀትና ሐሩር የአካባቢው መገለጫ ነው፡፡ የበረሃው ወበቅም ኃይለኛ ነው፡፡ በጣም ይፈታተናል፣ ይከብዳል፡፡ በአካባቢው እንኳን ለመቆየት ለአፍታም ለመቆም ይከብዳል፡፡ አገራዊ ተልዕኮ ሰንቆ የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ ግን ለእነዚህ ሁሉ ፈታኝ ተግዳሮቶች እጅ አልሰጠም፡፡ የድካም ስሜት አይታይበትም፡፡ በእልህና ቁጨት ሌት ተቀን ይሰራል፡፡ ለአገራዊ ዓላማ ስኬት ወገቡን ታጥቆ ተነስቷል፡፡ በይቻላል መንፈስ የተባበሩት እጆች ልማቱን እያጧጧፉት ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ባለበት ሥፍራ ላይ ይህ እውነታ ዛሬም በገሃድ ይታያል – በጉባና ሲርባባ።

 

የህዝቡን የዘመናት ቁጭት በደስታ የለወጠው፤ ለጥያቄውም ወቅታዊ ምላሽ የሰጠው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተጧጧፈ ነው፡፡ አባይ ለእናት አገሩ ልማት ሽር ጉዱን ተያይዞታል፡፡ ለዘመናት አስፈሪና አይበገሬነቱን ትቶ የኃይል ማማ ሊሆን ለልማት አርበኞቹ እጅ ሰጥቷል፡፡ በወቅቱ ለዘመናት የማይደፈር የሚመስለው አባይ ሲደፈር ብዙዎች ማመን አቃታቸው፡፡ በወቅቱ ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ የተዋጡም አልጠፉም፡፡

በቅዥት እንጂ በእውናዊው ዓለም ውስጥ መኖራቸውን የተጠራጠሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ብቻ ብዙዎች በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር ዜናውን የተከታተሉት፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረት ሲጣልና የግድቡ ግንባታ መጀመር ሲበሰር፡፡  ያኔ ታዲያ ነገሩ እውነት መሆኑ ሲረጋገጥ ብዙዎች በደስታ ፈነደቁ፡፡ የዘመናት ቁጭታቸውና ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ ደስታው በቃላት የማይገለፅበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

አባይን ለልማት የማዋሉን እርምጃ ተከትሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ በከፍተኛ የአገር ስሜት ተነሳስቷል፡፡ ጉዳዩን በእኔነት ስሜት ተቀብሎታል፡፡ ለስኬቱም እውን መሆን ህዝቡ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ መወሰኑንም በወቅቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መገለፁ ይታወሳል፡፡ የግንባታውን መጀመር ተከትሎ አንድ የኃይማኖት አባት «… የአባይ ጉዳይ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩትና በማህፀን ካሉ ህፃናት በስተቀር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይመለከታል…» ብለው ነበር፡፡

በተግባር የታየውም ታዲያ እሳቸው እንዳሉት ነው፡፡ ሁሉም ለድጋፍ እጁን ዘርግቷል፡፡ ሀብታም ደኃ፤ ህፃን አዋቂ፤ ሴት ወንድ፤ ተማሪ መምህር፤ ባለሃብት የቀን ሠራተኛ፤ ተቀጣሪ ነጋዴ፤ ሹፌር ረዳት፤ አርሶ አደር አርብቶ አደር፤ የኃይማኖት መሪ ፖለቲከኛ፤ የህክምና ባለሙያ መሃንዲስ፤ ዳያስፖራ…ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደየአቅሙ ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ድጋፍ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡

በከፍተኛ የህዘብ መነሳሳትና ተሳትፎ የታጀበው ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት መከናወኑን ተያያዘው፡፡ የግንባታው ሂደት ለአፍታም ሳይቆም ቀጥሏል፡፡ የግድቡን የግንባታ ሂደት ሥፍራው ድረስ ሄደው የጎበኙ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ጊዜያት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ተደምጧል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከሁለት መቶ ሺህ የማያንሱ ዜጎች ግድቡን ጎብኝተዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ መነሳሳትና መነቃቃትና ፈጥሯል፡፡ የጎበኙት እውነታውን በዓይናቸው ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ያዩትንም ለሌሎች ተናግረዋል፡፡ ድጋፋቸውን ለማጠናከር ቃላቸውን አድሰዋል፡፡

ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ዛሬም ርብርቦሹ ቀጥሏል፡፡ በግንባታው ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሌት ተቀን ሽር ጉዱን ተያይዘውታል፡፡ በራስ አቅም ለሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሀገርና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በንቃት እየተሳተፉ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ህዝቡ ለግድቡ እውን መሆን እያሳየ ያለውን በተግባር የተደገፈ ቁርጠኛ አቋምና ተነሳሽነት በማድነቅ ምሥጋና አቅርቧል፤ እያቀረበም ይገኛል፡፡

ቁጭትን ባነገቡና የአይቻልም መንፈስን በሰበሩ የአባይ ልጆች በአባይ ላይ የሚገነባው የኃይል ማማ  ጉዞው ባይገታም የተወሰኑ የተቃውሞ ድምፆችን ማስተናገዱ አልቀረም፡፡ በተለይም በግብፅ በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ የግድቡ መገንባት በግብፅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በተደጋጋሚ ለመግለፅ ሞክረዋል፡፡ እውነታው ደግሞ የዚህ ተቃራኒ መሆኑ በተጨባጭ መረጃዎች ቀርቧል፡፡ ግድቡ የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በባለሙያዎች ጥናት ተረጋግጧል፡፡ ፍትኃዊ የአባይ ውኃ ክፍፍልን መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑም ተወስቷል፡፡

የግድቡ መገንባት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለመኖሩ በኢትዮጵያ በኩል ቀድሞ የታወቀና በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን  በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ዘንድ ግልፅነትና በቂ ግንዛቤ እንዲኖር የኢትዮጵያ መንግሥት ተነሳሽነቱን ወስዶ ዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት እንዲያካሂድ ተደርጓል፡፡ ይህም በሦስቱ የተፋሰሱ አገራት (ኢትዮጵያ፤ግብፅና ሱዳን) ትብብር የተዋቀረ ነው። ዓለም ዓቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ከየአገራቱ የተውጣጡ ስድስት ባለሙያዎችና በሦስቱ አገራት በጋራ የተመረጡ አራት ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው፡፡

በወቅቱ የባለሙያዎቹ ቡድን ለአንድ ዓመት ያህል የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ተገቢውን የማጣራትና የመገምገም ሥራ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህም የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የጥናትና የዲዛይን ሰነድ በመመርመር፣ በግንባታው ቦታ በመገኘትና ሂደቱን በመቃኘት፣ በሦስቱ አገሮች ውስጥ ለስድስት ጊዜ ያህል በመሰባሰብና በተነሱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እንዲሁም ከግድቡ የግንባታ ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋር በመመካከር የደረሰበትን የመጨረሻ የጥናት ውጤት ለሦስቱ አገሮች መንግሥታት ግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲዛይን ሥራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የዲዛይን መመዘኛና መርሆዎች ላይ የተመሠረተ፤ ለሦስቱም አገራት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ እንዲሁም በሁለቱ ተጋሪ አገራት (ግብፅና ሱዳን) ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ቡድኑ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት ስትገልፀው የነበረው ይህንኑ እውነታ ነበር፡፡ «ተፈጥሯዊ የጋራ ሀብቱን ማንንም በማይጎዳ መልኩ ለልማት እናውል» የሚለውን አቋሟን የሚንድ አንዳችም ነገር በጥናት አልተረጋገጠም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በግድቡ ዙሪያ የተደረጉት ጥናቶች ኢትዮጵያ ስለ ግድቡ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስትገልፀው የነበረው መረጃ ትክክልና በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን ነው የመሰከሩት፡፡ በተፋሰሱ አገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል፣ በአንፃሩ ልማትን የሚያፋጥን መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት  የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የጀመረችው ጤናማ አካሄድ አንዱ አካል መሆኑንም ነው ብዙዎች የሚናገሩት፡፡

