ኢህአዴግ ሁሉንም ችግሮች በብቃት አልፏቸዋል!

ስንቱን ነገር አሳለፍነው። ስንቱን መልካምና መጥፎ ነገሮች አለፍን። ባለፉት 25 ዓመታት አገራችን በርካታ መልካም ነገሮችን አሳልፋለች። መጥፎ አጋጣሚዎችም ገጥመውን በድል ተሻግረናቸዋል። አንድ ወዳጄ እንደቀልድ አገራችን ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ያሳለፈችውን አንዳንድ ነገሮች እንዲህ ተረከልኝ። 

 

ከመልካሙ ልጀምርና አገራችን ባለፉት 25 ዓመታት መሠረታዊ ለውጦች ካሳየችበት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነትና ነጻነትን ያረጋገጠ ህገመንግስት ማግኘታችን ነው።  ይህ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የአገሪቱን አንድነት እንዲጠበቅ አድርጓል። የፌዴራል ስርዓቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው መተዳደር መቻላቸው፣ ባህላቸውን ማሳደግና ቋንቋቸውን መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። 

 

ይህ ለዘመናት በህዝቦች መካከል የነበረን  የተዛባ አሰራርና አስተሳሰብ ማረም አስቻለ። እንዲሁም አገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን መተግበር በመቻሏ በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ  ምርጫ በማካሄድ ህዝቦች ለመጀመሪያ  ጊዜ  ድምጻቸውን ይበጀኛል ላሉት ተወካዮቻቸው መስጠት ቻሉ። አገራችን እስካሁን አምስት አገራዊ ምርጫዎችን ማድረግ ችላለች። የምርጫ ስርዓቱ የራሳቸው እጥረቶች ቢኖሩባቸውም  ሂደታቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ  የታጀቡ ናቸው።     

 

ይህ ህገመንግስት የቆየውን የአገራችንን የተዛባ አካሄድ እንዲስተካከል በማድረጉ በአገራችን ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ማስፈን ተቻለ። ይህም በመሆኑ አገሪቱ ቢያንስ ለ13 ዓመታት በተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። አገሪቱ በፍጥነት በሚባል መልኩ ከድህነት መውጣት ጀመረች። በእርግጥ አሁንም በርካታ ዜጎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም መንግስት በተከተለው ትክክለኛ  ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በርካታ ዜጎችን ከድህነት ማላቀቅ ተችሏል። የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ25 ዓመታት በፊት ከነበረበት ከአራት እጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል።

 

ማህበራዊ መገልገያዎችንም በተመለከተ በርካታ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የዞን ሆስፒታሎች፣ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መገንባት ተችሏል። በትምህርት ረገድም ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ዘርፍ ነው።  በትምህርት ላይ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ከ28 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። በፌዴራል መንግስት ብቻ ከ40 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመገንባታቸው ዛሬ ላይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ብቻ ሳይሆን  ተማሪዎች በመረጡት የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን  መከታተል እንዲችሉ  ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

 

ሌላው ለእኔ ትኩረቴን የሳበው የአገሬ ስኬት ነው ብዬ የማነሳው በአገራችን በፍጥነት እያደገ ያለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። አገሪቱ ፈርሳ እንደገና የምትገነባ እስክትመስል ድረስ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢውች በርካታ ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። አገሪቱን ከጎረቤት አገራት የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች፣ ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች  ጀምሮ፣ ወረዳዎችን፣ ዞኖችን፣ ክልሎችን ከዋና ከተማ የሚያገናኙ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ መንገዶችን መገንባት ተችሏል። በከተሞች መሰረታዊ ለውጦች ተካሂደዋል። የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበትን ገጠሩን መዓከል ያደረገ ስለሆነ ሁሉን አቀፍ ነው።

 

በአገሪቱ የተረጋጋ ሰላም በመስፈን መንግስት አገሪቱን ከድህነት ማውጣት የሚያስችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው ርብርብ አድርጓል። በዚህም ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። ከ300 ሜጋ ዋት የማይበልጥ የነበረውን የአገሪቱን የሃይል አቅርቦት በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ወደ አስር ሺህ ለማድረስ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ ናቸው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከሃይል ማመንጫነት ባሻገር የህዝቦችን አንድነት ማሳያ፣ በህዝቦች መካከል “የይቻላል መንፈስ የፈጠረ”፣ እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ከተባበርን ሁሉን ማደረግ እንደምንችል ያመላከተ ፕሮጀክት ነው። እንደእኔ እንደኔ ታላቁ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለአገራችንና ለህዝባችን ትልቅ ስኬት ነው።   

