የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት የተንጸባረቀበት ሹመት

ኢሕአዴግም ሆነ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ላለፉት 15 ዓመታት ያደረጉትን ጉዞ በመገምገም ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ተሃድሶ አንዱና ለተሃድሶውም መነሻ ምክንያት የሆነው የመንግስት ስልጣን ዓላማና ባለስልጣን ለየቅል ሆነው በመገኘታቸው መሆኑም በተደጋጋሚ ተነግሯል።
መንግስትም ሆነ በርካታ ልሂቃን እንደሚናገሩት ከእድገታችን ጋር ተያይዘው የመጡ   ችግሮች ቢኖሩም በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት ዘንድ በሚታዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በምግባረ ብልሹነት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች በወቅቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ባለመፈታታቸው የተከሰቱት ግን ይልቃሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆኑ የህዝብን ተጠቃሚነት በተገቢው ደረጃ ያለማረጋገጥ ድክመት በዋነኛነት የምግባረ ብልሹነት ውጤት ነው፡፡ ምግባረ ብልሹነት ደግሞ በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተረከቡትን ህዝባዊ አደራ ለህብረሰባዊ ለውጥ ማምጫ በትጋት የሚሠሩበት መሣሪያ ማድረግን እየዘነጉ ስልጣንን የኑሮአቸው መሠረት የማድረግ አተያይና በዚህም ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስህተት ከመፈፀማቸው ጋር ተያይዞ የተከሰተ ውጤት ነው፡፡  
ይህንኑ መነሻ በማድረግ መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት በሚያስችለው ጥልቀት ያለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል የተጀመረውን አገራዊ ህዳሴ ከመቀዛቀዝ አውጥቶ ወደ ቀጣይ የለውጥ ሂደት ለማሸጋገር አንዱ ቁልፍ እርምጃ መንግስታዊ ስልጣንን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያ ለማሸጋገር የሚደረገውን ዝንባሌና ጥረት ማስቆምና በርግጥም ስልጣን የህዝብና የአገር መገልገያ መሳሪያ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነም ተነግሯል፡፡  
ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት ከፊታችን ባለው ወር ውስጥ የፌዴራል መንግስትን የአመራር ሥርዓት በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የተመለከተው የፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ የዚህ ተረክ ጭብጥና ዋነኛ አጀንዳ ነው ፡፡  
እንደ ክቡር ፕሬዝዳንት ማብራሪያ የመንግስት ስልጣንን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌን የሚገታና ከእንግዲህ በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የተቻለውን ያክል ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ግለሰቦች በኃላፊነት ላይ በማስቀመጥ የመንግስት የስራ አፈፃፀም በውጤትና በውጤት ብቻ የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ይጀመራል፡፡ ይህን ተከትሎ ውጤት ያላመጣ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሽፋን በመንግስት ስልጣን ላይ እንደማይቀጥል የሚያረጋግጥ ቋሚ የአሰራር ስርዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡
ስለሆነም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለፌዴራል መንግሥት ካቢኔ አባልነት የሚቀርቡለትን ተሿሚዎች በቅርቡ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ አዳዲስ ተሿሚዎችም ሆኑ በሥራ ላይ ያሉት ለሹመት ሲታጩ በትምህርት ዝግጅታቸው የተመሰከረላቸው፣ የዳበረ የሥራ ልምድና ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ባለቤት  መሆናቸው ለድርድር እንደማይቀርብ ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ብቻ ሳይሆን ከኦሮሚያ ምክር ቤት አዲስ የሹመት ስነስርአት ማጠየቅ ይቻላል። ከዚህ ቀደም የፓርቲ አባልነትና ታማኝነትን ያስቀድም የነበረው አሠራር ያሳደረው ተፅዕኖ ያደረሰው ጉዳት ይታወቃል፡፡ አገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑና ለሹመት የሚመጥን ብቃት ያላቸው ዜጎች የመገፉበት ዘመን ያበቃ ይመስላል። ጥቅማቸውን ብቻ የሚያነፈንፉ አስመሳዮችና አድርባዮች መድረኩን እየለቀቁና መልቀቃቸው ግድ እየሆነ መምጣቱን ከኦሮሚያ ክልል የካቢኔ ሹመት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡  
ጨፌው ጥቅምት 13 ቀን 2009 ዓ.ም ባካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባዔ የቀድሞውን አፈ ጉባዔና የኦሕዴድ አዲሱን ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳን ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩትን አቶ እሸቱ ደሴ ደግሞ የጨፌው አፈ ጉባዔ አድርጎ መምረጡም ይታወሳል፡፡