የዓለም ሃገራት ትልቅ ሥጋት እየሆነ የመጣው የከባቢ አየር ብክለትን ለመዋጋት አገሪቷ እየሄደችበት ያለውን የአረንጓዴ ልማት ጥረትንም ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላትና ምጣኔ ሀብቱን የሚሸከም ኃይል ለማቅረብ እየተጋች የመሆኗ ትልቁ ማሣያም ነው – ታላቁ የህዳሴ ግድብ፡፡ የአካባቢ ወዳጅ የሆነው ይኼ ግድብ ለጎረቤት አገሮች የሚኖረው ጠቀሜታ እጅጉን የላቀ ነው፡፡ ጎረቤት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይልን በቀላሉ የሚያገኙበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

 

በተለይም የተፋሰሱ የታችኛው አገራት ለሆኑት ሱዳንና ግብፅ ጥቅሙ ቀላል አይደለም፡፡ ከጎርፍ ሥጋትና ከደለል ሙሌት ይታደጋቸዋል፡፡ የውኃውን ትነት መጠን በመቀነስ ረገድም ድርሻው ጉልህ ነው፡፡ ለአካባቢ ጥበቃ ልማትም ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ውኃውን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የተጀመረውን ጥረት ያጠናክራል፤ ተነሳሽነትን ያሳድጋል፡፡

 

እውነታው ይህ ቢሆንም ቀደም ሲል የነበሩ የግብፅ ባለሥልጣናት ሀቁን ለመቀበል ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐሙድ ሙርሲና የተወሰኑ ባለሥልጣናት ውኃ የማይቋጥሩ የተለያዩ ሀሳቦችን ለመሰንዘር ሞክረዋል፡፡ ማስፈራሪያ አዘል ቃላቶችን ሲወረውሩም ተደምጧል፡፡

መሀመድ ሙርሲ «…ከአባይ ወንዝ አንዲት የውኃ ጠብታ እንድትቀነስ አንፈቅድም፡፡ እ.አ.አ በ1929 እና 1959 የተደረጉ ስምምነቶችን የሚንድ አካሄድ አንቀበልም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆም ግብፅ ኃይልን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን ትወስዳለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ (በገንዘብ በመግዛት) እንጠቀማለን…» በማለት ለማስፈራራት ቢሞክሩም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ ዛሬ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ለውስጣዊ ችግራቸው መፍትሄ ማበጀት ተስኗቸው ሥልጣናቸውን በኃይል ተነጥቀው ፍርደኛ ሆነዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታዲያ ምንም እንኳን የተወሰኑ የግብፅ ባለሥልጣናት የተሳሳተ አመለካካት ቢያናድዳትም ከግብፅ ህዝብ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ መጓዝ ትፈልጋለች፡፡ በዚህ የተነሳ ነው በግብፅ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎቷን ያንፀባረቀችው፡፡ በወቅቱም በግብፅ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሽግግሩ መንግሥትና ሌሎቹ አካላት ችግሩን በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱም በማሳሰብ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች፡፡

ዛሬም ቢሆን ከግብፅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የተፋሰሱ አገራት ጋር መልካም ግንኙነት አላት፡፡ ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር ትሻለች፡፡ ማንንም ሳትጎዳ ልማቷን ማፋጠን ትፈልጋለች፡፡ ከድህነት ለመውጣት የተያያዘችው ጉዞ እንዳይደናቀፍ ትሰራለች፡፡ ግቧን ለማሳካት ሩጫዋን ቀጥላለች፣ አፋጥናለች፡፡ ከሰሞኑ እንደተገለፀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ሥራ ዛሬ ላይ 54 በመቶ ደርሷል።

የግብፅ አንዳንድ ተቋማት ኦነግን ጨምሮ ተላላኪዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠላም ለማደፍረስና ሀገሪቱ ወደዕድገት ጎዳና ለመሸጋገር የምታደርገውን ጉዞ ለማሰናከል የማያደርጉት ጥረት የለም። ምንም እንኳን ምኞት ፍላጎታቸው ባይሰምርም። እየጎመዘዛቸውም ቢሆን ሀቁን ቢረዱት መልካም ነበር – የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ሥራ ለሰኮንድም ቢሆን እንደማይቆም።