እስኪ በእኔ እይታ ባለፉት 25 ዓመታት አገራችን ገጥሟታል ከምለው ችግሮች መካከል አንኳር የሆኑትን ላንሳቸው። የመጀመሪያውና ትልቁ በ1983 ዓ.ም አምባገነኑ ደርግ ስርዓት ውድቀትን ተከትሎ በርካታ የታጠቁ አካላት አገሪቱን ለመቀራመት በተነሱበት ወቅት በሽግግር መንግስቱ አርቆ አሳቢነት አገሪቱ ሳትበታተን፣ የህዝብ እልቂትም ሳይከሰት የአገሪቱ አንድነት መጠበቅ ችሏል። ይህ  አገራችንን  ከገጠሟት የከፉ አደጋዎች መካከል ቀዳሚው ነበር። ያ አስከፊ  ወቅት  አልፎ ዛሬ ላይ አገራችን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያለባት አገር ለመሆን በቅታለች።

 

እንደ እኔ እንደ እኔ ሌላው አስቸጋሪ ወቅት የነበረው የኤርትራ ወረራ ወቅት ነው። ከኤርትራ ወረራ ቀደም ባሉ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት መንገድና ትምህርት ቤት ሲያስፋፋ፣ ድህነትን ለመቅረፍ ሲጣጣር የኤርትራ መንግስት መንግስት የጦር መሳሪያዎችን አሰባስቦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ደፍሮ ነበር። በርካቶች ኢትዮጵያ ተከፋፍላለች፣ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አትችልም በተባለበት በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአምባገነኑን የኤርትራን ጦር ከመሸገበት ጠራርጎ እንዲወጣ አድርጓል። በዚህም በአጭር ጊዜ የአገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ወደ ልማት መመለስ ተችሏል። ይህ ለእኔ ሌላው ስኬት ነው።

 

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ሌላው ለአገራችን ፈተና ነበር። በአንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተፈጠረው የስልጣን መባለግ ምክንያት የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም ለማዋል የተደረገው  ሙከራ እንዲከሽፍ ተደርጓል። ኢህአዴግ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመገምገም  አዳዲስ  ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን  መንደፍ  በመቻሉ  አገሪቱ ፈጣን  የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገራችን ባለሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ የህዝቦችን የቆየ የልማት ጥያቄዎች መመለስ ጀመረች። በዚህም አገራችን ዛሬ ላይ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች። ይህ ውጤት ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ መስመር ሳቢያ መመዝገብ የቻለ ነው።

 

ሌላው ለአገራችን ፈታኝ የሆነ የምለው ጊዜ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ የተነሳው ሁከት ነው። በወቅቱ ቅንጅት አጠቃላይ ምርጫውን ያሸነፍኩት እኔ ነኝ በሚል ያስነሳው ሁከት የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል እንዲሁም የአገራችንን የዴሞክራሲ ሂደት ከፉኛ ጎድቶታል።  ያ ወቅት ብዙዎች ለአገራችን አስቸጋሪ ብለው ቢሉትም ኢህአዴግ በብለሃትና አርቆ በማሰብ ሁኔታዎች እንዲበርዱና መልክ እንዲይዙ አድርጓል። መንግስት በተከተለው የሰከነ አካሄድ ሁኔታዎች ተረጋግተው አገራችን የጀመረችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ተችሏል።

 

ባለፈው ዓመት  ጀምሮ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተነሱ ሁከቶች መሰረታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ በሂደትም የሚፈቱ ናቸው።  ከዚህም ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች የአንድ ወቅት ክስተቶችም አይሆኑም። ይልቁኑም  የዴሞክራሲ ባህላችን እየዳበረ ሲሄድም ሆነ ጠያቂ ህብረተሰብ  እየጎለበተ በሄደ ቁጥር የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይፈጠራሉ።  እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን በመቀራረብና በመነጋገር ብቻ ነው። በአገራችን የሰላማዊ ትግል ባህል ሊጎለብት ይገባል። በቀጣይ በየትኛውም መስፈርት ቢሆን በነውጥና በሁከት ወደ መንግስት ስልጣን መሰቀል አይቻልም። እንዲህ ያለ አካሄድ ህገመንግስታችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግቶታል። የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ወይም መፍትሄ ማፈላለግ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ጭምር ነው።