በአቶ ለማ መገርሳ ቀርበው ሹመታቸው በጨፌው ፀድቆ ቃለ መሃላ የፈጸሙት 21 የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ተሿሚዎች ምሁራንና ሙያተኞቹ ሲሆኑ፣ አራቱ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አንድ ኢንጂነርና ሌሎችም ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው የባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ ብዙዎቹ በተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ኃላፊነት፣ እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በግል ተቋማት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸው 16ቱ ከዚህ ቀደም በካቢኔ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ተሿሚዎች መሆናቸው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን ውጤት ያመላከተ ነው፡፡
በብዙዎች የተዋጣለት ሹም ሽር ተደርጎ እየታየ ያለው የጨፌው ኦሮሚያ ዕርምጃ ሲሆን፣ ስምንቱ የአዲሱ የካቢኔ አባላት የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አለመሆናቸው የኦህዴድ/ ኢህአዴግን ለመታረም ዝግጁ የመሆን ቁርጠኝነትና ህዝባዊ ውግንና የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ከዚህ በፊት በጥናትና ምርምር ላይ ተሰማርተው የነበሩና ከነጭራሽኑ የድርጅቱ አባል አይደሉም፡፡ ከተሿሚዎች መካከል ሁለቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የተሾሙ ናቸው፡፡ እነሱም አቶ ዓብይ አህመድ ዓሊ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ደግሞ አቶ ስለሺ ጌታሁን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተሿሚዎች በፌዴራል መንግሥት ሚኒስትሮች ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡  
በፌዴራል ደረጃም ሆነ በቀሩት ክልሎች ለተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሾሙ ሰዎች ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ አገርን የሚያስቀድሙ፣ የተሻለ የትምህርት ዝግጅት፣ የዳበረ የሥራ ልምድ፣ ምሥጉን የሆነ ሥነ ምግባርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ከበሬታን ያተረፉ እንደሚሆኑም ከዚህና የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ከታየበት ኦህዴድ እርምጃ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሙስና የተዘፈቁ፣ ግዴለሾች፣ ሕዝብን የሚያማርሩ፣ በሥልጣን የሚባልጉ፣ ከወሬ በስተቀር ችሎታ የሌላቸው፣ አድሎአዊና የተበላሸ ስብዕና ባለቤቶች በጥልቅ ተሃድሶው ከጫወታ ውጪ ስለመሆናቸው ጭምር በኦህዴድ ማረጋገጥ የተቻለ ይመስለናል፡፡ እነዚህ ከጫወታ ውጪ የሚሆኑ ሃይሎች ከተጨባጭ ሁኔታዎች የሚነሱ ዕቅዶችን ማዘጋጀት የማይችሉት ናቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በመደፍጠጥ ወደር የማይገኝለት ልምድ ያካበቱት ናቸው፡፡ ሕገወጥነት የበላይነት እንዲይዝ ሲያደርጉ የነበሩት ስለመሆናቸው ተሃድሶው እያረጋገጠ ነው፡፡  
በአገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ ለነበረው ቀውስ በመንስዔነት ሲጠቀሱ የነበሩት የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ የፍትሕ መጓደል፣ የሙስና መስፋፋት፣ የሕገወጥነት መብዛት፣ የፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት መበራከት፣ ወዘተ. ብቃት በሌላቸው ተሿሚዎች ምክንያት  መከሰታቸውን ጥልቀት ያለው የተሃድሶ ሂደት እያረጋገጠ ነው፡፡ 
የሕዝቡን ምሬት ያበዙ ጉዳዮች በየደረጃው ባሉ ሹማምንት ይፈጸሙ የነበሩ  ተግባራት መሆናቸውንም ተሃድሶው እያረጋገጠ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለ ተደንግጎ ሳለ፣ ብቃት አልባ ሹማምንት ግን የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደፈለጉ ሲጫወቱበት የነበረ መሆኑም በየደረጃው እየተደረጉ በሚገኙ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች እየተረጋገጠ ነው።
ከዚህ ጥልቀት ያለው ተሃድሶ እና ውጤቱም በኦህዴድ ከተንጸባረቀው ተነስተን በቅርቡ ይፋ የሚሆነውን አዲሱን የፌደራል መንግስት ካቢኔ ብንገምት በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያተረፉ፤ አገራቸውን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎችም ሆነ በአገር ውስጥ የሚወክሉ በመሆናቸውም ለዘመኑ አስተሳሰብ የሚመጥኑ ስትራቴጂዎችን የሚቀርፁ፤ በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ መወሰን የሚችሉ፤ ስህተትን በሌላ ስህተት የማያርሙ፤ ከዓለምና ከአገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጠቃሚ የፖሊሲ ሐሳቦችን የሚያመነጩ፤ ሙስናን በተግባር የሚፀየፉ፤ በመርህ የሚያምኑ፤ የማይዋሹ፤ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው የዳበረና ለማንኛውም ዓይነት መረጃ ቅርብ የሆኑ ንቁና ብቁ ተሿሚዎች መሆናቸው አያጠያይቅም።